ETHIOPIAN BEST PHOTO AND ORTHODOX TEWAHDO MAZEMURE


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: Religion


በዚኽ ቻናል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተዘጋጁ መዝሙራት እንዲሁም ሥዕለ ቅዱሳን እና ምርጥ እና የሚመቹ ደስ የሚሉ ፎቶዎች ይለቀቅበታል
ማንኛውንም ሀሳብ አስተያየት ካለ እንዲሁም አንዲለቀቅ የምትፈልጉትን ፎቶዎች እና መዝሙሮችን በዚህ ሊንክ አድርሱን 👉👉👉 @Mtrsetbot👈👈👈

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
Religion
Statistics
Posts filter




✥✥✥✥ በዚህች ዓለም ውስጥ የማይለወጥ ምንም የለም " ✥✥✥
እግዚአብሔርን የምትወዱት ይልቁንም እግዚአብሔር የሚወዳችሁ ክርስቶሳውያን ይህን እናውቅ ዘንድ እላችኋለሁ ።

በዚህች ዓለም ያለ ነገር ሁሉ መለወጡ አይቀርም ። ጤንነት በደዌ መለወጡ አይቀርም ፤ ሀብት በድህነት ፤ ክብር በውርደት ፤ ሹመት በሽረት ፥ ጥጋብ በረኀብ ፥ ሰላም በጦርነት ፥ ኃይል በድካም ፤ መግዛት በመገዛት ፥ ውበት በጉስቁልና ፥ ነጻት በባርነት ፥ አንድነት በብቸኝነት ፥ ዝና በኀፍረት ፥ ደስታ በኀዘን ይለወጣል ። ሕይወት በሞት ይለወጣል ።

ሰዎች እነዚህን ጉዳዮች መዘንጋታቸው ሁለት ችግሮን ያመጡባቸዋል ። የመጀመሪያው እጅግ ከመቀናጣት የተነሣ ቸልተኞቾ ፥ ለመንፈሳዊነት ግድ የለሾች ፤ ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን ደካሞች ፥ ጥጋበኞች ይሆናሉ ። እነዚህ ሰዎች ለፍላጎታቸው የሚስማማ እምነት በተነሣ ቁጥር ይኮበልላሉ ። ለሰውም የማያዝኑ አረመኔዎች ፥ ድኻ አስጨንቀው ቀምተው የሚከብሩ ፥ ሕዝብ ገድለው የሚሾሙ አውሬዎች ይሆናሉ ።

ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ አይነት ሰዎች ቁሳዊያን ናቸውና የዓለምን ከንቱነትን ያልተረዱ የዓለምን ግሣንግሥ መሠረት አድርገው የሚደሰቱ ስለሆኑ አንድ ነገር በጎደለ ቁጥር ጭንቀታሞች ናቸው ። ሳይነኳቸው ይደማሉ ፥ ሳይገድሏቸው ይሞታሉ ፥ እየተመሰገኑም ተሰደብን ይላሉ ። የዓለም ነገር ደስታነቱ ለዚያች ሰአት ብቻ ስለሆነ ቀጥሎ ደግሞ ሌላ ደስታ ያሻልና ዓለምን የሚወድ ሰው ሁል ጊዜ ብኩን ይሆናል ።

ከቅዱሳን አንዱ እንዲህ አለ ። ይህቺን ዓለም የሚወድ ሰው የአዳኞችን ውሻ ይመስላል ። የአዳኞች ውሻ አድኖ እንስሳ ባይዝም ይደበደባል ። ቢይዝም ይደበደባል ። ቢይዝ የሚደበደበው የያዘውን እንስሳ በአዳኞች ስለሚፈለግ እንዳይበላው ነው ። ባይዝ መደብደቡ ለምን አልያዝክም ተብሎ ነው ። ይህቺን ዓለም የሚከተል ሰውም እንዲሁ ነው ። ባያገኝ በማጣቱ ያዝናል ፤ ቢያገኝ በመለየቱ በማለፉ ያዝናልና ።

