ስሜ መስከረም ጌቱ ይባላል። በክርስቲያን ቤተ ሰብ ውስጥ እና በቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ባህል ውስጥ ያደግኹ ቢኾንም፣ ሲደረግ ያየኹትን ልማድ ከማድረግ ባለፈ በተደጋጋሚ ስሰማው የነበረውን፣ ኢየሱስ የተባለውን ጌታ ከእኔ የግል ሕይወት ጋራ የነበረውን ቀጥተኛ ግንኙነት አልገነዘብም ነበር። ነገር ግን ሁልጊዜ ሲነገሩኝ የነበሩትን አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እውነተኛነት እጠራጠር ነበር። አባቴ ጸሎት ስለመጸለይ ባስተማረኝ መሠረት ያኔ ትንሽ ልጅ እያለኹ “እግዚአብሔር የተባልኸው አምላክ ሆይ፥ ስለአንተ ብዙ የተነገረኝን ብቻ ሳይኾን በግሌ እንዳውቅኽ እፈልጋለኹ፤ እንዴት አንተን ማመን እንዳለብኝ አስተምረኝ” ብዬ እጸልይ ነበር። በጊዜ ኺደት ርሱ ኢየሱስ ራሱ ማን እንደኾነ ያስተምረኝ ጀመር። እንዲሁም የመስቀሉ ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣ አፈ ታሪክ ሳይኾን ከዛሬ ኹለት ሺሕ ዓመታት በፊት ፈጣሪ የፈጠራቸውን ፍለጋ ሰው ኾኖ መጥቶ በመስቀል በመሞት በኀጢአተኛ ሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አስወግዶ እንድንታረቅ ማድረጉ ሐቅና እውነተኛ ክሥተት መኾኑን ለትንሿ ልቤ አስረዳኝ። ይህ እውነተኛ መለኮታዊ ብርሃን በውስጤ መረጃ ኾኖ ከመቀመጥ ዐልፎ ሕይወት በመዝራት መላ እኔነቴን ቀይሮ ዐዲስ ሰው አደረገኝ። ይህ መገለጥ ከእግዚአብሔር ጋራ ያለኝን ግንኙነት ለወጠው። ርሱ የሚሰጠውን ጸጋና ዐላማ እንድቀበል፣ በሙሉ ልቤ ርሱን ለመከተል ኅሊናዊ ምርጫ እንዳደርግ በመንፈሱ መራኝ። ከዚያም “ጌታ ሆይ ስላንተ ብዙ ሰምቼ ነበር አኹን ግን ዐይኔ አየችኽ” በማለት የሕይወቴ ጌታና አዳኝ አድርጌ ተቀበልኹት።
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነና ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችል ብቸኛ መንገድ መኾኑን እኔም አይቻለሁ።
#እኔ #ምስክር #ነኝ
ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነና ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችል ብቸኛ መንገድ መኾኑን እኔም አይቻለሁ።
#እኔ #ምስክር #ነኝ