Posts filter


ማነው የተረዳኝ

ማነው የተረዳኝ የገባው ስሜቴ
እኔ በሱ ፍቅር እንቅልፍ ማጣቴ።
ታዲያ እስከ መቼ አፍኜው እኖራለሁ
አንድ ቀን በይፋ ግልፅ አወጣዋለሁ።

እስከዛች ደቂቃ እስከዛች ቀን ድረስ
ይህንን ሚስጥሬን ለማንስ ልተንፍስ።
እሱ ኩራተኛ ፍቅር የማይገባው
የፍቅርን ትርጉም የማይረዳው
መልክና ቁመናው ልብ የሚነዛው
ሳቁና ፈገግታው መንፈሰ የሚያድሰው
ከሁሉ ተግባቢ ያ ቆንጆ መልካም ሰው
የኔን ልብ ሰርቆ ወዴትስ ሰወረው?

እባክህ ተረዳኝ አስብልኝ አንዴ
እኔ ባንተ ፍቅር ተቃርቧል ማበዴ
ሌላ ሴት ጋር ሳይህ እቀናለሁ ባንዴ
ይህን እወቅልኝ እባክህን ውዴ።

አንተ ፈገግ ስትል እኔ የምስቀው
አንተ ስትከፋ እኔ አዝኜ የምውለው
እባክህ ተረዳኝ ስለወደድኩህ ነው።

    
       ፍቅርሽን ላልተረዳሽ ላኪለት 🫥


#ሩ_ቅ_ፍ_ቅ_ር

እሩቅ ማዶ ሆነሽ ከአድማስ ባሻገር
ከማላውቀው ስፍራ ከማላውቀው ሰፈር
ልቤን አንቺን ወዶ ካንቺው ዘንድ ቢቀር
እንዴት ብዬ ላግኝሽ አይቻለኝ ነገር

ከስልኬ መስታወት ፎቶሽን አይቼ
ልቤን ብትከፍዪው ቢወዱሽ አይኖቼ
ለኔ ያበጃጀሽ መርጦ ከፍጥረቱ
ያምላኬ ስጦታ መሰልሺኝ በእውነቱ

በኔ ላይ ሰልጥኖ ውበትሽ ማረከኝ
ገና ሳላገኝሽ አካሌን ነዘረኝ
ልቤ ከኔ ሸሽቶ ወዳንቺ በረረ
መንፈሴ በሃሳብ አንቺው ዘንድ አደረ

ቀናት ተቆጠረ
ልቤም እዛው ቀረ

አጃኢብ… ቁንጅና ስንቱ ተደነቀ
አምላክም ለይቶ ባንቺ ተራቀቀ
ተመኘው በውስጤ አልኩኝ ባገኘኋት
ወይም ከጅምሩ ምነው ባላየኋት……!
 ❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️❤️


ጊዜ ይፈርዳል!

ዛሬ ከፍታ ላይ ያላችሁ፣ ዛሬ ዓለምን በመዳፋችሁ የጨበጣችሁ የመሰላችሁ፣ ዛሬ ምቾት ያንገላታችሁ፣ ህይወት የመረጠቻችሁ፣ ኑሮ የፈካላችሁ፣ በላይ በላይ ስኬት የተደረበላችሁ፣ ወዳጅ ዘመድ ፈላጊ አጨብጫቢ የበዛላችሁ አስተውሉ አንድ ቀን ዝቅ ትሉ ይሆናል፣ አስተውሉ የሆነ ጊዜ ያገኛችሁትን ሁሉ ታጡ ይሆናል፣ አስተውሉ የሆነ ሰዓት ብቻችሁን ትቀሩ ይሆናል። ዛሬ ዝቅታ ላይ የተገኛችሁ፣ ዛሬ ዓለም የናቀቻችሁ፣ ዛሬ እድል የጠመመችባችሁ፣ ወዳጅ ዘመድ የራቃችሁ፣ ግፊት ጥላቻን የተቸራችሁ፣ ሳትፈልጉ ብቻችሁን የቀራችሁ፣ ህይወት ፊቷን ያዞረችባችሁ፣ ስኬት እንደ ሰማይ ደስታም እንደ ጨረቃ የራቀቻችሁ አስተውሉ ዝቅታ መጨረሻችሁ አይደለም፣ አስተውሉ በዓለም እንደተናቃችሁ አትቀሩም፣ አስተውሉ ብቸኝነት የዘላለም እጣፋንታችሁ አይደለም። ጊዜ በጊዜው ይፈርዳል፣ ትክክለኛው ሰዓት ሁሉን ነገር ያስተካክላል። ገዢ የነበሩ ተገዢ ይሆናሉ፣ መሪ የነበሩ ተመሪ ይሆናሉ፤ በተቃራኒውም ተገዢ የነበሩ ይገዛሉ፣ ሲመሩ የነበሩ የመሪነትን ዙፋን ይረከባሉ። ስታገኙም ስታጡም፣ ስትሔዱም ስትመለሱም፣ ሲያልፍላችሁም ሲያልፍባችሁም ስሜታችሁን በልክ አድርጉት።

አዎ! ጊዜ ይፈርዳል! ጊዜ ሁሉን በግልፅ ያሳያል፣ ጊዜ ስንዴውን ከእንክርዳዱ፣ ደጉን ከክፉን፣ መልካሙን ከጎጂው ይለያል። አለኝ ብላቹ አትመፃደቁ፣ አጣው ብላችሁም አንገት አትድፉ። ሰጪም ነሺም ፈጣሪ መሆኑን አስታውሱ። ማግኘታችሁ አጥፊያችሁ ከሆነ አይሰጣችሁም፤ ማጣችሁም የሚጎዳችሁ ከሆነ ይሰጣችኋል። ችግር በዝቶባችኋል ማለት እግዚአብሔር ከሰው ሁሉ ለይቶ ይጠላችኋል ማለት አይደለም፤ ምቾት በምቸት ሆናችኋል ማለትም ፈጣሪ ከሰው ሁሉ ለይቶ ይወዳችኋል ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ነገር የሚሆነው በምክንያት ነው። ቻዩን ፈጣሪ ያውቃል፣ ደካማውንም እርሱ ያውቃል። እርሱ የሰጣችሁን የሰጠበትን ምክንያት የሚያውቀው እራሱ ብቻ ነው። የእናንተ ድርሻ መቀበልና መቀበል ብቻ ነው። ባለስልጣኑ ባለበት ስልጣን ፈላጊ አትሁኑ፤ ፈላጭ ቆራጩ እያለ በእርሱ ስራ ጣልቃ አትግቡ። ህይወት ምርጫ ነች አንዳንድ ወሳኝ ሁነቶች ግን የፈጣሪ ገፀበረከቶች ናቸው። ሮጣችሁ ማምለጥ ከማትችሉት ነገር ስር አትሩጡ፤ መጨነቅ፣ መጠበብ፣ መዋከብ ለማያስተካክለው ነገር ራሳችሁን አታስጨንቁ፣ ራሳችሁን አታዋክቡ።

