ቋንቋችን በቁርኣን አቀራራችን ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድርብን
~
ቋንቋዎች በአካባቢና በዘመን መለያየት የተነሳ ልዩነቶችን ያንፀባርቃሉ። ዐረብኛን እንደ ምሳሌ ብንወስድ በተለያዩ ሃገራት የተለያዩ ዘዬዎች አሉ። አንዳንዶቹ ለኛ ቀርቶ ለዐረቦቹም የሚከብዱ ናቸው። የሆነ ቦታ አንድ ግብፃዊ ያወራኛል። እኔ ከአንዳንድ ቃላት በስተቀር የሚያወራው አልገባኝም። የሌላ ሃገር ዐረብ ቦታው ላይ ነበርና ሁኔታዬን የተረዳ መሰለኝ " የተናገረው ገብቶሃል?" አለኝ። "አልገባኝም" አልኩት። አጠቃላይ የሚናገራቸው እንደሚከብዱኝ ነገርኩት። "እኛም እነሱ ስላስተማሩን ነው ቋንቋቸውን የለመድነው" አለኝ። እንዲያውም የሚገርም ገጠመኝ ነገረኝ። ልጁን ትምህርት ቤት እንዳስገባው ጥቂት ቀን ከሄደ በኋላ "ከዚህ በኋላ እዚያ ትምህርት ቤት አልሄድም። በዐረብኛ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ነው የሚያስተምሩት። እኔ እየገባኝ አይደለም አለኝ። ለህጃቸው (ዘያቸው) እንግዳ ስለሆነበት ነበር እንደዚያ ያለው" አለኝ።
ወደ ራሳችን ስመልሰው በየቋንቋው አካባቢን መሰረት ያደረገ ሰፊ የዘዬ ልዩነት አለ። አንዳንዴ ታዲያ ቋንቋችን ወይም ዘያችን የቁርኣን አቀራራችን ላይ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል። ለምሳሌ ያክል
* ሀምዛ (أ) እና ዐይን (ع)፣
* ሓእ (ح)፣ ኻእ (خ) እና ሃእ (هـ) ፣
* ዛል (ذ) እና ዛይ (ز)
ወዘተ በቋንቋ ተፅእኖ ምክንያት ብዙ ሰው ያለ ልዩነት አደባልቆ ያወጣቸዋል። خير ለማለት ከይር ወይም ሀይር የሚለው ብዙ ነው። {غَیۡرِ ٱلۡمَغۡضُوبِ عَلَیۡهِمۡ وَلَا ٱلضَّاۤلِّینَ} ለማለት "ገይሪል መግዱቢ አለይሂም ወለድዷልሊን" የሚለው ብዙ ነው። 0ረብኛ ደግሞ ጥልቅ የድምፅ አጠቃቀም አለው። ثم፣ سم እና صم አንድ አማርኛ ተናጋሪ በአንድ ድምፅ ሊያወጣቸው ይችላል። ሶስቱም ቃላት ግን የተለያየ ድምፅ እና የተለያየ ትርጉም ነው ያላቸው። እነዚህ ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ቁርኣን አቀራራችን ላይ በትክክል ካልተማርን ትርጉም በሚቀይር መልኩ ግድፈት እንድንፈፅም ሊያደርጉን ይችላሉ። ሁለት አካባቢዎችን እንደምሳሌ ልጥቀስ። አዲስ አበባ እና ወሎ።
1. አዲስ አበባ፦
በአብዛኛው የሃገራችን ህዝብ ዘንድ የዐረብኛዋ ض ድምፅ የለችም። (ሁሉም ያላልኩት ለምሳሌ ዐፋር እና ምስራቁ የወሎ ክፍል አነጋገር ላይ ይሄ ድምፅ እንዳለ ስለማውቅ ነው።)
እና ይሄ ድምፅ (ض) የሌላቸው ተናጋሪዎች { وَوَجَدَكَ ضَاۤلࣰّا فَهَدَىٰ } የሚለውን "... ዳለን ... " ብለው ቢያነቡት ትርጉም የሚቀይር ግድፈት ነው። ضر እና در የተለያየ ድምፅ ያላቸው የተለያዩ ቃላት ናቸው። ትርጉማቸውም ፍፁም የተለያየ ነው። በተመሳሳይ
ضال እና دال
ضرس እና درس
ضرب እና درب
እያልን ብንዘረዝር ብዙ ድምጻቸውም ትርጉማቸውም የሚለያዩ ቃላትን ማየት እንችላለን። ضን በትክክል የማያወጣ ሰው እነዚህን ቃላት ትርጉም በሚቀይር መልኩ ነው የሚያወጣቸው።
