የኢትዮዽያ ልማት ባንክ ክልሉን ለማገዝ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ
ባንኩ ከክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡
መንግስት ትኩረት በሰጣቸው የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ብድር በማቅረብና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ የሚገኘው የኢትዮዽያ ልማት ባንክ በክልሉ ይህን መሰል ልዩ ስልጠና ከማዘጋጀቱም ባሻገር ተደራሽነቱን እያሰፋ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ ዶ/ር ኢ/ር ምትኩ በድሩ ገልጸዋል፡፡
ክልሉ አብዛኛውን አምራች የሰው ሃይልና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የያዘ ክልል በመሆኑ ባንኩ ይህን ሃብት ወደ ልማት ቀይሮ ለመጠቀም የሚያስችል ስልጠና ያዘጋጀ በመሆኑ ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተልና ከስልጠናው በሚያገኙት ዕውቀት ለክልላቸው ብልፅግና የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ በበኩላቸው የሀገራችንን ብልጽግና ዕውን ከማድረጉ አንጻር የአምራቹ ዘርፍ ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በክልሉ በአጠቃላይ 7 መቶ 37 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስተሪዎች እንደሚገኙ የጠቆሙት ሃላፊው እነዚህን በማገዝና በማብቃት የክልሉን ዕድገት ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የልማት ባንኩ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በበቨርቿል የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮዽያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው አበራ ስልጠናው በክልሉ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ባለሀብቶች ጥያቄ መዘጋጀቱ ቀደም ሲል ባንኩ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ይሄኛውን ለየት እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
የበለጸጉ ሀገራት መሰረቶች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስተሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህም የዓለማችንን 50 በመቶ ሀብት በማንቀሳቀስ ትልቅ ድርሻ ይይዛሉ ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ባንኩ እነዚህን ኢንተርፕራይዞች ሚና ከግንዛቤ በማስገባት የሊዝ ብድር ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ይህን ውጤታማ ለማድረግ ይህ ስልጠና መዘጋቱን ጠቅሰው ሰልጣኞቹ ይህን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ከራሳቸው አልፈው ለክልላቸው ዕድገት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ባንኩ ለክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሽ ባለሀብቶች የጀመራቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡ ለ5 ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና ላይ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች የተውጣጡ ከ6 መቶ 70 በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ባለቤቶች እየተሳተፉ ይገኛል ሲል ደሬቴድ ቦንጋ ቅርንጫፍ ዘግቧል፡፡
@Southwest Communications
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