ሀበሻ 🇪🇹


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


🇪🇹 ኢትዮጽያዊነታችንን የምናሳይበት 🤝 አንድነታችንን የምናጠነክርበት 🥰 ፍቅርን የምንማርበት ቻናል ነው ።
☞☞ @Ferhanhabesha

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter


ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ “አሞራው ካሞራ” ሲል ያዜመላቸው…

ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ ከሰሞኑ በለቀቀው የብዙዎችን ቀልብ በሳበው ነጠላ ዜማው “አሞራው ካሞራ” ሲል ያዜመላቸው ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ማን ናቸው?

ግጥሞቹ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው የአሞራው ውብነህ ተሰማን ታሪክና ጸባይ አብጠርጥረው የሚገልጹ ናቸው። ራስ አሞራው ውብነህ የፋሽስትን ጦር የሰማይ አሞራ ሆነው መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡት ጀግና እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል።

ለዚህ ጀብዳቸው በሚመጥን መልኩ ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ “አሞራው ካሞራ” በተሰኘው ድንቅ የሙዚቃ ሥራው…

ያየም ሰው ይናገር የነበረም ያውጋ
ተጋጥሟል ይባላል አሞራው ከአሞራ
ጎንደር ጀግና ትውለድ ታሳድግ ፀንሳ
እንደአሞራው ውብነህ ስሙ ማይረሳ … ሲል ለጆሮ በሚስማማ ድምጹ ለጀግናው ይቀኛል። ታሪኩን እያነሳሳም ያወድሳል።

“አሞራው ውብነህ” ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በምዕራብ በጌምድር ግዛት በተደረገው የፀረ-ፋሽስት ትግል ግንባር ቀደም መሪ ነበሩ።

ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ቆላማ አካባቢ የአርማጭሆ አውራጃ ተወላጅ የሆኑት ውብነህ ተሰማ ገና በ16 ዓመታቸው ነበር ትግል የጀመሩት።

በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በጎንደር በኩል ታላቅ ጀብዱ ከፈጸሙ ስመ ጥር አርበኞች መካከል ውብነህ ተሰማ አንዱ ናቸው። አገርንና ወገንን የሚወዱ፣ ከአገር የሚበልጥብኝ ነገር የለም በማለት ራሳቸውን ያሳመኑ እና ጸሎተኛም እንደነበሩ የልጅ ልጃቸው ገብርኤላ አድማሱ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ታዲያ ይህንን ሀገር ወዳጅ፣ አርበኛ እና ጸሎተኛ ባህሪያቸውን ጽምጻዊ አስቻለው ፈጠነ…

ያ የአርበኛው ምንጣፍ ያ ምጅምር ገጡ
የጦሩ መሳፍንት ፈሪሀ እግዜር ያለው
ከጦር መሀል ሲሄድ ይመስላል ክንፍ ያለው
አሞራው ከአሞራ … ሲል በተመጠኙ እና ውብ በሆኑ ቃላት ይገልጸዋል።

ልጃቸው ኢትዮጵያ ውብነህ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከነፃነት በኋላ እንግሊዞች ጎንደር ገብተው የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ የተመለከቱት ራስ አሞራው ውብነህ፤ በአገሬ ላይ የውጭ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ አይሰቀልም በማለት የእንግሊዞችን አስገድደው አውርደው በምትኩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከሱዳን ገዳሪፍ ተስቦ እንደ ሰርዶ
ኢትዮጵያን ሰቀላት ያን ሰንደቅ አውርዶ
የአበቅየለሽ ልጆች ዳር እስከዳር ኩሩ
ጎንደር ጀግና አታጣም አትጠራጠሩ … በማለት አስቻለው “አሞራው ካሞራ” በተሰኘው ሙዚቃ ላይ የተቀኘለትም ለዚሁ ነው።

አርበኛው ውብነህ ተሰማ ባለቤታቸውን ጨምሮ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመጣ ሀገር ወዳድ አርበኞች ጋር በዱር በገደል ስለተዋደቁ ፋሽስት ኢጣልያ በጌምድርን ተረጋግቶ መቆጣጠር ሳይቻለው ቀርቷል።

ራስ አሞራው ውብነህ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው መስከረም በ1975 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ቀብራቸውም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

ድምጻዊው ስለግጥሞቹ ይዘት፣ በግጥሞቹ ውስጥ ስለተካተቱት ስሞች እና አጠቃላይ ስለ ታሪካዊ ዳራቸው አስተያየቱን ጠይቀነው አድማጭ እና ተመልካች በተረዳው ልክ እንዲተረጉመው፤ ለተደራሲያን ትችዋለሁ ከማለት በዘለለ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ከሶስት ዓመታት በፊት በፋና ቴሌቪዥን በ#ፋና_ቀለማት የታላቁ አርበኛ ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ታሪክ በልጆቻቸው አንደበት የተገለጸበትን ዝግጅታችንን ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ተጭነው እንዲከታተሉ ጋበዝንዎት።

ማስፈንጠሪያው👇👇
https://www.youtube.com/watch?v=WWSnijy3a3c


https://www.tiktok.com/@ferhanhabesha?_t=ZM-8t9iXVhZBBu&_r=1
Ferhan Habesha on TikTok
@ferhanhabesha 86 Followers, 254 Following, 74 Likes - Watch awesome short videos created by Ferhan Habesha


ይድረስ ለወገን ደራሽ🙏🙏
ከስር በፎቶ ላይ የምትመለከቷት ልጅ ተምራ ራዕዋን አሳክታ እራሷን ችላ ለሌላ መትረፍ በሚትችልበት ጊዜ ባጋጠማት ህመም ከቤት ውጭ እንኳን በሰው ድጋፍ የምትወጣ ሆናለች ይርጋለም ነው ተወልዳ ያደገችው #ፋሲካ_ብርሃኑ ትባላለች ሀዋሳ ባሉ ሆስፒታሎች ሁሉ ታክማለች ተመርምራለች ከአቅማቸው በላይ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ አዲስ አበባ በሚገኝ ሆስፒታል እንድትመረመርና እንድትታከም ሪፈር ተጽፎላታል ሆኖም ግን ያላትን ገንዘብ ስለጨረሰች ተስፋ ቆርጣ ጨልሞባት ያገኘናት ቤት ቁጭ ብላ ነው 😭 ተቀይራለች መልኳ ሌላ... አይናችን እያየ መሞት የለባትም ብለን የቻልነውን አድርገን ለእርዳታ ለወገን post እናረጋለን ብለን ሀሳብ ስናቀርብ እምቢ "ሰው ምን ይለኛል..." ስትል ከብዙ ማሳመን በዃላ እሽ ብላን ነው post ያደረግነው። ወገኖቼ #አይጨልምባችሁ! የኑሮ ውድነት ቢኖርም ከጤና የሚበልጥ ሀብት የለምና ለሰጠን ጤና እያመሰገንን ፋሲካን ፈጣሪ እንድፈውሳት እንጸልይላት ቀጥለን ደግሞ #Awash_Bank account 013361112541700 ካለን ገንዘብ ላይ ቀንሰን 100 ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ለ 100 ሰዉ ግን ጌጥ ነውና ይህችን እህት ከፈጣሪ ጋር እንድረስላት #CBE_የምንጠቀም_ደግሞ #transfer_to_other_banks በሚል ገብተን ካሉት ምርጫዎች #awash_bank መርጠን መላክ እንችላለን ይሰራል። ፖስቱን SHARE በማድረግም ተባበሩን መልካምነት መልሶ ይከፍላል ስለምታደርጉት በጎነት ፈጣሪ ይባርካችሁ 🙏

ከጓደኞቿ😭


#ልዩመረጃ ትናንት ምሽት በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የታየው ክስተት የሰው ሰራሽ ጠፈር ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ የተፈጠረ መሆኑን የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ ለመሠረት ሚድያ አስታወቀ

- ስብርባሪው የቻይና ሺጂያን-19 መንኩራኩር ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል

(መሠረት ሚድያ)- ትናንት ከምሽቱ 1:30 ገደማ በደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ዞኖች አንድ ግዙፍ 'ክስተት' ሰማይ ላይ መታየቱን በአካባቢ ያሉ ሰዎች መመልከታቸውን ሲናገሩ እና ምስሎችን ማህበራዊ ሚድያ ላይ ሲያጋሩ ቆይተዋል።

በዚህ ዙርያ መሠረት ሚድያ ለአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ (European Space Agency) ማብራርያ የጠየቀ ሲሆን በኢትዮጵያ የታየው ክስተት ሰው ሰራሽ የጠፈር ቁስ ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ (re-entry ሲያደርግ) መሆኑን አብራርቷል።

ኤጀንሲው አክሎም ስብርባሪው የቻይናው ሺጂያን-19 (ShiJian-19) ሊሆን እንደሚችል ጨምሮ ገልጿል።

"በየአመቱ ከመቶ ቶን በላይ የሰው ሰራሽ የጠፈር ቁሶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ወደ መሬት ይመለሳሉ" ብሎ መረጃውን ለመሠረት ሚድያ ያጋራው የአውሮፓ ስፔስ ኤጀንሲ ይህም በየአመቱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ክስተቶች መታየት ምክንያት ነው ብሏል።

አክሎም "አንዳንዱ [የጠፈር ቁስ ስብርባሪ] መሬት ላይ ሊወድቅ ይችላል፣ ነገር ግን እንደ ጠፈር ሮኬት ያሉ ሁሉንም ቁሶች ተቆጣጥሮ ሰው በማይኖርበት አካባቢ እንዲወድቁ ማድረግ አይቻልም። አነስተኛ ቁሶች ራሳቸው ተቃጥለው ያልቃሉ፣ ትልልቅ አካላትን ግን ተቆጣጥሮ ወደ ምድር መመለስ ገና እያደገ ያለ ቴክኖሎጂ ነው፣ እድገቱም ዘገምተኛ ነው" በማለት የኤጀንሲው ቃል አቀባይ ለሚድያችን ተናግሯል።

የትናንት ምሽቱ ክስተት እንደ ምዕራብ ጉጂ፣ ወላይታ፣ አርባ ምንጭ እና ሞያሌ አካባቢ መታየቱ የተገለፀ ሲሆን በኬንያ ማርሳቢት ግዛትም መታየቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በበኩሉ የክስተቱን ተፈጥሮ በእርግጠኝነት ለማብራራት ሁኔታውን በቅርበት እያጣራን እንደሚገኝ አስታውቋል።

የጠፈር ስብርባሪ ማለት አገልግሎታቸው ያበቃ ሳተላይቶች፣ ግልጋሎት የማይሰጡ መንኩራኩሮች፣ የሮኬት ማቀጣጠያ ተተኳሾች፣ ከጠፈር ላይ ግጭት የተረፉ ስብርባሪዎች እንዲሁም በጠፈር በረራ ወቅት ተገንጥለው ያመለጡ ቁሳቁሶች ሊሆኑ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቀማሉ።

እነዚህ በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዙ ስብርባሪዎች ለሌሎች ሳተላይቶች ስጋት ቢሆኑም መሬት ላይ ላሉ ሰዎች የሚፈጥሩት የሞት ወይም የአካል ጉዳት ስጋት ከአንድ ትሪሊየን ውስጥ አንድ ብቻ መሆኑን የ 'ዘ ኦሮስፔስ ኮርፖሬሽን' መረጃ ይጠቁማል።

መረጃን ከመሠረት!