አዎ! ጀግናዬ..! ከቀረበልህ የመምረጥ ምርጫ አለህ፣ የተመረጠልህን ግን ከመምረጥ በላይ የመኖር ግዴታ አለብህ።  የትናንት ድካምህ፣ የዛሬ ጥረትህ፣ የአሁን ልፋትህ ፍሬ የሚያፈራበት ጊዜ አለ። የተሻለ ነገን ቁጭ ብለህ አትመኝ፣ ያለስራ መልካም ነገር እንዲገጥመህ አትፈልግ። ጊዜ ሁላችንም ላይ ፈጣሪ የሾመብን ፈራጃችን ነው። ማንም ያልሰራውን ያገኝ ዘንድ አልታዘዘለትም፣ ማንም ያልደከመበት እንዲሰጠው አልተፈረደለትም። ዛሬ የትም ሁን፣ አሁን ምንም ስራ ነገር ግን በስራህ የምታምን፣ ነገህን መቀየር የምትችል፣ ሰው ከሚያስብልህ በላይ ፈጣሪ እንደሚያስብልህ ካመንክ በእርግጥም ምንም ነገር ሊቀየር ይችላል፣ የትኛውንም ከባድ ጊዜ ማለፍ ትችላለህ። ድህነት የህይወት ዘመን እጣፋንታህ አይደለም፣ ማጣት፣ መቸገር፣ መገፋት የተፈረዱብህ ፍርጃዎችህ አይደሉም። ላንተም ቀን እንደሚመጣ፣ ላንተም ፀሃይ እንደሚወጣ፣ ህይወትህ በአምላክ ፀጋና በረከት እንደሚታነፅ ከልብህ እመን። እየተገፋህ፣ እየተጠላህም ቢሆን ጊዜ ከፍ ያደርግሃል፤ ዛሬ ብትረሳም በሞገስ በግርማ አበይት የምትሆንበት ጊዜ ይመጣል። በራስህንም ሆነ በፈጣሪህ መቼም ተስፋ እንዳትቆርጥ።


ነፍሳችሁን አትርፉ!

ወጣን ውረድን፣ ስራን አረፍን፣ ሞከርን ሳንሞክር ቀረን፣ ደከምን ሳንደክም ቀረን፣ ዓለምን ዞርን ምድርን አሰስን በስተመጨረሻ አንድ መዳረሻ አለን። እርሱም ወደ አንድ አምላክ ወደ ቅዱስ ፈጣሪ መሔድ ነው። ያኔ እርሱ ፊት የቆምን እለት ምን እናሳየው ይሆን? የትኛው መልካም ስራችን ይመሰክርልን ይሆን? ከየትኛው ትርፋችን ቀድተን እናሳየው ይሆን? ማንም ሆንን ማንም ዳኛችንና ገዢያችን ፈጣሪ ብቻ ነው። በዓለም ሳላችሁ ምን ገዝቷችኋል? በምድር ስትመላለሱ ምን ነፍሳችሁን ወስዷታል? አሁን በዚህች ቅፅበት የሚያሳስባችሁና ቀልባችሁን የሰረቀው ነገር ምንድነው? በውሸት ዓለም እየኖራችሁ ራሳችሁን አትካዱ፣ ነገ ዞር ብሎ ለማያያችሁ ሰው ብላችሁ ራሳችሁን አትጡ፣ በአንድ ጀምበር አመድ በሚሆን ንብረት ፈጣሪያችሁን አትካዱ። የሰው ልጅ ስጋው ብቻ የስጋ ፍቃዱን ስለፈፀመ አይኖርም። ነፍሱም የራሷ ፍቃድ አላትና ፍቃዷ ሊፈፀም ይገባል። ነፍስ እለት እለት የአምላኳን መንፈስ ትጠማለች፣ ነፍስ በየጊዜው ሰማያዊ ሀሴትን ትናፍቃለች።

አዎ! ነፍሳችሁን አትርፉ! የማትሞላዋን ዓለም ለመሙላት አስር ቦታ አትበጣጠሱ፣ የሌለውን ፍፁም ህይወት ለመኖር ብኩን አትሁኑ። ዞሮ ዞሮ ማንም ሰው የሚበላው ያንኑ የዘራውን ነው፤ በስተመጨረሻ ማንም ሰው በእጁ የሚያስገባው ያንኑ የደከመለትን ነገር ነው። ያለ ምንም እረፍት ስጋውን ብቻ ሲመግብ የነበረ ሰው የስጋ ፍቃዱ ሲያይል፣ ለዓለም ብልጭልጭ ሲገዛ፣ ነፍሱ ተጨንቃ ስታስጨንቀው፣ በቁስ ተከቦ ባዶነት ሲያሰቃየው፣ ብዙ ወዳጅ እያለው አንዱም መፍትሔ ሳይሰጠው ሲቀር ራሱን ይመለከታል። ስጋና ዓለም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ዓለምን የሚወድ የስጋው ባሪያ ነው፣ መንፈሱን የሚሰማ ግን የነፍሱ ተገዢ ነው። ነፍሳችሁን ጥላችሁ ሁለንተናዊ ብልፅግናን እንዳታስቡ፣ የነፍሳችሁን ፍቃድ ችላ እያላችሁ ደስተኛ እሆናለሁ ብላችሁ እንዳታስቡ። ስጋ የሚበላውን የሚጠጣውን ያህል ነፍስም እንዲሁ የምትበላውና የምትጠጣው ነገር ያስፈልጋታል፣ ስጋ መሳቅ መጫወት እንደሚወድ ሁሉ ነፍስም እንዲሁ የአምላኳን ፍቅር አብዝታ ትናፍቃለች፣ ከእርሱ የሚገኘውን ሀሴት ትጠብቃለች።

አዎ! ጀግናዬ..! በስጋ ፍቃድ ተታለህ ነፍስህን አትበድላት፣ በዓለም ፍቅር ታውረህ የፈጣሪህን በረከት አትጣ። ምንም ያህል ዓምት ምድር ላይ ብትመላለስ፣ ምንም አይነት የተንደላቀቀ ህይወት ብትኖር፣ ከማንም በላይ ትልቅ ስልጣን ቢኖርህ፣ ምንምያህል ታዋቂና ዝነኛ ብትሆን አንድ ቀን እንደ ማንኛውም ሰው ለዓለም ባዳ ለምድርም ወዳጅ መሆንህ አይቀርም። ሁሉን ትተህ ወደ አምላክህ መሔድህ ግልፅ ነው። መሔድህ ካልቀረ ግን ባዶ እጅህን አትሔድ ዘንድ ነፍስህን የሚያስደስት፣ አምላክህንም የሚስመሰግን በጎ ስራን ስራ፤ ከሰው ፊት በላይ ፈጣሪህ ፊት ሞገስን የሚያሰጥህን መልካሙን ምግባር ፈፅም። ጠፍተህ እንደሆነ ራስህን በጥልቀት መርምር፣ ራስህን አጥተህም እንደሆነ ማንነትህን ለመረዳት ሞክር። ፀሃይ በአንዴ አታቃጥልም የዓለም ግለትም እንዲሁ ቀስበቀስ እያሞቀ አለማምዶ በዛው አቅልጦ ያስቀራል። በዓለም እስታ ተቃጥሎ ከመጥፋት ራስህን ጠብቅ፣ በስጋ ፍቃድ ከመገዛት ተቆጠብ፣ ነፍስህን ዋጋ አታሳጣት። መንፈስህን ታደግ፣ ራስህን ግዛ፣ ዓለምንም በፍቃድህ ስር አድርግ።


ከፍጥረታት ተማር!

