🛑 The Golden Rule
ኢየሱስ በወንጌሉ ያስተማረው፤ ነብዩ ሙሀመድም በአስተምህሮቱ ፣ ቻይናዊው ፈላስፋ ኮንፊሽየስም በፍልስፍናው የሚመክረው ተመሣሣይ ሃሳብ ያለው አባባል አለ፡፡ ይሄ አባባል በየትኛውም እምነት ተከታይ አማኝ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃሳብ ነው፡፡ አይደለም እምነት ላለው ሰው ቀርቶ በኢአማኙም ዘንድ የሚደገፍና የሚከበር ሃሳብ ነው፡፡ ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ በዚህ ሃሳብ ይስማማል፡፡ ይሄ አባባልም ወርቃማው ህግ ይባላል፡፡ ወርቃማነቱ በሁሉም ሠዎች ዘንድ ተቀባይነቱን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ያገኘው ስያሜ ነው፡፡
ሕጉም እንዲህ ይላል፡-
🔑‹‹ለራስህ የማትፈልገውንና የማትመርጠውን ነገር ሌሎች ላይ አትጫን!›› ወይም ‹‹አንተ ላይ ሊሆንብህ የማትፈልገውን ነገር ሌሎች ላይ አታድርግ! (“Never impose on others what you would not choose for yourself.")
🔷ይሄን ሕግ ተለማምዶ መተግበር የቻለ ሠው በሌሎች ሰዎች ላይ ስቃይ፣ እንግልት፣ ማፈናቀል፣ ማሰደድ፣ ግድያ አይፈፅምም፡፡ የወገኖቹን፣ የብጤዎቹን ንብረታቸውንና ጥቅማቸውን፣ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ያከብራል፡፡ ‹‹ነግ በእኔ›› በሚል ሌሎችን እንደራሱ ይወዳል፡፡
📍‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ›› የሚለው ታላቅ ሕግ ወርቃማውን ህግ አቅፎና ደግፎ ይዟል፡፡ ራሳችንን የምንወድበትን ያህል ከፍታ ሌሎችን መውደድ ከቻልን ዓለም ሠላማዊና በፍቅር የተሞላች ትሆናለች፡፡ እኛ ላይ ሊሆን የማንፈልገውን ሌሎች ላይ እንዲደርስባቸው አንመኝምም፣ አናደርግምም፡፡
ነገር ግን በገሃዱ ዓለም የሚታየው እውነታ ከዚህ በተቃራኒ የቆመ ነው፡፡ ትዕዛዙ ሳቢና በሁሉም ሠዎች ዘንድ የተወደደ ቢሆንም የሠው ልጅ ግን በተግባር እየኖረበት አይደለም፡፡ የአንዱ መጥፋት ለሌላው መልማት ዋና ምክንያት እስኪመስል ድረስ በተንኮል፣ በሴራ ፖለቲካ፣ በጥላቻ ጥልፍልፍ ደባ መጠፋፋት የዘመናችን ልማድ ከሆነ ሠነባብቷል፡፡ ራስን መውደድ ብቻ የተጋነነበትና ሌሎችን እንደምንም በመቁጠር ሰውነትን እስከመዘንጋት ተደርሷል፡፡ የሰው ልጅ በራሱ ወገን እንደአውሬ እየተባረረ ይጨፈጨፋል፣ አካሉ ይጎድላል፣ ይገደላል፡፡ በጣም ብዙ በደልና ስቃይ በገዛ ብጤው የሰው ልጅ ይደርስበታል፣ በወገኑ ይጨቆናል፡፡