አርቲስት ጌትነት እንየው

አምነው የወደዱ፣
ወደው የተካዱ፣
ተክደው የራዱ፣
ፍርሃት አንሸራቶ ቁልቁል የጣላቸው፣
የብቸኛ ልቦች የትነው መውደቂያቸው?
የትነው መድረካቸው?
ማነው አጃቢያቸው?
እንዴት ነው ምታቸው?
የተካዱ ልቦች አጋር የራቃቸው፣
የሚያቀነቅኑት ምንድን ነው ዜማቸው?
የተመረኮዙት እምነት ታጥፎባቸው፣
ድንገት የወደቁ ፍቅር ያዳጣቸው፣
ሚስጥር የሚያጋሩት ሰው የበረዳቸው፣
ብቸኝነት ሰርጎ ብቻ ያስቀራቸው፣
ዝምተኛ ልቦች ምን ይሆን ቋንቋቸው?
ከየት ነው ጥሪያቸው?
በየት ነው ጉዟቸው?
የት ነው መድረሻቸው?
እንደ ሰብአሰገል ጠቅሶ የሚመራቸው፣
የቃተቱ ልቦች የታል ኮከባቸው?
መቼም ከአምላክ ትንፋሽ ከውሃ ከአፈሩ፣
ከእምንት እና እውነት ከፍቅር ሲሰሩ፣
ዝምተኛ ልቦች ጥንቱን ሲፈጥሩ፣
ተገፍትረው ወድቀው፣
ደቀው እንዳይቀሩ፣
በተስፋ ጸንተው ነው ዘላለም ሊኖሩ።


ትላንት ሌሊቱን መነጋገሪያ ነበር እናቱ በጠና የታመመችበት አይመስልም እየጀነጀናት መስሏታል የወጣትነት እድሜ አብሯት እየተሳሳቀ ነው የእናቱን ሂሳብ ሊያወራርድ ነው በሆቴሉ የተገኘው የሆቴሉ እንግዳ ተቀባይ ጋር ወሬያቸው ሞቅ ብሏል። አንድ የ26 አመት ወጣት ከፊትለፊቷ ጃኬት ተጀቡኖ ከፊቷ ቆሞ እያወሩ ነው።

ከቀናት በፊት የሊዩጂ ኒኮላስ እናት ይታመማሉ ታድያ በአሜሪካ የህክምና ወጪ ከእኛም ሃገር በበለጠ እጅጉን ውድ ነው ለዚህም ተብሎ የተለያዩ የመድህን ( Insurance ) ተቋማት በዚህ የጤና ዘርፍ ቢሰማሩም ላለመክፈል ግን ሰውን ያንገላታሉ።

የሊዩጂ እናትም ታማ የደረሳት ነገር ቢኖር እንግልት ነበር በዚህም እናቱ በጣም ስትሰቃይበት ጊዜ ሊዩጂ ኒውዮርክ ውስጥ በሚገኘው ሆቴል አመታዊ የመድህን ድርጅቶች ስብሰባ ላይ የተንገላታበትን የአሜሪካ መድህን ድርጅት ዋና ሃላፊ ብሪያን ቶምሰንን ለመግደል ያስባል።

ታህሳስ 9 2024, ኒውዮርክ ሆቴል ውስጥ በመገኘት ከእንግዳ ተቀባይ ሴት ጋር ወሬያቸውን ያደሩታል እርሱ ብሪያን እየጠበቀ ያወራታል። እርሷም በወሬው መሃል ፈገግታዋን እየሰጠችው ማስክህን አውልቅ እስኪ ስትለው ያወልቅና ፈገግ ካለላት በውሃላ መልሶ ያደርገዋል። ከሆቴሉም ወጥቶ በረንዳው ላይ ብሪያንን ጠብቆ ይገለዋል። ከዛም ወደመጣበት በመመለስ ሳለ በዛች ማስኩን ባወለቀበት ቅፅበት ያለችው ምስሉ በካሜራ በመያዙ ፖሊሶች እጅ ይገባል።

ተመልከት ምስሉ ላይ ያለችው እናቱ እንዳትመስልህ ካረን ፍሪድማን ትባላለች። መቼም ላምበርጊኒ መኪና ሲባል ሰምተህ ታውቃለህ የአምራች ድርጅቱ እሳት የላሰች በረዶ ፈልጣ ቤተመንግስት አፋር ላይ ያቆመች ጠበቃ ናት። አሁን ደግሞ ለሊዩጂ ጥብቅና ቆማ ከወንጀሉ ነፃ ልታወጣው ተሰይማለች።

ከአሜሪካኖች ሁለት ነገራቸው ይገርመኛል የፍትህ ነፃነት ስርአታቸው።

ግርምት አንድ ፍትህ

ብሪያንን የገደለበት የቪዲዮ ማስረጃ አለ ግን ሊዩጂም ትላንት ፍርድቤት ሲቀርቡ ሽምጥጥጥ አድርገው ክደዋል ጠበቃዋም ነፃ እንደምታወጣው ታምናለች።

ግርምት ሁለት ነፃነት
አሜሪካ ውስጥ የጠበቆች ክፍያ እና ነፃ ሲወጣ እንዳይቸገር ተብሎ GoFundMe እየተሰበሰበለት ሲሆን አሁን ያለበትን ባላቅም በመጀመሪያ ቀን ነበር ግን $150,000 ዶላሮችን ያለፈው። ከዚህ በላይ አሜሪካኖቹን በየመንገዱ እያቆመ የጠየቀው SkyNews ሁሉም ተጠያቂዎች ሊዪጂ ልክ ሰርቷል የሚሉ ሲሆኑ ጭራሽ ቦስተን ውስጥ ኮንሰርት ተዘጋጅቶ ለሱ አዲስ ሙዚቃ ተዘፍኖለት ነበር።

እኛ ሃገር ቢሆንስ ኖሮ. . . እስክንደርስባቸው ለሌላ ሃገር ፍትህ እንጠይቃለን ፍትህ ለሊዪጂ

(✍️ፕ/ር ሔኖክ አረጋ)


የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አለባበስ ባጠቃላይ በ3 ይከፈላል።

የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አልባሳታቸውን እና ጌጣ ጌጦቻቸውን በጥንቃቄ በመያዝ ልምዳቸው ይታወቃል።

ልብሶቻቸው እና ጌጣ ጌጦቻቸው ጥሩ መዓዛ እንዲኖራቸው የተለያዩ የዛፍ ሥራ ሥሮች ፣ቅጠላ ቅጠሎች እና ቅርፊቶች በማደባለቅ የተቀመመ ንጥረ ነገር ያዘጋጃሉ።

የሲዳማ ሕፃናት ሴት ልጆች የሚለብሱት ከበግ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ (Lande) ይሰኛል።

ወጣት ልጃገረዶች ደግሞ ከውስጥ ቆሎ (Qolo) የሚባል ልብስ የሚለብሱ ሲሆን ከላይ ከጥጃ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ (Qonxolo) ይደርባሉ፡፡

የልጃገረዶች ቆሎ የተሰኘው ልብስ ከጥጥ የሚሠራ ሆኖ ከላይ እስከ ታች ተደርጎ የሚሰፋ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው አዝራሮች፣ ጨሌዎችና ፈትሎች እንዲያሸበርቅን ይደረጋል፡፡

ዕድሜያቸው ለትዳር የደረሱ የሲዳማ ሴቶች ዱቤ (Dubbe) የሚባል ከቆዳ የሚሠራ ልብስ ይለብሳሉ፡፡

ላገባች ሴት ባሏ ዎዳሬ (Woodare) ይገዛላታል፡፡

ዎዳሬ ከበሬ ቆዳ የሚሠራ ሲሆን ቆዳው እጅግ የለሰለሰ ነው፡፡ አለባበሱም በሁለት በማጠፍና በወገብ ላይ በቆዳ የሚሠራ መቀነት በቁኔ (Qu’ne) በማሠር እጥፋቱ ወደ ታች በመልቀቅ ነው፡፡

ለጋብቻ የደረሰች ልጃገረድ ስታገባ ከእናቷ በስጦታ መልክ የሚሰጣትን ዎዳሬ ታጥቃ በልዩ ጌጣ ጌጦች ያሽቆጠቆጠ ለምድ ደርባና ተሞሽራ ስትወጣ በተለየ ሁኔታ የተጌጠ ቆሎና ቆንጦሎ ደርባ ነው፡፡

የሲዳማ ሴቶች ጎርፋ (Gorfa)፣ ቱባ (Tuba)፣ ዱዳ (Dudda)፣ ቦኬ (Boke) የሚባሉ ከቆዳ የሚሠሩ አልባሳትን ይለብሳሉ፡፡

ቦኬ፣ ወዳሬ የክት ልብሶች ሲሆኑ ቱባና ዲዳ በአዘቦት ቀናትና በሥራ ቀናት ጊዜ የሚለበሱ አልባሳት ናቸው፡፡

ከጎርፋ በስተቀር ከላይ የተጠቀሱ አልባሳት ከወገብ በታች የሚታጠቋቸው ሲሆን ጎርፉ በተለያየ ጨሌዎች ያጌጠና ሴቶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ከላይ የሚደርቡት ካባ ነው፡፡

ሁለት ቆንጦሎ ከፊትና ከኋላ በማጠፍ መልበስ በሲዳማ ሴቶች ዘንድ የድሎት ወይም የቅንጦት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በዚህ አለባበስ የሚታወቁ አበዛኞቹ ሴቶች “La’ma Lamu Landite” ተብለው ይወደሳሉ ትርጉሙም በሁለት ለምድ የተቀማጠለች መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡

(አዲስ1879)
(VOA)
እርስዎ የሚያውቁትን ባህላዊ አለባበስ ቢያጋሩን!