የእድገት ነፃነት አለውና በተቻለው አቅም እስከመጨረሻው ያድጋል። ዛፍን ተመልከት እስክ ጫፍ ያድጋል፤ አንበሳን ተመልከት እስከመጨረሻው ታግሎ አድኖ ይበላል፤ ንስርን ተመልከት ከየትኛውም አዕዋፍ በላይ በከፍታ ላይ ይበራል። እያንዳንዳቸው ፍጥረታት የመጨረሻውን አቅማቸውን ይጠቀማሉ። የሰው ልጅ ግን በምርጫው ይታለላል፤ ድክመቱን ይንከባከባል፤ አለመቻሉን ደጋግሞ ያወራል፤ አደጋን በመፍራት ይታሰራል። ማሰብ መቻሉ ብዙ መስራት እንዲችል እንደሚያደርገው ረስቶታል። አንድ ቦታ ታስሮ ከእፅዋት ባነሰ የእድገት ደረጃ ውስጥ እራሱን ያገኘዋል። ፍጥረታት ምርጫ የላቸውም፤ እድገታቸው ግዴታ ነው፤ አድኖ መብላታቸው ምርጫ ውስጥ አይገባም። ወድቀው ተነስተው፣ ተሰብረው ተጋግጠውም ቢሆን የፈለጉትን ያሳካሉ፤ በእጃቸውም ያስገባሉ። በእንስሳት አለም ሰዶ ማሳደድ፣ ማደን መታደን ህይወታቸው ነውና አንዱ አንዱን አድኖ ለመብላት እስከመጨረሻው መፋለም ይኖርበታል፤ ሌላኛውም ነፍሱን ለማትረፍ ሙሉ አቅሙን ይጠቀማል።

አዎ! ጀግናዬ..! ከፍጥረታት ተማር! ከእድገት፣ ከለውጥና ከስኬት ውጪ ምርጫ እንደሌለህ አስብ። ብዙ አማራጮች ባስቀመጥክ ቁጥር የምትወድቀው አንተ ነህ። አንድ የምትተማመንበት ነገር የለምና ሁሉን ለመያዝ ስትሞክር አንዱንም ሳትይዝ ባዶ እጅህን ትቀራለህ። የያዝከው ብቻ እንደሚያዋጣህ እመን፤ የሚያስከፍልህን ለመክፈል እራስህን አዘጋጅ፤ እንዳታደርገው የሚያደርጉህ ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩም ከማድረግ በቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለህ አስተውል። ከውሃ የወጣች አሳ በደቂቃዎች ትሞታለች፤ አንተም ህልምህን መኖር እንዳቆምክ የህይወትን ትርጉም ታጣለህ፤ አላማህ ይጠፋብሃል፤ በመኖርህ ውስጥ ስሜት ታጣለህ፤ የሚገባህን ባለማግኘትህ ስብራት ይሰማሃል። ብዙ ምርጫ ቢኖርህም ምርጫህን እርሳው፤ ብዙ የገቢ ምንጭ ቢኖርህም አንዱን አጥብቀህ ያዝ፤ በብዙ ሰዎች ብትከበብም ጥቂቶቹን ብቻ አቅርብ።

አዎ! የበዛው ምርጫህ እንዳይሸውድህ ተጠንቀቅ፤ የምታገኘው ገቢ እንዳያሰንፍህ፣ የከበቡህ እንቅፋቶች፣ የሚወሩብህ ወሬዎች ከሚገባህ ህይወት እንዳይነጥሉህ እራስህን ጠብቅ። ዛሬን ብቻ ብኖር፣ ህይወቴ ባይስተካከል፣ እራሴን ባላስተምር፣ በሒደት ባላድግ የሚጠብቀኝ ጥፋት ነው ብለህ ማሰብ ጀምር። ምርጫ የሌለው ሰው ተኝቶ አያድርም፤ ቀን ከሌሊት ሲለፋና ሲተጋ ይውላል፤ ያድራል። እድገት ምርጫው ሳይሆን ግዴታው ነው፤ ለውጥ አይቀሬ ቢሆንም በአዎንታዊውና ጠቃሚው ለውጥ ግን አይደራደርም። እድገትን የማይፈልግ፣ ስኬትን የማይመኝ ሰው አይኖርም፤ ፍላጎቱ ግን በሃሳብ ወይም በምኞት ብቻ ስለሆን ምንም ሊያመጣ አይችልም። እድገትን በተግባር፣ ስኬትን በጥረት፣ ደስታን በስራ፣ ህይወትንም በመኖርን ፈልግ። በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን ለውጥና እድገት ምርጫ የሌለው አማራጭህ እንደሆነ አስተውል።


ልቤን መልስልኝ!

ፍቅር ነህ፤ አባት ነህ፤ ደግ፣ አዘኛ፣ አሳቢ ንፁህ ጌታ፣ ፍፁም አምላክ ነህ። ለስራህ የሚመጥን ቃል ባይኖርም፣ የሚገልፅህ አገላለፅ ባይገኝም አንተ ግን የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ ነህ። ትናንት ነበርክ፣ ዛሬም አለህ፣ ነገም ለዘለዓለም ትኖራለህ። ይቅርታህ እጅግ ግሩም ነው፤ ሳትለመን የምትምር፣ ሳትጠየቅ የምትፈውስ፣ ሳይማፀኑህ፣ ሳያለቅሱብህ ይቅር የምትል፣ ትዕግስትህ ገደብ የሌለው፣ ጠብቀህ የማይደክምህ፣ ለቅንነትህ ዳርቻ፣ ለቸርነትህ መጨረሻ የሌለህ አንተ በእርግጥም ፍቅር ነህ፣ አባት ነህ፣ ቸር ጠባቂ ነህ። ስትምር ልኩን ታውቀዋለህ፣ ይቅር ስትል ማሳረፉን ትችላለህ። ቃል አለህ በሰማይ በምድር ልጆችህን ደጋግመህ ለመማር፣ ይቅር ለማለት፣ ለማስተማር። ቃልህንም ስትጠብቅ ኖረሃል፣ ከአባትም በላይ አባት ሆነህ በቃልህ ልክ ተገልጠሃል፤ ምህረትህንም ያለገደብ ሰጥተሃል።

