Ethiopia Insider


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic


Ethiopia Insider is a digital media that provides news, updates, analysis and features.

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Statistics
Posts filter


ባለፉት ስድስት ወራት የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ፤ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው “በሁለት እጥፍ” ጨምሯል ተባለ

የወባ ወረርሽኝ ስርጭት፤ ተፈናቃይ ዜጎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች እንዲሁም የመስኖ ስራ እና የስንዴ ልማት ባሉባቸው ቦታዎች ላይ “በእጅጉ መጨመሩን” የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ስድስት ወራት የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ፤ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር “በሁለት እጥፍ” መጨመሩም ተነግሯል።

ይህ የተገለጸው ዛሬ ረቡዕ ጥር 28፤ 2017 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። የፓርላማው የጤና፤ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን መድረክ ያዘጋጀው፤ የጤና ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለማዳመጥ ቢሆንም በስብሰባው የቀረበው ግን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት ብቻ ነው።

የኢንስቲትዩቱ የመንፈቅ ዓመት ሪፖርት በዋነኛነት ያተኮረው፤ በኢትዮጵያ ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በወረርሽኝ ደረጃ በተከሰተው በወባ በሽታ ስርጭት ላይ ነው።

በተቋሙ ሪፖርት መሰረት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 658 ሰዎች በወባ ወረርሽኝ ህይወታቸው አልፏል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ በወባ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት ሰባት ሚሊዮን ገደማ እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል።

በመንፈቅ ዓመቱ ከፍተኛው የወባ ህመምተኞች የተመዘገቡበት ክልል ኦሮሚያ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 3.2 ሚሊዮን መድረሱን የኢንስቲትዩቱ ሪፖርት አመልክቷል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15011/

@EthiopiaInsiderNews


በታገዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ “ተጨማሪ ምርመራ” እየተከናወነ መሆኑን ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ አስታወቀ

የእግድ እርምጃ በተወሰደባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጨማሪ “የማጣራት” እና “የምርመራ” ስራ እያከናወነ መሆኑን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ በዚህ ምርምራ ግኝቱ ላይ ተመስርቶ፤ እግዱ “በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲነሳ” ሊያደርግ አሊያም ድርጅቶቹ “እንዲፈርሱ” ወይም “እንዲሰረዙ” ለመስሪያ ቤቱ ቦርድ የውሳኔ ሃሳብ ሊያቀርብ እንደሚችልም ገልጿል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ብቻ ሰባት ድርጅቶች ላይ የእግድ ውሳኔ አስተላልፏል። ባለስልጣኑ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለ10 ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ መስጠቱም፤ ዛሬ ረቡዕ በፓርላማ በተካሄደ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ይፋ ተደርጓል።

በቋሚ ኮሚቴው ስብሰባ የጥያቄ እና ምላሽ ወቅት የመናገር ዕድል የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ፤ መስሪያ ቤታቸው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የሚያደርገው “ክትትል፣ ቁጥጥር እና ምርመራ” “ተጠናክሮ ቀጥሏል” ብለዋል።

“የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለተቋቋሙለት ዓላማ፣ በዚያ መስመር ላይ እንዲሰሩ፤ ህግን እና ህግን ብቻ አክብረው እንዲሰሩ ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉም አቶ ሳምሶን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ተናግረዋል። እርሳቸው የሚመሩት መስሪያ ቤት፤ “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” ያላቸውን 4 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ማገዱ ይታወሳል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15007/


ቪዲዮ፦ ከቀናት በፊት አዳዲስ አመራሮችን የመረጠው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው ያለውን “የእርስ በእርስ ጦርነት” ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ መወሰኑን ገለጸ። ፓርቲው “የተበላሸ” ሲል የጠራውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ለማረምም “ከምንጊዜውም በላይ እታገላለሁ” ብሏል።

መኢአድ ይህን ያለው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ ያካሄደውን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ነው። ፓርቲው በዚሁ ጉባኤው፤ የድርጅቱን ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ፣ የማዕከላዊ ምክር ቤት እንዲሁም የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላትን መርጧል።

