❤ "በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤
❤ #ጥር ፲፩ (11) ቀን።
❤ እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ከቀብራቸው በሚወጣው አፈር #በእምነታቸው_ከተለያዩ_በሽታ (ቁስል) ለሚፈውሱት ለታላቁ አባት #ለአቡነ_ሐራ_ድንግል_ለዕረፍታቸው_በዓል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።
✝ ✝ ✝
❤ #አቡነ_ሐራ_ድንግል፡- ጻድቁ ከአባታቸው ከሬማው ካህን ከቅዱስ ዮሐንስ ከእናታቸው ብፅዕት ወለተ ጊዮርጊስ የተወለዱት ጥቅምት 19 ቀን 1534 ዓ.ም ነው፡፡ የትውልድ ሀገራቸው ጥንት በጌምድር ደብረ ታቦር አውራጃ ደራ ወረዳ ይባል በነበረው አሁን በምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ላጉና ቀበሌ ነው፡፡ ቅዱሳን የሆኑ ወላጆቻቸውም አባታችንን ከልጅነታቸው ጀምሮ በሃይማኖት በምግባር ኮትኩተው አሳደጓቸው፡፡ አባታችንም የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት በሙሉ ተምረው በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎና አገልግሎት ከኖሩ በኋላ ዓለምን ፍጹም ንቀው መንነው ወደ ሸዋ ተጉዘው ግራርያ ከሚባል አገር ደረሱ፡፡
❤ በዚያም ዘመዶቻቸው ፈልገው ስላገኙዋቸውና ወደ ሀገራቸው ስለመለሷቸው በሌላ ጊዜ ጥቅጥቅ ያለውን ጫካ አቋርጠው አሁን ገዳማቸው ካለበት ጫካ ውስጥ ገቡና ገዳመ ወንያትን መሠረቱ፡፡ በዚያም ፈተናውን ሁሉ ድምጸ አራዊቱን፣ ግርማ ሌሊቱን፣ ብርዱን፣ ሐሩሩን፣ ረሃብ፣ ጥማቱን ታግሰው በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ፡፡ ሰይጣንም በፈተና ሊጥላቸው አንድ ጊዜ በተዋበች ቆንጆ ሴት እየተመሰለ አንድ ጊዜ ደግሞ በሞተ ሰው እየተመሰለ እስከ ሰባት ተከታታይ ቀናት ድረስ ቢፈትናቸውም ድል አድርገውታል፡፡ አባታችን ቀን ላይ ጸሎት እያደረጉ እያለ ነብር የሚያባርራት አንዲት ሚዳቋ መጥታ ከቤት ገብታ ከአቡነ ሐራ ድንግል እግር ስር አረፈች፡፡ ነብሩም ደርሶ ከደጅ እየተቆጣ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ አባታችን "እርሷን ገድለህ ትበላ ዘንድ እግዚአብሔር አልሰጠህምና ሂድ" ባሉት ጊዜ ቃላቸውን ሰምቶ ሄደ፡፡ ሚዳቋዋም እዛው አድራ ሲነጋ በሰላም አሰናብተዋታል።