አዎ! ጀግናዬ..! የሚመጥነው ቃል ብታጣ፣ የሚወክለው አገላለፅ ባታገኝ ፍቅር ነህ፣ ደግ ፍፁም አምላክ ነህ በለው። ነገር ግን ፍቅሩ እስኬት ይሆን? ከፈጣሪ ውጪ ምህረትን ማን ያውቃል? ይቅርታን ማን ይወክላል? በንፅህና ማን ይገለፃል? በትዕግስት ማን ይወከላል? ምህረቱ እንጂ ስራችን መቼም ከፊቱ አያቆመንም፤ ቸርነቱ እንጂ ምግባራችን ስሙን ለመጥራት አያበቃንም፤ ርህራሔው እንጂ ማንነታችን ከቤቱ አያቀርበንም። እለት እለት ብንበድልም እለት እለት እየማረ እዚህ አደረሰን፤ በየቀኑ ብናሳዝነው እስከዛሬ ታገሰን፤ ሳናቋርጥ ብናስቀይመው፣ ከትዕዛዙ ብንወጣ፣ ከመንገዱ ብንለየ ጥበቃው ግን ሁሌም አብሮን ነው። ልጅ በአባቱ ይመካል፤ በእናቱም ይፅናናል። አባትነቱ በፈጣሪነት ውስጥ ነውና ክብርን ክብር ላይ እየጨመረ እዚህ አድርሶናል፤ ለዚህም አብቅቶናል።

አዎ! በእርግጥም አምላክን ምን ይገልፀው ይሆን? ፍቅር ነው መባሉ የፍቅርን ዋጋ ከማግዘፉ በላይ እርሱን አይወክለውም፤ ፍፁም መባሉም የፍፁምነትን ዳርቻ ቢያሳይ እንጂ ብቻውን ሊገልፀው አይችልም። መምከር፣ ማስተማር፣ መገሰፅ ሲያውቅበት፣ በምህረቱ ብዛት እያስነባ፣ በማያልቀው ይቅርታው እያስለቀሰ፣ በማይገደበው ቸርነቱ ልብን እየሰረሰረ ዘልዓለማዊ ትምህርትን ያስተምራል፤ እንከን አልባውን ምክር ይለግሳል፤ በቃሉ ብቻ ሰላምን ያድላል፣ ፍቅርን ይሰጣል፤ ፈውስን ይቸራል። አውቀህ የምትጨርሰው ሳይሆን የሚውቅህ አምላክ አለህ። እውቀቱም ፍፁም ነውና ሳትነግረው የሚያስፈልግህን ያውቀል፤ ለዛም ከሌላው የተለየ መንገድን ሰጠህ፣ በሚመጥንህ ልክ አጠነከረህ፣ አስተማረህ፣ ደገፈህ። ምህረቱን እያሰብክ ቀና በል፤ በይቅርታው ዳግም አንሰራራ፤ በቸርነቱ በሚገባ ተማር። "የማያልቀው በደሌን ፍፃሜ በሌለው ምህረትህ ሸፍንልኝ፤ ዳግም እንዳልበድል ልቤንም መልስልኝ" በለው።


ልክህን አስቀድም!

አንተ ማለት ትክክለኛው ማንነትህ ነህ። ዛሬ ታይቶ የሚጠፋ ማንነት የለህም፤ በየጊዜው የሚቀያየርና ለሰዎች እይታ ብቻ የሚኖር ስብዕና የለህም። የምታደርገውን ሁሉ ሰዎች አይተው እንዲያደንቁህ አትፈልግ፤ በሰው ፊት ተወዳጅና ጥሩ ስም ያለው ለመምሰል ከአቅምህ በላይ አትኑር። ሁላችንም ደረጃ አለን፤ እያንዳንዳችን የሚወክለን የገቢ ምንጭ፣ ማንነትና ስብዕና አለን። ለእራሳችን ከመገዛታችን፣ እራሳችንን ከማስደሰታችን፣ በእራሳችን ከመኖራችን በፊት ግን ለታይታና እይታ ውስጥ ለመግባት የምናወጣው ወጪ፣ የምናባክነው ጊዜና ንብረት ሁሉ ዋጋችንን የሚያወርድ እንጂ የሚያሳድግ አይደለም። ሳይኖርህ እንዳለህ ስለታሰብክ፣ ከደረጃህ በላይ ስለተለካህ፣ በማይወክልህ ማንነት ስለታወቅክ ጊዜያዊና የውሸት ኩራት (pride) ሊሰማህ ይችላል፣ ነገር ግን በስተመጨረሻ እራስህን ስታታልል እንደነበር ትገነዘባለህ። መኖራችን ለሰዎች፣ ለስም፣ ለይውንታ፣ ለመወደድና ለክብር አይደለም። መኖራችን ከእራሳችን በላይ ሰዎችን በትክክለኛው መንገድ ለመርዳትና ለማገዝ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ልክህን አስቀድም! እንደ አቅምህ፣ በደረጃህ ተንቀሳቀስ። ሃብታም መስለህ መታየትህ ያለህንም ከማሳጣቱ ውጪ ምንም የሚያተርፍልህ ነገር የለም፤ የቤትህን ክፍተት ሳትሞላ በሔድክበት ሁሉ ካላጋበዝኩ ማለትህ ክፍተትህን አይሞላም፤ ባልሆንከው ሰውነት ለመታወቅ መጣርህ ትክክለኛውን አንተነትህን አይቀይርም። እውነት እውነት ነው፤ ምንም ብትደብቀው፣ ብታስመስልበት፣ በውሸት ብትሸፍነው በጊዜው መታወቁና መገለፁ አይቀርም። ያንቺ ባልሆነው ጌጥ ብታጌጪ አንድም ድጋሜ በእራሱ ጌጥ ለመታየት ትቸገሪያለሽ፣ ሌላም ያለጌጥ ያለውን ማንነት ለማሳወቅ አጣብቂኝ ውስጥ ትገቢያለሽ። ማንም የሚችለውን ያውቃል፤ ወጪውን ገቢውን ጠንቅቆ ይረዳል፤ መጠኑ ለእራሱ ግልፅ ነው።

አዎ! ለጊዜያዊ ከንቱ አድናቆትና ውዳሴ ብለህ እወነተኛ ማንነትህን (identity) አትጣ፤ ከምትችለው በላይ ለመኖር አትሞክር፤ አቅምህን ተረዳው፤ ችሎታህን በሚገባ እወቅ። ማስመሰል ከከፋው ውድቀት በቀር የሚያመጣው ነገር የለም። ሙሉና የተረጋጋ ህይወት የሚገኘው ሰዎች ፊት መስሎ ለመታየት በሚደረገው ጥረት ሳይሆን፣ የእራስን መልክና ገፅ፣ አቅምና ደረጃ በመቀበል በእርሱ ልክ በሚገባ በመኖር ነው። ከሌለህ የለህም፤ እንዳለህ ለማስመሰል የምታስመስልበት ምክንያት የለም። ድህነትህን አይቶ የሚርቅህ ካለ ቢመጣም አንተን ብሎ ሳይሆን ንብረትህን ብሎ እንደሆነ ተረዳ። በየጊዜው እራስህን ከማሻሻል በላይ ለታይታ በመኖርና በማስመሰል እራስህን አታድክም። መኩራት ካለብህ ባለህና እጅህ ላይ ባለው ነገር ኩራ፤ መደሰት ካለብህ ከውጭ በሚመጣ አድናቆትና ውዳሴ ሳይሆን ከገዛ ማንነትህ ከውስጥህ በሚመነጨው ጥልቅ ስሜት ተደሰት።


ከአሉታዊነት ተጠበቅ!

