✍
አላህ ዘንድ በድሎ የሚድንም ይሁን: ተበድሎ የሚከስር የለም!! "በሻር አል_አሰድ" የተባለው የዘመናችን ፊርዐውን እስካሁን ከሰራው ከፊሉን እንጂ ከአሁን በኋላ ስለ ሚኖረው ሕይወቱ የምናውቀው ነገር የለም። ቀሪ እድሜው በዚሁ የኩፍር ዐቂዳ እና ጁርም ጨርሶት ጀሀነም ይወረወራል? ወይስ በእድሜው መጨረሻ ቀልቡ ለስልሶ በተውበት ታጥቦ ከደጋጎች ተርታ ይሰለፋል? የሚለው አላህ ብቻ ነው የሚያውቀው። ስለሱ አኼራ መተንበይም ይሁን መደምደም አንችልም፤ ከመሆኑም ጋ…… እንደሱ ያሉ ወደር የለሽ አረመኔዎች በጁርማቸው ልክ የእጃቸው የሚያገኙበት እና በጅምላ የተጨፈጨፉ በርካታ ንፁሃኖች ለተሰራባቸው ግፍ ካሳ የሚያገኙበት
"አኼራ" የተባለ የክፍያ ሀገር ባይኖር: ምን አልባትም ብዙ ሙጅሪሞች ባስታወስን ቁጥር በቁጭት እና በሀዘን ለእብደት እንቃረብ ይሆን ይችል ነበር።
የበሻር የአኼራ እጣ_ፋንታው ከላይ በተገለፀው መልኩ ማወቅ ስለ ማንችል; በምናባችሁ አንድ ገፀ_ባህሪ ሳሉና ስለሱ እንተርክ………
አንድ ሰው ነው…………
በዱንያ ላይ ማንኛውም ሰው ሊነቀንቀው የማይችል የተመቻቸ ስልጣን እና የበረታ ሰራዊት አለው። የፈለገውን ያስራል፣ ያሻው ይገርፋል፣ የፈለገው ይሰቅላል፣ ከፈለገው ይዘርፋል፣ እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ንፁሃኖች በበደል ጨፍጭፎ ገድሏል፣ ሰዎች በሕይወት ሳሉ ያቃጥላል፣ ሰውነታቸው እየቆራረጠ ያሰቃያል፣ እስከነ ሕይወታቸው ይቀብራቸዋል፣ በጣም ብዙ ብዙ የሆኑ ግፎች ይፈፅማል።
ይህ ሰው አኼራ የሚባል ሀገር ባይኖር ዱንያ ላይ ምን ዐይነት እርምጃ ቢወሰድበት ለሰራቸው ግፎች ተመጣጣኝ የሚሆን ቅጣት የሚያገኝ ይመስላችኋል???
በፍፁም ተመጣጣኝ የሚሆነው ቅጣት አታገኙም። "በእሳት ይቃጠል" ብትሉ, እሱ ብዙ ሰዎች አቃጥሏል: ስለዚህ የአንድ ሰው ብቻ ነው ለእሱ የሚደርሰው፤ "በዘይት መጠበስ አለበት" ብትሉ, እሱ ብዙ ሰዎች በዘይት ጠብሶ አሰቃይቷል: ስለዚህ የአንድ ሰው ድርሻ ብቻ ነው እሱ የሚያገኘው። ስለዚህ ምንም ዐይነት እርምጃ ቢወሰድበት ለሰራው በደል ተመጣጣኝ ሊሆንለት አይችልም።
ይህ ብቻም አይደለም………
ቁጥራቸው እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ ተበዳዮች ወይም ተገዳዮች ሁላቸውም ለደረሰባቸው በደል ካሳ ማግኘት ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ በዱንያ ላይ ሊከፈላቸው አይችልም። ምክንያቱም ሰዎቹ ሙተው ከዱንያ ወጥተዋል።
እንግዲያውስ አላህ ዘንድ በድሎ የሚተርፍም ይሁን ተበድሎ የሚከስር የለምና ሁሉም የሚገባው የሆነ ምንዳ እና ቅጣት አኼራ ላይ ያገኛል። አኼራ ላይ
