የእርስዎ የወላጅነት ዘዴና ዘይቤ (Parenting Style) ልዩ-ፍላጎት ባለው ልጅዎ ላይ ተፅዕኖ እንዳለው አስተውለዋል?
ወላጆች/አሳዳጊዎች ለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና አላቸው። የወላጆችና የልጆች ግንኙነት (Parent-Child Relationship) በተለይም በልጆች የቀዳማይ የልጅነት ወቅት (Early Childhood Period) ጤናማና የተጠናከረ ካልኾነ መዘዙ አስቸጋሪና ከባድ ይኾናል። ብዙ-ጊዜ ልዩ-ፍላጎት ያለው ልጅ መኾኑ ሲታወቅ ሊደርሱ የሚችሉ ሥነ-ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ማለትም፦ ለረዥም ጊዜያት/ዓመታት ችግሩን ሳይቀበሉ መቅረት፣ የቤተሰብ መበታተን፣ የተረጋጋና የተጠና ጥረት አለማድረግ ወ.ዘ.ተ በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት፣ ተገቢ ድጋፍ/ቴራፒ (Intervention) የማግኘት ዕድል በእጅጉ ይቀንሳል።
በዕድገተ-ሰብዕ የሥነ-ልቡና ጥናት (Developmental Psychology) ዋና ዋና የልጆች የአስተዳደግ ዘይቤዎች፦
1. ወላጅ-መር የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች ልዩ-ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ፍላጎት፣ ዝንባሌ እና ጥያቄ የማያዳምጡ ብሎም ጥንካሬና ድክመቶቻቸውን ሳይለዩ እንደነሱ ፍላጎት ብቻ የሚያሳድጉ ናቸው። በዚህም ልጆቹ የሰው ጥገኛ፣ ከሰው የሚጠብቁ ይኾናሉ።
2. ነፃነት የበዛበት የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች ልጆች በተሣሣተ ሩቲን ውስጥ ሲገቡ የማያርሙ፣ አላስፈላጊ ባህርይ ሲያሳዩ ችላ የሚሉ፣ አብዝተው ነፃነት የሚሠጡ ናቸው።
3. አሣታፊያዊ የአስተዳደግ ዘይቤ
እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸውን ጥያቄ የሚያስተናግዱ፣ የሚያሣትፉ፣ ሚዛናዊ የሆኑና ሕይወታቸውን በፍላጎታቸው ላይ ተመርኩዘው እንዲኖሩ የሚያስችሉ ናቸው።
4. ቁብ-የለሽ የአስተዳደግ ዘይቤ
ልጆቹ ቴራፒ እንዳያገኙ በቤት ውስጥ የሚተዉ፣ እክሎቻቸው ለመቅረፍ ምንም የማይጥሩ፣ በልጃቸው ላይ ምንም ፍላጎትና ፍቅር የሌላቸው ናቸው።
ሌሎች፦ Helicopter Parenting, Attachment Parenting, Gentle Parenting, Tiger Parenting, SnowPlow Parenting, Free-Range Parenting, Neglectful Parenting, Blending Parenting, Single parent, Nuclear Family, Extended Family, Stepfamily ... ተጠቃሽ ናቸው።
ታድያ ለልጅዎ ምን አይነት ዘይቤ/ዘዴ አለዎት?አሉታዊ የአስተዳደግ ዘይቤ ልዩ-ፍላጎት ባላቸው ልጆች ላይ የሚከተሉትን ተፅዕኖዎች ሊያሳድር ይችላል፦
▹ በፍጥነት ቅድመ-መፍትሔ (Early Intervention) እንዳይሰጥ፣
▹ ችግሩ/እክሉ እንዲባባስ፣
▹ ተጓዳኝ እክሎች እንዲከሱቱ፣
▹ ድርብርብ/ውስብስብ ዕድገት እንዲኖር፣
▹ ለረዥም ጊዜ የማይፈታ መዘዝ፣
▹ ቴራፒው/ትምህርቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል።
በመኾኑም ሁሉም ወላጅ ለተሳካ እና ጤናማ የወላጅነትና የአስተዳደግ ዘዴ የወላጅ ውጤታማ ማድረጊያ ሥልጠና (Parent Effectiveness Training-PET) ቢሠለጥኑ፣ ባለሞያ ቢያማክሩ እና አጠቃላይ የግልና የቤተሰብ ደኅንነታቸውን በመጠበቅ ለልጆቻቸው ዕድገትና ድጋፍ (Intervention) ሊሠሩ ይገባል።
ዋኖስ መስፍን (
@WanosMesfin)
የልዩ-ፍላጎት ትምህርት ባለሙያ