የሲቪል ምዝገባና ስታትስቲክስ መረጃን በመላ አገሪቱ ወጥ ለማድረግ የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተጠቆመ።
የሲቪል ምዝገባና ስታትስቲክስ መረጃን በመላ አገሪቱ ወጥ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ዝግጅት ስራ እየተደረገ መሆኑን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገልፀዋል።
በዋና ዳይሬክተሯ የተመራ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ልዑክ የኢትዮጵያን የሲቪል ምዝገባና ስታትስቲክስ መረጃ ላይ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በታይላንድ ባንኮክ ይገኛል። ልዑኩ በታይላንድ የሲቪል ምዝገባና ስታቲስቲክስን ከሚመሩ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በመገናኘት የልምድ ልውውጥና ምክክር አድርጓል።በዚህ ወቅትም ታይላንድ በዘርፉ ያላትን ምርጥ ተሞክሮ ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አተገባበር ላይ ያስመዘገበችውን ስኬት፣ ያጋጠማትን ተግዳሮትና ፈተናዎችን የተወጣችበት መንገድ በሚመለከት ገለፃ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በልምድ ልውውጡ ወቅት የወሳኝ ኩነት የሆኑ የሞት፣ልደት፣ጋብቻና ፍቺ መረጃዎችን በተገቢው መልኩ መዝግቦ መያዝ በተለይ ለማደግ እየተጋች ለምትገኝ አገር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ በታይላንድ ከተዘረገው የቴክኖሎጂ ስርዓት ውስጥ ለኢትዮጵያ የሚሆኑ ጠቃሚ ልምዶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ታይላንድ እ.አ.አ ከ1956 ጀምሮ የሲቪል ምዝገባና የስታትስቲክስ መረጃን የመመዝገብ ልምድ ያላት ሲሆን ለስርዓተ ምዝገባው የዘመኑን የመጨረሻ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ካደረጉ አገራት መካከል የምትገኝ መሆኗንም ወ/ሮ ሰላማዊት ጠቁመዋል። ዋና ዳይሬክተሯ ታይላንድ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር በዘርፉ ያለፈችባቸው ሂደቶች ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ፣ የህዝቧ ቁጥርና የአሰፋፈር ሁኔታ ልምድ ለመውሰድ ተመራጭ እንዳደረጋት አሳውቀዋል።
ታይላንድ ተግባራዊ ያደረገችው የቴክኖሎጂ ስርዓት ከመረጃ አያያዝ ባሻገር ተቋሙን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስተሳሰር ወሳኝና አስፈላጊ የመረጃ ልውውጥ በተገቢው ጊዜ እንዲከናወን ያገዘ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ልዑኩ በታይላንድ ቆይታው ከአገሪቱ ዋና ከተማ ባሻገር በወረዳዎች አከባቢ የምዝገባ ስርዓቱና አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ሂደት በአካል ተገኝቶ ጎብኝቷል።
--
Telegram:
https://t.me/ICS_EthiopiaFacebook:
https://www.facebook.com/ICSEthiopiaTwitter:
https://twitter.com/ics_ethiopiaTikTok:
https://www.tiktok.com/@ics_ethiopiaLinkedIn:
https://www.linkedin.com/company/icsethiopiaYouTube:
https://www.youtube.com/@Ics_Ethiopia