ተመራጮቹ ፓርቲውን “ለቀጣዩ ሶስት ዓመታት ሊመሩ የሚችሉ” እና ድርጅቱን “ወደተሻለ ደረጃ ያደርሳሉ” በሚል በጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች የታመነባቸው እንደሆኑም መኢአድ አስታውቋል። ጠቅላላ ጉባኤው “አዳዲስ እና ወጣት የሴት አመራሮችን ወደፊት እንዲመጡ አድርጓል” ሲልም ፓርቲው በመግለጫው አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 መኢአድ በዛሬው ዕለት የሰጠውን መግለጫ ይህን ሊንክ ተጭነው ይመልከቱ 👉 https://youtu.be/6mj2ndmiGOA

@EthiopiaInsiderNews


ከዩ.ኤስ.ኤይድ ገንዘብ የሚያገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ንብረቶቻቸውን እንዳይሸጡ እና እንዳይስተላልፉ ክልከላ ተጣለባቸው

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ድርጅቶች ያለ መስሪያ ቤቱ “ግልጽ ፍቃድ”፤ ንብረት የማስተላለፍ፣ የማስወገድ እና የመሸጥ ድርጊቶችን እንዳያከናውኑ ከለከለ። መስሪያ ቤቱ የሰጠውን “ጥብቅ ማሳሰቢያ” በመተላለፍ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ “ተገቢውን እርምጃ” እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማሳሰቢያውን እና ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፈው፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 27፤ 2017 ባወጣው “አስቸኳይ መግለጫ” ነው። መስሪያ ቤቱ መግለጫውን ያወጣው፤ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ስራቸውን ለሚከታተላቸው እና ለሚቆጣጠራቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ ነው።

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ በዚሁ መግለጫው፤ ከሰሞኑ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኩል “የእርዳታ ማቆም ውሳኔ” መተላለፉን መረዳት እንደቻለ ጠቅሷል። “ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ” እንደሚገኝ የገለጸው ባለስልጣኑ፤ “ዝርዝር ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ” በቀጣይ ባሉት ጊዜያት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል” እንደሚያከናውን አስታውቋል።

እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ከUSAID የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ ያላቸውን ንብረት “ማስተላለፍ”፣ “ማስወገድ” እና “መሸጥ” እንደማይችሉ ባለስልጣኑ ገልጿል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ከመደበኛ ወይም ፕሮጀክት ስራዎቻቸው ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ፤ ሃብት እና ገንዘባቸውን “በማናቸውም መልኩ” ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑንም መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ እንዲያሻሽል፤ የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት አቅጣጫ ሰጠ

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የቦርድ ውክልናን ጨምሮ “በርካታ ክፍተቶች አሉበት” ያለውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ እንዲሻሻል ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

ባለስልጣኑ “አላሰራ ያሉ አዋጆችን እንዲሻሻሉ ለማድረግ” ለሚያከናወናቸው ስራዎች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ተገቢውን ድጋፍ” እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ይህ የተገለጸው የፓርላማው የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን የስራ እንቅስቃሴ ትላንት ሰኞ ጥር 26፤ 2017 ተዘዋውሮ በተመለከተበት ወቅት ነው።

በመስክ ምልከታው የተገኙ አምስት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የስራ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችን እና ተገልጋዮችን ማነጋገራቸውን ከተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ ጊዜ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ያለፉትን የስድስት ወራት የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ፤ የመስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ገለጻ አድርገዋል።

አቶ ሳምሶን በዚሁ ገለጻቸው፤ ባለስልጣኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ለማሻሻል “እየሰራ” እንደሆነ መናገራቸውን የተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ ላይ አስፍሯል።

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14994/

@EthiopiaInsiderNews


መኢአድ ፓርቲውን በፕሬዝዳንት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚመሩ አዲስ አመራሮችን መረጠ 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ትላንት እሁድ ጥር 25፤ 2017 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ አብርሃም ጌጡን ፓርቲውን እንዲመሩ መረጠ። ፓርቲው በዚሁ ጉባኤው፤ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ መሰረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ህጋዊነት ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለባቸው።

ሀገር አቀፍ ፓርቲ የሆነው መኢአድ፤ በትላንትናው ዕለት ያካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ለ10ኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።

በአዲስ አበባ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመኢአድ ዋና ጽህፈት ቤት በተካሄደው በትላንትናው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ 550 ገደማ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጉባኤ ላይ በተደረገው የአመራር ምርጫ፤ መኢአድን ስድስት ለሚጠጉ ዓመታት ሲመሩ በቆዩት አቶ ማሙሸት አማረ ምትክ አቶ አብርሃም ጌጡ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

