ከትምህርት ላይ እጃችሁን አንሱይህ ያለ ዕውቀት የማይኖርበት ዘመን ነው። ትምህርት ለኢትዮጵያ ከማንኛውም አገር በላይ ያስፈልጋታል። ከዓለም አካሄድ የምንለይበት ምክንያት የለንም። ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ያለው ትምህርት እንደሚያስፈልግ ማስገንዘብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ነን። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ትምህርት እንደማያስፈልግ በሚናገርበት በአሁኑ ወቅት ስለ ትምህርት አስፈላጊነት መናገር ይኖርብናል። መምህራን ሆነው ሳይቀር ትምህርት ምን ይሰራል የማይሉ በርካቶች አጋጥመውኛል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲከፈት ዶክተር እጓለ ገብረዮሐንስ በሬዲዮ ስለ ዩኒቨርስቲ ምንነትና አስፈላጊነት ተናግረው ነበር። ይህም ንግግራቸው 'የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ' በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልኩ ታትሟል። ትምህርት የሚያስፈልገው ለዕውቀትና ሠናይት (መልካም ለማድረግ) መሆኑን በሰፊው ገልጸዋል። በቅርብ ዓመታት ከላይ እስከታች ትምህርትን የሚያጠፉ ተግባራት በግልጽና በረቂቅ መንገድ እየተካሄዱ ነው። ትምህርት ለዓመታት የማይማሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆች በአገሪቱ አሉ።
በጥድፊያ የተጀመረና በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት የትምህርት ፖሊሲ ተተግብሯል። መጽሐፍ ሳይደርስ፣ መምህር ሳይዘጋጅ ወዘተ አዲስ ፖሊሲ ተተግብሯል። መጽሐፍን ያህል ነገር በአንድ ወር አዘጋጁ ሲባል የሚጠቅምም የማይጠቅምም ነገር ማጨቅ እየተለመደ ይሄዳል። ይህ ከሚሆን ጊዜ ተሰጥቶት ቢሆን ጥሩ ነበር። ካልሆነ ትምህርት ሊባል አይችልም።
በሌላ መንገድ 12ኛ ክፍል ተፈትኖ የሚያልፈው ተማሪ ተመጥኖ አንድ ዩኒቨርስቲ ቢያስተምረው የሚበቃ ከሰላሳ ሺህ ያልበለጠ ተማሪ ዩኒቨርስቲ እንዲቀላቀል ተደረገ። በዚህ ሁኔታ መምህሩ ሥራ እንዲፈታ ተደረገ። ይህንን መሠረት አድርጎ የሠራተኛ ቅነሳ እንዲደረግ በረቂቅ መንገድ ይሠራል። ዲፓርትመንቶች እንዲዘጉ ይወሰናል።
ይህ ሲደረግ ተጠንቶ ወይም በዲሞክራሲያዊ አካሄድ ባለድርሻ አካላት ተጠይቀው አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላሳ ዓመት ውስጥ 200 ሚሊዮንን ያልፋል። ያን ጊዜም ሆነ አሁን ዩኒቨርስቲ ያስፈልጋል። ዕውቀት ያስፈልጋል።
ምሩቃን ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። ባይሆን መመረቅና ሥራ መያዝን ለመነጠል መስራት ይቻላል። የበጀትንም ጉዳይ ማስተካከል ይቻላል። የግልንም ሆነ የመንግሥትንም ዩኒቨርስቲዎችንና ኮሌጆችን በህግና መመሪያ ብዛት መዝጋትና ማስቸገር ለማንኛውም አገር አይጠቅምም። ይህንንም አስመልክቶ መጠየቅ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
አንድ ሚኒስትር ወይም የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዩኒቨርስቲ እዘጋለሁ ሲል በዝምታ ማለፍ ያልተገባ ነው። ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው ጉዳዩ የመምህራን ሥራ ማጣት ብቻ አሳስቦኝ እንዳልሆነ ነው። መምህራን ሥራ ቢለቁ እንኳን ከዚህ የተሻለ እንጂ ያነሰ ገቢ እንደማያገኙ አስባለሁ። ሁሉም አካላት ተመካክረውና አስበውበት ለትምህርት አስፈላጊው ትኩረት እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ። ሐሳባችሁን ስጡኝ። እንወያይበት።
Mezemir Girma
@Ethiopian_Digital_Library@Ethiopian_Digital_Library