በሜታ ወልቂጤ በአንዲት ታዳጊ ህጻን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ አንዲት ህጻን ከቤት ተወስዳ ከተደፈረች በኋላ ተገድላ መገኘቷ ቁጣ ቀስቅሷል። “በኛ የደረሰ በማንም አይድረስ” የሚሉት የተጎጂ ቤተሰብ በታዳጊ ልጃቸው ላይ ለደረሰው ቀሰቃቂ ወንጀል ፍትህ እንሻለለን ብለዋል።
ሲምቦ ብርሃኑ ትባላለች፡፡ የስምንት ዓመት ታዳጊ ህጻን ናት፡፡ የአንደኛ ክፍል ተማሪ፡፡ በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ባለፈ ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ከትምህርት ቤት ተመልሳ ምሳ እንደበላች ከመኖሪያ ቤቷ የደረሰችበት ሳይታወቅ ቀርቷል ፡፡ በዕለቱ ፍለጋ የወጣው ቤተሰብ ታዳጊዋን ከነሙሉ ጤንነትና በህይወት ለማግኘት ግን አልታደሉም፡፡
ሮጣ ያልጠገበች ታዳጊዋ ለአዕምሮም በሚከብድ ሁኔታ ከተደፈረች በኋላ “እንዳትናገር በሚል” ከመኖሪያ ቤታቸው ጀርባ በቅርብ ርቀት ላይ ህይወቷ አልፎ መገኘቱን አንድ የቤተሰቧ አባል ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። ታዳጊዋ ከተገደለች በኋላ ተሰቅላ መገኘቷን የገለጹት የቤተሰብ አባሉ “ጫማዋን ያወለቁባትና የሰቀሏት ቦታ አንድ አይደለም የ50 ሜትር ገደማ ርቀት አለው” ብለዋል።
በወረዳው የኤላ ከተማ በታዳጊዋ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አባት የመንግስት ሰራተኛ መሆናቸው እና በስራ ቦታ መሆናቸው እንዲሁም እናት የ2 ወር እመጫት በመሆናቸው አጋጣሚውን በመጠቀም እንደነበር የቤተሰቡ አባል ተናግረዋል።
የተጎጂ ቤተሰብ አባል የሆኑት አስተያየት ሰጪ ቀጥለው፤ “የታዳጊዋ ቤተሰብ ቤት በፊት ለፊት በኩል ሆቴል በመሆኑ የሚገባውና የሚወታው ብዙ ነው፡፡ በጓሮ በኩል ፑል መጫወቻም አለ፡፡
ደፋሪዎችም በዚያው በጀርባ በር እንደወሰዷት ነው የቤተሰብ ስጋት” ያሉን አስተያየት ሰጪው፤ 2009 ዓ.ም. የተወለደችው ታዳጊዋ ሲምቦ ገና በ8 ዓመቷ ለዚህ ለአሰቃቂው ድርጊት ሰለባ መሆኗን በቁጪት ተናግረዋል፡፡
“ባለሙያዎች በሰውነቷ ላይ የታየውን ፈሳሽ በመውሰድ ምርመራ እያደረጉ ነው” ያሉን የቤተሰብ አባል እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ተኩል የተገኘው የታዳጊዋ አስክሬን በትናንትናው እለት ስርዓተ ቀብሩ መፈጸሙን የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ ዘግቧል።
ዶቼ ቬለ በታዳጊዋ ላይ ስለደረሰው አሰቃቂ ድርጊት እና ቀጣይ እርምጃዎች ለመጠየቅ ለወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አጀማ በእጅ ስልካቸው ላይ ቢደወልም ስልካቸው ስለማይነሳ አስተያየታቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም፡፡
ምስል ፤ ከቤተሰብ አባል የተገኘ
#DW #ዶቼ_ቬለ
@Ethiopian_Digital_Library@Ethiopian_Digital_Library