አቶ አብርሃም በአቶ ማሙሸት የኃላፊነት ዘመን የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። አዲሱ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ይዘው የቆዩትን የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ በጉባኤው ምርጫ የተረከቡት አቶ ሰማኝ አብርሃም ናቸው።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14987/

@EthiopiaInsiderNews


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች ጠንሳሾች፤ “ትላንትና ፖለቲካ ሲያንቦራጭቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው” አሉ

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች “ጠንሳሽ” እና “ጨማቂዎች”፤ “ትላንትና ፖለቲካ ሲያንቦራጭቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወነጀሉ።

አብይ በሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ዛሬ አርብ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ “ሰው torture አይደረግም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ገዢው ፓርቲ እስከ መጪው እሁድ ጥር 25፤ 2017 የሚቆየውን ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ያለው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አብይ፤ ፓርቲው ቃል ከገባቸው ጉዳዮች መካከል “በኢትዮጵያ ቶርቸር ይቁም” የሚለው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል።

ብልጽግና ፓርቲ “ባለፉት ጥቂት ዓመታት” በተጓዘበት “የመጀመሪያ ምዕራፍ” ካሳካቸው ጉዳዮች አንዱ፤ ይኸው እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉባኤው ታዳሚያን ተናግረዋል። “ላለፉት ስድስት ዓመታት፤ ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ torture አይደረግም። በዚህ እኛ እንኮራለን” ብለዋል አብይ።

አብይ በዚህ ንግግራቸው “ፖለቲካን በቅጡ አልተለማመዱም” ያሏቸውን “አባቶች” ወርፈዋቸዋል። “አባቶቻችን ሀገርኛ ሀሳብ አላፈለቁም። በተዋሱት ሃሳብ ሲጨቃጨቁ፣ ሲጋደሉ የኖሩ ስለሆነ፤ አሁንም ያንን ማስቀጠል ይፈልጋሉ” ብለዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14973/

@EthiopiaInsiderNews


አዲሱን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ሹመት አስመልክቶ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባላት ምን አሉ?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ጥር 22፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዲስ ዋና ኮሚሽነር ሾሟል። ብሔራዊውን የሰብአዊ መብት ተቋም እንዲመሩ ስለ ተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የፓርላማ አባላት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

🔴 የአብኑ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ እና የኢዜማው ዶ/ር አብርሃም በርታ የሰጡትን አስተያየት እና የአፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎን ምላሽ ይህን ሊንክ ተጭነው https://youtu.be/tDX2wcAcfDA?feature=shared ያድምጡ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን እንዲመሩ ተሾሙ

በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን ለስድስት ዓመት ገደማ የካቤኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው የሰሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን (ኢሰመኮ) እንዲመሩ በፓርላማ ተሾሙ።

አቶ ብርሃኑ የብሔራዊው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት፤ ተቋሙን ለአምስት ዓመታት የመሩትን ዶ/ር ዳንኤል በቀለን በመተካት ነው። ዶ/ር ዳንኤል ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት፤ የስራ ዘመናቸው ባበቃበት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነበር።

ላለፉት አምስት ወራት ኢሰመኮን የመምራት ኃላፊነት በተጠባባቂነት ተረክበው የቆዩት የእርሳቸው ምክትል የነበሩት ራኬብ መሰለ ናቸው።

ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው ኢሰመኮ፤ ለሰብዓዊ መብቶች መስፋፋት፣ መከበር እና ጥበቃ የመስራት ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ነው።

በ2012 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢሰመኮ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙን በዋና ኮሚሽነርነት፣ በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት እና በዘርፍ ኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ ኃላፊዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሾሙ ይደነግጋል። 

ዛሬ ሐሙስ ጥር 22፤ 2017 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ ኮሚቴው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር እንዲሆኑ አቶ ብርሃኑ አዴሎን በዕጩነት አቅርቧል። ላለፉት አስር አመታት በግል አማካሪነት እና ጠበቃነት እየሰሩ የቆዩት አቶ ብርሃኑ፤ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ የሰሩ ናቸው። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2025/14962/

@EthiopiaInsiderNews


የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት መዘግየት፤ ዘንድሮም በፓርላማ ማነጋገሩን ቀጥሏል

የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎች የሩብ፣ የመንፈቅ፣ የዘጠኝ ወር አሊያም የዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ወደ ፓርላማ በሚመጡበት ጊዜ ሁልጊዜም ከአንድ ጉዳይ ጋር የተያያዙ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል። ጉዳዩ አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ ብዛት የሚወክለውን አርሶ አደር በቀጥታ የሚመለከተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትላንት ሰኞ ጥር 19፤ 2017 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ይህ ጉዳይ ተነስቶ መወያያ ሆኗል። ለልዩ ስብሰባው በቀዳሚነት የተያዘው አጀንዳ፤ “የግብርና ሚኒስቴር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ማዳመጥ” የሚል ነበር።

በዚህም መሰረት የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ የመስሪያ ቤታቸውን የመንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸም፤ ግማሽ ሰዓት ያህል ወስደው በንባብ አሰምተዋል። ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ካነሷቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የአፈር ማዳበሪያን የተመለከተው ይገኝበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለዘንድሮ በጀት ዓመት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚውል 1.3 ቢሊዮን ዶላር እና 156 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ዶ/ር ግርማ በሪፖርታቸው ላይ አስታውሰዋል። በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት፤ ለመኸር፣ ለበልግ የምርት ወቅቶች እና ለመስኖ ልማት የሚውል 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በእቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ሪፖርት ከተጠናቀቀ በኋላ በተከተለው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ የመናገር ዕድል ያገኙ የፓርላማ አባላት የአፈር ማዳበሪያን ጉዳይ በድጋሚ አንስተዋል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14946/

@EthiopiaInsiderNews


ኢዜማ ከመጪው ምርጫ ጋር “የተያያዘ በሚመስል መልኩ”፤ “አባላቶቼ እየታሰሩብኝ ነው” አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) 75 አባላቶቹ በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታወቀ። ፓርቲው በአባሎቹ ላይ እስር እና ማዋከብ እየተፈጸመ የሚገኘው፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው ሀገራዊ ምርጫ ጋር “የተያያዘ በሚመስል መልኩ ነው” ሲል ወንጅሏል። 

ኢዜማ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 20፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ በአባሎቹ ላይ ድርጊቶቹ እየተፈጸሙ ያሉት በአማራ፣ ሀረሪ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንደሆነ ገልጿል። ፓርቲው “ታስረውብኛል” ካላቸው አባላቶቹ ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ፣ ዘይሴ ቀበሌ መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል። 

የዘይሴ ቀበሌ በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ ኢዜማ የተወካዮች ምክር ቤት ያሸነፈበት ነው። የኢዜማ የህግ እና የአባላት ደህንነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ በቀበሌው ባሉ የኢዜማ አባላት ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው እስር እና መዋከብ “ከፍተኛ” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

አቶ ስዩም እነዚህ እርምጃዎች በቀበሌው በሚገኙ የጸጥታ አካላት እየተወሰዱ ያሉት፤ ኢዜማ በአካባቢው “ጠንካራ የፖለቲካ መሰረት ስላለው ነው” ባይ ናቸው። “የፖለቲካ መሰረታችን ጠንካራ የሆነባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ጠንካራ ዱላ አለ። ዘይሴ አንዱ ነው” ይላሉ የፓርቲው የመምሪያ ኃላፊ። 

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14943/

@EthiopiaInsiderNews


የግብርና ምርምር ተቋማት 312 ሄክታር መሬት “መነጠቃቸውን” የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አደረገ

የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት “312 ሄክታር መሬት መነጠቃቸውን” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይፋ አደረገ።

መሬታቸውን ከተነጠቁ መካከል አንጋፋዎቹ የሆለታ፣ የጅማ እና የቢሾፍቱ የግብርና ምርምር ማዕከላት እንደሚገኙበት ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል።

ጉዳዩ የተነሳው የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ የመስሪያ ቤታቸውን የ2017 የመጀመሪያ መንፈቅ የስራ ሪፖርት፤ ትላንት ሰኞ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ ቋሚ ኮሚቴው ከሰጣቸው አስተያየቶች እና ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል የግብርና ምርምር ተቋማትን የተመለከተው ይገኝበታል።

