አልመህ ተኩስ!
አንድ ንጉስ ከአጃቢዎቹ ጋር በአንድ ጫካ ውስጥ ሲዘዋወር አንድ ዛፍ ላይ ያየው ነገር ትኩረቱን ሳበው፡፡ በዚህ ትልቅ ዛፍ ላይ የተለያዩ ክብ ቅርጽ ያላቸው ኢላማዎች ተስለዋል፡፡ የገረመው ነገር፣ እያንዳንዳቸው ኢላማዎች መካከል ምንም ሳይስቱ ኢላማቸውን በትክክል የመቱ ቀስቶች ተሰክተው ይገኛሉ፡፡ ንጉሱ በጣም ተገረመና፣ “እነዚህን ኢላማዎች ሁሉ በትክክል አነጣጥሮ የመታውን ሰው ለሰራዊቴ አለቃነት እፈልገዋለሁና ፈልጋችሁ አግኙልኝ” አለ፡፡
ልክ ይህንን ተናግሮ እንደጨረሰ አንድ ወጣት ልጅ ብዙ ቀስቶችን ተሸክሞ እየገሰገሰ ንጉሱ ጋር ደረሰ፡፡ ንጉሱ፣ እነዚህን ሁሉ ኢላማዎች በትክክል የመታው ሰው እሱ መሆኑን ጠይቆ የአዎንታ መልስ ካገኘ በኋላ እንዴት እንደዚህ አነጣጣሪ ሊሆን እንደቻለ ጠየቀው፡፡ የልጁ መልስ አጭርና ግልጽ ነበር፣ “በመጀመሪያ ቀስቴን ወጥሬ በዛፉ ላይ እሰካዋለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ዛፉ በመሄድ በተሰካው ቀስት ዙሪያ የክብ ምልክትን አስቀምጥበታለሁ” በማለት እንደዚያ አነጣጣሪ ያስመሰለውን እውነት ፍርጥ አደረገና ነገረው፡፡
ይህ መሰረታዊና ቀላል አፈ-ታሪክ የብዙ ሰዎችን የሕይወት ዘይቤ ያንጸባርቃል፡፡ ይህ ወጣት በመጀመሪያ ዓላማን አድርጎ አልነበረም ያንን ዓላማ ለመምታት ጥረት ያደረገው፡፡ በቅድሚያ ወዳሻው ቀስቱን ከለጠጠና ከሰነዘረ በኋላ ቀስቱ ያረፈበትን ስፍራ ነው እንደዓላማ በመቁጠርና ልክ ዓላማውን እንደመታ ለማስመሰል በዙሪያው ክብን ያበጀለት፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ዒላማንና ግብን አቅደው በዚያ ባቀዱት መሰረት ሊተኩሲ ሲገባቸው ከተኩሱ በኋላ ቀስቱ ያረፈበትን ነው እንደግብ የሚቆጥሩት፡፡ በሌላ አባባል፣ ያገኘነውን፣ የመሰለንንና የቀለለንን ነገር ካደረግን በኋላ በዚያ ባደረግነው ተግባር ዙሪያ ዓላማን ለመፍጠር መሞከር የሞኝነት ሁሉ ሞኝነት ነው፡፡ ዓላማ ከሌለን የምንሄድበትን አናውቅም፡፡ ግብም ከሌለን ተኩሰን የመታነው ነገር ሁሉ እንደ ግብ ስለሚቆጠር ይህንና ያንን ስናደርግ ጊዜያችን ይባክናል፡፡ ለዚህ ነው በዓላማና በግብ የምንመራ ሰዎች መሆን ያለብን፡፡
አንድ በር ተከፍቶ ስላገኘህ ብቻ ከገባህ በኋላ የገባህበትን ዓላማ ለማግኘት አትሯሯጥ፤ በመጀመሪያ በዚያ በር የመግባትህ ጉዳይ ከሕይወትህ ዓላማ ጋር መስማማቱን አረጋግጥ፡፡
አንድ ሃገር የመሄድ እድል ስለተገኘ ብቻ ከሄድክ በኋላ ዓላማ ለመፍጠር አትሂድ፤ በመጀመሪያ ወደዚያ ሃገር የመሄድህ ጉዳይ ከሕይወትህ ዓላማህ ጋር አለመጣረሱን አረጋግጥ፡፡
አንድ ሰው ትኩረትና የመፈቀር ስሜት ስለሰጠህ ብቻ ሁለንታንህ በመስጠት ግንኙነት ውስጥ ከገባህ በኋላ ዓላማ ለመፍጠር አትታገል፤ ጓደኛንም ሆነ ፍቅረኛን ከዓላማህ አንጻር ምረጥ፡፡
ስራህንም እንደዚያው! ትምህርትህንም እንዲዚያው! የሕይወትህን ዋና ዋና ክፍሎችም እንደዚያ!
ከዓላማ ተነሳ እንጂ ተነስተህ ከተጓስክ በኋላ ዓላማህን ለማግኘት አትባክን፡፡ ዓልመህ ተኩስ እንጂ የተኮስከው ነገር የመታውን ነገር ሁሉ ዓላማህ እንደሆነ በማሰብ ራስህን በማታለል ዘመንህን አታባክን፡፡
Join us.....
@Ab_book @Ab_book @Ab_book