አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ዛሬ ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም አቶ ጃዋር መሀመድ አሞኛል ብለው በችሎት በተደጋጋሚ መውጣት እና መግባት የምስክር ሂደቱን ስለሚያስተጓጉል በሚል ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አቶ ጃዋር እንደታመሙ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ንፋስ ለማግኘት ከችሎት ወጥተው የነበረ ሲሆን ዐቃቤ ህግ የምስከሮቹን ጭብጥ እያስመዘገበ ባለበት በድጋሚ ወደ ችሎት ገብተዋል፡፡
ይህ ወጣ ገባ ሁኔታ የዐቃቤ ህግ የምስክር ሂደትን ያስተጓጉለዋል ያለው ፍርድ ቤቱ ለነሃሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ፖሊስ የማረፊያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር የኔነሽ ገብረእግዚአብሄርም ቀርበው የተጠርጣሪዎችን የአያያዝ ሁኔታ መስተካከሉን እና አምስት ተጠርጣሪዎች ኮቪድ-19 እንደተገኘባቸው የሚገልጽ የህክምና ማስረጃ አቅርበው ማብራሪያም ሰጥተዋል፡፡
አቶ ጃዋር መሃመድ ልጄን እና ባለቤቴን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ላግኛቸው እንዲሁም ከጤናቸው ጋር በተያያዘ የግል ሃኪሜ እንዲያየኝ ይፈቀድልኝ ብለው አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የጤናቸው ሁኔታ ባለው የህክምና አሰጣጥ ህክምና እንዲያገኙ እንዲደረግ እና ወጪውን ሸፍነው ከልጃቸው እና ከባለቤታቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲገናኙ እንዲመቻችላቸው እንዲሁም የጤናቸው ሁኔታ ታይቶ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላቸው አዟል፡፡
ፖሊስም የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የተጠርጣሪ ጠበቆች ከደንበኞቻችን ጋር ለመገናኘት ስንሄድ ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ ቦታ እንድንገናኝ ይፈቀድልን በሚል አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆች ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲገናኙኝ አዟል፡፡
በተያያዘም አቶ በቀለ ገርባ በቅድመ ምርመራ ሂደት ማለፍ የለብንም በሚል ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡
በዚህ መሰረት የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማትም ለነሃሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ
👇👇👇👇👇👇👇👇👇
https://t.me/joinchat/AAAAAEmc0vHVCxyOHTCBFA