ቋሚ ኮሚቴው ያዘጋጀውን ጥያቄ እና አስተያየት በንባብ ያቀረቡት አቶ አለሙ ዳምጠው የተባሉ የፓርላማ አባል “በአንዳንድ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ያሉ የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት፤ የመሬት ይዞታቸው በከተማ አስተዳደሮች እየተነጠቀ ይገኛል” ብለዋል።

ተቋማቱ እና በስራቸው የሚገኙ ንዑስ ማዕከላት፤ ለምርምር እና ለስራቸው የሚጠቀሙበት “መሬታቸውን እያጡ” በመሆኑ “ህልውናቸው ለአደጋ ተጋልጧል” ሲሉ የፓርላማ አባሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14934/

@EthiopiaInsiderNews


ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል የ550 ሚሊዮን ዶላር ብድር በፓርላማ ጸደቀ 

ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል 550 ሚሊዮን ዶላርን ያካተተ የብድር ስምምነት፤ ዛሬ ሰኞ ጥር 19፤ 2017 በፓርላማ ጸደቀ። የካፒታል ማሳደጊያው፤ ባንኩን “የተሻለ ተወዳዳሪ” እና በቀጠናው መስራት የሚችል “ጠንካራ ባንክ እንዲሆን የሚያስችለው” ነው ተብሏል።

ለመንግስታዊው ባንክ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውለው ገንዘብ፤ ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ለኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው 700 ሚሊየን ዶላር ብድር አካል ነው።

በዓለም ባንክ ስር የሚገኘው ዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ብድሩን የሰጠው፤ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓትን ለማጠናከር በማሰብ ነው።

ይህንኑ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አጭር መግለጫ ያቀረቡት በፓርላማ ረዳት የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ፤ በብድሩ በዋነኛነት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሶስት የመንግስት የገንዘብ ተቋማት እንደሆኑ አስታውቀዋል።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ብድሩን ለካፒታል ማሳደጊያነት ከማዋል በተጨማሪ “መሰረታዊ የመዋቅር ማሻሻያ ለማድረግ” “እና “የዘርፉን የስጋት አስተዳደር ከአለም አቀፍ የባንኪንግ ደረጃዎች ጋር በማጣጣም ለማጎልበት” እንዲጠቀምበት የቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

ከአጠቃላይ የብድሩ ማዕቀፉ ውስጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሻሻያ፣ ማዋቀር እና መልሶ ማቋቋም የተያዘው የገንዘብ መጠን 560 ሚሊዮን ዶላር ነው።

ከዚህ ውስጥ 550 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ፤ ለባንኩ የካፒታል ማሳደጊያ የሚውል መሆኑን ለፓርላማ በቀረበው የማብራሪያ ሰነድ ላይ ሰፍሯል።


🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14921/

@EthiopiaInsiderNews


ብልጽግና ፓርቲ በመጪው ጠቅላላ ጉባኤው የከፍተኛ አመራሮች ምርጫ ሊያካሄድ ነው

ከመጪው አርብ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የገዢው ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮች እንደሚመረጡ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።

ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ እንደሚካሄድ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ከአርብ ጥር 23 እስከ እሁድ ጥር 26 በአዲስ አበባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በሚካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በፓርቲው ፕሮግራም እና ደንብ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሚጸድቁበት እንደሆነ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ባለፈው ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች አፈጻጸም በአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚገመገም አቶ አደም ተናግረዋል። እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ ፓርቲውን የሚመሩ ከፍተኛ አመራሮችም በዚሁ ጉባኤ ላይ እንደሚመረጡ አቶ አደም አክለዋል።

በሁለተኛው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ፤ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪ የስራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫ በተመሳሳይ መልኩ እንደሚካሄድ ምንጮቹ ገልጸዋል።

የፓርቲው የኢንስፔክሽን እና የሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትም በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚመረጡ ምንጮች አክለዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14912/

@EthiopiaInsiderNews


Video is unavailable for watching
Show in Telegram
ጤፍ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከመደበኛው ገበያ በ40 ብር ልዩነት እየተሸጠ ነው

ቪዲዮ፦ በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች የአትክልት እና ፍራፍሬ ሽያጭ መመልከት እንግዳ አይደለም። ጤፍን በብትኑ መንገድ ዳር ዘርግቶ መሸጥ ግን እምብዛም አይስተዋልም።

