💙 የጥያቄዎች መልስ ክፍል 156 💙
▶️፩. "ክፉ አሳብ የሰው ጥበብ ፍሬ የሌለው የማስጌጥ ድካም ወይም ቀለም በመቀባት መልካቸው የሚለወጥ ሥራዎች አያስቱንምና" ይላል (ጥበ.15፥4)። ስለ cosmetic አጠቃቀም የቤተክርስቲያን ትምህርቷ ምንድን ነው? ራስን ከመጠበቅና በሌላው መካከል ያለው balance የት ላይ ነው? ከዚህ ጋር አያይዤ አርቲፊሻል ፀጉር፣ ለውበት ሲባል የአካል ቀዶ ጥገና ፀጉር የማስተካከል እና መሰል ከውበት መጠበቅ ጋር በሚያያዙ ነገሮች ዙሪያ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ ውበትን የመረዳት አቅማችን ዝቅተኛ ሆኖ ነው እንጂ የሰው ልጅ በተፈጥሮው ራሱ ውብ ነው። እግዚአብሔር የሰጠውን መልክ ንቆ መልኩ ባልሆነ ነገር መገለጥ ግን ከማንም አይጠበቅም። ይህ የውሸት ሌላ ገጽታ ነውና። ራስን መጠበቅ ማለት የተሰጠንን ውበት መጠበቅ ማለት ነው እንጂ ያልሆንነውን መስሎ መታየት አይደለም። ለውበት ሲባል ቀዶ ጥገናም ተገቢ አይደለም። በተሰጠን እግዚአብሔርን ማመስገን እንጂ ያልተሰጠንን መሻት አይገባምና። ራስን መጠበቅ ሰውነትን በውሃ በመታጠብ ንጽሕናን መጠበቅ ነው። ከዚህ ውጭ የእኛ ያልሆነን ጸጉር የእኛ አስመስለን ብናደርገው የውሸት ሌላ ገጽታ ስለሆነ አይገባም።
▶️፪. ስለ ጣዖት ውጤት ሲናገር "ሰውነትን ከማስተዳደፍ ጋር ፍጥረትንም ከመለወጥ ጋር" ይላል (ጥበ.14፥26)። "ፍጥረት መለወጥ" የሚለው ላይ በዚያን ሰዓት የፆታ መቀያየር ነበር? ከዚህ ጋር አያይዤ በሕክምና ፆታን ስለመቀየር የቤተክርስቲያን ትምህርቷ ምንድን ነው? ሁለት ፆታ ይዘው ስለሚወለዱ ሰዎችስ?
✔️መልስ፦ ፍጥረትን መለወጥ የሚለውን ግእዙ "ሙያጤ ልደት" ብሎታል። በአንዱ ማኅፀን ያለውን ወደ ሌላ ማኅፀን መገልበጥ ብለው ሊቃውንቱ ተርጉመውታል። የፆታ መቀያየር ሳይሆን ከተፈጠረልን ነገር ማፈንገጥን ለመግለጽ የመጣ ነው። በሕክምና ፆታን መቀየር በክርስትና አይፈቀድም። ሁሉም እግዚአብሔር በሰጠው ጾታ መኖር አለበት እንጂ ጾታን መቀየር እግዚአብሔርን ሲፈጥረን ተሳስቷል እንደማለት ስለሆነ ተገቢ አይደለም። ሁለት ጾታ ይዘው የሚወለዱ ሰዎች ካሉ በጥምቀት ጊዜ በሚሸኑበት ጾታ መሠረት ይጠመቃሉ። በወንዱ ጾታ የሚሸና ሰው በ40 ቀን፣ በሴት ጾታ የሚሸና ካለ በ80 ቀን ይጠመቃል።
▶️፫. "ልጁ ሕፃን ሳለ ፈጥኖ በሞት ስለ ተነጠቀ አባቱ ለአንድ ልጁ ይጨነቅና ያለቅስ ነበርና ቀድሞ ለሞተው ልጁ ምስል ሠራለት። ዛሬ ግን እንደ አምላክ አድርገው አከበሩት። ለኀጢአት የተገዙ ሰዎችም በስውር በዓል አደረጉለት። የምሥጢር መሥዋዕትንም ሠዉለት" ሲል እነዚህ አባትና ልጅ እነማን ናቸው?
✔️መልስ፦ አባት የተባለው ሴሩህ ሲሆን ልጅ የተባለው ብኑ ነው። ሴሩህ ብኑ የሚባል ልጅ ነበረው። ብኑ በሕፃንነቱ ሞተ። ሴሩህ ከኀዘን ጽናት የተነሣ እህል አልቀምስም ውሃም አልጠጣም አለ። ከዚያ ዘመዶቹ እንጨት ጠርበው የሞተውን ብኑን አስመስለው ቀርጸው ቀለም ቀብተው ልጅህ ብኑ ተነሣ አሉት። ሴሩህም መጥቶ ልጄ ብኑ ነህ ሲለው በጣዖቱ ያደረ ሰይጣን አዎ ነኝ አለ። ከዚህ በኋላ ሰይጣን በጣዖቱ እያደረ አምላክ ነኝ እያለ ሲያታልል ኖሯል። ይህን ለመግለጽ የተነገረ ነው።
▶️፬. "የዝሙት መጀመሪያዋ ጣዖትን የመሥራት ዐሳብ ነውና። እርሱንም ማግኘት የሕይወት ጥፋት ነው" ሲል በዚህ አገብብ የዝሙት ትርጕሙ ምንድን ነው?