በሐመር ወረዳ ሴቶች በሕይወት ለሌለ ሰው ተድረው ከሟች ዘመድ እንዲወልዱ የሚያደርገው ባህላዊ ስርዓት መቀጠሉ ተገለጸ

👉በወረዳው በሩብ ዓመቱ ሦስት ሴቶች በሕይወት ለሌሉ ወንዶች ተድረዋል

በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ሴቶች ለሞተ ሰው ተድረው ከሟች ዘመድ እንዲወልዱ የሚያደርገው ባህላዊ ስርዓት መቀጠሉን የወረዳው ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።

"በወረዳው 'ኮይካ' ወይም ጥሎሽ ለማግኘት ሲባል ሴት ልጅ አትማርም፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ሴት ልጅ የገቢ ምንጭ ተደርጋ በእርሷ ገቢ ወንድ ልጅ እንዲያገባ ይደረጋል" ሲሉ፤ በቢሮው የሴቶችና ሕጻናት መብት ደህንነት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ ሙሉነሽ ጨረና ለአሐዱ ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎም በወረዳው ያለእድሜ ጋብቻ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ቡድን መሪዋ ገልጸዋል።

"በተለይም ደግሞ ለ'ቦርከካ' ወይም ለሞተ ሰው ይዳራሉ፤ ይህ የሚሆነው ለሞተ ሰው ሚስት መኖር አለበት በሚል ምክንያት" እንደሆነ የተናገሩት ወ/ሮ ሙሉነሽ፤ "በዚህ ሳያበቃ ሴቷ ከሟች ዘመድ እንድትወልድ ተደርጎ የሚወለደው ልጅ በሞተው ሰው ሥም እንዲጠራ ይደረጋል" ብለዋል።

በዚህም በወረዳው በ2017 ሩብ ዓመት ሦስት ሴቶች በሕይወት ለሌሉ ወንዶች መዳራቸውን ተናግረዋል።

"በሌላ በኩልም ያለአቻ ጋብቻ በሐመር ወረዳ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ ነው" ያሉም ሲሆን፤ በጣም በእድሜ የገፋ አባት ከስምንት ዓመት ሕጻን ልጅ ጀምሮ እንደሚያገባ ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ሰው ሃብት ካለው፤ ድርብ ጋብቻ ወይም ሁለት ሚስት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ወንድ ልጅ የሚያገባው ከብት መዝለል ሲችል ብቻ መሆኑን በመግለጽ፤ "በዚህ የተነሳ ለወንዱ ቤተሰቦች እንደ ስጦታ የሚታሰብ እናቶችን ጨምሮ ሴቶች ይገረፋሉ" ብለዋል።

በዚህ ምክንያት የሚገረፉ ሴቶች ሰውነት ስለሚተለተል የእጅና የጡት አካል መጉደልን ጨምሮ በሕመም ሲሰቃዩ ቆይተው ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

"ይህን መሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት በወረዳው በስፋት ይስተዋላል" የሚሉት ወይዘሮ ሙሉነሽ፤ ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንደማይላኩም ጨምረው ገልጸዋል።

ወደ ትምህርት ቤት የማይላኩበትን ምክንያት ሲያስረዱም፤ "ሕጻናት ቶሎ ታጭተው ከጥሎሽ ከብት፣ ፍየል፣ ማር እና የተለያዩ መሳሪያዎች የሚገኙ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

"ትልቁና ዋነኛው ችግር ሴት ልጅን አሳንሶ ማየት ነው" ያሉት ቡድን መሪዋ፤ ሴት የንብረት ባለቤትነት እንደሌላትም ገልጸዋል።

"ችግሩን ለመቅረፍ ከግንዛቤ መፍጠር ጀምሮ የተወሰኑ ሥራዎች ቢሰሩም፤ ጠንከር ያለ ሥራ ተስራቷል ለማለት አያስደፍርም" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተጨማሪም "ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሻሻሎችን ያሳዩ አካላትም የማበረታቻ ድጋፍ አልተደረገላቸውም" ብለዋል።

(አሐዱ ሬዲዮ)


🇸🇾 ሶሪያ : ልብ የሚሰበር ክስተት

#Ethiopia | አሳዛኝ እውነት፤ ማንም ሰው መሸከም ከሚችለው በላይ መከራ የወረደበት አባት

አንድ እግሩን በአደጋ በማጣቱ በሁለት ክራንች ( የብረት ድጋፍ) እየታገዘ ይራመዳል ።

ከስደት ወደ ትውልድ ቄዬው ከነልጁ እየተመለሰ ነው።

የስድስት ዓመቱ ኡመር ተልሃ የአባቱን ሰዉ ሰራሽ እግር በሁለት እጆቹ አቅፎ ፈጠን እየለ ለመሄድ በማሰብ ይወተረተራል ። አባቱ አይኑን ከልጁ አልነቀለም ።

የተሸከመው ሰው ሰራሽ እግር እይታውን ጋርዶት እንዳይወድቅ ስጋት ገብቶታል ።
ኡመር አንድ የቀረው ብቸኛው የአይኑ ማረፊያ ነው።

በባዕድ ሀገር በስደት ዓለም ሆስፒታል እግሩ ተቆርጦ ከአጠገቡ ሳይለይ ያስታመመው ትንሹ ኡመር በህይወት ያለው ብቸኛው ልጁ ነው ።

እንደ ዛሬው ሁለቱ ብቻ ሳይቀሩ የዛሬ 11 አመት ጦርነት ሸሽተው አገራቸውን ሶሪያን ጥለው ሲሰደዱ አምስት ነበሩ።

ቆይቶ እዚያው የተወለደው ኡመር ደግሞ 6ኛ የቤተሰቡ አባል ሆኖ ተቀላቀለ ።

በወቅቱ ሰውን ከሚበላው የጦርነት አቶን እሳት መሃል ሙሉ አካላቸውን እና የቤተሰብ ቁጥራቸው ሳይጐድል ቱርክ መግባታቸውን እንደ ትልቅ ዕድል ቆጥረውትም ነበር ።

ከ11 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ለ61 ዓመታት ሶሪያን ረግጦ የገዛው የባዝ ፓርቲ ሲሸነፍ የቱርክ ድንበርን አቋርጠው ሁለቱ ፤ አባትና ልጅ ብቻ ወደ መንደራቸው እየተመለሱ ነው ።

6 አመቱ ኡመር የተወለደው ቱርክ ቢሆንም ያጣውን የእናት ናፍቆት ሶሪያ ባላቸው አክስቱ ፍቅር ሊያስታግስ ጉዞውን ለመጨረስ ጓጉቷል ።

ባለ ክራንቹ መሐመድ እና የአባቱን ሰው ሰራሽ እግር የተሸከመው ከስደት ተመላሽ ኡመርን ያየው የአናዶሉ ዘጋቢ ጠጋ ብሎ ወደ ሀገር መመለስ የሚፈጥረውን ስሜት አባቱን ጠየቀ ።

የመሐመድ ዓይኖች በእንባ ተሞሉ ያሳለፈው መከራ ከፊቱ ተደቀነ ።
የህይወት ታሪኩን ውጣ ውረድና የዕጣ ፋንታን አይቀሬነት ዘርዝሮ ነገረው ።

የዛሬ 11 አመት ባለቤቴንና የዚህን ልጅ ታላቅ ወንድም አለ መሐመድ ወደ ኡመር በእጁ እየጠቆመ ፣ የልጆቼን ወንድ እያት እና የሴት አያትን ይዥ ነበር ቱርክ የገባሁት ።

በዚሁ አገር ደቡባዊ ቱርክ ሃታይ ግዛት የካቲት 6 ቀን 2023 የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰለባ ሆነን እንጂ አለ በትካዜ።

የመሬት መንቀጥቀጡ የበርካቶችን ህይወት ቀጥፎ ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ንብረት አውድሟል፡፡

ከአምስት ቀን ፍለጋ በኋላ በነፍስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሽ ስር እኔና የስድስት ዓመት ልጄ ዑመር ብቻ ተረፈን ወጣን ሲል ዘረዘረ።
በደረሰብኝ ጉዳት ምክንያት አንድ እግሬ ተቆረጠ ።

ታድያ ይህንን እንዴት ብዬ ስሜቱን ልንገርህ ሲል ከእንባው ጋር እየታገለ ገለጸ ።

እኔ የናፍቀኝ የትውልድ ሀገሬ ሶሪያ ስመለስ ልጄ ከአክስቱ ይገናኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ በቃ ይኸው ነው ።
ከመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በኋላ በቱርክ ዜጐች የተደረገልኝ ድጋፍ ከምናገረው በላይ ነው ።

ከህዝቡ በተጨማሪ የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጠይብ ኤርዶጋንን ማመስገን እፈልጋለሁ በብዙ አግዘውኛል ሲል ተናግሯል ።