"ጀሀነም" የምትባል ለበደለኞች የተዘጋጀት የስቃይ ሀገር አለች። ዱንያ ላይ የትኛውንም ያህል የገዘፈ በደል ሰርቶ የሞተ ሰው ይህ ጀሀነም ውስጥ ለሰራው በደል የሚገባ የሆነ ቅጣት ያገኛል። ጀሀነም ውስጥ ሕይወትም ሞትም የለም። ሕይወት እንዳይባል ሞት የሚያስመኝ የስቃይ ሕይወት ነው፤ ሞት እንዳይባል እየተቃጠለ እየተሰቃየ ይኖራል እንጂ ሙቶ አይገላገልም። አንድ ሰው ዱንያ ላይ ሚሊየን ሰዎች አሰቃይቶ እንደሆነ ጀሀነም ውስጥ ሚሊየን ጊዜ ይሰቃያል። አንዴ ተቃጥሎ, አንዴ ተሰቃይቶ አያበቃም።
አላህ እንዳለው፦
📖
{كُلَّمَا نَضِجَتْ جُلُودُهُم بَدَّلْنَاهُمْ جُلُودًا غَيْرَهَا لِيَذُوقُوا الْعَذَابَ}
{ቆዳቸው በተቃጠለች ልክ ቅጣት እንዲቀምሱ ሌሎች ቆዳዎች እንቀይርላቸዋለን።} [አል_ኒሳእ:⁵⁶] ሰውነቱ አንዴ ተቃጥሎ ሲያልቅ ሌላ ቆዳ ይቀየርለትና በድጋሚ ሌላ ስቃይ ይቀምሳል። እያለ… እያለ… ይሰቃያል።
"እሱ ለሰራው በደል እና ግፍ በዚህ መልኩ እየተሰቃየ የሚገባውን ቢያገኝም
በእሱ ግፍ እና በደል የደረሰባቸው ሰዎች ካሳቸው የሚያገኙት በምን መልኩ ነው?" የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው።
አኼራ ላይ? አዎን በትክክል ካሳቸውን ያገኛሉ!! በዱንያ ቆይታ በሌሎች ላይ በደል አድርሶ በደሉን "ይቅር" ሳይባል ወይም ካሳ ሳይከፍል የሞተ ሰው አይቀሬ በሆነ መልኩ አኼራ ላይ ለተበዳዮች ካሳቸው እንዲከፍል ይደረጋል። ይህንን ግልፅ አድርጎ የሚያስረዳ ሓዲስ ነብዩ እንዲህ ነግረውናል።
ከዕለታት በአንዱ ቀን የዕዝነቱ ነብይﷺ ከውድ ባልደረቦቻቸው በተቀማመጡበት ነብዩ ለሰሀባዎች ጥያቄ አቀረቡ። "መናጢ ደሀ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁን?" አሏቸው። ሰሀባዎች ሲመልሱ "ደሀ ማለት ምንም ዐይነት መጠቃቀሚያ ቁስም ይሁን ሀብት የሌለው ነው" አሉ። ነብዩ "ትክክለኛ ደሀ ማለትማ፦ አንድ ሰው ነው: የቂያማ ቀን በርካታ ሰላት፣ ምፅዋት፣ እና ጾም ይዞ ይመጣል፤ ከዚያም የዘረፋቸው፣ የደበደባቸው፤ የገደላቸው ሰዎች ይመጡና ለዚህ ከምንዳው: ለዛኛውም ከምንዳው እየተሰጠ የሰውየው ምንዳ ለተበዳዮች ተከፋፍሎ ያልቃል። ለተበዳዮች ካሳቸው ተከፍሎ ሳያበቃ የሰውየው ምንዳ ካለቀ: ከወንጀላቸው እየተነሳ ሰውየው ላይ ይጫንና ወንጀላቸው ተሸክሞ ወደ ጀሀነም ይወረወራል።" ብለው አስረዷቸው።
"በዳዩ ሰውዬ ካፊር (ምንም ምንዳ የሌለው) ቢሆን ለተበዳዮች ምን ሊሰጥ ይችላል?" ለሚለው ጥያቄ ይህ ሐዲስ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። ከተበዳዮች ወንጀል እየተነሳ በዳዩ ላይ ይደረብና በስቃዩ ላይ ስቃይ እንዲጨምር ይደረጋል። በዚህ ሰበብ እነሱም ወንጀላቸው ይቀንስና ደርሶባቸው ለነበረው በደል ካሳ ይሆናቸዋል።
አላህ ዘንድ በድሎ የሚተርፍም ይሁን ተበድሎ የሚከስር የለም!!
ይህንን ስትረዳ እንደ በሻር ባሉ ፊርዓውኖች ላይ የነበረህ ቁጭት ፋታ ያገኛል።🖊
ሐምዱ ቋንጤ ከፉርቃን ሰማይ ስር!!https://t.me/Al_Furqan_Islamic_Studio