ሁሉንም በአንድ የያዘ ስማርት ካርድ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ተብሏል።የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የፋይዳ መታወቂያ ቁጥር የያዘ፣ የመንጃ ፍቃድ ቁጥር ያለው እንዲሁም እንደ ኤቲ ኤም ካርድ የሚያገለግል ሁሉንም በአንድ የያዘ የነዋሪነት መታወቂያ ስማርት ካርድ ወደ ሥራ ለማስገባት በፕሮጀክት ደረጃ እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያን ስማርት አርጎ አሁን ከምንጠቀምበት የተሻለ ተደርጎ ሰዎች የተለያዩ ካርድ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ ሁሉንም አገልግሎቶችን በአንድ የያዘ ካርድ በቀጣዮቹ 6 ወራት ውስጥ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በእቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከኤጀንሲው ሰምቷል።
ካርዱ የሚሰራበት ዋነኛ አላማም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ፣ ነዋሪዎች 3 ወይም 4 ካርድ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ በ1 ካርድ ሁሉንም አገልግሎቶች አግኝተው አገልግሎት አሰጣጥና ተጠቃሚነትን ቀላል ለማረግ መሆኑን አሳውቋል።
ኤጀንሲው ለቲክቫህ እንደገለፀው ይህ ጉዳይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ትስስር ሊኖር እንደሚገባና በአሁኑ ሰዓትም ፋይዳ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።
ለወደፊት ደሞ ስራው ተጠናቆ ካርዱ ወደስራ ሲገባ ባንኮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት የጋራ ትብብር እንደሚፈጠርም ተገልጿል።
ይህ አገልገሎት በሚቀጥሉት 6 ወራት ውስጥ ወደ ስራ ለማስገባት እቅድ የተያዘለት ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ማሳያዎች (Samples) እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ የሚሻሻለው የመታወቂያ አገልግሎት ፕሮጀክት ተግባር ላይ መዋል ሲጀምር ወይም የሚሻሻሉ፣ የሚጨመሩ ጉዳዮች ሲኖሩ ኤጀንሲው ለህዝብ በይፍ እንደሚያሳውቅም ነው ያስታወቀው።
Source: tikvahethmagazine@Ethiopianbusinessdaily