የሀገሬ ሰው "ለመከራ የጣፈው ፤ ቢነግድ አያተርፈው" የሚለው ይሄኔ ነው ።

ምስጋናው ሀይሉ


ሲያነቃቁን ለምን አንነቃም? ሙተን ይሆን እንዴ?
(አሌክስ አብርሃም)

ለመጀመሪያ ጊዜ self-help book የሚሏቸውን ሳነብ በጣም ነቅቸ ነበር! አስታውሳለሁ የ Rhonda Byrne ን The secret ሳነብ በጣም ከመንቃቴ የተነሳ ለስራ እጀን ከመጠቀም ይልቅ አዕምሮየን ለመጠቀም ወስኘ ነበር። ለምሳሌ መብራት አጥፍቸ ከመተኛት ተኝቸ መብራቱ ልክ እንቅልፍ ሲወስደኝ ይጠፋል ብየ ለራሴ እነግረዋለሁ፤ጧት ስነሳ እንደበራ ባገኘው አልደነቅም፣ ከእንቅልፌ ከመንቃቴ አንድ ደይቃ በፊት በራሱ ጊዜ እንደበራ አምናለሁ። የወሩ የመብራት ሂሳብ ግን የነገረኝ ሌላ ሆነ፤ ተው ወንድሜ በጣም አትንቃ አለኝ። እናም እያጠፋሁ መተኛት ጀመርኩ። ከ1890 ዓ/ም ጀምሮ መብራት ሀይል መብራት ያላጠፋበት ብቸኛ ወር ነበር። ስንነቃ አይወዱ😀

ኦሾን ያነበቡ የኔ ዘመን ወጣቶች ደግሞ "ሐይማኖት ባህል ገለመሌ ከጫነብን ፍዘት ወጣን" አሉና በየመንገዱ ፀጉራቸውን በመፍተል መቆዘም ጀመሩ፤ ይህንንም "ውስጣዊ ንቃት" አሉት። ከአመታት በኋላ ሁሉም ጠበል ገብተው እየጮሁ ከንቃታቸው በጣም ነቁ። በቀን አምስቴ ኡዱ የሚያደርጉ፣ ለጁመዓ የሽቷቸው መዓዛ ከሞያሌ የሚጣራ ፣ እንዴት ያሉ ንፁህ ሙስሊም ወዳጆቸ ሳይቀሩ ጀዝበው ገላቸውን መታጠብ አቁመው ነበርኮ! ስንት ተቀርቶባቸው ተመለሱ። የዛን ሰሞን ወጣቱ ሁሉ ውስጣችን በራልን እያለ ስንት ጨለማ ተከናነበ። ራሳቸውን ያጠፉም ነበሩ። ኦሾና አለቃ ገብርሃና ተረታቸው እንጅ ኑሯቸው አያምርም።

ይሄው በዚህኛው ዘመን ደግሞ አነቃቂወች እንደአሸን ፈሉና "ያሰብከውን ትሆናለህ፣ ነኝ በል፣ አለኝ በል፣ ደርሻለሁ በል፣ እችላለሁ በል፣ በሀሳብህ መኪና አስነሳ፣ አሉ፤ ወጣቱ የሀሳብ መኪና አስነሳ፤ በሀሳብ ሲጋልብ ራሱጋር ተጋጨ፣ ቤተሰቡ ጋር ተጋጨ፣ አገሩ ጋር ተጋጨ፣ፈጣሪው ጋር ተጋጨ ። ከሆነስ ሆነና ለምንድነው በዚህ ዘመን ይሄ ሀሁሉ አነቃቂ ንግግር ያላነቃን? የእውነት የሆነ ጊዜ ያነቃን ነበርኮ፣ እየቆየ ግን እንኳን ሊያነቃን ያስተኛን ጀመረ፤ እኮ ለምን?

የህክምና ባለሙያወች ከተሳሳትኩ አፉ ብለው ያርሙኝና በእነሱ ሙያ Drug tolerance የሚሉት ነገር አለ አሉ፤ በትክክል ከተረዳሁት ለሆነ ህመም የተሰጣችሁ መድሀኒት ከሆነ ጊዜ በኋላ በሽታችሁ ጋር ይግባቡና ፍሬንድ ይሆናሉ። በሽታው መድሃኒቱን ይላመደዋል።ጉቦ እንደበላ ደንብ አስከባሪ በሽታችሁ መንገድ ዳር ሲያሰጣችሁ መድሀኒቱ እንዳላየ ያልፈዋል። ለምሳሌ የእንቅልፍ ችግር ገጠማችሁና በሐኪማችሁ የእንቅልፍ ኪኒን ታዘዘላችሁ እንበል ፤ የመጀመሪያ ሰሞን ድብን ያለ እንቅልፍ ያስወስዳችኋል፤ እየቆየ ሰውነታችሁ ሲላመደው መድሀኒቱን ውጣችሁም ቁልጭ ቁልጭ ስትሉ ታነጋላችሁ። ወይ አይነቱን ወይ መጠኑን ባለሙያ ካልቀየረው በቃ ለውጥ የለም። አይ መጠኑን ራሴ እቀይረዋለሁ ብላችሁ ጨመር አድርጋችሁ ከወሰዳችሁ ደግሞ ትተኙ ይሆናል ግን እንደገና ላትነሱ ትችላላችሁ።

ወደህይወት ስናመጣው እኛ ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ሰዓት ማንኛውንም ማነቃቂያ ከመላመድ አልፈን እንደዘፈን ሸምድደነው አብረን እየደገምነው ነው። ገና ፊቱን ስታዮት አብራችሁ "ብሮሮሮሮሮ" አትሉም?! ለዛ ነው ከነዋሪ መካሪና ዘማሪ የበዛው። የፈለገ ብንመከር ብንዘከር ብንሰበክ ብንወገዝ ወይ ፍንክች። አሁን ሞራል፣ ሐይማኖት፣ የአገርም ይሁን የሰው ፍቅር፣ ይሉኝታ ፣መማር ፣ የራስ ክብር ተተተወዘተ አእምሯችን ተላምዷቸው ተራ ነገር ሁነውብናል።

የሞራል ተቋሞቹ በሞራል ድሽቀት ከተራው ህዝብ ቀድመው ባፍጢማቸው ተተክለዋል፤ የትዳር ሰባኪወቹ ማግባትና መፍታት መድረክ ላይ እንደመውጣትና መውረድ ቀሏቸዋል። እንደውም የጓዳቸውን ውድቀት እንደባንዲራ በአደባባይ እየሰቀሉ እዮልን ባይ ሆነዋል። አሁን እንደህዝብ ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው የሚያነቁን ወይ (((ብር ማጣት))) አልያም (((ብር ማግኘት)))። ይሄ የመጨረሻው ዶዝ(መጠን) ነው! ሰው ክብሬ ገመናየ ማንነቴ የሚለውን ነገር ሁሉ ይዞ ገበያ ከወረደ ምን ይመልሰዋል?! ከዚህ በኋላስ? ምን ያነቃን ይሆን? ምክንያቱም በብር የሚመጣ ንቃት በአንዴ አይረካም፤ እንደአደንዛዢ ዕፅ በየቀኑ መጠኑን እየጨመሩ ካልተወጉት መጨረሻ የለውም። መመለስም መቀጠልም የማንችልበት አውላላ ሜዳ ላይ የሚያስቀር መርገምት ነው!! ምን ላድርግ ቸገረኝ፣ የማደርገው አጣሁ በሚል ሰበብ ከሰውነት ድንበር ከምንርቅ በየግላችን "ይሄንኛው ነገሬ ለገበያ ከሚቀርብ ሞቴን እመርጣለሁ" የምንልለት የሆነ መስመር ልናሰምር ግድ ነው። ሰው ራሱ ወስኖ ያሰመረውን መስመር ከሞት በስተቀር ምን ያሻግረዋል?!


''ተምሬ የት ልደርስ?'' የሚለው አስተሳሰብ እየሰፋና እየሰረገ መምጣቱ አላሳሰባችሁም?

የምር ከማልጠብቃቸው ሰዎች ሁሉ መስማት ጀምሬአለሁ።

ብቸኛው የችግር መፍቻ ቁልፍ ንግድ/ ''business'' እንደሆነ ብቻ እየታሰበ መምጣቱ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ልክ ያልሆነም ነው።

በአንድ ዘርፍ ብቻ ዓለም ልትቆም አትችልም።

በታላላቅ ሃይማኖቶች አስተምህሮ የፈጣሪ ስጦታ የተለያየ እንደሆነ ተነግሮናል። ንግድ ጥበብ ነው። ሁላችንም ነጋዴ ልንሆን አንችልም።

ምርጥ ነጋዴ ለመሆን ራሱ ከፈጣሪ የተሰጠህን ጸጋ በትምህርትና በክሂሎት ልታሳድገው/ልታበለጽገው ግድ ነው።

እሺ አንተ ነጋዴ ሆንክ፤

- ልጅህን ማስተማር የምትፈልገው የት ነው?
መርካቶ ነው?
- ስኳር ሕመምተኛ ሆንክ። የት ልትሔድ ነው?
- ንብረትህን/እድሜህን የሚያሳጣ ችግር ገጠመህ። ጠበቃው ከየት ሊመጣ ነው?
- ልጅህ የመደፈር አደጋ ደረሰባት። ማንን ልትጠራ ነው?
- ሚስትህ ምጥ አፋፋማት፤ ማን ጋ ልትሮጥ ነው?
- ታክስ አናትህ ላይ ቢቆለል ማንን ልታማክር ነው?
- በቅርቡ የሚደረመስ ሕንፃ መሥራት ነው የምትፈልገው?
- ገንዘብህ በአግባቡ ማኔጅ መደረግ የለበትም?
- አዳዲስ ግኝቶችን የሚያመጡልን ተመራማሪዎች አያስፈልጉንም?
.
.
.
ሁላችንም ነጋዴ መሆን አንችልም። ከፈጣሪ የተሰጠንን የተለያየ ጥበብ በትምህርትና ክሂሎት ካዳበርን ባለጸጋነትን የሚከለክለን የለም።

