ኮሚሽኑ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ
************************
(ጉምሩክ ኮሚሽን ፣ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም )
የጉምሩክ ኮሚሽን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ሀይል፣ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ፣ ከፌደራል ፖሊስ ፀረ ኮንትሮባንድ አባላት፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር እና ከኦሮሚያ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት፤ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሲቲ ዞን ሙሉ ወረዳ ሱመዳዮ ቀበሌ የተከማቸ የኮንትሮባንድ እቃን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ይህን ታላቅ እና ታሪካዊ ህግ የማስከበር ዘመቻ እና በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክተው በዛሬው እለት ለሚዲያ ባለሙያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኮሚሽነር ደበሌ በመግለጫቸው እንደገለጹት፣ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ የምትገኘው ሱመዳዮ ቀበሌ፤ የኮንትሮባንድ እቃዎች ማከማቻ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማሰራጫ መጋዘኖች መኖራቸውን በተደጋጋሚ ጥናቶች መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡
ጥናቱን መሠረት በማድረግ ጥር 14 እና 15 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገ ኦፕሬሽን 1 በሊዮን 16 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
በቁጥጥር የዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች አዳዲስ አልባሳት፣ ልባሽ ጨርቆች፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች፣ መድሀኒት፣ ሲጋራ እና ሺሻ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም፣ በዚህ ኦፕሬሽን 18 ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ እንደያዙ በቁጥጥር የዋሉ መሆኑን ገልፀው ቀሪዎቹ የኮንትሮባንድ እቃዎች በጉምሩክ አዋጅ መሰረት መጋዘን በመበርበር የተያዙ እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋሉትን የኮንትሮባንድ እቃዎች በአጠቃላይ በ34 ተሽከርካሪዎች በማጓጓዝ አዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት መጋዘን መግባታቸውንም ኮሚሽነር ደበሌ ተናግረዋል፡፡
ኦፕሬሽኑ የኮንትሮባንዲስቶችን ቅስም የሚሰብር፣ ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያዳክም እንዲሁም ኮንትሮባንድን በመከላከል እና በመቆጣጠር መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በኮንትሮባንዲስቶች ላይ የሚወስደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ኦፕሬሽን እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለዋናው መ/ቤትና አዋሽ ጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤት አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ምስራቅ እዝ 503ኛ ኮር፣ ለፌደራል ፖሊስ እና ለክልል የፀጥታ ተቋማት እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ ኮሚሽነር ደበሌ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/ecczenaበድረ ገጽ፦
www.ecc.gov.etበቴሌግራም፦
https://t.me/EthiopianCustomsCommission