❤ አባታችን መንኵሰው በገዳማቸው ከገቡበት ፈጽመው ሳይወጡ ለ14 ዓመት በተአቅቦ ተቀምጠዋል፡፡ በአንድ ወቅት ጠላት ተነስቶ አካባቢውን በሙሉ በመውረር ሁሉን ሲማርኩ ገዳሟን አይተው ወደ እርሷም ሊገቡ ሲሉ በተአምራት ባሉበት ተይዘው ቆመው በመቅረታቸው ጉዳት ሳይደርሱባት ተመልሰዋል፡፡ ሱስንዮስ "ሁለት ባሕርይ ሁለት አካል" የሚለውን የሮማን የረከሰ ሃይማኖት በሀገራችን ላይ አውጆ ብዙዎች ሰማዕትንትን ሲቀበሉ አቡነ ሐራ ድንግል በገዳማቸው ለብዙዎች መጠጊያ ሆነው ሃይማኖታቸውን ሲያስተምሯቸውና ሲያፀኗቸው ነበር፡፡ በንጉሡም ፊት ቀርበው በድፍረት "አንድ አካልና አንድ ባሕርይ የሆነውን መለኮትና ትስብእትን ለምን ከሁለት ወገን ትከፍለዋለህ?" ብለው ሲገስፁት ፈርቶ አሽከሮቹን "ይህን መነኵሴ ከቤቴ አውጥታችሁ በፍጥነት ወደ ገዳሙ አድርሱልኝ" ብሏቸዋል፡፡
❤ እመቤታችንን እጅግ አድርገው ይወዷት ነበርና ምስጋናዋን ሲያደርሱ ሦስት ክንድ ከምድር ከፍ ይሉ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም የሁልጊዜ ጠባቂያቸው ነበር፡፡ በ1574 ዓ.ም አሁን በስማቸው ወደሚጠራው ገዳመ ወንያት መንነው ገቡ፡፡ በዚያም ወንጌልን እያስተማሩ፣እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን እያደረጉ፣ ሙት እያስነሱ፣ ድውያንን
እየፈወሱ እግዚአብሔርን ሲያገለገሉ ኖረዋል።
❤ አባታችን ሐራ ድንግል "የማነ ብርሃን" የሚባል ታማኝ አገልጋይ አህያ ነበራቸው፡፡ አህያውም ጸሎታቸው ይጠብቀው ነበር እንጂ እረኛ አልነበረውም፡፡ አንገቱ ላይ ቃጭል አስረው ወደ ገበሬው አውድማ ይልኩትና አህያውም ቃጭሉን እያጮኸ ወደ አውድማው ሁሉ ሄዶ እየዞረ "ማርያም ባርኪ" በረከት ሰፍረው ይጭኑታል፡፡ አህያውም ከገበሬው ሁሉ የሰበሰበውን እህል ይዞ ወደ አቡነ ሐራ ድንግል ይገባል፡፡ በፈለጉትም ሰዓት ራሱ አውቆ ይመጣላቸው ነበር፡፡ አህያውም አርጅቶ ሲሞት እንደ ሰው አልቅሰውና በአዲስ ጨርቅ ጠቅልለው ቀብረውታል፡፡ አህያቸው የማነ ብርሃን ከተቀበረበት ቦታ ላይ ጸበል ፈልቆ አስደናቂ ተአምራትን አድርጓል፡፡ የቅዱሳኑ በረከታቸው እስከምን ድረስ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ታላላቆቹ ቅዱሳን እንደነ በትረ ማርያም፣ ጽጌ ድንግል፣ ወለተጴጥሮስ ያሉ ሌሎችም በርካታ ደጋግ ቅዱሳን ዝናቸውን እየሰሙ ከያሉበት እየሄዱ ይጎበኙዋቸውና በረከታቸውን ይቀበሉ ነበር፡፡
❤ አባታችን አቡነ ሐራ ድንግልም በክብር ካረፉ በኋላ በመካነ መቃብራቸው ላይ ለ40 ቀን ብርሃን ሲወርድ በገሃድ ታይቷል፡፡ አፅማቸውም ከዚያው ከገዳማቸው በክብር አርፎ ይገኛል፡፡ በጸሎታቸው ያፈለቁት ጸበልና የመቃብራቸው አፈር ሕመምተኞችን ከተለያዩ ደውያት ሰውንም እንስሳትንም እየፈወሰ ይገኛል፡፡ አፈራቸውና ጸበላቸው ለሥጋ ደዌ፣ ለእብጠት፣ለቁስል፣ ለለምፅና ለመሳሰሉት ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ በዓለ ዕረፍታቸው ጥር 11 ቀን 1624 ዓ.ም ነው፡፡ ከአቡነ ሐራ ድንግል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤት በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።
https://t.me/Gedelat