እንዲህም ስለሆነ በተሾምህ ጊዜ እንደምትሻር አስብና ቅን ፍረድ ። ባገኘህ ጊዜ እንደምትደኸይ አስበህ ሥጥ ፥ ንብረትህ ፈጥኖ ሳይሸሽህ አንተ ለድኾች በመስጠት ቅደመው ፥ በጤንነትህ ጊዜ ደዌ እንዳለ አውቀህ የታመመ ጠይቅ ካለህ ጊዜ ድኾችን የታመሙትን ለመጎብኘት ጊዜ ይኑርህ ፤ ዝና ባለህ ጊዜ የሚበልጡህ ዝነኞች ሲመጡ እንዳትዋረድ ሰዎችን አታዋርድ ። ኃይል ባጣህ ጊዜ ኃይለኞች እንዳያስጨንቁህ በኃይልህ ዘመን ሰው አትግፋ ። ደስ ሲልህ የኀዘን ቀን አለና ከተጨነቁት ጋር አብረህ እዘን ። ውበትህ የሚጎሰቁልበት ዘመን ይመጣልና ውበቴ ይታወቅልኝ አትበል ፥ ነገ በሚገሰቁል ውበትህ ሰዎችን አሰናክለህ የዘለዓለም ጉስቁልና እንዳያስከትልብህ ተጠንቀቅ ። ይህ ዓለም ቁም ነገር አይምሰልህ ፤ ለመጣል ይስብሃል እንጅ ስትወድቅ የሚያነሣህ አይምሰልህ ። ስለዚህ ብላሽ የሆነን ዓለም አገኘሁ ብለህም ደስ አይበልህ አጣሁት ብለህም አትዘን ።

ዓለምን መውደዴን በምን አረጋግጣለሁ ትለኝ እንደሆነ አንድን ነገር ፈልገኸው ስታጣው የምታዝን በመሆንህ ነው ። ዳግመኛም አግኝተኽ በማጣትህም ስትተክዝ ነው ። ዓለም ከንቱ ነው ካልክ መመሪያህ የጻድቁ ኢዮብ ሕይወት ይሆናል ። ስታገኝ እግዚአብሔር ሰጠ ስታጣም እግዚአብሔር ነሣ ትላለህ ማለት ነው ። ክርስቲያናዊ ሕይወትህ በማጣትና ማግኘት ላይ እንዳይመሠረት ተጠበቅ ። ሳገኝ እንዲህ አደርጋለሁ አትበል ፥ በሌለህ ነገር እግዚአብሔር አይፈርድብህምና ። ስለሌለኝ ነው መልካም ያልሆንኩት ብለህም አታመካኝ ። ድኽነት ከጽድቅ አያስቀርምና ። መንግሥተ ሰማያትን ሰብከው ያወረሱ አንዳች የሌላቸው ሐዋርያት ናቸውና ።

ዓለም መለወጡ የማይቀር ነው ስንል በክፉ ብቻ አይደለም ። በመልካምም ነው እንጅ ። መልካሙ በክፉ እንዳለፈ ክፉውም በመልካም ማለፉ አይቀርም ። ሠለስቱ ደቂቅን ያከበሩ ባቢላውያን ማክበራቸውን ትተው በእሳት የወረወሩበት ቀን መጥቷል ። ከእሳቱ ደኅና ወጥተው ንጉሡ ራሱ እንደሰገደላቸውም ግን አትዘንጋ ።

የፈርዖን ጭካኔ እንደነበረ የሙሴ ነጻነት መጥቶ የለምን ? ምን በዚህ እንደነቃለን ! የአምስት ሺው ዘመን የዲያብሎስ መንግሥት በክርስቶስ መስቀል ፈርሶ የለምን ! ምንም መከራ ቢደርስብን መከራው እንደሚያልፍ እንወቅ ፥ እስንሞት የማያልፍ ቢሆን እንኳን ስንሞት እናርፈዋለንና ለመንግሥቱ እንቸኩል ።

ይህን በዐይነ መንፈስ ያየ ቅዱስ ይስሐቅ እንዲህ አለ ፦
" ኢተሃሊ ከመ ምንትኒ ዘውስተ ዓለም ዘኢይትወለጥ ከመዝ ሀሉ - በዚህ ዓለም ካለው ምንም ምን ቢሆን አይለወጥም
አትበል ። ዓለም ኃላፊ ነው እያልክ እንዲህ ሆነህ ኑር እንጅ "።

"ርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረኪዳን"




ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ!
ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ!
(አሌክስ አብርሃም)

ፍቅር ብቻውን መልስ የሚሆንበት ጊዜ  ላይ አይደለንም።
በማንም ላይ መፍረድ ከባድ ነው። ሲቸገሩ መርዳት አለመቻል ከሚፈጥረው ህመም ለመራቅ ከምንወዳቸው  ወዳጆቻችን እንርቃለን። ዓይናቸው ውስጥ ያለውን ስቃይ ላለማየት ዓይናችንን እንሰብራለን።የአቅማችንን መደገፍ እንኳን ከአቅም በላይ ሆኗል። የተወለድንበት እና ያደግንበት ስር የሰደደ አብሮነት፣ መረዳዳት አሁን እግር ከወርች ካሰረን ኑሮ ጋር አብሮ አልሄድ ብሎ አስጨንቆናል። ረስተነው ወደወዳጆቻችን መንገድ ከጀመርን ፣ልንደውል ስልክ ካነሳን በኋላ ባዶ አይናቸው እጃችሁ ከምን ቢለንስ ብለን ተመልሰናል። ከመሄዳችን በላይ ምን ይዛችሁ መጣችሁ የሚለን አንደበታቸው ሳይሆን ኑሯቸው ሁኗል። የተጨነቀ መንፈስ፣ የተጨነቀ አየር። የማንንም እርዳታ የማይፈልጉ መንፈሰ ፅኑ ወዳጆቻችን ነገሮች ከአቅም በላይ ሆነውባቸው በዓይናቸው ባዶ ኪሳችንን ሲቃኙ ብናይ መርዳቱ ቢቀር አንታዘባቸውም። "እንትናም ተቸገረ?" ብለን አናሾካሹክም። ይገባናል ሰው ወደገደል ቢወድቅ አዳነውም አላዳነውም አጠገቡ ያገኘውን ሳርም ይሁን ቅጠል በደመነፍስ ጨምድዶ እንደሚይዝ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።ልብሳችንን አንቀው የሚማፀኑን እኛም የሌሎችን ልብስ አንቀን መንጠልጠላችንን ያውቃሉ። የመያያዙ መጨረሻ፣ የገደሉ ጫፍ የት እንደሆነ ማን ያውቃል?! እጃችን እየዛለ ነው። ደመነፍስ ላይ ነን። ማንንም ለመዳን እንይዛለን በማንም እንያዛለን።  ችግራችሁን እያየን ያልደረስንላችሁ ይቅርታ። ችግራችንን እያያችሁ ያልደረሳችሁልንም ይቅርታ። ሁላችንም ገደሉ ውስጥ ነን።




➣በሥራ ወይም በሌላ አጋጣሚ የዶሮ እርባታ ሥፍራዎችን፣ የቆዳ ፋብሪካዎችን፣ የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማቀነባበሪያ ቦታዎችን የመጎብኘት ሁኔታ አጋጥሞን  ከሆነ  መጥፎ ጠረኑ አፍንጫችንን እንድይዝ አስገድዶን ሊሆን ይችላል። በተለይም ራሳችንን እንደ ቀበጥ የከተማ ልጅ /City boy/ የምንቆጥር ከሆነ የመጥፎ ሽታውን ጠረን ለመቋቋም በጣም እንቸገራለን~እንዴውም "ኡፍፍፍፍ" እያልን እንጠየፋለን።

  ወዳጄ ሆይ~ እየሸተተን ያለው ግን አዛባና የዶሮ ኩስ ሳይሆን የገንዘብ /ዶላር ሽታ ነው። it's the smell of money. በዓለማችን የዚህን አዛባና ኩስ ሽታን ተቋቁመው ጠንክረው በመሥራት ወደ ከፍተኛ የብልጽግና ማማ ላይ የተፈናጠጡ አያሌ ባለጸጎች እንዳሉ ፎርቢስ ላይ ማንበብ ወይም በዙሪያችን ያሉትን ጥቂት ባለጸጎች መመልከት በቂ ነው። በከተሞች መንገድ ላይ የተከመረ ቆሻሻን በማጽዳት፣ እንደ ችቦ ብርሀን በመፈንጠቅ የሥራ ባህልና ሞራል ለገነቡልን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል።