💡ነገር ግን የታላቅነት ሚስጥር፣ የአዋቂነት ጥጉ ሌሎችን በነጻ መውደድ እንጂ ጥቅምና መብታቸውን ጨፍልቆ ክፋትና ጭካኔን፣ ተንኮልና ሴራ መስራት አይደለም፡፡ በዚህ ዘመን የፖለቲከኝነት ጣሪያው፣ የታዋቂነት ዙፋኑ ሴራ ጎንጉኖ ሌሎችን መጣል እንጂ በሀሳብ ልዩነት ተከባብሮና ተግባብቶ መኖር አይደለም፡፡ መቼም ቢሆን ታላቅነትና ሊቅነት ሌሎችን በማቀፍ እንጂ በመገፍተር የሚገለፅ አይሆንም፡፡
ለዚህ ጉዳይ የኮንፊሽየስን ምክር ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አንድ ቀን ኮንፊሽየስ ለተማሪዎቹ ምክር በመስጠት ላይ ሣለ፤ አንዱ ተማሪ አቋረጠውና፡-
‹‹ታላቅ መሆን እፈልጋለሁና መንገዱን አሳየኝ›› አለው፡፡ ኮንፊሽየስ ሲመልስ፡-
‹‹ታላቅ የሚባል መንገድ የለም፤ ነገር ግን ሰው መንገዱን ታላቅ ያደርጋል›› አለ፡፡
💡እውነት ነው! ሰው መንገዱን ታላቅ የሚያደርገው ሰውነቱን በማረጋገጥ ነው፡፡ የመጀመሪያው ስኬት ሰውነትህን ፈትነህ፣ ስሜትህን ገርተህ ፣ ልቦናህን አቅንተህ ፣ ማስተዋልን ተግብረህ ሰው መሆንህን ማስመስከር ነው፡፡ ሰው መንገዱን ታላቅ የሚያደርገው ወደ ሰውነቱ መመለስ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ሰው ሰውነቱን አጥብቆ መያዝ ከጀመረ የሌሎችን ሰውነት ያከብራል፡፡ የሌላው ሰውነት የተሠራውና የተዋቀረው እሱ በተሠራበት የሠውነት አካል መሆኑን ይረዳል፡፡ ሌላውም እንደእሱ ፍቃድ፣ ፍላጎት፣ መብትና ነፃነት እንዳለው ይገነዘባል፡፡ በዚህም በሌላው ላይ ክፉ አያደርግም፤ ነጻነቱን፣ መብቱን፣ ጥቅሙን፣ ወዘተ ያከብራል፡፡
ወዳጆች ሠብዓዊነት ማለት ሰውን ሁሉ ያለአድሎ ማፍቀር ነው፡፡ ዕውቀትም ሠውን ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡፡ ማወቁ ለፍቅር ይዳርገዋል፡፡ ሰውን ያህል ድንቅ ፍጥረት የተረዳ ሰው በገዛ ወገኑ ላይ ክፉ አያደርግም፡፡ በራሱ ሊደርስበት የማይሻውን በሌሎች ላይ አያደርግም፡፡ ይሄን ህግ ሁላችንም ብንለማመደውና ብንተገብረው ሠላም፣ ፍቅር፣ ደስታ፣ መስማማት፣ መተቃቀፍ፣ መግባባት ሀብቶቻችን ይሆናሉ፡፡
📍እናም ሰው ሆይ አንተ ላይ የማትፈልገውን ሁሉ ሌሎች ላይ አታድርግ፡፡ ምን ስልጣን ይኑርህ፣ ምን ሊቅ ሁን፣ ምን ሃብት ይኑርህ፣ ምን ዝነኛ ሁን፣ ምን ዘመድ ይኑርህ፣ ምን ባለጊዜ ሁን፣ ምን ተከታይ ይኑርህ ሌሎችን በእጆችህ እቀፋቸው አንጂ አትገፍትራቸው፡፡ እጆችህን ለማቀፍ፣ ልብህን ለመውደድ፣ ዓይንህን ቅን ለማየት፣ አንደበትህን ለበጎ ቃላት ተጠቀምበት፡፡ ሕሊናህን ሌሎችን ለማፍቀር እንጂ በመጥላት አታባክነው!
✍እሸቱ ብሩ ይትባረክ
ያማረች ቅዳሜን ተመኘን ❤️
@EthioHumanity@EthioHumanity✍
@EthiohumanityBot