በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
📖መጽሐፍ ቅዱሳን እንዴት ላንብብ📖
ክፍል ፯
#መጽሐፍ_ቅዱስን_በጊዜና_በሰአት_ከፋፍሎ_የማንበብ_ስልት
ሰዓትና ጊዜ የሁሉም ፍጡራን እኩል ስጦታዎች ናቸው። የሰዓትና የጊዜ ጥቅም ጎልቶ የሚታወቀው በሚሰራ ሰው ህሊና ውስጥ ነው። ቀድሞ ሰዓትና ጊዜን ውድ ከሆነው ወርቅ ጋር ሲነፃፀር ነበር። አሁን ግን ሰዓት ሰዓት ነው ጊዜም ጊዜ ነው። እግዚአብሔር ለሁሉም እኩል ነው ሰዓትና ጊዜን የሰጠው። ለሁሉም ፍጡራን ሐፕት ላለውም ድሀ ለሆነውም እኩል ይነጋል ይመሻል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰው ሕይወቱን በትክክለኛ አቅጣጫ መርቶ ዘመኑን በምስጋና በሽልማት መቋጨት ከፈለገ የመጽሐፍ ቅዱስ ወዳጅ እና አንባቢ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ዕለት ዕለት እራስንና እግዚአብሔርን ወደማወቅ ደረጃ ከፍ ማለት ነው። ጊዜና ሰዓትን በቀጥታ ከማየታችን በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈል በምዕራፉ ብዛት እንመልከትና እንዴት ማንበብ እንዳለብን እንይ። ወደ ኋላ መለስ ብለን የመጽሐፍ ቅዱስን አከፋፈል (ክፍል ፪) ካስታወስን መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ተብሎ በሁለት እንደሚከፈል ተመልክተናል። በዚህ አከፋፈል ውስጥ ያሉትን ምዕራፎች ነው የምናየው
#በብሉይ_ኪዳን
የህግ መጻሕፍት፦
ከኦሪት ዘፍጥረት - ኦሪት ዘዳግም ያሉ 5 መጻሕፍት ሲሆኑ በውስጣቸው 187 ምዕራፎች ይገኛሉ።
የታሪክ ክፍል፦
ከመጽሐፈ ኢያሱ - መጽሐፈ አስቴር ያሉት 12 መጻሕፍት ሲሆኑ 249 ምዕራፎች ይዘዋል።
የመዝሙርና የቅኔ ክፍል፦
ከመጽሐፈ ኢዮብ - ማኃልየ ማኃልይ ዘሰለሞን ድረስ ያሉት 5 መጻሕፍት ሲሆኑ በውስጣቸው 243 ምዕራፎች ይዘዋል።
የትንቢት ክፍል፦
ከትንቢተ ኢሳይያስ - ትንቢተ ሚልኪያስ ድረስ ያሉ 17 የትንቢት መጻሕፍት ሲሆኑ በውስጣቸው 250 ምዕራፎች ይገኛሉ።
በአጠቃላይ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 929 ምዕራፎች አሉት።
#በሐዲስ_ኪዳን
የወንጌል ክፍል፦
ከማቴዎስ ወንጌል - ዮሐንስ ወንጌል ያሉት 4 ወንጌላት ሲሆኑ በመጻሕፍቱ ውስጥ 89 ምዕራፎች ይገኛሉ።
የታሪክ ክፍል፦
የሐዋርያት ሥራ ብቻ ሲሆን 28 ምዕራፎች አሉት።
የመልዕክት ክፍል፦
ከሮሜ መልዕክት - ይሁዳ መልዕክት ያሉት 21 መጻሕፍት ሲሆኑ 121 ምዕራፎች ይዘዋል።
የትንቢት ክፍል፦
የዮሐንስ ራዕይ ብቻ ሲሆን 22 ምዕራፎች አሉት።
የሐዲስ ኪዳን አጠቃላይ ምዕራፎች 260 ናቸው።
የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ምዕራፎች አጠቃላይ ድምር 1189 (አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ዘጠኝ) ነው። በዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አከፋፈል ውስጥ የምዕራፎቹ ቁጥር የሚያሳየው የ66ቱን መጽሐፍት ብቻ ነው። ከላይ የመጽሐፍ ቅዱስን የምዕራፍ ብዛት ካየን በዓመት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ ለመጨረስ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስን በአከፋፈሉ ከተረዳነው ግን ለንባብ በጣም ይቀለናል። የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሲደመሩ 1189 ናቸው።
እንዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፎች በዓመት ውስጥ አንብቦ ለመጨረስ በጊዜና በሰዓት መከፋፈል ያስፈልጋል። 1189 ሲካፈል ለ365 ቀናት = 4 ቀን ይደርሳል። ይህ ማለት በቀን 4 ምዕራፍ እናነባለን። ጠዋት 2 ማታ 2 ወደ ወር ስንቀይረው 120 ምዕራፎች ማለት ነው።
በቀን ውስጥ ለማንበብ የምንሰጠው ደቂቃ ጠዋት 10 ደቂቃ ማታ 10 ደቂቃ በድምሩ 20 ደቂቃ ነው። በወር ውስጥ 600 ደቂቃዎች ነው የምንጠቀመው።
እንግዲህ እንደ ንባብ ያለ ሕይወትን የሚሰጥ ታላቅ ነገር የለምና ከላይ በተቀናበረ መልኩ በተዘጋጀው ዘዴ በመጠቀም እንድናነብና የእግዚአብሔርን ቃል እንድናውቅ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን።
ተፈጸመ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
https://t.me/Abalibanos333