መሠረትን ማናጋት ሁሉንም ሥርዓት ማናጋት ነው። ትምህርት የሁሉም ሥርዓቶች መሠረት ነው። የትምህርት ሥርዓት መበላሸት እና በትምህርት ተስፋ መቁረጥ በሁሉም ሥርዓቶች ላይ ለመቆጣጠር የሚያዳግት የካንሰር ሴል እንደመዝራት ያለ ነው።

Via Hawlet Ahmed

🙏🙏🙏

🌴🌴🌴


'መልኬ-ዜፓም'
=========
ቤንዞዳኣዜፒን (Benzodiazepine) የሚባሉ የአእምሮ መድሀኒቶች አሉ። ሰዎች እንቅልፍ እንዲወስዳቸው (hypnotic)፣ እንዲረጋጉ (Sedative)፣ እና ጭንቀት እንዲቀንስ (anxiolytic) ያደርጋሉ። እነዚህ መድሀኒቶች ጭንቀትን የሚቀንሱት ወዲያው ነው። ሆኖም ግን አእምሮ ላይ ሱስ ሊሆኑ ስለሚችሉ የግድ አስፈላጊ ካልሆነ አይታዘዙም። ሲታዘዙም ሱስ እንዳያስከትሉ ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። በዚህ መደብ ውስጥ ያሉት መድሀኒቶች አብዛኞቹ ስማቸው መጨረሻቸው ላይ 'ዜፓም' አላቸው። ዲያዜፓም፣ ሎራዜፓም፣ ክሎናዜፓም...ወዘተ።

የአእምሮ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ስንማር አማኑኤል ሆስፒታል ዋርድ አራት የመርመርያ ክፍል ብዙ የተናደዱ፣ ወይም በጣም የተጨናነቁ ታካሚዎች የመመርመሪያ ክፍል ገብተው ሲወጡ ተረጋግተው እናያቸዋለን። እዚያ ክፍል ውስጥ "ዳያዜፓም ወይም ክሎናዜፓም የሚሰጣቸው ሰው አለ እንዴ?" ብለን እንገረም ነበር።

ዋርድ አራት የመመርመሪያ ክፍል ዳያዜፓም አይታደልም። አንድ የአእምሮ ሀኪም እጅግ በተረጋጋ ሁኔታ ታካሚዎችን ያናግራሉ። በፅሞና ስለሚያዳምጡና ድምፃቸው በጣም ለስለስ ያለ ስለሆነ ተናዶ የሚጮህን ሰው የማረጋጋት አቅም (soothing quality) አለው- ዶ/ር መልካሙ አግደው። ከዛ በኋላ ሬዚደንቶች 'መልኬ-ዜፓም' የሚል ቅፅል ስም አወጣንላቸው። የተቆጣ ወይም የተበሳጨ ታካሚ ወደ ዋራድ አራት መመርመርያ ክፍል ሲሄድ ካየነው "ቆይ መልኬ-ዜፓም ሲያገኝ ይረጋጋል።" እንል ነበር። 😂

ዶ/ር መልካሙ ለሆስፒታሉ ሰራተኞችና ለሬዚደንቶች መልካም አርአያ ናቸው። ያልተገባ ነገር ከተመለከቱም ረጋ ባለ አንደበት "ልጆች እንደሱ አይደረግም እ?" ብለው ይገስፃሉ።

ለጋለ ስሜት ነገር መፍትሄው ቀዝቃዛ ውሀ እንደሆነ ዶ/ር መልካሙ 'መልኬ-ዜፓም' እየሰጡ በተግባር አስተምረውናል። ዶ/ር መልካሙ ለብዙ አስርት አመታት አማኑኤል ሆስፒታልን አገልግለው አሁን በጡረታ ላይ ናቸው።

ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ስለረጅም ጊዜ አገልግሎትዎ እናመሰግናለን።
ዶ/ር ዮናስ ላቀው


ታሪክ ታሪክ ካሉማ ከመጀመሪያው ነው!
..
.
ታሪክህ...
-2 ኛው ሚኒሊክ በሜንጫ ጡት ሲጨረግድ አይጀምርም!
ወይም...
- ሳባ ለሰሎሞን ገልባ 1 ኛው ሚኒሊክ ከጠይምነቱጋ ጠብ ሲልም አይጀምርም።
.
.
የመጀመሪያውን ታሪክ ለማወቅ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች እንተዋወቅ።
የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች እነማን ናቸው?
.
99 % አንባቢ መልሱን ይስታል።
.
እኔም ለመጀመርያ ስጠየቅ አዳምና ሔዋን ብዬ ስቻለሁ። እነሱ ፍጡራን እንጂ የሰው ልጆች አይደሉም።
.
አቤል እና ቃኤል።
.
አይገርምም የመጀመሪያው ታሪካችን መገዳደል መሆኑ! ቃኤልና አቤል ወንዝ ዳር ተቃቅፈው ሲሮጡ፤ ጋደም ብለው ስለብቸኝነታቸው እያወሩ "እኔ አለውልህ፣ ካንተ ወደማን እሔዳለሁ" ሲባባሉ፤ ምድር የሁለቱ ብቻ የመሆኗ ስፋት አስደስቷቸው ስላላዩአቸው አዳዲስ ቦታዎች በምናብ ሲሔዱ አልተጻፈው። ገደለው ነው ታሪክህ።
.
ታላቅየው ታናሽየው ገደለው።
ለምን?
መስዋእቱ ስለተወደደለት። በማ ስለተወደደ? በፈጣሪው። ታሪክን የምንፈትሽ ከሆነ ግለሰቦቹን የተዋወቅንበት መንገድ ላይ እናተኩር። በጎሳቸው ሳይሆን በስነ-ምግባራቸው ጎልተው ይታያሉ። ስለዚህ ሁለቱን ስብእና(personality) እናድርጋቸውና ቀደዳችንን እንቀጥል። personal-reality።
.
የተገደለው ስብዕና ምን አይነት Reality ነው?
.
1. አቤል።
ጩጬ ነው። የሚደክላት የታላቅ ወንድሙ እህት አሪፍ ነበረች አሉ። (ይሔ በአዋልድ የተጻፈ እንጂ በዘፍጥረት የተጻፈ ስለሆነ በከፊል ተቀብለነው እንቀጥል።) አርብቶ አደር ነው። ይሔ ግን ተጽፏል። ከእለታት አንድ ቀን የድካማቸው ፍሬ ለአምላካቸው በማቅረብ ልማድ ላይ አቤል ከከብቶቹ መሀል የሰባውን ለአምላኩ #ተጨንቆ ያቀርብ ነበር።
.
2. ቃኤልስ?
.
(ይሔ አባታችን ሆኖ ስለሚቀጥል ከአቤል በተሻለ ራቅ እና ጠለቅ አድርገን እንቆፍረዋለን)
.
ቃኤል ታላቅ ነው።
የሚደክላት የወንድሙ መንትያ ጉጭማ ሆናበት ነዶታል አሉ። (ይሔም አልተጻፈም) ገበሬ ነው። አቤል ያቀረበ ቀን እሱም ከፍሬው ለአምላኩ ያቀርብ ነበር።
መተርጉማን ቃኤል #ተጨንቆ ያለማቅረቡን ምክንያት ሲያፈላልጉ በአቤል እህት ጉጭማ መሆን ተናዶ ሊሆን የሚችለውን የሳቡ ይመስላል። ሊያስማም ላያስማማም ይችላል።
.
✔️ ከ ንባቡ ብዙም ሳንርቅ ግን ሌላ ታኮ ብናስቀምጥ የሆነ የትርጉም ገንቦ ይቆማል።
.
.
ከወላጆቹ የሰማው የመዘበጥ ታሪክ አለ። ታሪኩ ያስቆጣው ይመስላል። #ክፍ ብሎ ያባረረን መለማመጥ አያስፈልግም አይነት ቂም።
.
Bro..ወላጆች ከሚኒሊክም ባይጀምሩ የሚነግሩህ የመጠለዝ ታሪክ ከሆነ Fuck it. አትቀበል ዘባጩ ፈጣሪም ይሁን ምኒሊክ #ተዘብጠን_ነበር ካሉህ መሰዋትህን ታበላሻለህ።
.
የሱ ልጆች የመሰሉህን ትጠምዳለህ ነገር።
ግን ደሞ ወላጆቹ ትርክቱን ለታላቅየው ብቻ ስለማይነግሩ እንዴት የተነገረው ቂም ታናሹ ላይ አልሰራም የሚል መከራከሪያ ይነሳል!
(ዘር ሁሉ መልካም መሬት ላይ አይወድቅም። ጭንጫ፣ እሾህ፣አለት ላይም ይወድቃል ብለን ብንመክትስ? 😁 መንታ ሆነው ጽንፍ የረገጡ ወንድማማቾች ብዙ አናቅም!!)
.
እንዲህም ብቻ ላይሆን ይችላል። ቃኤል ግን አምላኩ ለሚበላው #አለመጣሩ ፈጥጦ ታይቷል።
አለመጣር #nihilism! ነው።
.
ኒሒሊዝም "ሁሉ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነፋስን እንደመከተል..." የሚል የጠቢብ ቃል ላይ የቆመ ኩርፊያ። እኮ? ማን የፈጠረውን ከንቱ የምትለው? ግጥምህን ከንቱ ልበል? ሚስትህን ወይስ ልጅህን ጎዶሎ ብዬ ፈገግታህን ልጠብቅ(👊 አፍንጫዬ ላይ)
.
ንግግሩ ወይም ሀሳቡ እውነት ቢሆንኳ ጥበብ ነገር ይጎለዋል። ከንቱ መሆን ወይም መጠለዝ ማነው መጥፎ ብቻ ያደረገው?
.
❤ መፍረስ ውስጥ ህይወት የለምን? ቅጠሎች ባይረግፉ?(አፈር ለምነቱን ያጣል)! በሽታ እንዳይኖር ባክቴሪያ ከምድር ቢጠፋ( ሰገራህ አይበሰብስም)! አሲድ ባይኖር(ጨጓራህ አይፈጭም) ወይም በቀላሉ ሴጣን ገነት እንዳይገባ እባብ ባይፈጠር..አዳም ባይበላ..እግዜር አዳምን ባይፈጥረው
.
.
ስለዚህ ወንድሜ ሆይ እህ ብለህ ስማኝ....ወላጆች "አባትህ ተዘብጦአል"ን ከሚኒሊክም ባይጀምሩ የሚነግሩህ የመጠለዝ ታሪክ ካለ Fuck it. አትቀበል ዘባጩ ፈጣሪም ይሁን ምኒሊክ #ተዘብጠን_ነበር ካሉህ መሰዋትህን ተቀባይ ተጣለህ። ተቀባይ-ነትን ደሞ ትፈልግ የለ?
accepted መሆን😍
በሀይሉ ሙሉጌታ


