ኢትዮጵ
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አጠቃላይ መረጃ
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ4 አሰተዳደራዊ ዞኖች ፣ በአንድ ልዩ ዞን ፣ በ35 ወረዳዎች እና በ74 ከተማዎች የተዋቀረ ነው። የክልሉ ምክር ቤት የከፍተኛ አስተዳደር አካል ሲሆን 152 የካቢኔ አባላትን የያዘ ነው። የህግ አስፈፃሚው አካል በ16 ተወካዮች የተዋቀረ ነው።
የስፍራው አቀማመጥ
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ጫፍ የሚገኝ ሲሆን ክልሉ በሰሜን ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከአፋር ክልል፣ በደቡብ ከአማራ ክልል እንዲሁም በምእራብ ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር ይዋሰናል፡፡
ርእሰ ከተማ
መቀሌ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ ከተማ ነች፡፡
የቆዳ ስፋት
የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት 80000 ስኩ.ኪ.ሜ የሚገመት የቆዳ ስፋት ይሸፍናል፡፡
ስነ-ህዝብ
በ1994 በተገኘው የህዝብ ቆጠራ መሰረት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ብዛት 3,136,267 ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1,542,165 ወንዶች እና 2,667,789 ሴቶች ናቸው።
በሀይማኖት ረገድም 95.5% የኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ 4.19% የእስልምና እና 0.4% የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነው።
በብሄር ስብጥር ረገድም 94.98% የትግራዊ፣ 2.6% የአማራ፣ 0.7% የኢሮብ እና 0.05% የኩናማ ብሄረሰቦች ይኖራሉ፡፡ ትግርኛ የክልሉ የስራ ቋንቋ በመሆን ያገለግላል።
ዋነኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች
በትግራይ ብሔራዊ ክልል ከሚገኘው ህዝብ 83% የሚሆነው በግብርና ስራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡
ጤፍ፣ ስንዴ እና ገብስ ዋነኛ የሰብል ምርቶች ሲሆኑ ባቄላ፤ የጥራጥሬ እህሎች፣ ሽንኩርት እና ድንች እንዲሁ በክልሉ ይመረታሉ፡፡
ተዳፋታማ የመሬት አቀማመጥ ባላቸው የክልሉ አካባቢዎች የመስኖ እና የእርከን መፍትሄዎችን በመጠቀም የእርሻ ስራ ይከናወንባቸዋል፡፡
የትግራይ ክልል የጥጥ፣ የእጣን፣ የሰሊጥ እና የተለያዩ ማእድናትን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማቅረብ ይታወቃል፡፡
ከክልሉም የመሬት ይዞታ 1.5 ሚሊዮን ሄክታር መልማት የሚችል ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1 ሚሊዮን ሄክታሩ ለእርሻ አገልገሎት የዋለ ነው፤ የተቀረው 420,877 ሄክታር መሬት ደግሞ የእርከን ስራን በመጠቀም የለማ ነው፡፡
የተለያዩ የእደ-ጥበብ(እንደ ወርቅ ማንጠር፣ የስዕል እና የእንጨት ቅርፃ ቅርፅ) ስራዎች ሌላው በክልሉ በሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ የሚስተዋሉ የስራ አንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
የመሬት አቀማመጥ እና የአየር ንብረት
ምንም እንኳን ክልሉ ከ3,250 - 3,500 ሜትር ከፍታ ባላቸው የተራራ ሰንሰለቶች እና የተፈጥሮ መስህቦች የተከበበ ቢሆንም፤ ለዘመናት ሲፈራረቅበት የቆየ የመሬት መሸርሸር፣ የደን መጨፍጨፍ እና ከመጠን በላይ የሆነ የግጦሽ መሬት አጠቃቀም የክልሉን መሬት ለደረቅና ዛፍ-አልባ ሜዳዎች፣ኮረብታዎችና ተራራዎች አጋልጦታል፡፡
ይህ ክልል እጅግ በጣም የተለያዩ የከፍታ ልዩነቶችን ያስተናግዳል፡፡
የክልሉ የከፍታ መጠን ከባህር ጠለል በላይ ከ600 - 2,700 ሜትር ሲሆን
የተከዜ ሸለቆ ከባህር ጠለል በላይ 550 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ
"የክሳድ ጉዶ" የተራራ ጫፍ ደግሞ ከባህር ጠለል በላይ በ3,935 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም በመሀከላዊ ደጋማ አካባቢዎች ከሚገኙ የትግራይ ውብ የተፈጥሮ እይታዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ የአየር ንብረት ያላችው አካባቢዎች ሲገኙ 39% ቆላማ፣ 49% ወይና ደጋማ፣ 12% ደጋማ ቦታዎች ናቸው፡፡ የክልሉ አመታዊ አማካኝ የዝናብ መጠን ከ450 – 980 ሚ.ሜ ይደርሳል፡፡
ወንዞችና ሀይቆች
ከአማራ ብሄራዊ ክልል የሚነሳው የተከዜ ወንዝ እንዲሁም ከኤርትራ የሚነሳው የመረብ ወንዝ የትግራይ ክልልን የሚያቋርጡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ናቸው፡፡
እንደ ገባ፣ ወሪ፣ በርበር፣ አርቋ እና ጠጠር የተባሉ ለመስኖ ስራ ጠቃሚ የሆኑ አነስተኛ ወንዞችም በክልሉ ይፈሳሉ፡፡
የተከዜ ወንዝ የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫነት እያገለገለ ይገኛል፡፡
የተከዜ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ግድብ
ሌላው በክልሉ የሚገኘው የአሸንጌ ሀይቅ ውብ የሆኑ አእዋፋትን ለመመልከት እና አሳ ለማጥመድ የተመቸ እና ቀልብን የሚስብ የተፈጥሮ መስዕብ ነው፡፡
ውብ አእዋፋት በአሸንጌ ሃይቅ
የቁም ከብት ሀብት
በክልሉ ወደ 11.51 ሚሊዮን የሚጠጋ የቤት እንስሳት ሲገኙ ከነዚህም ውስጥ 2.15 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 5.63 ሚሊዮን በጎችና ፍየሎች እንዲሁም 392,000 የጋማ ከብቶች ናቸው፡፡
የዱር እንስሳት
ዝሆን፣ ነብር፣ አጋዘንና የምኒሊክ ድኩላ በክልሉ የሚገኙ የዱር አራዊቶች ናቸው፡፡
ማዕድን
የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ በማዕድን ሀብት ከበለፀጉ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡
በክልሉ ከተገኙ የብረት ማዕድናት ውስጥ ወርቅ፣ መዳብ፣ የብረት ኦር, ዚንክ, ሊድ እና ኒኬል ይገኙበታል፡፡
አስቤስቶስ, የሲሊከን አሸዋ, ካኦሊን, ግራፋይት, ላይም ስቶን, እብነ-በረድ, ግራናይት እና ዶሎማይት የተባሉ ብረት ያልሆኑ ማዕድናት በክልሉ ይገኛሉ፡፡
ቱሪዝም እና ቅርሶች
የትግራይ ክልል በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ የሰው ልጅ የስልጣኔ እና የባህል ዝርዝሮች ውስጥ የሚገኝ እና በአለም ላይ ከሚታወቁ ጥቂት ታሪካዊ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
ክልሉ በአህጉራችን ከሚገኙ እጅግ በጣም ወሳኝ የሆኑ የታሪክ ሀውልቶች የሚገኙበት ነው፡፡ ይህም ማለት ከቅድመ - ክርስትና በፊት የቆሙ ታላላቅ ሀውልቶች ይገኙበታል፡፡
ከክርሰቶስ ልደት በፊት በ2ኛው ክፍለ ዘመን የቆመው የአክሱም ሀውልት፣
ከክርሰቶስ ልደት በፊት በ5ኛው ክፍለ ዘመን እና ከቅድመ አክሱም ግዛት በፊት የተገነባው "የጨረቃ ቤተ-መቅደስ"፣
የንግስት ሳባ የመታጠቢያ ቤት እና ቤተ-መንግስት፣ የታቦተ ፅዮን ማደሪያ ይህ ሁሉ በክልሉ የሚገኙ ዋናዋና ቅርሶች ናቸው፡፡
የአክሱም ሃውልት
ታቦተ ጽዮንም ከእየሩሳሌም ቤተ-መቅደስ የመጣ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ክልሉ በአለም ላይ ታላቅ የሆኑትን ሁለት ሀይማኖቶች እነሱም ክርስትናን በ4ኛው እንዲሁም እስልምናን በ6ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እንደ በር አገልግሏል፡፡
የነጃሺ መሰጊድም በክልሉ የሚገኝ ሌላው የታሪክ እና የሀይማኖት መስህብ ነው፡፡
በክልሉ ከ120 በላይ የሚሆኑ ለገዳም አገልግሎት የሚውሉ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት እና ዋሻዎች ሲገኙ በትግራይ በሚገኙ ተራራዎች ሁሉ ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡
እነዚሁ ገዳማትና ዋሻዎች በውስጣቸው የተለያዩ የብር መስቀሎችን፣ የሚያንፀባርቁ ዘውዶችን፣ ጥንታዊ የብራና ፅሁፎችን እና የሳባ ፊደላት የተቀረጸባቸውን ድንጋዮች ይዘዋል፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል የባህል ቅርሶች ተደማምረው ክልሉን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ተመን የለሽ አካባቢ ያደርገዋል፡፡