ሰው እንጂ እግዚአብሔር አልረሳኝምበጸሎት ኃይል የሚያምን አንድ ፅኑዕ ክርስቲያን ነበር፡፡ ይህም ክርስቲያን ጥሪት የሌለው ደኃ ፣የሚበላውን የሚቸገር ረሃብተኛ ፣ልብሱ በላዩ ላይ አልቆ የታረዘ ምስኪን ነው፡፡ ከእለታት አንድ ቀን በጸሎት ሕይወቱ የነበረውን ትጋት በቅርብ ሆኖ ይታዘብ የነበረው ወዳጁ እንዲህ አለው ‹ቢያንስ ለረሃብህ ማስታገሻ ቁራሽ ዳቦ እንኳን ማስገኘት ካልቻለ የመጸለይህ ትርጉም ምንድር ነው? በቃ ፈጣሪህ አልሰማህም ማለት ነው!› ሲል ተስፋ በሚያስቆርጥ ቃል ተናገረው፡፡ ያ ምስኪን ክርስቲያን ግን እንዲህ ሲል መለሰለት
‹እግዚአብሔርማ አልረሳኝም! ለአንዱ ሰው ከዕለት እንጀራው የበለጠ አትርፎ በመስጠት ለእኔ እንዲያካፍለኝ ነግሮት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን አደራ የተቀበለው ሰው ዘነጋኝ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሳይሆን ይህ ሰው ረስቶኛል!!!›
ክርስቲያኖች ለምን አንዳንዶች ከዕለት የሚተርፍ ብዙ እንጀራ ሲያገኙ፤ አንዳንዶች ደግሞ ለዕለት እንኳን የሚሆን ቁራሽ እንጀራ ያጣሉ? መቼም ‹ለሰው ፊት የማያዳላ› እግዚአብሔር አድልዎ ኖሮበት ነው አትሉም?! (ሐዋ. 10፥34) ይህስ የሆነው እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት አትርፈው ያገኙት ምንም የሌላቸውን በመርዳት እና በመመገብ በባሕርይው መግቦትን ገንዘብ ያደረገውን አምላክ በጸጋ እንዲመስሉትና በፈጠራቸው ሰዎች መካከል ያለውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ነው፡፡
ስለዚህ ‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ› ብለን የለመንነው አምላክ ከዕለት እንጀራችን አትርፎ የሚሰጠን ይህን አምላካዊ አደራ እንድንወጣም ስለሚፈልግ እንደሆነ ብንረዳው እንዴት መታደል ነበር!!!
🌷
መልካም ቀን ይሁንልን✝
💚
@Ethiopian_Ortodoks💚
💛
@Ethiopian_Ortodoks💛
💛
@Ethiopian_Ortodoks💛