✔️መልስ፦ዝሙት የሚባለው ሴትና ወንድ በመኝታ የሚያደርጉት ብቻ አይደለም። እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖትን ማምለክም ከዝሙት የሚቆጠርበት አግባብ አለ። ከዚህ የተገለጸው ይህ ነው።
▶️፭. "እርሷ በውዱሱ ነቢይ እጅ ሥራቸውን አቃናች" ይላል (ጥበ.11፥1)። ውዱሱ ነቢይ የተባለው ማን ነው?
✔️መልስ፦ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው።
▶️፮. "የተሠራው ሥራ ከሠሪው ጋራ ይፈረድበታልና" ይላል (ጥበ.14፥9)። እንዴት ግዑዝ የሆነ ነገር ይፈረድበታል?
✔️መልስ፦ ጣዖቱን የሠራው ሰው እንደሚፈረድበት የሚያመለክት ቃል ነው። ሥራው ይፈረድበታል ያለው ጣዖቱ ይፈረድበታል ለማለት ነው። አሁን ጣዖት ግዕዛን ያለው ሆኖ ለፍርድ የሚቆም ሆኖ አይደለም። በጣዖቱ አድረው ሳይፈጥሩ ይመለኩ በነበሩ አጋንንት ይፈረድባቸዋል ማለት ነው።
▶️፯. "ማንም ማን ወዳልኖረበት ምድረ በዳ ሄደው ኖሩ። ያልተረገጠች ቦታም የድንኳኖቻቸውን ካስማ ተከሉ" ይላል (ጥበ.11፥2)። ከምድረ በዳ ሄደው ኖሩ የተባሉት እነማን ናቸው?
✔️መልስ፦ እስራኤላውያን ናቸው። ከግብፅ ወጥተው ከነዓን እስከሚገቡ ድረስ ለአርባ ዓመት በምድረበዳ ኖረዋልና።
▶️፰. "ይህም ባይሆን ድንገት የተፈጠሩ የማይታወቁ የሚያላልብና የሚፋጅ እሳትን የሚተነፍሱ ይህም ባይሆን የሚከረፋ የጢስ መዓዛን የሚተነፍሱ ይህም ባይሆን ክፉ ከሚሆን ዓይናቸው የብረት ፍንጣቂ የመሰለ ቦግ ቦግ የሚያደርጉ መዓትን የተመሉ አውሬዎችን ላክህባቸው" ይላል (ጥበ.11፥19)። እነዚህ አውሬዎች የተባሉት እንደምን ዓይነት እንስሳት ናቸው? ምሳሌ ቢጠቀስልን።
✔️መልስ፦ እነዚህ አውሬዎች ግሩማን አራዊት ይባላሉ። ከአስፈሪነታቸው የተነሣ ሰው እነርሱን ካየ ነፍሱ ከሥጋው እንደሚለይ ይነገራል። ስለዚህ በዚህ ዓለም ቢኖሩም ከሰባቱ የመሬት ክፍሎች በአንዱ የሚገኙ ስለሆነ አናያቸውም።
▶️፱. ጥበ.፲፬፥፳፯ ላይ "ስም የሌላቸው ጣዖቶችን ማምለክ የክፋት ሁሉ መጀመሪያ ነውና። የፍጻሜውም ምክንያት ነውና" ይላል። ስም የሌላቸውን ሲል ስም ልዩነት ያመጣል እንዴ?
✔️መልስ፦ የክፋት ሁሉ መጀመሪያ ያሰኘው ጣዖቱን ማምለኩ ነው እንጂ ለጣዖቱ ስም አለመኖሩ አይደለም። አንድ ሰው ጣዖት ካመለከ ለጣዖቱ ስም ይኑረውም አይኑረውም ያው ክፋት ስለሆነ ፍዳውን መቀበሉ አይቀርምና።
▶️፲. መጽሐፈ ጥበብና መጽሐፈ ተግሣጽ በግእዙና በአማርኛው የምዕራፉ ብዛት የተለያየ ሆኖ ይታየኛል። ልዩነቱ የተፈጠረበትን ሁኔታ ቢያስረዱን።
✔️መልስ፦ ለመጻሕፍት አርእስት የሰጡ የኋላ ሊቃውንት ናቸው። ለአጠናን እንዲያመች ምዕራፍና ቁጥር የሰጡት ደግሞ ልዩ ልዩ ሊቃውንት ናቸው። ስለዚህ ሐሳቡ በሁሉም በምልአት የተቀመጠ ነው። የምዕራፉና ቁጥሩ መብዛትና ማነስ ሐሳቡን አይቀንሰውም። ይህ ልዩነት የሚፈጠር ቁጥሩን የተለያዩ ሊቃውንት ስለሰጡት ነው።
▶️፲፩. ጥበ.15፥2 ላይ "ኃይልህን እያወቅን ብንበድል የአንተ ነን" ሲል ሰው እያወቀ (intentionally) ኃጢአት ቢሠራ የዲያብሎስ የግብር ልጅ ቢሆን እንጂ እንዴት የጌታ ይሆናል?
✔️መልስ፦ ብንበድልም ባንበድልም የአንተ ነን ማለት በተፈጥሮ ማንኛውም ፍጡር የእግዚአብሔር ገንዘብ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ሰው ኃጢአት ሲሠራም ቢሆን በግብሩ የሰይጣን ልጅ ቢሆን በተፈጥሮ ግን የእግዚአብሔር ፍጥረት ነውና።
© በትረ ማርያም አበባው
✝️የዩቲዩብ ቻናሌ:- ንሕነ ዘክርስቶስ
https://youtube.com/@edenawizechristos?si=6V4y-73OM3LTzhAf ነው።
🌻የፌስቡክ ገጼ Betremariam Abebaw
https://www.facebook.com/profile.php?id=100075547015721 ነው።