ከእውነተኛ ሀብት ጀርባ ሁልጊዜ ትልቅ ድካም፣ ትልቅ ትዕግስት፣ መጥፎ ጠረን የተሞላ የሥራ ቦታን መታገስ፣ እንቅልፍ የሚያሳጣ ረጅም የሥራ ሰዓት፣ ጅማት የሚያዝል ጡንቻ የሚያሸማቅቅ አድካሚ ሥራ፣ አዕምሮ የሚያነሆልል እሳቤ የሚጠይቅ ተግባር፣ የእጅ መዳፍ የሚገሸልጥ፣ የእግር ተረከዝ የሚሰነጥቅ፣ ጥፍርን የሚቀረድድ አድካሚ ሥራ መሥራት፣ ወገብ የሚያንቀጠቅጥ ተጋድሎ መፈጸም የግድ ይላል። በእንዲህ ያለ ድካም የሚገኝ ገንዘብ የኅሊና እርካታ፣ የሞራል ልዕልና ከምቾት ጋር ያጎናጽፋል። እንዲህ ባለ ሁኔታ የሚገኝ ሀብት ባለ ጸጋ ያደርጋል። ባለጸግነት የሞራል ልዕልና ደግሞ ትጋትን፣ ቅንነትና እውነትን ትይዛለች። ገንዘብ በስርቆትና መሰል በማጭበርበር ተግባራትም ሊገኝ ይችል ይሆናል። በዚህ መልኩ የተገኘ ገንዘብ ሀብታም ያደርግ ይሆናል እንጅ ባለጸጋ አያደርግም።

በአገራችን ብዙ ሀብታሞች አሉ፤ ብዙ ባለጸጎች ግን የሉንም። ሀብታሞች ከባለጸጎች የሚለዩት ገንዘብ የሚያገኙት የሌሎችን በመቀማት፣ ጉልበት በመበዝበዝና እንዲሁም በማደህየት ሲሆን ባለጸጎች ግን ሀብትን በድካማቸው ይፈጥሩታል። ታላቁ የአሜሪካ የመኪና አምራች ኩባንያ ባለቤት ሚስተር ፎርድ ሥራውን የጀመረው አካፋና ዶማ በማምረት ነበር። ባለጸጎች ለሌሎች ይተርፋሉ እንጅ አይቀሙም።

ሀገራችን ባሳለፈቻቸው ሰላሳና አርባ ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት ጭላንጭል ቢታይበትም በሞራልና በሕግ ባለመመራት ብዙ ባለ ሀብቶችን እንጅ ብዙ ባለጸጎችን አልታደለችም።

እነዚህ ድካምን ሳያዩ፣ ልፋትን ሳይቀምሱ ገንዘብ ያግበሰበሱ ባለሀብቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ከማናጋታቸው በላይ በወጣቱ ሥነልቦና ላይ የፈጠሩት ጠባሳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ ከጠባብ ወደ ሰፊ፣ ከውድቀት ወደ ስኬት፣ ከኮረኮንች መንገድ ወደ ደልዳላ ጉዞ፣ ከመሳሳት ወደ መታረም፣ በመጨረሻም ከማጣት ወደ ማግኘት ከአካልና ከአዕምሮ ብስለት ጋር እንደሚታደግ ለወጣቶች ያስተማራቸው አርዓያ የሚሆናቸው አልነበረም።

  ትናንት ምንም ያልነበረው ሰው ድንገት ዛሬ በርካታ ሚሊዮን ብሮች፣ ብዙ ህንጻዎች፣ ቅንጡ ተሽከርካሪዎች፣ በርካታ ድርጅቶች እንዳሉት ይሰማሉ። በቃ የሀብት መንገድ አጭርና አቋራጭ ብቻ እንደሆነ፣ በድካም በጊዜ ሂደት መበልጸግ ሞኝነት እስኪመስላቸው ድረስ ስነ ልቦናቸውን የተጣመመ ሆኗል።

