በመንገዳችን ላይ
(በእውቀቱ ስዩም)
በዚያ ሰሞን፥ በቦሌ መድሀኒያለም ጀርባ የተሰመረችውን ጎዳና ይዤ በእግሬ እወዘወዛለሁ፤ ብዙ ሳልርቅ፥ የእግረኞች መንገድ ላይ ሶስት የጎዳና አዳሪዎች ጎንለጎን ተደርድረው በጀርባቸው ተንዘራግተው እንቅልፍ ወስዷቸው ተመለከትኩ፤ አንድ በእድሜና በአካል የሚልቅ ብጢያቸው አጠገባቸው ቁጭ ብሏል፤ ሌላ አንድ ጎረምሳ ከ “ጽጌ” ሽሮ አቅጣጫ አንድ ፌስታል ሙሉ ፍርፋሪ ይዞ ደረሰ፤ ቁጢጥ ብሎ የፌስታሉን አፍ ለመክፈት ሲቃጣ ጠና ያለው ልጅ ወደ ተኙት ብላቴኖች በአገጩ እየጠቆመ እንዲህ ሲል አዘዘው፤
“ መጀመርያ እነሱን ቀስቅሳቸው !“
ደነቀኝ! ለምን ደነቀኝ? ሞልቶ ተርፎት ከማካፈል መድፋት የሚመርጥ ብዙ ሰው ያለበት አለም ውስጥ ነው እምንኖረው፤ ብዙዎቻችን በዚህ ጎረምሳ ቦታ ብንሆን ምንድነው የምናረገው? ነቅተው ሳይሻሙን እንበላ እንደምንል እገምታለሁ፤ ያንዳንድን ሰው ቸርነት እጦት እና ድሀነት አያከስመውም፤ በኔ ግምት ጠና ያለው ጎዳና አዳሪ ያንን ያደረገው ለታይታ አይደለም፤ የቲክቶክ ካሜራ እንዳላነጣጠረበት ያውቃል፤ ከተኙት ልጆች ደቃቃነት አንጻር ወጠምሻ እሚባል አይነት ነው፤ እና ብቻውን ቢበላ ፥ ቀጭም ሆነ ተቆጭ ያለበት አይመስልም፤ እንደመታደል ሆኖ፥ በመናመን ላይ ያለው የሰው ልጅ ህሊና እዚህ ልጅ ላይ ጨርሶ አልጠፋም፤ እንዲህ አይነቱ ትእይንት በሰው ልጅ ተስፋ እንዳትቆርጪ ያደርግሻል::
በአለማችን ሩህሩህ ሰዎች ብርቅ ናቸው፤ ርህራሄም ደረጃ አለው፤ ብዙ ሰው ፥ ለራሱ እና ለቤተሰቦቹ ብቻ ይራራል፤ ያንዳንዱ ሰው ደግነት ደግሞ ለጎረቤቱ ለወዳጆቹ ለዘመዶቹ ብቻ ተወስኖ ይቀራል ፤ ከሁሉ የላቀ መንፈስ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ፥ ለሰው ዝርያ ብቻ ሳይሆን ለአራዊት አዋፋት ለነፍሳት ሳይቀር ቸርነታቸውን ያሳያሉ::
ሰዎች ሆድ የሚባል ጉድ የተገጠመልን ፍጡሮቸ ነን፤ ቢቸግረን ዶሮ ፥ በግ ፍየል በሬ አርደን እንበላለን፤ ግን ሳይቸግረን በእብሪት ወይም በግዴለሽነት ተነሳስተን የምናደርገው ጭካኔስ ምን ይባላል? ባለፈው እዚህ አክሱም ሆቴል ፊትለፊት ባለው መንገድ ላይ አንዱ አህያ እየነዳ ይሄዳል፤ አህያዋ በፍጥነት ትራመዳለች፤ ነጂው ግን በጎማ ዱላ እያከታተለ ይወግራታል፤ ለግማበት ነው እንዳልል በምትችለው አቅም እየተጣደፈች ነው፥ ሰውየው ከጭካኔ የተሻለ መዝናኛ ያለው አይመስልም፤ ወይም ደሀነቱ የፈጠረበትን ብስጭት እሚወጣው አገልጋዩን በመደብደብ ይሆናል፤ እስቲ ወደ ባለቤት አልባ ውሾች ተመልከቱ! አንድ አይኑ ያልጠፋ፥ ወይም እግሩ ያልተቀለጠመ ውሻ ማግኘት ይከብዳል!
ከሩቅ ምስራቃውያን የመነጨ አንድ ፍልስፍና ሀሳብ እንዲህ ይላል፤ እኛ ሰዎች በዚህ አለም መኖር የምንፈልገውን ያህል አራዊት አእዋፍ እና ነፍሳት መኖር ይፈልጋሉ፤ ስለዚህ ሌሎች ፍጡራን ያንተ ብጤ ናቸው፥ ባንተ ልክ ተንከባከባቸው!
ጋዜጠኛ ገነት አየለ ሸጋ አድርጋ፥ የተረጎመችውን የሚካኤል ዳባዲ ማስታወሻ ሳነብ ያገኘሁት አንድ ውብ አንቀጽ የድብርት መዳኒት ነው፤ ላጋራውና ልሰናበት፤
ደአባዲ የተባለ የፈረንሳይ አሳሽ የዛሬ ሁለት መቶ አመት ገደማ ጎጃም ሳርምድር ውስጥ አደን ለማደን ይሰማራል፤ ድንገት በለስ ቀንቶት አንድ አጋዘን ያይና አነጣጥሮ ሊኩስበት ሲዘጋጅ፥ በከፊል የተራቆተ ሰውየ ብቅ ይልና ተኩሱን ያደናቅፍበታል ፤ሰውየው በዳባዲ አጃቢዎች ተይዞ ሲመጣ በበረሀ የሚኖር ባህታዊ መሆኑ ይገለጣል፤ ባህታዊው አደኑን በማደናቀፉ ይቅርታ ከጠየቀ በሁዋላ እንዲህ አለ፤
“ይህ አጋዘን የከፋው(የተከፋ) እንስሳ ነው፤ በአቅራቢያ እያገሱ ያሉት ብዙ አንበሶች በጣም ያስጨንቁት ነበረ፤ ለኔ እንደ ባለንጀራየ ነው፤ አንዳንዴ በበረሀ አቁዋርጨ ስጓዝ ቀኑን ሙሉ እየተከተለኝ አብሮኝ ይሄዳል፤ አሁን በኔ ምክንያት ህይወቱ ድኖ ከሆነ ደስ ይለኛል “
ከ በእውቀቱ ስዩም የፌስቡክ ገጽ !
@books_worldd #ሼር