ጥቃቅን ችግሮች አድገው የጭንቀት መንስዔ ይሆናሉ፣ ሰላምን ያሳጣሉ፣ ህመምን ያስከትላሉ። ከስር መሰረታቸው መቀረፍና መወገድ ሲኖርባቸው በቸልተኝነት በመተዋቸው መዘዛቸው ብዙ ሆኖ ይገኛል። አሉታዊ የተባሉት ሃሳቦችም ለእነዚህ ችግሮች ዋንኞቹ መንስኤዎች ናቸው። በትንሹም በትልቁም ሆድ የሚብስህ፣ ለማማረር የቀረብክ፣ ለአሉታዊነት የፈጠንክ፣ ምስጋናን የዘነጋህ ከሆንክ እምቅ አቅምህ እያነሰ፣ ማንነትህ እየወረደ፣ መልካም ስብዕናህ እየተመረዘ፣ በፍቃድህ ነፃነትህን እያጣህ፣ ተናዳጅና ወቃሽ ሆነህ ትቀራለህ። አስተዋይ ልቦና የሚያስብ፣ የሚያመዛዝን አዕምሮ አለህ፣ እርሱም ከአሉታዊነት የፀዱ አዎንታዊነት ላይ የተመረኮዙ ሃሳቦችን ታስተጋባ ዘንድ ይረዳሃል። በአሉታዊነት አለም ድንቅ ተዓምራት አይኖሩም፤ አስደማሚ ክስተቶች አይታሰቡም፤ የተሻሉ አማራጮች መኖራቸውም አይታወሰም። በምሬት ተጀምረው በምሬት የሚያልቁ ቀናቶች ብቻ ይደጋገማሉ፤ የትኛውም ስራ ችግርና ክፍተቱ ብቻ ጎልቶ ይወጣል።

አዎ! ጀግናዬ..! ከአሉታዊነት ተጠበቅ! አሳሪ ሃሳቦችህን ፍታቸው፣ አሰናካይ እይታዎችህን ተፋታ። በግዴታ ሳይሆን ፈልገህና መርጠህ አሉታዊ ሰዎችን ከህይወትህ አስወጣ፤ ራቃቸው፤ ከእነርሱ ጋር ከመመሳሰልህ በፊት ተነጥለሃቸው ሂድ። እነርሱም እንዳንተው ሃሳብ አላቸው፣ ፅኑ አቋም ይኖራቸዋል፤ ይቻላል ስትላቸው በአንቻልም ይመልሱልሃል፤ ልታስረዳቸው ብትሞክር የማይቻልበትን መንገድ በሚገባ ያብራሩልሃል፤ ባለህ ብትኮራም እነርሱ የተሻለ ኖሯቸው ሲያማሩ ትመለከታለህ፤ ችግር ከአፋቸው አይጠፋም፤ ዘወትር ሌላ አካል ለመውቀስ ቆርጠው ተነስተዋል፤ ሃላፊነት መውሰድ የሚባል ነገር አይወዱም፤ የችግሩ ግዝፈት እንጂ መፍትሔው አይታያቸውም። አሉታዊነት ጨለማ ሳይኖር ድቅድቁን ጨለማ፣ ችግር ሳይኖር ግዙፉን ችግር፣ ምንም ጉድለት ሳይኖር የበዛውን እጥረት የመፍጠር አቅም አለው።

አዎ! ሃሳብ ይታሰራል፤ አቅም ይገደባል፤ በምን? በአሉታዊነት፣ በወረደና በዘቀጠ አመለካከት። ለውጥን የሚዘክሩ ሃሳቦች፣ የተሻሉ አማራጮች የማይማርከውና የማያስደስተው ሰው በፍፁም የእድገት ሃሳብህ ደጋፊ ሊሆን አይችልም። ለአመታት ስታቅደው የኖረከው ግዙፍ ተግባር በአንድ አሉታዊ ሃሳብ ብቻ ዋጋ ሲያጣ፣ አፈር ሲሆን፣ ወደ ምንም ሲቀየር ልትመለከት ትችላለህ። ማሰብ የሚከብደው፣ ማቀድ የሚሳነው፣ መመኘት የማይችል ሰው የለም። ነገር ግን ከብዙ አቅጣጫ የሚመጡ አሉታዊና የወረዱ ሃሳቦችን እንዴት መጋፈጥና ማለፍ እንዳለበት የሚያውቀው እጅጉን ጥቂት ነው። ማንም ሰው ያንተን ህልም አይቻልም ቢልህ፣ የማይችለው እርሱ እንጂ አንተ አይደለህም፤ የሚያወራው ከእራሱ እይታ (perspective) እንጂ ካንተ አይደለም፤ ሃሳቡ የእርሱ እንጂ ያንተ አይደለም። በእይታዎችህ ከተሻልክ፣ በሃሳብህ ከበለጥክ፣ በውሳኔዎችህ ካሸነፍክ፣ በእራስህ ከተማመንክ ማንም አያስቆምህም። የምሬት መዓት ሲደረድሩለህ በምስጋና ታከሽፈዋለህ፤ መሰናክሉን ሲዘረዝሩልህ ድልድዩን ትዘረዝርላቸዋለህ፤ ፍረሃታቸውን ሲያስረዱህ ድፍረትህን ታስረዳቸዋለህ። አሉታዊነትን በአዎንታዊነት፤ ምሬትን በምስጋና፣ ቸግርን በመፍትሔ፣ ፍረሃትን በድፍረት ተጋፍጠህ አሸንፋቸው፤ በይቻላል መንፈስም ችለህ ተገኝ።


ይቅርታ መጠየቅ አቁሚ!

ስለ ማንነትሽ ይቅርታ መጠየቅ አቁሚ፤ ስለ አስተሳሰብሽ፣ ስለ እይታዎችሽ፣ ስለ አቋምሽ አንገት መድፋት አቂሚ፤ እራስሽን ስለመሆንሽ፣ የተለየ ምርጫ ስለ መምረጥሽ፣ በተለየ አኳሃን ስለ መራመድሽ፣ ስለ ተለየው የህይወት ትርጉምሽ፣ የህይወት አረዳድሽ ይቅርታ መጠየቅ አቁሚ። ማንም በማንነትሽ፣ በአስተሳሰብሽ፣ በምርጫዎችሽ፣ በእይያዎችሽ የመውቀስ መብት የለውም። ከፍርድ ለማምለጥ፣ ከጥላቻ ለመራቅ፣ ከመኮነን ለመሸሽ ያላመንሽበትን፣ ያልተመቸሽን፣ ያልወደድሽውን ተግባር የመፈፀም ግዴታ የለብሽም። ይቅርታ የምትጠይቂው ለስህተትሽ እንጂ ለማንነትሽ አይደለም፤ ለጥፋትሽ እንጂ ለአንቺነትሽ አይደለም። አምነሽ የተቀበልሽው የገዛ ማንነትሽ የሃፍረት ምልክት፣ ለአንገት መድፋትሽ መንስዔ ሳይሆን የኩራትሽና አንገትሽን ቀና የማድረግሽ ምክንያት ነው። የማንም ያልሆነ፣ የእራስሽ ብቻ የሆነ፣ አንቺነትሽን የሚገልጥ፣ ለተመካችሽና ለአስተዋይሽ መለየ የሆነ የሰውነት አቋም አንዲሁም የፀና የአመለካከትና የእሳቤ አቋም አለሽ። ይህ አቋም የሚያኮራ እንጂ የሚሸማቅቅ አይደለም፤ የሚያስደስት እንጂ የሚያሳዝን አይደለም፤ ቀና የሚያደርግ እንጂ አንገት የሚያስደፋ አይደለም።