በጥቅሉ ከባለጸጎች ስኬት ጀርባ ብዙ የፈሰሰ ወዝ፣ የተንጠባጠበ ላብ፣ የተኮማተረ ጅማት፣ የታጠፈ አንጀት የተላጠ ትከሻ አለ። ከሀብታሞች ታሪክ ጀርባ ግን ቅሚያ፣ ጉልበት ብዝበዛ፣ ውንብድና እና ማጭበርበር አለ። ሀብት ከፈጠረው የቀላ ደረት፣ የወዛ ፊት ጀርባ የቆሸሸ ህሊና ሊኖር ይችላል።

ከህይወት ልምዴና ከመጽሀፉ ንባብ የተረዳሁት  "የገንዘብ ሽታ ፍልስፍና" ነገር ቢኖር~ የንጹህ ገንዘብ ሽታ የከብት አዛባ፣ የዶሮ ኩስ ሽታ ነው። የእውነተኛ ገንዘብ ጠረን የጭቃ፣ የኬሚካል፣ የጭስ፣ ከሰውነት ድካም የሚመነጭ የላብ ጠረን ነው። አሁን ሲገባኝ ለካ መጥፎ ሽታ የከብቶች አዛባ አይደለም፣ የዶሮ ኩስም አይደለም፣ የድካም ላብ ጠረንም አይደለም። መጥፎ ሽታ ድህነት ነው። መጥፎ ጠረን የሰው እጅ ማየት፤ ተቸግሮ ከሠው ፊት መቆም ነው። መጥፎ ቅርናት ማለት ስንፍናና ስርቆት ነው። ክርፋት ማለት ውድ ሱፍና ካራባት ለብሶ እንደ አገር እርዳታ መቀበል ነው።

#ችቦ መጽሀፍ~ዘር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሀይማኖት ቢለያየንም በዓለም ላይ ያለ ሁሉ የአንድ አዳምና ሄዋን ልጅ ነው። ትክክልና ስህተት /Right and wrong/ ለሁሉም ተመሳሳይ ነው።  በሞራልና በዕምነት ጎዳና ላይ ከሚያሳስቱን ይልቅ የሚያርሙን ይበልጣሉ። ከሚያሰናክሉን ይልቅ የሚያርሙን ይልቃሉ። ከዛህ ረገድ ከያዝነው መርህ መንሸራተት እንደሌለብን በአጽንኦት ይነግረናል። "Take care your self! Do not slide down from your principles!"

መጥፎ በምንለው የአዛባ ሽታ፣ አስቀያሚ በምንለው የዶሮ ኩስ ጠረን ውስጥ ገንዘብ ይታፈሳል፣ ላብን በሚያንጠባጥብ ከባድ በምንለው ሥራ ውስጥ ወርቅና ዳይመንድ ይገኛል። ሽታውን ውደደው፣ ሽታው የገንዘብ /የዶላር ነው። it's the smell of money. Don't Worry!

እኔም ከዓመታት በፊት ቀለምና ቡርሽ አዋህጄ ስዕልና ጽሁፍ እየሰራሁ በነበረበት ወቅት የቅርብ ጓደኞቼ የቀለሙንና የማዋሀጃውን ኬሚካል ሽታ ይጠየፉት እንደነበረ አስታውሳለሁ። በበኩሌ የቀለሙን ሽታ ባልጠላውም የዶሮ ኩስ፣ የከብት ሽንትና አዛባ ባለበት ቦታ ሁሉ ሽታውን ለመቋቋም አፍንጫየን እይዝ ነበረ። ይሁን እንጅ  ከጥልቅ መረዳት በኋላ መጥፎ ጠረን ባለበት የሥራ ቦታ ሁሉ አፍንጫን መያዝ ሳይሆን አብሮ የመስራት ጥልቅ ፍላጎት አደረብኝ።

"ችቦ"




† #ሐምሌ ²¹ #እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም : ቅዱስ ዑራኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።

† ድንግል እመቤታችን እና ቅዱስ ዑራኤል፦ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት በዚህች ቀን ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል:-

1.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጓታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም ተሸክሞ: አስቀድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ: የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::

2.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በአራቱም አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጓል::

3.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮጵያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::

4.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል::

† ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟን ፍቅሯን : ከቅዱሳኑ ሁሉ ጸጋ በረከትን እግዚአብሔር ያድለን::



9 last posts shown.