የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ( #አብን )የፌዴራል መንግስቱ/ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከንቲባን ከስልጣን እንዲያስነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠየቀ።
አብን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዛሬ ለምክር ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት አጥብቆ አውግዟል።
ፓርቲው ከንቲባ አዳነች አበቤ ዛሬ ለአዲስ አበባ ከተማ ም/ ቤት ባቀረቡት ሪፖርት " ከአንዳንድ ክልሎች የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት መንግስትን በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር ያለመ ነው " ሲሉ ሪፖርት ማቅረባቸውን ከተለያዩ ሚዲያ ዘገባዎች እና ከውስጥ ምንጮቻችን አረጋግጠናል ብሏል።
ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ይህን ማለታቸው አደገኛ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ነው ያለ ሲሆን ይህም አገረ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው ሲል ገልጾታል።
አብን ፤ ዜጎች በነፃነት ተዘዋውረው የመስራት እና የመኖር ሰብዓዊ መብት ያላቸው መሆኑ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች ድንጋጌዎች እና በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት ጭምር የተረጋገጡ ተፈጥሯዊ መብቶች ናቸው ብሏል።
ፓርቲው በመግለጫው ፤ ከንቲባዋ " የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ " እየተባለ በሚጠራው ጽንፈኛ እና በአንድ ወቅት መንግስት ራሱ " የሽብርተኞች መጠቀሚያ ነው " ብሎ በፈረጀው ሚዲያ በተከታታይ የወጡ ቅስቀሳዎች ቅጥያ የሆነ አደገኛ የወንጀል ቅስቀሳ አድርገዋል ሲል ከሷል።
" ዓለም አቀፍ ከተማን በከንቲባነት እመራለሁ ከሚል የመንግስት ባለስልጣን እንዲህ ዓይነት አደገኛ ቅስቀሳ በሪፖርትነት መሰማቱ እስካሁን ሲፈፀሙ ለነበሩ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች እና እየታወጀ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከለላ የሚሆን አደገኛ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው " ሲል ፓርቲው ገልጿል።
አብን በመግለጫው ፤ " ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ትኩረት በመስጠት አስቀድሞ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ታሪካዊ ጥሪ እያደረግን፤ በተለይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ይኼንን ባያደርግ በሩዋንዳ የፈፀመውን ታሪካዊ ስህተት የሚደግመው መሆኑን ማስረገጥ እንሻለን " ብሏል።
በሌላ በኩል ፥ የፌደራል መንግስቱ ሆነ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከስልጣን እንዲያነሳና ለፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ እናቀርባለን ያለ ሲሆን " መሰል ድርጊት በድጋሚ እንዳይፈፀም መንግስታዊ ማረጋገጫ ጭምር እንዲሰጥ ጥሪ እናቀርባለን " ብሏል።
@Adis_Media@Adis_Media