አዎ! ጀግኒት..! ይቅርታ መጠየቅ አቁሚ! ስለሆንሽው፣ ስላመንሸበት፣ ስላስደሰተሽ፣ ስለተቀበልሽው ማንነት ይቅርታ መጠየቅ አቁሚ። ሰዎች እንዲቀበሉሽ፣ ሰዎች እንዲወዱሽ፣ እንዲከተሉሽ፤፣ እንዲያደንቁሽ ያልሆንሽውን ከመሆን፣ ያላመንሽበትን ከማድረግ፣ የማይመለከትሽ ቦታ ከመገኘት ተቆጠቢ። ላንቺ ትክክል የሆነ፣ አንቺን ያሳመነ፣ አንቺን የሚገልፅ ተግባር ለሌሎች ስህተትና አሳማኝ ስላልሆነ ብቻ ይቅርታ የመጠየቅ ግዴታ የለብሽም። አቋምሽን የማንፀባረቅ፣ እምነትሽን የመግለፅ፣ ማንነትሽን የማሳየት፣ እራስሽን ሆነሽ የመታየት፣ በሚጠቅምሽ መንገድ የመጓዝ ነፃነት አለሽ። አቋም ስታጪ ብቻ በጥፋተኝነት አጥር ትታጠሪያለሽ፣ በይሉኝታ ትከበቢያለሽ፣ ለተግባርሽ ጥብቅና መቆም ያቅትሻል፤ ሁን ብለሽ ለፈፀምሽውም ጭምር ይቅርታ መጠየቅ ይዳዳሻል። አቋም አልባ ሰው ሲያወላውል፣ ተቀባይነትን ለማግኘት ሲጥር፣ አጉል ትሁት ለመሆን ሲጣጣር፣ ለመወደድ ሲለፋ ጀንበር ትጠልቅበታለች፤ ቀኑም ይጨልምበታል።

አዎ! ጀግናዬ..! ክብርን በፀነው አቋምህ እንጂ በበዛው ይቅርታና ማጎብደድህ አታገኘውም። አንተ አንተ የሚያደርግህ የተለየ አቋም፣ የተለየ አመለካከት፣ የተለየ እይታ፣ ሃሳብና የገዘፈ ህልም መኖርህ ነው። ለአንተነትህ መገለጫና ለማንነትህ መለያ ደግሞ ይቅርታ የመጠየቅም ሆነ የመሸማቀቅ ግዴታ የለብህም። ማንኛውም ሰው እርሱን እርሱ ያደረገው፣ ከሌሎች የነጠለው፣ ለይቶ የሚያሳውቀው የእራሱ ባህሪ፣ አቅም፣ መልክ ወይም ሃሳብ ይኖረዋል። ፈልጎ እንኳን ባያደርጋቸው መታወቂያው ለሆኑ መገለጫዎቹ ይቅርታ የመጠየቅ ግዴታ የለበትም። ትልቅ ህልም ስላለምክ፣ አስደንጋጭ ሃሳብ ስላመነጨህ፣ አይቻልም የተባለውን ለመቻል ስለተነሳህ አትሸማቀቅ፣ አትሳቀቅ፣ ለይቅርታ አትሽቀዳደም። ይቅርታ የሚያስጠይቁና የማያስጠይቁ ነገሮችን ለይተህ እወቅ። ለበደልህ፣ ለጥፋትህ፣ ለጫናህ ይቅርታ መጠየቅ ሊኖርብህ ይችላል። እራስህን ለመሆንህ፣ ፍላጎትህን ለመግለፅህ፣ ስሜትህን ለማስተጋባትህ፣ እውነተኛውን አረዳድህን ለማንፀባረቅህ ግን ይቅርታ የምትጠይቅበት ምክንያት አይኖርም። እራስህን ሆነህ ኑር፤ መገለጫዎችህን በነፃነት ከውን፤ ማንነትህን ግለፅ፤ አምነህ ስለሆነከው ሁሉ ይቅርታ መጠየቅ አቁም።


መጠጋትህን ቀጥል!

አዎ! የቻልከውን እያደረክ፣ ከቻልከው በላይም እየጣርክ፣ እየለፋህ፣ እየተጋህ፣ በአዳዲስ መንገዶች እየሞከርክ ህይወት ላላትሞና የታሰበችውን ያክል ላትሆን ትችላለች። ያዝኩት ስትላቸው የሚበተኑ፣ ደረስኩ ስትል የሚርቁህ፣ አገኘዋቸው ስትል የሚበኑ አያሌ ጉዳዮች ይኖራሉ። ጭራዉን አጥብቀህ መያዝህ እንኳን ላሰብክበት መዳረሻ ዋስትና ላይሆንህ ይችላል። ብዙ ዋጋ ከፍለህ የገነባሀው የፍቅር ህይወት የከፈልክለትን ዋጋ ያክል ሳይሆንልህ ሲቀር፤ ለዘመናት የለፋህበት ትምህርት ምንም ሳይጠቅምህ ሲቀር፣ የተማመንከው ስራ ውጤቱ አልባ ሲሆን፣ ተስፋ ያደረከው ሰው እየሸሸህ ሲመጣ፣ ነገሮች በተገላቢጦሽ መጓዝ ሲጀምሩ የተለየ ግንዛቤ፣ የተለየ አረዳድና ከወትሮው የላቀ ጥረት እንደሚጠበቅብህ አስተውል። በአንዳንድ የህይወት አጋጣሚ አንዳንድ ጉዳዮች ከሚጠቅባቸው ላነሰ እርካታ ይዳርጋሉ፣ ደስታ መስጠት ላይ ችግር ይኖርባቸዋል፣ የተሻለ ነገር ለመፍጠር አቅም ሲያንሳቸው ይስተዋላል።

አዎ! ጀግናዬ..! ውጤትህ ከጠበከው በታች በመሆኑ፣ የጓጓህለትን ያክል እርካታ ስላልሰጠህ፣ ስሜትህን ስላልቀየረ ብቻ ካመንክበት ተግባር እንዳትገታ። መጠጋትህን ቀጥል! የህይወትህ ትልቁ ሚስጥር ልታቆምበት ከነበረው አንድ እርምጃ ቦሃላ ሊሆን እንደሚችል አስብ፤ አንተነትህን የሚለካው፣ አቅምህን የሚያሳየው፣ ጥረትህን የሚያስመለክተው ውጤት በቅርብ ሊሆን እንደሚችል አስተውል። ምንም እንኳን የተጓዝከው አጭር መንገድ፣ በፅናት የታገልከውም ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም የሚቀርህና የሚጠበቅብህ ግን ካለፈው ጥረትህ በእጅጉ ያነሰ ነው። ስትነሳ በነበረህ ተነሳሽነት፣ ስትጀምር በነበረህ እውቀት፣ በጠዋቱ በነበረህ ሰሜትና ብቃት ላይ አይደለህም። አንድ በሞከርክ ቁጥር ምንም ካለመሞከር ተሽለህ ትገኛለህ፤ ወደጓጓህለት ግኚት በአንድ እርምጃ ትቀርባለህ፤ የሚቀርህን መንገድ ታሳጥራለህ።