አልቃሽና አጫዋች
(በእውቀቱ ስዩም)

ቦጋለ በሚባል ስም የሚታወቁ ሁለት ስመጥር ሰዎችን አውቃለሁ፤ የመጀመርያው የ”ፍቅር እስከመቃብሩ” ገበሬ፥ ቦጋለ መብራቱ ነው፤ ሁለተኛው በገሀድ ኖሮ አልፏል፤ድሮ በጎጃም ሽማግሌዎች ክፉ ሰው ሲራግሙ፥ “ ቦጋለ ያይኔ አበባ ስምህን ይጥራው “ይሉ ነበር ይባላል፤

ቦጋለ ያይኔ አበባ ስመጥር አልቃሽ ነበር፤ የጥንት አልቃሾች ቀላል ሰው እንዳይመስሏችሁ፤ በለቅሶ ወቅት የሚታየውን ትርምስ እና ጫጫታ ወደ ኪነጥበብ ትርኢት የሚቀይሩበት ተሰጥኦ ነበራቸው ::

ቦጋለ ያይኔ አበባ በወጣትነቱ ያገሩን መሬት አርሷል፤ እንዲሁም ያገሩን መሬት በእግሩ አዳርሷል፤ ወደ አልቃሽነት ሙያ እስኪገባ ድረስ ግን የረባ ስኬት አላገኘም ነበር፤ ይህንን በማስመልከት፥ እንደ ግለ-ታሪክ እና Cv በምትቆጠርለት እንጉርጉሮው እንዲህ ብሎ ነበር፤

“አርሼም አየሁት ፥
ነግጄም አየሁት
አልሰሰመረም ሀብቴ
አልቅሼ እበላለሁ እንደ ልጅነቴ “

ቦጋለ ያይኔ አበባ ከዘመናት ባንዱ ወግ፥ ደርሶት ሴት ልጁን ዳረ፤ እንጀራ ሆኖት የቆየው ሞት አሁን በሌላ ገጹ ተከሰተ፤ ሙሽሪት በሰርጓ በሳምንቱ ተቀጠፈች፤ እልልታው ወደ እሪታ የተቀየረበት ቦጋለ በተሰበረ ልብ ይቺን ውብ እንጉርጉሮ ወረወረ፦

“እንዲህ ያለ አምቻ፥ ክብሩን የዘነጋ
በፈረስ ሰጥቼው ፥ መለሰልኝ ባልጋ”

ኪነጥበብ ፥ አስቀያሚ መከራን ወደ ውበት መቀየር እንደምትችል ይቺ እንጉርጉሮ ምስክር ናት፤

ከሞት ሁሉ ቅስም ሰባሪው የልጅ ሞት ይመስለኛል ፤ ከወሎ የፈለቀች ከወዳጄ የሰማሁዋት ፥አንድ ጨዋታ ትዝ ትለኛለች፤ አያ ሙሄ የተባለ ገበሬ ልጁ ሞቶበት ፥ጎጆው በርንዳ ላይ ከርትም ብሎ ይቆዝማል ፤ ባለንጀራው አዋ ይመር አጠገቡ ተቀምጧል፤ አዋ ይመር ወዳጁን በቃል ማጽናናት በቂ ሆኖ አላገኘውም ፤ የወዳጁን ልጅ የቀሰፈውን ፈጣሪ ለመበቀል ስለፈለገ ፥ ጠመንጃውን አነጣጥሮ ወደ ሰማይ ተኮሰ፤

ተኩሱ በረድ ሲል አዘንተኛው አያ ሙሄ ወዳጁን እያየ እንዲህ አለ፤

“ካገኘከው ገላገልኸን፤ ከሳትኸው ግን አስፈጀኸን”🙂


#አሁንና_በመጨረሻ
*****
ይህቺ ዓለም ለማንም ደንታ የላትም ። አንተም ለእሷ ደንታ አይኑርህ ። አንተ ኖርክ አልኖርክ ይህቺ ዓለም ምንም አይመስላትም ። አንተ ቁጥር ነህ ። እንዳንተ አይነት የትዬለሌ ሚሊዮኖች በዚያ መንገድ አልፈዋል ። በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩት መሀል አንተ አንዱ ቁጥር ነህ ። ማንም ከዚያ መሀል አንተን ለይቶ አያውቅህም ። ስጋ የለህም ፤ ውበት የለህም ፤ ሀብት የለህም ፤ ልጆች የሉህም ፤ እውቀት የለህም ፤ ዝና የለህም ። ምንም የለህም ። አንተ ራስህ የለህም ። ቦርጭህ ፣ ቁመናህ ፣ ዳሌዋ ፣ ሽንጧ ፣ ስንቱን ያደባደበ ውበት ደም ግባቷ ፣ " በየት አለፈች ? " ያስባለ መልኳ በመጨረሻ አንዱ ጋ አፈር ውስጥ ተጥሎ ሁሉም ረግፎ አንዱ ከሌላው የማይለይ ያገጠጠ አጥንት ሆኖ ይቀራል ። ነበር ነህ አንተ ። ነበርሽ ነሽ አንቺ ። ዓለምን በጥፍርህ ቆንጥጠህ የያዝካት የሚመስልህ ነገር በመጨረሻ በቃ ምንም አይደለም ። አንተም ራስህ ምንም አይደለህም ።

" እፀድቃለሁ " እና " እኮነናለሁ " ን ተወው ። እሱ ባንተ እጅ አይደለም ። በሰሪው እጅ ነው ። ራስህን የማታውቅ ፍጡር የሰሪውን ሀሳብ ልትረዳ አትችልም ። አሁን ነህ አንተ ። ነገ አይደለህም ። ነገ የለህም ። ደግ ብትሆን ፤ መልካም ብትሆን ለአሁን ነው ። ለጽድቅ አይደለም ። አሁን ላይ መልካምነት የሚባል የብዙሀን ስምምነት አለ ። ለእሱ ተዘጋጅ ። ነገን ተወው ። ከሞትክ በኋላ የሚሆነውን በማሰብ ጊዜህን አታቃጥል ። ስለማታውቀው ነገ በማሰብ የምታውቀው ዛሬን አታበላሽ ። ከቻልክ ዛሬህ ነገህን እንዲሰራ አድርገው ። ዛሬን ስራው ። ዛሬ አይቆጭህ ። ዛሬህ ተስፋ መሆን ባይችል እንኳን ፀፀት አታድርገው ። ዓለምን ልቀቃት ። ለህሊናህ እንጂ ለዓለም አትጨነቅ ። ዓለምን ለመለወጥ አትነሳ ። ማንም ዓለምን የለወጠ ግለሰብ የለም ። ይልቁን ህሊናህን ለመለወጥ ተነሳ ። ህሊናህ ነው ዓለም ።

አንተ አሁን ማንንም ሁን ። በመጨረሻ ግን ከታች በምስሉ የምታየውን ነህ ። የአሁን ማንነቴ በስተ ቀኝ የተኛው እንደሚሆን በየዕለቱ አስባለሁ ። ማን እንደዚያ ያልሆነ ፤ የማይሆን አለ ? ማንም የለም ። ለወሬ ነጋሪ የሚቀር እንኳን ማንም የለም ። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁን ፣ ጳጳሱን ሁን ፣ ቱጃሩን ሁን ፣ ማንንም ሁን ፣ ምንንም ሁን ፤ በመጨረሻ ከታች ያለውን ነህ ። ብትፈልግ ለመርሳት ሞክር ። ግን ምንም አይረዳህም ። አይቀርልህም ። እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ሰው መርሳት የሚፈልገው ይህንን ነው ። ለዚህም ይሆናል ክፋታችን የበዛው ። ብትፈልገውም ብትጠላውም በመጨረሻ ላይ " አስከፊ " ውን ምስል ነህ ። እሱን መርሳት ነው ህሊናችንን ሆድ የሚያደርገው ። አፈር ቤት በለው ሰማይ ቤት መቆጨት መናደድ የለም ። መመለስ የለም ። ስህተትን ማረም የለም ። ያኔ ቢቆጭህ የሚቆጭህን ዛሬ አስወግደው ። አውቀን እየካድነው እንጂ ክፋት ይታወቃል ። ሰውን ማስቀየም ፣ ሰውን መበደል ይታወቃል ። እሱን ታገል ።

ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ


ምን አልባት እኛ ያለን የሆነ ሰው ህልሙ ነው!
ምን አልባት እኛ ያለን የሆነ ሰው ፀሎቱ ነው !
ምን አልባት እኛ ያለፈን የማይጠቅመን ነው!
ምን አልባት ያሳመመን ሊያስተምረን ነው!
ምን አልባት የሆንነው የሆኑትን እንድንረዳ ነው !
ምን አልባት የተበለሻሸው እንድንቀያይረው ነው!
ምን አልባት አማራጭ ያጣነው አማራጭ እንድናመጣ ነው !
ŠAdhanom Mitiku


ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ!
ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ!
(አሌክስ አብርሃም)

