፨ ልጅ ወለዱ ፨
ከተፈጥሮ በተጣላ መንገድ... እንዴት?
የተጣለ ፍሬ ዘር ሆኖ ይበቅላል... ድንጋይ ሆኜ በቀረሁበት የ አረም ሽበት ከወረረኝ... ቦታ ተመላላሽ በዛ ፣ ከጎኔ ሌላ ተሸናፊ ወደቀኣ... በ ትንሽ የ አፈሩ ጉብታ ላይ የተጎነጎነ አበባ በየኑ የሚቀይሩለት በየቀኑ ያልወየበ ልዩ ልዩ ጥቁር ልብስ ( መልኩ ቢመሳሰልም ማስታወቁ መች ይቀራል) እየለበሱ እንባቸውን በ ሶፍት እያበሱ በትልቅ መነጥር ተጋርደው የሚመጡ ብዙ ወዳጆች ያሉት ሬሳ ከጎኔ አረፈ
አዲስ ጫማ... ጥቁሩን፤ የሚቅለጨለጭ ቁልፍ በጃቸው... ባጁ ያልተነቀለ ኮፊያ ካናታቸው ደፍተው በየተራ ይመላለሳሉ .... የሃውልቱን መብቀል በጉጉት ይጠብቁት ይመስል... አንዱማ እየነዳሁ ካልገባሁ ብሎ የተገለገለ ነው አሉ አስር ጊዜ የመኪና ቁልፉን የሚያቅለጨልጨው ፣ ግን የወደቀ ሁሉ ጊዜውን ጠብቆ ይረሳል( ይነሳል ለ ሬሳ አይሰራም)... ወዳቂውን ይዞ መውደቅ የትም አያደርስ ብለው አልፈው ሂያጆች በረከቱ... ጉንጉኑ የ አበባው ፣ ከውሃ ጠገብ ወደ ጠወለገ ተቀየረ... ደረቀ... ከሰመ... ረገፈ.... ተረሳ... ሃውልቱ ብቅ ያለ ጊዜ ግር ብለው መጥተው አዳነቁ ( ውድ ነበራ ፣ እምነ በረድ ውድ ነበራ) ጥበቡን አዩ በነዛ ትላልቅ መነጥሮች የተደበቁት ጥቃቅን አይኖቻቸው በ ቅናት የተንገበገቡ ይመስላል
ሰው እንዴት በሟች ይቀናል? ፣ ሃውልቱ በቶሎ ተረሳ የሟች ታሪክ እንደወደቀ ቀርቶ በ ሆነ ጊዜ የሚያነሳው ሰው ተገኘ... አልለቅም ያለ... አልለቅም ያለች በየቀኑ የምታለቅ ተገኘች...
[ ሰው እንዴት ያለተፈጥሮ ይወልዳል? ፤ ሌላ እንቆቅልሽ... ደሞ እኔ ምን ቤት ነኝ? ]
ጊዜዋን ጠብቃ የማትቀር አንድ እሷ ኖረች ለሟች... አንድ አይነት ጥቁር ልብስ... ትላንት የነካትን አዋራ ዛሬም ለብሳው ምትመጣ... ፈጠን ቸኮል እያለች ደርሳ የወጓን አድርሳ እየተንደረደረች ትኼድ የነበረች ከጊዜ በኋላ ቀስ እያለች እየተራመደች ትመጣ ጀመረቻ
ከፊት በርከክ ብላ ጉልበቷን በመቃብሩ አፈር እንዳላቦካች አሁን ቆማ ሆነ የወጉን ምታደርሰው... እንባዋ ግን አልተቀየረም... በሆዷ ያለው ሃዘን ሁሌ እንደከበዳት ነው ግን ልጇ ባሰ... ተባብረው ከበዷት ሆዷ ገፋ...
በማታ መጣች ያልለመደባትን... ጥድፍ ብላ... እንባዋ ታንቆ ረገፈ... ጉልበቷ መሬት ነካ
... የሃዘን ሳይሆን የጭንቅ እንባ... በ እኩለሌሊት አጋነንንት ለቡና ሲጠራሩ የሷ ልጅ እያለቀሰ ፈልቅቋት ወጣ... በሙሉ ጨረቃ
ቀጥቁር ሻርፗን ጠቅልላ ታቀፈችው... አይን አይኑን አየችው... ጨረቃ ይቺ አሽቃባጭ ጉድ አልደብቅ ብላ ታበራባታለች... ልጅቷ ልጇ ላይ አመነታችና... ለመወሰን አንገራግራ ከነጨርቁ ሸፋፍና ከ መቃብሩ ላይ አኖረችው
ከኔ መቃብር ላይ... ሽበታም ድንጋይ እንዴት ካለቀሰችለት አፈር በላይ ይታመናል?... ድንጋይ እንዴት ለዚህ ሃላፍትና ይበቃል?... አላየችም እንዴ ምንም እንደሆንኩ?... አይታ የለም እንዴ?
ሌላ ቀዝቃዛ ደሞ የጨቅላ ሬሳ በላዬ ላይ ሲደረብ ተሰማኝ... ቸኮለች... አውቃ ይሆን?... ሊኖር የወጣ ገና አንዴ በማገው አየር ድፍት ይላል?... ደሞ የሷ እየፈገጉ መሄድ?
መረጋጋቷስ እ?
ሄደቻ... እኔ ባለ አደራ ህእ? ማን እንዲወስደው ማን እንዲበላው? በምኔ ላሞቀው ከብርዱ ላስጥለው እ?... ጨነቀኝ ፤ ሟች እንደሚጨንቀው ነዋሪ ሆኜ አለማወቄ
ማን አወቀ?
አይነጋ የለ... አነጋሁት
መሞት አያምም... ይሄ ግን ያማል... ነግቶ ጠሃይዋ አየሩን ማሞቅ ጀመረች... ያረፈደ... ለሃውልቱ ምርቃት
የተራውን ቅራቅንቦ እያቅለጨለጨ መጣ... አይኑን ወደላይ አንጋጦ ሃውልቱ ጋር ሲደርስ መለስ አለ... መነጥሩን አውልቆ ከላይ እስከታች ቃኘው... ፊቱን አጣሞ
ከዛ... መለስ አለ... ማየት ባንፈልግም የምናያቸው ነገሮች አሉ አደል?... የተጠቀለለ ከፊቱ በቀር፣ የተደገፈ በኔ መቃብር አፈር ህፃን ልጅ አየ...
ድንጋጤ ፣ ወድቆ ያገኘው ወርቅ ይመስል ዞሮ መቃኘት ፣ ድጋሚ ድንጋጤ... ቀረብ፣ ራቅ ፣ሄድ ፣መጠት ማለት
ተጠግቶ ትንፋሽ ካለው ማየት... ልብ ምቱን ለማዳመጥ ከመሬት አንስቶ መደ ጆሮው ማስጠጋት... አቀፍ እንደማድረግ ማለት... የልጁ ነብስ መዝራት... ከ እንቅልፉ ተቀስቅሶ እንደነቃ ህፃኖ ከ እናቱ ሆድ የወጣ ጊዜ የጀመረውን ለቅሶ ካቋረጠበት ቀጥሎ እሪሪሪሪሪሪ አለ
ልጅ ወለዱ... እንደዚህ
ውሃ
https://t.me/wuhachilema