ትላንት ቅዳሜ ጥር 17 በልደታ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ምርቶቻቸውን ሲሸጡ ከነበሩ ነጋዴዎች መካከል በአንደኛው ድንኳን የነበረው ይኸው የጤፍ ንግድ ነበር። ነጋዴዎቹ በመንገድ ዳር ድንኳን ዘርግተው ጤፍ መሸጥ ከጀመሩ ሶስት ወራት ሞልቷቸዋል።

ጤፍ በቀጥታ ከገበሬው እንደሚገዙ የሚናገሩት የጎዳና ነጋዴዎቹ፤ ምርቱን የሚሸጡት በኪሎ 120 ብር ነው። በአሁኑ ወቅት በመርካቶ፣ በእህል በረንዳ እና በወፍጮ ቤቶች፤ አንድ ኪሎ ጤፍ ከ150 ብር እስከ 160 ብር ዋጋ ይጠይቅበታል።

የጎዳና ነጋዴዎቹ አንደኛ ደረጃ የምንጃር ማኛ ጤፍ “በቅናሽ” የሚያቀርቡት፤ የየአካባቢው አስተዳደሮች በሚያደርጉላቸው ትብብር እንደሆነ ይናገራሉ። ሽያጭ የሚያከናወኑበትን ቦታ ያለምንም ክፍያ በነጻ ማግኘታቸውንም ለዚህ በማሳያነት ያነሳሉ።

“በዋጋው መቀነስ” እና “ያልተቀላቀለ ጤፍ” በማቅረባቸው ምክንያት “በርካታ ገዢ” እንዳላቸው ነጋዴዎቹ ያስረዳሉ። ከታች የተያያዘውን ቪድዮ ተጭነው፤ የጎዳና ላይ የጤፍ ሽያጩን ይመልከቱ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


በጅማ ከተማ “በትንሹ 15 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸውን” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከባለቤታቸው፣ ከሚኒስትሮች እና ከሌሎችም እንግዶች ጋር በመሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በትላንትናው ዕለት ተዘዋውረው ጉብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጉብኝት በኋላ በሰጡት ገለጻ፤ በጅማ ከተማ ለተከናወኑ “የገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች “በትንሹ 15 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸውን” ተናግረዋል።

በከተማይቱ የነበረ መስጂድ እና ከአንድ ሺህ በላይ የመቃብር ቦታ ቀድሞ ከነበሩባቸው ቦታዎች መነሳታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የጅማ ከተማ ነዋሪዎች “ቤቶቻቸውን ሲያፈርሱም” ሆነ ቦታዎችን ለፕሮጀክቶቹ ሲያስረክብ “ካሳ አለመጠየቃቸውን” አብይ በአድናቆት አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተወለዱበት በሻሻ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የጅማ ከተማ ህዝብ፤ ካሳ ከመጠየቅ ይልቅ “ ‘እስቲ ሃሳባችሁን አፍሱት፤ ልየው ነው’ ያለው” ሲሉም በገለጻቸው ላይ ጠቅሰዋል።

“የጅማ አካባቢ ማህበረሰብ ለእነዚህ ህልሞች፣ ለእነዚህ ሃሳቦች መወለድ የነበረው ሚና፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት መሆን ያለበት ነው” ሲሉም አብይ በገለጻቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 350 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ጅማ፤ ከሌሎች ቦታዎች በተለየ መንግስት ለሚያፈልቀው ሃሳብ “የተከታይነት” (followership) አመለካከት እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

🔴ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14902/

@EthiopiaInsiderNews


በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የግብጽ ተሳትፎ፤ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

የግብጽ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ መሳተፍ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ “የሶማሊያን ደህንነት እና መረጋጋት ለማስፈን” ያለመ ባሉት አዲሱ ሰላም አስከባሪ ውስጥ፤ የግብጽ “ተሳትፎ አዎንታዊ” እንደሆነ ገልጸዋል።

አል ሲሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ዛሬ ሐሙስ ጥር 15 ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ሐሰን ሼክ ወደ ካይሮ ያቀኑት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገናኝተው፤ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በተስማሙ በ12ኛው ቀን ነው።

ግብጽ እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ወደ “ስልታዊ አጋርነት (strategic partnership) ለማሳደግ የጋራ ፖለቲካዊ ቃል ኪዳን” እንደተፈራረሙ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል።

በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ግብጽን ከ30 ዓመታት በላይ ሲያሳስብ የቆየ እንደሆነ በዚሁ መግለጫ ላይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት አልሲሲ፤ ሀገራቸው በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ በዋናነት “ለሶማሊያ ህዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት ያለመ” እንደሆነ አስረድተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14893/

@EthiopiaInsiderNews


በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት የአምራች ኢንዱስትሪዎች የብር ፍላጎት “በእጥፍ መጨመሩን” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ተናገሩ

የኢትዮጵያ መንግስት ከስድስት ወራት በፊት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት፤ የሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች “የብር ፍላጎት” “በእጥፍ እንደጨመረ” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የቀረበው ብድር “አጥጋቢ” እንዳልሆነ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።

አቶ መላኩ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ባለፈው መንፈቅ ዓመት ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ ማስኬጃ ብድር እና የሊዝ ፋይናንስ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 3.4 ቢሊዮን ብር ነው።

ሆኖም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለኢንዱስትሪዎቹ የቀረበው 7.8 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የገንዘብ መጠኑ ከ2016 ተመሳሳይ ወቅት ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው።

ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 28.7 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ለፓርላማ አባላት ቤቱ ያስረዱት አቶ መላኩ፤ የተሳካው 24.87 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል።

ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሰጠው ብድር ከዕቅዱ አኳያ ዝቅ ቢልም፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን 4.9 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14887/

@EthiopiaInsiderNews


የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች ሹመት፤ የፓለቲካ ገለልተኝነትን “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት ቀረበበት

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች የአመራረጥ ሂደት፤ “ከፓለቲካ ገለልተኝነት” ነጻ መሆን የሚለውን መስፈርት “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት በፓርላማ አባል ቀረበበት።

ተሿሚዎቹ ለፓርላማ የቀረቡት፤ የፖለቲካ ገለልተኝነትን ጨምሮ እያንዳንዱ ጉዳይ “በደንብ” እና “በዝርዝር” ታይቶ መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገልጸዋል።

ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሶስት የኃላፊነት ቦታዎች 345 ግለሰቦች ተጠቁመው እንደነበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል። ለዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት የተጠቆሙ ሰዎች ብዛት 60 እንደሆነም የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

ዛሬ በፓርላማ ከጸደቀው የተቋሙ ሶስት አመራሮች ሹመት አስቀድሞ፤ የዕጩዎቹ አመራረጥ በአዋጅ የተቀመጠውን መስፈርት የተከተለ መሆኑ ላይ ጥያቄ ተነስቶበታል።

አንድ ግለሰብ በዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት ለመወዳደር ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ መሆን እንዲሁም በህግ ወይም በተዛማጅ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው እንደሚገባ በአዋጅ ተደንግጓል።

የአብን የፓርላማ ተወካይ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ “ሶስቱም ኃላፊዎች ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች ሆነው የሰሩ ናቸው። በተለመደው አሰራር ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች፤ ከገዢው ፓርቲ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ገለልተኝነት የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14876/

@EthiopiaInsiderNews


በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ አሊያም “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ኢህአፓ ጠየቀ

በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ (ኢህአፓ) ጠየቀ። የትግራይ ህዝብ “በመረጣቸው እንደራሴዎች እስኪወከል ድረስ “፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም “ህጋዊ” የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ፓርቲው ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ጥር 14፤ 2017 አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በኢህአፓ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተጠራው የዛሬው መግለጫ፤ በክልሉ በቅርቡ በተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

የትግራይ ክልል በፌደራል ምክር ቤቶች ያለው የውክልና ጉዳይም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ ካሉት ወራት ወዲህ፤ ክልሉ በህዝብ ተወካዮችም እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያለው ውክልና ተቋርጧል።

“የትግራይ ህዝብ እንደ ፌዴሬሽን አባልነቱ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 ወንበሮች ያሉት ቢሆንም፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወክሎ አያውቅም” ሲል ኢህአፓ በዛሬው መግለጫው አስታውሷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው “ባለፉት አራት ዓመታት በፓርላማው እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎች፤ የትግራይ ህዝብን ፍላጎቶች ያካተቱ አልነበሩም” ብሏል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14869/

🔴 የኢህአፓን መግለጫ እና ለጥያቄዎች የተሰጡትን ምላሾች በቪዲዮ ለመመልከት ➡️ https://youtu.be/3gxeQtoadn4

@EthiopiaInsiderNews

20 last posts shown.