ፍቅር ብቻውን መልስ የሚሆንበት ጊዜ ላይ አይደለንም።
በማንም ላይ መፍረድ ከባድ ነው። ሲቸገሩ መርዳት አለመቻል ከሚፈጥረው ህመም ለመራቅ ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን እንርቃለን። ዓይናቸው ውስጥ ያለውን ስቃይ ላለማየት ዓይናችንን እንሰብራለን።የአቅማችንን መደገፍ እንኳን ከአቅም በላይ ሆኗል። የተወለድንበት እና ያደግንበት ስር የሰደደ አብሮነት፣ መረዳዳት አሁን እግር ከወርች ካሰረን ኑሮ ጋር አብሮ አልሄድ ብሎ አስጨንቆናል።

ረስተነው ወደወዳጆቻችን መንገድ ከጀመርን ፣ልንደውል ስልክ ካነሳን በኋላ ባዶ አይናቸው እጃችሁ ከምን ቢለንስ ብለን ተመልሰናል። ከመሄዳችን በላይ ምን ይዛችሁ መጣችሁ የሚለን አንደበታቸው ሳይሆን ኑሯቸው ሁኗል። የተጨነቀ መንፈስ፣ የተጨነቀ አየር። የማንንም እርዳታ የማይፈልጉ መንፈሰ ፅኑ ወዳጆቻችን ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነውባቸው በዓይናቸው ባዶ ኪሳችንን ሲቃኙ ብናይ መርዳቱ ቢቀር አንታዘባቸውም። "እንትናም ተቸገረ?" ብለን አናሾካሹክም።

ይገባናል ሰው ወደገደል ቢወድቅ አዳነውም አላዳነውም አጠገቡ ያገኘውን ሳርም ይሁን ቅጠል በደመነፍስ ጨምድዶ እንደሚይዝ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።ልብሳችንን አንቀው የሚማፀኑን እኛም የሌሎችን ልብስ አንቀን መንጠልጠላችንን ያውቃሉ። የመያያዙ መጨረሻ፣ የገደሉ ጫፍ የት እንደሆነ ማን ያውቃል?! እጃችን እየዛለ ነው። ደመነፍስ ላይ ነን። ማንንም ለመዳን እንይዛለን በማንም እንያዛለን። ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ። ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።


በስዕሉ ላይ የወጣትነትና የስተርጅና ሥዕሎች ይታያሉ፣ ጋሽ ስብሐት የጠላውና የተቸው ዕርጅና መጥቶ እፊቱ ገጭ አለ። ጋሽ ስብሐት በመስተዋት ራሱን እያየ በርጅናው ይቀልድ እንደነበረ ይወሳል፣ ቀስ ብሎ ራሱንና ፊቱን እያሻሸ፦

"ተይኮ ተይኮ ተይኮ ተይኮ
እኔ ሰሞንኛ ቆራቢ ነኝኮ
እያሉ በናፍቆት መሰንቋቸው
ወጣትነቴን አስታወሱኝ
ባይቀሰቅሱኝ ምንቸገራቸው?
ውብ ወጣትነቴ ሄደች
እየተንሳፈፈች
ያመጣት የግዜ ወንዝ ወሰዳት
እንግዲህ
ቀስ በቀስ
ሳይታወቀኝ
ግንባሬ እየገፋ
በራዬ እየሰፋ
ሽበቴ እየበዛ
ዕድሜዬ እየገፋ ሄደ
አልፈልግም እምቢ
ማርጀት አልፈልግም
መሞት አልፈልግም
እምቢ አልፈልግም
እምቢ እምቢ እምቢ"

ብሎ ነበር በሌሊቱ አይነጋልኝ ሌላው መፅሐፉ። ዋ! ጋሽ ስብሐት ምስኪንና አሳዛኝ ሠው፣ እምቢ አላረጅም አለ ግን አረጀ፣ እምቢ አልሞትም አለ ግን ሞተ።

ነፍስ ይማር እንላለን፣ ትኩሳት እንደ ተገለፀው ትምህርት አዘል ነው፣ ወጣትነታችሁን ተንከባከቡ ይላል፣ እንዴት ? አንብቡ መልሱ እዚያው አለ።

በቸር እንሰንብት።


ታላቁ ደራሲ / ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፦

ጋሼ ስብሐት ብለው ይጠሩታል ብዙዎቹ፣ ለሕይወት ቁብ የሌለው፣ በመፃፍና በድርሰት የታጠረ፣ ኢንተርቪው ሲደረግ በቀልድ አዋዝቶ የሚመልሳቸው መልሶች፣ ሕይወትንና የኑሮ ውጥንቅጥን አቅሎ የሚያይ፣ በሕይወት የሚያጋጥሙትን ክስተቶች ለመቀበል ቸል የማይል ሠው ነበር ጋሽ ስብሐት።

የፃፋቸውን ድርሰቶችና፣ በጋዜጦችና መፅሔቶች ያስተላለፋቸው ፅሑፎች ሲታዩ ይዘታቸው ገራሚ ነው፣ ቅርፃቸውም የሚያምርና የተሽሞነሞነ። ከጋሽ ስብሐት ድርሰቶች ልብን የሚሠቅሉና በተለዬ መልክ የተፃፉ ትኩሳትና ሌቱም አይነጋልኝ ናቸው፣ ለትውስታ በትካሳት ላይ ከዚህ በፊት ያስተላለፍኩት ፅሑፍ ተለጥፏል። በሌቱም አይነጋልኝ ድርሰቱ ያስተላለፋቸው መልእክቶች ገራሚ ናቸው። በተለይ በአማርኛ ሥነ ፅሑፍ ያልተለመዱ ቃላትን እንደወረዱ ፈሰስ ለማድረግና ታቡን ለመጣስ የመጀመሪያው ሠው ጋሽ ስብሐት ይመሥላል። ለምሳሌ ከዚሁ ድረሰቱ ተቀንጭባ የተለጠፈች ፅሑፍ አለች፣ ስብሐት ለምንም ታቡ ደንታ እንደሌለው የምትገልፅ። በዚያች ፅሑፍ ታቡን አጥባቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የማያጠብቁም ሠዎች "የማይጋሩት" ክስተት እናያለን አንዲት ሴትን ለብዙ መጋራት። በድርሰቱ ሙሉ ተብላ የምትጠራ ከማሚት ጋር የምትኖር ሴተኛ አዳሪ አለች፣ እርሷን አንዱ ለአዳር ይዟት ሄደ ከአምሥት ጓደኞቹም ጋር ተጋሯት፣ ግንኙነትን የፈፀሙ ስድስት ናቸው፣ አንድ ለስድስት ብንል ያስኬደን ይሆን ? በብዙዎች አስተያዬት ይህ ሰብአዊ ባኅሪይ ሳይሆን እንደ እንሰሳዊ ባኅሪይነት የሚታሰብ ነው /የፈረደበት እንስሳ ብዙ ሥም ይሰጠዋል/። በውነት ነውን ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ አይደለም ነው። ስብሐት ያነሳው የሠው ልጅ ከሚኖርበት ሕይወት በመነሳት ነው፣ የሠው ልጅ ጨለማን ወይም አለመጋለጥን ተገን አድርጎ የሚፈፅመው ተግባር። ክስተቱን ፈፃሚዎች እንስሳትም ሠዎችም ናቸው፣ ልዩነቱ እንስሳት በግልፅ የሠው ልጅ በሥውር ማድረጋቸው ብቻ ነው። እንግዲህ ጋሽ ስብሐት የሠው ልጅ በሥውር የሚከውነውን ነው አደባባይ ያወጣውና፣ ጥፋተኝነቱ እምኑ ላይ ነው።

ጋሽ ስብሐት ነባራዊ እውነታን ለምን እንሸፋፍነዋለን ባይ ነው፣ የሚወደደውም በዚህ ፀባዩ ነው። ለምሳሌ ለማንኛውም የሠውነት ክፍል ስም እንዳለው ሁሉ ለመራቢያ አካላትም ሥም አለ። መራቢያ አካላትን በሥማቸው መጥራቱ፣ ሥማቸውን አደባባይ ማውጣቱ ክፋቱ ምንድርነው በማለት ራሡን ከጠየቀና ከራሡ ጋር ከተስማማ በኋላ ነው አደባባይ ያወጣው። በዚህ ቅንጣት እንደማያፍርና ተፈጥሯዊ በሆነ ነገር አፋችንን መሸበብ እንደሌለብን ነው የገለፀልን። ለምሳሌ እንደነ ሮዛ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለትን የመሣሠሉ ድርሰቶች ታቡን መጣስ የተማሩት ከጋሽ ስብሐት እንደሆነ ይታሠባል።

ይህን ከብልግና ጋር የምናያይዘው ከሆነ ነው ትልቁ ስሕተት፣ ተፈጥሮን በተሠጠው ሥም በአደባባይ መጥራት በምንም መልኩ ብልግና ሊሆን አይችልም፣ ይህን እውነታ የማንም ልብ ሊዘነጋው አይገባም ከነባራዊ እውነታ ልንርቅ ስለማንችል።

በተለጠፈው ትኩሳት ድርሰቱ አስተያዬት ላይ ብዙ ሀሳቦች ተሰንዝረዋል የጋሽ ስብሐት፣ በዚያ ድርሰቱ ብዙ ነገር እንዳስተማረን፣ ወጣትነትን፣ እርጅናን፣ ሪቮሊሲዮንን፣ ፍቅርን፣ የመለየት ምሬትን፣ የጓደኝነት ሚስጥራትን፣ ሌሎችንም ክስተቶች። የተለጠፈውን አስተያዬት አንብባችሁ ተረዱ፣ ሀሳብም ሰንዝሩ። አስተያዬቱን እነሆኝ፦

ትኩሳት የስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ወጣትነት ትውስታ ድርሰት፦

ስብሐት በወጣትነቱ፣ ስብሐት በስርጅናው ስዕሎቹ እታች ይታያሉ፣ ስብሐት ወጣትነትን እንደሚያደንቅ ሁሉ እርጅናን ይፈራ ነበር፣ እርጅና ቃሉ ያሸማቅቀዋል። በፈረንሣይ ሀገር የ፪ኛ ዲግሪ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት በየቦታው የፈረንሣይ ሴትና ወንድ አዛውንቶች ያጋጥሙታል፣ የእርጅናንም አስፈሪነት ያስገነዝቡታል፤ ስብሐት ይህንን በትኩሳት መፅሐፉ እንዲህ ይገልፀዋል፦