አዎ! ያለዋጋ የሚገኝ ጠቃሚና ዋጋ ያለው ነገር የለም። መሃበራዊ ግንኙነትህ ያድግ ተዘንድ ተግባቢነት ላይ፣ ሰዎችን መረዳት ላይ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት ላይ መስራት ይኖርብሃል። የፍቅር ህይወትህ እንዲያድግ፣ ትርጉም እንዲሰጥህ፣ እንዲረጋጋና ሰላማዊ የደስታ ምንጭ እንዲሆንህ እለት እለት በመታደስ፣ በአዳዲስ ማራኪ ክስተቶችና ትርጉም ሰጪ ክንውኖች መሞላት ይኖርበታል። ሙያዊ አቅምህ እንዲዳብር፣ በብቃትህ የመተማመን ደረጃ ላይ እንድትደርስ፣ ተፈላጊነትህ እንዲጨምር፣ ያንተም ዋጋ ጎልቶ እንዲወጣ የበዛ ጥረት ከማያቋርጥ መስተጋብር ጋር ይጠበቅብሃል። የዛፉ ፍሬ ላይ ሳይሆን መወጣጫው ላይ አተኩር፣ በእርሱ ተማረክ። በስተመጨረሻ ከምትጎናፀፈው ድል በበለጠ ከትግሉ ጋር በፍቅር ውደቅ፣ በስሜት ተገናኘው፤ ከሂደቱ ጋር ተሳሰር፣ ከልብህ ውደደው። እንደ መዓድን አውጪው መዓድኑን ለማግኘት የመጨረሻው አንድ ቁፋሮ ሲቀርህ ጥረትህን እንዳታቆም።


ጥበቃ ይብቃህ!

ወደፊት ለመራማድ፣ አዲስ ነገር ለመሞከር፣ አዲስ ሰው ለመተዋወቅ፣ ወደ ግብህ ለመቅረብ ጥበቃ፤ ጥበቃ፤ ጥበቃ። ማንን ይሆን የምትጠብቀው? ጓደኛህን፣ ወንድምህን፣ መንግስትን ወይስ እራስህን? የእስከዛሬው ጥበቃህ ምን እንዳሳጣህ ተመልክት። ከዚህ ቦሃላም ምን ሊያሳጣህ እንደሚችልም አስብ። ኑሮ ውድነቱ እንደቀጠለ ነው፤ የህይወት ክብደት እየባሰበት ነው፤ ችግሮችህ እየጨመሩ ነው፤ ሃላፊነት በየጊዜው እየተጨመረልህ ነው። የሚያደክሙህ ሸክሞች እየተደራረቡብህ እርምጃ ሳትወስድ ቆመህ የምትጠብቃቸው እስከመቼ ነው? ተዘጋጅተህ ለቁጪት እራስህን አሳልፈህ የምትሰጠው ለምንድነው? በምኞት አለም የምትንሳፈፈውስ እስከመቼ ነው?

አዎ! ጀግናዬ..! ጥበቃ ይብቃህ! ምክንያት መደርደር ይብቃህ፤ ሰበብ ማብዛት ይብቃህ፤ ሃላፊነት አለመውሰድ ይብቃህ፤ ተጠያቂነትን መሸሽ ይብቃህ፤ ማለቃቀስ ይብቃህ። ያንተ ጉዳይ ያንተና ያንተ ብቻ ነው። የሚያለፋህና የሚፈትንህ እንጂ እየተንከባከበ ወደ ከፍታው የሚመራህ መንገድ የለም። ጥበቃህ ነገሮች እስኪመቻቹ? እስክታድግ? ገንዘብ እስኪመጣ? የሚረዳህን ሰው እስክታገኝ ነውን? እውነታውን ተቀበል! ነገሮችን ለእራስህ የምታመቻቸው ማንም ሳይሆን እራስህ ነህ፤ የምታድገው ስትንቀሳቀስ ብቻ ነው፤ ገንዘብ የሚኖርህ ያመንክበትን እስከ ጥግ ስታደርገው ነው፤ የሚረዳህ ሰው የሚመጣው ጥረትህን ተመልክቶ ነው። ባለህበት ቆመህ በምኞት ያሰረህ ጥበቃ ምንም አያመጣልህም።

አዎ! ትርጉም ሰጪ ትርፋማ ነገር የሚገኘው በጥበቃ ሳይሆን በፍለጋ ነው። ተንቀሳቀስ፣ ዞር ዞር በል፣ ዙሪያህን ተመልከት፣ ለእራስህ መፍጠር ባትችል የመጣልህን አጋጣሚ በሚገባ ተጠቀም። ብለሃትህ ከጥበቃ ካላወጣህ፣ ብልጠትህ እንቅስቃሴ ውስጥ ካልከተትህ፣ ከባቢህን ካልቀየረ ትርጉሙ ምንድነው? እንዴትስ ብለሃት ሊባል ይችላል? በእራስህ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያለህ እውቀት በጣም በቂ ነው፤ በመረጥከው መንገድ ህይወትን ለመጀር ያለህ አቅም በቂ ነው። ጥበቃህ እንቅፋትህ እንጂ አሻጋሪ መሰላል እንዳልሆነ አስታውስ። ወደኋላ የምትቀረው ተግባርን ረስተህ በሃሳብ ብቻ መኖርን ስለምትመኝ ነው። ያልተኖረ እውቀት፣ ያልተሰራ ሃሳብ፣ ያልተጀመረ እቅድ ጥበቃውን ያራዝም እንደሆነ እንጂ የተሻለ ነገር ሊያመጣ አይችልም። ጥበቃ ይብቃህ፣ ቀጠሮ ማብዛት ይቅርብህ፣ ሃሳብህን መኖር ጀምር፣ ወደ እንቅስቃሴ ግባ።


ጊዜ ይጠራችሁ!

