ሐሙስ 30/01/17
የ2ኛ ጴጥሮስ መልዕክት ( ክፍል 01 )
የመልዕክቱ ታሪካዊ ዳራ
መጽሐፉን ማን ጻፈው?
ሐዋርያው ጴጥሮስ በሁለቱም መልዕክቶቹ መጀመሪያ ላይ ራሱን ያስተዋወቀው “ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ” እንደሆነ ሲሆን መልእክቱንም የጻፈው “ … በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ ” 2 ጴጥ 1: 1 በሚል ነው ። ጴጥሮስ ይህንን ሁለተኛውን መልእክቱን የጻፈው በመጀመሪያው መልዕክቱ ለጻፈላቸው ሰወች እንደሆነ ራሱ “ወዳጆች ሆይ ፥ አሁን የምጽፍላችሁ መልእክት ይህች ሁለተኛይቱ ናት “ 2ኛ ጴጥ 3፡1 በማለት ግልጽ አድርጎታል ። ጴጥሮስ ይህን መልዕክት በሮም ውስጥ ሆኖ በ64-66 ዓ.ም. ጻፈው መልዕክቱን እንዲጽፍ ያነሳሳው ዋንኛ ነገር ቢኖር ከመልዕክቱ ይዘት በመነሳት በትንሿ እስያ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በመካከላቸው የሐሰት አስተማሪዎች እንደነበሩ በመስማቱ ነው ። በዚህም በቅዱሳኑ መካከል የኑፋቄን ትምህርት የሚያሰራጩ ሰዎች ስላላቸው ስውር መገኘትና ስራ በጽኑ አስጠንቅቋቸዋል 2ኛ ጴጥ 2፡1
የመልዕክቱ ጭብጥ አሳብ
ጴጥሮስ በዚህ መልዕክቱ በተደጋጋሚ ያነሳው የእግዚአብሔር ቃል 1:4, 19-21, 3:1,2, 14-16 እግዚአብሔርን ለመምሰል ወይም መልካም ህይወት ለመግለጥም ይሁን ከሐሰት አስተምህሮ ለመጠበቅ ወሳኙ የቅዱሳን መሳሪያ መሆኑን አስረግጦ ተናግሮአል ። የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ማወቅና በቃሉ መሰረት መኖር አታላይ ከሆነው ከሐሰተኞች ቃል ለመጠበቅ ፣ በመከራ መካከል ጌታን አስከብሮ በእምነት ለማለፍ ቃሉ ዋና የጸጋ መሳሪያ መሆኑን ይናገራል ።
መልዕክቱ ለኛ የሚያስተላልፈው አሳብ
ዛሬም እኛ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፍን እንገኛለን እነዚህን ፈተናዎች መጋፈጥና በድል መመላለስ የምንችለው ሐዋርያው እነዚህን ቅዱሳን እንደመከረ የእግዚአብሔርን ቃል የህይወታችን መሰረት ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ፡፡ ጴጥሮስ ሲናገር “ … በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ … “ 2ኛ ጴጥ 3፡17,18 ይህ ነው ወሳኙ ነገር ፡፡ ጴጥሮስ በዚህ መልዕክቱ የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ እንደሚጣ የገለጠ ሲሆን ሁልጊዜ በቃሉ ህያው ሆኖ የጌታን መምጣት መጠባበቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግሮአል ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በቃሉ የመለኮት ባህሪ ተካፋዮች እንድንሆን ስላደረገን እኛም አእምሮአችንን በቃሉ እየገነባን በተቀደሰ ኑሮ ለሚመጣው ለየትኛውም ፈተና ዝግጁ ለመሆን ትጋትን ሁሉ ማሳየት እንደሚገባ ተናግሮአል ።
የመልዕክቱ ዋና ዋና አሳቦች
- እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ባለው ጸጋ ከመለኮታዊ ባህሪይ የመካፈል መብት ሰጥቶናል 2ኛ ጴጥሮስ 1፡2-4
- የእግዚአብሔር ጸጋ እርሱን ለመምሰል ያስችለናል 2 ጴጥ 1:5–15
- ሰው ሰራሽ ተረት ሳይሆን እውነተኛ መገለጥ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት አረጋግጠዋል 2ጴጥ 1፡16-21
- ሐሰተኛ አስተማሪዎች በእግዚአብሔር እጅ ለጥፋት ተጠብቀዋል 2ኛ ጴጥሮስ 2፡1-10
- ሐሰተኛ አስተማሪዎች በስነ ምግባር የዘቀጡ መሆኑን ይናገራል 2ኛ ጴጥ 2፡11-22
- ቅዱሳን እየኖርን ያለነው በመጨረሻው ዘመን በመሆኑ በብዙ ጥንቃቄ መኖር እንደሚገባ 2ኛ ጴጥ 3፡1-13
- ጌታ በፍቅሩ ምክንያት ማንም እንዳይጠፋ በማሰብ ይታገሣል ነገር ግን እንደ ሌባ በጨለማ ላሉ ለፍርድ ተመልሶ ይመጣል 2ኛ ጴጥ 3፡8-10
ተባረኩ
telegram :-
@mentesnotkebede2020👉 join በማድረግ ሌሎች እንዲሳተፉ ሼር አድርጉት
Email :- mentesnot_kebede@yahoo.com
ስልክ :- 0911693190