" በጣም ይቀፋሉ የፈረንጅ ሽማግለዎችና አሮጊቶች። ጨምዳዳ ቆዳቸው የተሰነጣጠቀ ደረቅ ሠም ይመስላል። ቀጥቃጣዎች። ዝምተኞች። አገጫቸው ተገንጥሎ ወደ ታች የወደቀ፣ ከንፈራቸው የተንጠለጠለ፣ ጥርሳቸው የፈራረሰ ሽማግሌዎች። ጥርሳቸው አልቆ አፋቸው ወደ ውስጥ የጎደጎደ ፅማም አሮጊቶች። የመኖር ግዜያቸው አልፎ የሞት ግዜያቸውን ዘመናዊ ህክምና ከልክሏቸው ፣ ታችኛ ከንፈራቸውን እንደ ጡጦ እየጠቡ ሞትን ሲጠብቁ የሚውሉ የሕይወት ኦናዎች። ለዓይን ብቻ ሳይሆን ለአፍንጫም ይቀፋሉ ። የልዩ ልዩ መድኃኒት ፣ የእርጅና፣ የሞት ሽታ፣ ሳይቀበር መግማት የጀመረ ሥጋ።"

ለስብሐት አስፈሪው እርጅና እንደዚያ ነበር የሚታየው፣ አበስኩ ገበርኩ የሚያሰኝ፣ ተላላፊ በሽታን የመሠለ። ወጣትነትስ? እንዲህ ይገልፀዋል፦

" ጥሩ ነው ወጣት መሆን ገንዘብ ባይኖርህም ጤና ይኖርሀል፣ መልክ ባይኖርህም አንጎል ይኖርሀል፣ ዕውቀት ባይኖርህም ጉራ ይኖርሀል፣ ፍቅር ባይኖርህም ተስፋ ይኖርሀል፣ ደስታ ባይኖርህም ንዴት ይኖርሀል፣ መጨቆን ቢኖርብህ ሪቮሉሽን ታነሳለህ-------መኖር ቢያስጠላህ ወይም ቢያቅትህ ራስህን ትገድላለህ፣ ሠው ባያውቀም ቅሉ ታሪክ ይኖርሀል ወጣት ነህና።"

ወይ ጋሽ ስብሐት የሚገርም ነው። እስቲ የንዴት መኖር፣ የጉራ መኖርና ራስን መግደል እንዴት እንደ መፍትሔ ሀሳብ ይቆጠራል። ምናልባት የወጣትነት ድፍረትና ቆራጥነት እነዚህንም እንደ መፍትሔ ሀሳብ ያስቆጥር ይሆን።

ጋሽ ስብሐት በትኩሣት መፅሐፉ ብዙ ነገር ይላል፣ በብዙ ነገር ይፈላሰፋል፣ በፈረንሳይ ተማሪ በነበረበት ግዜ ማነሁለል ይችልበት ነበር፣ ከቆነጃጅት የፈረንሳይ እንስት ወጣቶች ጋር ዓለሙን ቀጭቷል፣ በቋንቋው ያነሆልላል፣ ዐዕምሮው ለዕውቀት ክፍት ነበር፣ በጥቂት ግዜ የፈረንሳይኛ ቋንቋን በቁጥጥሩ ስር አድርጎት ነበር፣ ችሎታው በዛዚ ርዕስ የንኮሎን መፅሐፍ በአማርኛ እንዲተረጉም አብቅቶታል፣ ጨዋነቱ፣መልከ መልካምነቱና ከፍተኛ የቀለም ቀበኛነቱ ተወዳጅነትን አትርፎለት ነበር።

የምትወደውንና መልከመልካሟን ፈረንሣይት ወጣት እንዲህ ይገልፃታል፦

" ሲልቢ በጣም ቆንጆ ናት፣ እጥር ምጥን ያለች ፈረንሳዊት ሆና ቡናማ ጉልህ አይኖችዋ ውስጥና ውብ አፍዋ ዙሪያ እንደ ነበልባል የሚውለበለበው ፈገግታዋ ልብ ያሞቃል። ወደ ኋላ የተለቀቀው ንፁህ ጥቁር ፀጉሯ ያብለጨልጫል ------ከታች ደግሞ አበጥ ያለው ዳሌዋ እንደ ፀጉሯ ይወዛወዛል። እግርዋ በብዙ ጥንቃቄ የተቀረፀ ውብ ፍጥረት ነው። ፍቅርም ምቾትም የምትቀሠቅስ ወጣት ትመስላለች።"

ስብሐት ቀላል ሠው አልነበረም። በሲልቢ እጅግ በጣም የሚወደድና የሚፈቀር ወጣት ነበር። በመፅሐፉ እንደተገለፀው የስብሐት ጨዋነትና በራስ ላይ የነበረው ዕምነት፣ ደንታ ቢስነት ብዙም ለሴትም ሆነ ለሌላ አለመጨናነቅ በሲልቢ ተወዳጅ አድርጎታል። ባይታወቅበትምና በድብቅ ቢይዘውም ቅብጥብጥ ወጣቷን ማፈቀሩና እንደምታስቀናውም በመፅሐፉ ገልጿል።

ባጠቃላይ ትኩሳት መፅሐፉ ትኩስ ጉልበት ስላለው የወጣቶች ከስብሐት ስራዎች ቀዳሚ ምርጫ መሆኑን ብዙ ወጣቶች ያወሳሉ።

በዚህ መፅሐፉ ስብሐት ስለ ፍቅርና ቅናት ተቃርኖና ጥምርታዊ ግንኙነት፣ ገፅታን ስለማንበብ፣ ስለ ሪቮሊሲዮን፣ የወጣትነትና አዛውንትነት የሕይወት ሂደት፣ የሴት ልጅ ውበትና መስህብነት፣ የፍቅር ሳይኮሎጂ፣ የቋንቋ ክህሎት ጠቀሜታ፣ ሠውን ከእንስሳት የሚለዩ ሠብአዊ ባኅሪያት፣ የወጣትነት ትርጉምና መገለጫዎቹ፣ ግዜን ስለ መመንዘርና መጠቀም፣ ምሳሌያዊ አገላለፆች፣ ስለ ጭቡና ጭቆናንም አካቶ በሚያስደምም ሁኔታ ከሽኖ አቅርቧል።


''ሰው ሲታመም የምንጠይቀው ከቋጠሮ ሰሐን ጋር ነው"
አለማየሁ ገላጋይ

ሰው ሲታሰር ' እግዚአብሔር ያውጣህ ' የምንለው ከፍትፍት አገልግል ጋር ነው ....አራስ የምትጠይቀው ከፔርሙዝ አጥሚት ጋር ነው ... የክርስትና አባታችን ለፋሲካ አክፋዩን የሚጠብቀው ድፎ ዳቦ ና አረቄ ነው ...እዝንተኛ የምናስተዛዝነው ሰባት እንጀራ ከአንድ ሰሐን ወጥ ጋር ነው ...ሟች የምንሸኘው ከገንቦ ጠላና ከለምለም እንጀራ ጋር ነው ...የቅዱሳንና የመልአክታት ተራዳኢነት የሚጎበኘን በስማቸው ከዘከርን ነው።

...ሰዕለታችን በሬ ወይም በግ ነው ...ሰርጋችን ፣ ልደታችን፣ እርቃችን፣ ሹመታችን፣ አምልኳችን፣ የሚበላ ነገርን ሙጥኝ ያሉ ናቸው ... ...ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው ተምሮ ሲመረቅ ይዘን የምንሄደለት ስጦታ ብዕር ወይንም መጽሐፍ አይደለም ፤ ኬክ ፣ ብርቱካን ፣ ሙዝ ...ነው ።

በሽተኛ ስትጠይቅ ከብርቱካንና ከሙዝ ይልቅ መጽሐፍ መውሰድ እንደማላገጥ ይቆጠራል ። ጊዜውን ይገፋበት ዘንድ መጽሐፍ ማበርከት በሽተኛው እንዳይድን ከመመኘት እኩል ነው ። ለኛ ለኢትዮጵያውያን መጻሕፍት ከባዶ ገበታችን በስተዚያ የተቀመጡ ትርፍ ነገሮች ናቸው ። መጻሕፍት የሚያስፈልጉት ገበታችን ሞልቶ ከገነፈለ በኃላ ነው ብለን በይነናል። ገበታችንም አይሞላ ፤ መጻሕፍቱም አይነሱም ። ያልተረዳነው ቢኖር ለገበታ መትረፍረፍ ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ መጻሕፍት አቋራጭ መንገድ መሆናቸውን ነው ።እንዴት ታዲያ ማንበብ መብላትን ይቅደም ? መቼ ይሆን ከምንኮራባቸው ባህሎቻችን በላይ ማንበብ ባህላችን ሆኖ የምንታወቅበት ናየምንኮራበት?......'''''

አለማየሁ ገላጋይ

20 last posts shown.

6 642

subscribers
Channel statistics
Popular in the channel

#ልዩመረጃ ትናንት ምሽት በደቡባዊ ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የታየው ክስተት የሰው ሰራሽ ጠፈር ስብርባሪ ወደ ምድር ንፍቀ ክበብ ሲመለስ የተፈጠረ መሆኑን የአው...
ይድረስ ለወገን ደራሽ🙏🙏 ከስር በፎቶ ላይ የምትመለከቷት ልጅ ተምራ ራዕዋን አሳክታ እራሷን ችላ ለሌላ መትረፍ በሚትችልበት ጊዜ ባጋጠማት ህመም ከቤት ው...
https://www.tiktok.com/@ferhanhabesha?_t=ZM-8t9iXVhZBBu&_r=1
ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ “አሞራው ካሞራ” ሲል ያዜመላቸው… ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ ከሰሞኑ በለቀቀው የብዙዎችን ቀልብ በሳበው ነጠላ ዜማው “አሞራው ካሞራ...