ይሄ ክፍተት የአዲስ አበባ ልጆች ላይ በሰፊው ይታያል። ልጆች ቁርኣን ሲቀሩ ይቸገራሉ። ከዱዓቶች ራሱ እንዲህ አይነት ግድፈቶች የሚታዩባቸው አሉ። {سَنَشُدُّ عَضُدَكَ بِأَخِیكَ} የሚለውን የቁርኣን አንቀፅ "0ዱደከ" እያሉ የሚቀሩ አሉ። {أَنقَضَ ظَهۡرَكَ} የሚለውን "አንቀደ ..." ብሎ መቅራት ስህተት ነው። አዲስ አበባን በቅርብ ስለሚገጥመኝ በምሳሌነት አነሳሁት እንጂ ችግሩ ሌሎችም ጋር ይኖራል።
2. ወሎ፦
የወሎ አማርኛ የቃላት ሃብቱ ስፋት አለው። እጅግ በርካታ ቃላት ከዐረብኛ እና ከኦሮምኛ አስገብቷል። ከሌሎችም አጎራባች ቋንቋዎች በስሱም ቢሆን ይዋዋሳል። ቁልምጫዎቹ፣ ስሜትን (ፍቅርን፣ መቆርቆርን፣ ሃዘንን፣ ...) ገላጭ የሆኑ ለየት ያሉ ቅላፄዎቹ ለቋንቋው ተጨማሪ ውበት ናቸው።
እዚህ ላይ ማንሳት የፈልግኩት ግን ከቁርኣን ጋር በተያያያዘ የተለመደው የ "ዴ" ድምፅ ተፅእኖን ነው። የወሎው አማርኛ ዘዬ ላይ "ደ"ን "ዴ"፣ "ድ"ን ደግሞ "ዲ" አድርጎ ወይም ወደዚያ አቅርቦ ማውጣት የተለመደ ነው። ችግር የሚሆነው ይሄ የአነጋገር 'ስታይል' ወደ ቁርኣን አቀራር ሲመጣ ነው።
* ከላይ ያቀረብኳትን ኣያ {وَوَجَدَكَ ضَاۤلࣰّا فَهَدَىٰ} ብንወስድ አንድ ሰው "ወወጀዴከ ... ፈሀዲያ" ብሎ ቢቀራ ልክ አይሆንም። "ወወጀደከ ... ፈሀዳ" መሆን አለበት። {عَبۡدًا إِذَا صَلَّىٰۤ} የሚለውን "ዐብዴን ኢዛ ሶልላ" ብሎ ቢቀራው ልክ አይደለም።
* እንዲሁም {قُلۡ هُوَ ٱللَّهُ أَحَدٌ} የሚለውን "... አሐዲ" በሚል፣ {وَمَاۤ أَدۡرَاكَ} የሚለው "ወማ አዲራከ" በሚል መቅራት ስህተት ነው።
ተመሳሳይ ሁኔታዎች በጣም ብዙ ናቸው። ይሄ መታረም ያለበት ነው።
በሌላ በኩል አንዳንዶች ይህንን በመሸሽ ሌላ ግድፈት እያመጡ ነው። "ዴ" እና "ዲ" እኮ የራሳቸው ቦታ አላቸው። ስህተት የሚሆነው ያልቦታቸው ሲውሉ ነው። በቦታቸው አለመጠቀም ሌላ ስህተት ነው። "እንዴት ነህ?" ለማለት "እንደት ነህ?"፣ "አዲስ" ለማለት "አድስ"፣ "ወልዲያ" ለማለት "ወልድያ" ይላሉ። ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸው ብዙ ስህተቶች አሉ። የትም ቦታ "ዴ" እና "ዲ" ላለመጠቀም ይጠነቀቃሉ። ይሄ ስህተት ነው። በርእሴ እንደጠቆምኩት የኔ ትኩረት ከቁርኣን አነባበብ ጋር ያሉ ግድፈቶችን ማስታወስ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው {وَٱلۡعَـٰدِیَـٰتِ ضَبۡحࣰا} የሚለውን "ወልዓድያቲ " ብሎ ከቀራ ስህተት ነው። ትክክለኛው "ወልዓዲያቲ " ነውና።
አዲስ አበባንና ወሎ ለማሳያ መዘዝኩ እንጂ በየቋንቋ የተለያዩ የተለመዱ ግድፈቶች አሉና ትኩረት እንስጣቸው። አላማዬ ቁርኣንን በትክክል እንድንማር እና በአቀራራችን ላይ ቋንቋችን ተፅእኖ እንዳያሳድርብን ማስታወስ ነው። ተጅዊድን በጥልቀት እንደተማረ ሰው ባንሆን እንኳ ቢያንስ ትርጉም በሚቀይር መልኩ እያዛነፍን እንዳንቀራ መጠንቀቅ ይገባል።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor