ሰሞንኛ
(በእውቀቱ ስዩም)
በአብማይቱ እምላለሁ፥ ማይክ ታይሰን ቢያሸንፍ ኖሮ ትንሽ ቅር ይለኝ ነበር፤ የአምሳ ስምንት አመት ሰውየ የሀያ ስምንት አመት ጎረምሳ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ባፍጢሙ ደፋው ፥ ቢባል የሰውየው የፍጽምና ማሳያ ይሆን ነበር፤ ፍጹምና እንከን አልባ የሆነን ሰው ደግሞ አርአያ ማድረግ ያደክማል፤
ከትልልቅ ሰዎች የምጠብቀው ልከተለው የምችለው አይነት አርአያነት ነው፤ ለካ በአምሳ ስምንት አመቴ ፥ጡንቻ መገንባት እችላለሁ፥ ስምንት ዙር ሪንግ ውስጥ የሚያስቆይ ትንፋሽ ማካበት እችላለሁ፤ ለካ በዚያ እድሜ የልጆቼን እጅ ሳልጠብቅ በጥረቴ እንጀራ መብላት እችላለሁ ፥ ብለህ እንድታስብ የሚያደርግ አንጋፋ ጀግና ሲገጥምህ ልብህ በተስፋ ይሞላል፤ ማይክ ታይሰን ምን ፈየደልህ ብትይኝ መልሴ ይሄ ነው፤ አምሳ አመትን ከዘራ በማማረጥ እንዳልጠብቀው አድርጎኛል፤ ከዚህ በላይ አነቃቂ የለም!
“ምንም ደሀ ቢሆን ባይኖረውም ሀብት
ከደጃፍ ሲቀመጥ ደስ ይላል አባት “
የሚል ጥቅስ እየተመሰጥን ነው ያደግን፤ አብዛኛው ሰው ወጣትነትን ሲሻገር የአካል እንቅስቃሴ እንዲያቆም ውጫዊና ውስጣዊ ግፊት ያድርበታል፤ ውጫዊው “ ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ “ እያለ ይለጉምሀል፤ ውስጣዊው ደግሞ አሁን ከዚህ “በሁዋላ ቀንድ አላበቅል” እያልህ የሰውነትህን እምቅ አቅም ሳትረዳ እንድትሞት ያደርግሀል፤
ታይሰን ሀያ ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል ተብሏል፤ ቀላል ጥሪት አይደለም፤ አያትየው የልጅ ልጆቹን መጦር ይችላል፤ ባንድ ሚሊዮን ብሩ የተጠረመሱ ፥ የመንገጭላው አጥንቶቹን ያስጠግንበታል፤ የተዳጠ አፍንጫውን ያስበይድበታል፤ በቀረው ደግሞ አለሙን እንደ ጥንቅሽ ይቀጭበታል፤ ምናልባት ሳይንቲስቶች በጥቂት አመታት ጊዜ ውስጥ የእድሜ ማደሻ ቅመም መፍጠር ከቻሉ ደግሞ የመሸመት አቅሙን አዳብሯል፤
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ደጃፍ ላይ የሚያስቀምጠውን መንፈስ በካልቾ ብላችሁ በነገው ታላቁ ሩጫ ላይ ተሳተፉ፤
ልዝብ ደሀ ቢሆን ባይኖረውም ሀብት
ታላቅ ሩጫ ላይ፥
ወልመጥ ወልመጥ ሲል። ደስ ይላል አባት🙂
📱ከወደዱት ለወዳጅዎ ያጋሩት!📱
@bewketuseyoum19 @bewketuseyoum19