❤ ከዚያንም ጊዜ ንጉሥ መልክተኞችን ልኮ ቅዱስ መርቆሬዎስን ወደርሱ አስመጣው በመዘግየቱም አድንቅ "ለአማልክት ዕጣን ለማድረግ ከእኔ ጋር ያልወጣህ የእኔን ፍቅር እንዴት ተውህ" አለው። በዚያንም ጊዜ ትጥቁንና ልብሱን ወረወረለትና ንጉሡን እንዲህ አለው "እኔ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም ለረከሱ ጣዖታትም አልሰግድም"። ንጉሥ ዳኬዎስም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ እርጥብ በሆኑ የሽመል በትሮች እንዲደበድቡት አዘዘ። ሁለተኛም ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ይገርፋት ዘንድ አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘ ይህን ሁሉ አደረጉበት።
❤ በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ስለ ቅዱስ መርቆሬዎስ እንዳይነሡበት ፈርቶ የቀጰዶቅያና የእስያ ክፍል ወደ ሆነች ወደ ቂሣርያ በብረት ማሠርያ አሥሮ ላከው። በዚያም እንዲአሠቃዩት አዘዘ ከአሠቃዩትም በኋላ ንጉሥ ዳኬዎስ እንዳዘዘው ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ተጋድሎውን ፈጽሞ በመግሥተ ሰማያት የሕይወት አክሊልን ተቀበለ። የማይጠፋ ሰማያዊ አክሊልንም ተቀዳጅቶ ወደ ዘላለም ሕይወት ከገባ በኋላ በዓለሙ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ታነፁለት እግዚአብሔርም ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን በውስጣቸው ገለጠ።
❤ ከተአምራቱም አንዲቱ ዑልያኖስ በነገሠ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ካደ በዚያንም ወራት ቅዱስ ባስልዮስ የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ነበረ ተአምራቱ በተጻፈበት መጽሐፍ እንደተጻፈ ምእመናን በጽኑዕ ሥቃይ ዑልያኖስ ባሠቃየ ጊዜ መክሮ አስተምሮ ከስሕተቱ ይመልሰው ዘንድ ቅዱስ ባስልዮስ ወደርሱ መጣ።
❤ ዑልያኖስም ቅዱስ ባስልዮስን በአየው ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ሰደበ ቅዱስ ባስልዮስንም አሠረው በዚያ በእስር ቤትም የቅዱስ መርቆሬዎስን ሥዕል አይቶ በፊቱ ቅዱስ ባስልዮስ ጸለየ ሥዕሉም ከቦታው ታጣ። ያን ጊዜ ወደ ዑልያኖሰሰ ሒዷልና በጦርም ወግቶ ገደለውና ወዲያውኑ ወደቦታው ተመለሰ ከጦሩም አንደበት ደም ይንጠፈጠፍ ነበር። ቅዱስ ባስልዮስም ከሀዲ ዑልያኖስን እንደገደለው አውቆ እንዲህ ብሎ ተናገረ "የክርስቶስ ምስክር ሆይ የእውነት ፀር የሆነ ዑልያኖስን ገደልከውን?" ያን ጊዜ አዎን እንደሚል ሥዕሉ ራሱን ዘንበለሰ አደረገ ቅዱስ ባስልዮስም ደስ ብሎት እግዚአብሔር አመሰገነ። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ ገድለ መርቆሬዎስና የኅዳር 25 ስንክሳር።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የማኅሌት_ምስባክ፦ "ልሳነ ከለባቲከ ላዕለ ጸላእቱ። አስተርአየ ፍናዊከ እግዚኦ። ፍናዊሁ ለአምላክነ ለንጉሥ ዘውስተ መቅደስ"። መዝ 67፥23-24 ወይም መዝ 88፥14-15። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 10፥17-32 ወይም ማቴ 20፥20-24።
✝️ ✝️ ✝️
❤ #የዕለቱ_የቅዳሴ_ምስባክ፦ "ቅረብ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ። ወኢይትኀፈር ገጽክሙ። ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ስምዖ"። መዝ 33፥5-6 የሚነበቡት መልዕክታት ዕብ 12፥25-ፍ.ም፣ ያዕ 3፥4-13 እና የሐዋ ሥራ 21፥27-ፍ.ም። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 8፥22-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ እግዚእነ ነው። መልካም የሰማዕቱ የቅዱስ መርቆሬዎስ የዕረፍት በዓልና፣ ዕለተ ሰንበትና የነቢያት (የገና) የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።
@sigewe https://t.me/joinchat/AAAAAFGQ22bI0Ij80hYpFA https://www.facebook.com/profile.php?id=100063896616886 https://www.facebook.com/profile.php?id=61552828743736&mibextid=ZbWKwL