ራሳችሁ ላይ በመስራታችሁ ሰዎችን ለመጥላት ጊዜ ይጠራችሁ፣ ራሳችሁን በመውደዳችሁ ሰዎችን ለመናቅ ጊዜ ይጠራችሁ፣ ራሳችሁን በማክበራችሁ ሰዎችን ለመግፋት ጊዜ ይጠራችሁ። ትኩረታችሁ ሁሉ ራሳችሁ ስትሆኑ ለአሉታዊነት ጊዜና ቦታ ታጣላችሁ፣ በራሳችሁ ችግር ላይ ስታተኩሩ፣ በዋናነት ለራሳችሁ ቅድሚያ ስትሰጡ፣ ሁሌም በራሳችሁ የግል ጉዳይ ስትወጠሩ ከአላስፈላጊ ድራማና ጫወት ነፃ ትሆናላችሁ። አይናችሁን ጨፍኑ፣ በልባችሁ ፊትለፊታችሁን ተመልከቱ፣ ጥልቅ ፍላጎታችሁ ላይ አነጣጥሩ፣ ስሜታችሁን፣ ትኩረታችሁን፣ ሀሳባችሁን ሁሉ እርሱ ላይ ጣሉ። ማንንም በክፉ አይን ለመመልከት፣ ከማንም ጋር በቅራኔ ለመቆም፣ ማንንም ለማስቀየምና ለማሳዘን ጊዜ ይጠራችሁ። ሰዎችን መክሰስ ያቆማችሁ እለት ራሳችሁን መቀየር ትጀምራላችሁ፣ በሰው መመቅኘትን ከውስጣችሁ ያወጣችሁ እለት በረከታችሁ መብዛት ይጀምራል። ከምንም በላይ ውስጣችሁ ባለው ጥሩ ስሜትና ፍላጎት እመኑ፣ ከየትኛውም ውጫዊ ሃይል በተሻል ከውስጥ ባለው ብርቱ ሃይል ተመሩ።

አዎ! ጊዜ ይጠራችሁ! ለክፋት፣ ለምቀኝነት፣ ለተንኮል፣ ለሴረኝነትና ለዘረኝነት ጊዜ አይኑራችሁ። ብዙዎች ጊዜ ለማሳለፍ ብለው መጥፎ ስራ ላይ ይሰማራሉ፣ ብዙዎች በትርፉም በዋናውም ጊዜያቸው አጀንዳቸው ሰዎች ይሆናሉ። ከራሳቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ የማይፈልጉ፣ የውስጥ ጩሀታቸውን ማዳመጥ የሚፈሩ፣ በአንድም በሌላም አጀንዳዎች የታጠሩ ሰዎች ከራስ በላይ ለሰውና ለማይመለከታቸው አጀንዳዎች የሚሰጡት ብዙ ጊዜ አላቸው። "ራሴን እወደዋለሁ፣ ለራሴ ቦታ አለኝ፣ ራሴን አከብረዋለሁ፣ ራሴን የተሻለ ቦታ ማድረስ እፈልጋለው" ካላችሁ ለየትኛውም ዋጋቢስ ከንቱ ነገር ጊዜያችሁን አትስጡ፣ ከማንኛውም የማይረባ ጎጂ የውድቀት አስተሳሰብ ካለው ሰው ጋር ህብረት አይኑራችሁ። ከእናንተ ውዴታና ፍላጎት ውጪ ማንም ሰው ወደ ህይወታችሁ መጥቶ ጊዜያችሁን ሊወስድባችሁ አይችልም። ከራስ ተርፎ ለማይጠቅም ነገር የሚውል ትርፍ ጊዜ እንደሌላችሁ አስታውሱ፣ ራስን ከማዳን የሚቀድም ምንም ብርቱ ጉዳይ እንደሌላችሁ እወቁ።

አዎ! ጀግናዬ..! ውጭ ውጩን መሮጥህን ቀንስ፣ የማይመለከትህ ጉዳይ ውስጥ መግባት አቁም፣ ዙሪያህን ፋታ በማይሰጥ ነገር ማጠር ይቅርብህ። ስለሰዎች ክፉ ማሰብህን እስክትረሳ፣ ከዓለም ፍቅር መላቀቅህን እስክታስተውል፣ በአምላክህና በፈጣሪህ ሀይል መተማመንህ እስኪገባህ ከራስህ ጋር የጠበቀ ትስስር ይኑርህ፣ ከገዛ ማንነትህ ጋር በፍቅር ውደቅ። የለውጥ ሁሉ መጀመሪያ ራስን መውደድ ነው፤ የእድገት ሁሉ መሰረት ደግሞ ራስን ከልብ ማፍቀር ነው። ብልጭልጯ ዓለም ጊዜያዊ ነገር እየሰጠችህ እንድታዘናጋህ አትፍቀድ፤ በዙሪያህ ያሉ ሰዎች ብዙ ጉዳይ እያቀበሉህ የራስህን እንድትረሳ እንዲያደርጉህ አትፍቀድ። ምርጫህ ከባድም ይሁን ቀላል ታመንለት፣ ፍላጎትህ ብዙ ጥረት የሚፈልግ ቢሆንም ባይሆንም ራስህን ስጠው። ራስን መውደድ ምንም ይሉኝታ የለውም፣ ለራስ መልካም ፍላጎት መገዛት ነውር አይደለም። ትርፉን ሳይሆን ዋናውን ጊዜ ለራስህ ስጥ፣ ትኩረትህን የሚስብ ነገር ስላጣህ ሳይሆን መጀመሪያውኑ ራስህ ላይ አተኩር፣ ራስህን በማብቃት ቢዚ (Busy) ሁን።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን!
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


ሰበብ ባይኖርስ?

አዎ! በሔድንበት ሁሉ ድክመታችን እንዳይታወቅ፣ ስንፍናችንን ላለማመን፣ መጥፎ ስሜታችንን አለባብሶ ለማለፍ የማናቀርበው ምክንያት፣ የማንደረድረው ሰበብ የለም። ሃላፊነት መውሰድ፣ ለእራስ ጥፋት ተጠያቂ መሆን የሚባለውን ነገር አብዝተን እንሸሸዋለን። ተጠያቂነትን ፍራቻ ሁሌም ምክንያት የምትደረድር ከሆነ የትም እንደማትደርስ እወቅ፤ ሰበብ እያበዛህ አንድ እርምጃ እደማትጓዝ ተገንዘብ። የስሜቱ ባሪያና በሰበብ አስባቡ የተገዛ ሰው አንድም የእራሴ የሚለው ታማኝ ማንነት የለውም፣ ሌላም በሰው ፊት ድፍረትና በእራስ መተማመን አይኖረውም። በሚያሳዝን ሁኔታ የሚያቀርበው ምክንያት እንኳን ሌሎችን ይቅርና እራሱንም የሚያሳምን አይደለም። ለገዛ እራሱ የሰጠው ግምትና የበታችነት ወደ ውድቀትና ተስፋ ቢስነት ያንደረድረዋል። እላይ ታች ብለህ እራስህን ማዳን በሚገባህ ጊዜ ምክንያት በመደርደር የተጠመድክ እንደሆነ ከእራስህ በላይ ለእራስህ ጠላት አይኖርህም።

አዎ! ጀግናዬ..! ሰበብ ባይኖርስ? ምክንያት መደርደር ባይቻልስ? ለጥፋቱም ሆነ ለልማቱ ሃላፊነት አለመውሰድ ባይቻልስ? የት በደረስክ ነበር? የህይወትህ መልክ፣ ገፅታው፣ ማንነቱ ምን ይመስል ነበር? አንተስ ምን አይነት ሰው ትሆን ነበር? ሰበብ በእርግጥም አለ ነገር ግን በመኖሩ የሚጨምርልን ነገር ከሌለ፣ ወደፊት ለመጓዝ ካላገዘን፣ እንድንጠነክር ካላደረገን፣ ካላበረታን ምንድነው ነጥቡ? ቆዳን ማልፋት ቢያደክምም በመጨረሻ ውጤት ያመጣል፤ ሰበብ ማብዛቱ፣ ምክንያት መደርደሩ፣ ሁኔታዎችን ማገለባበጡ ግን እራስን ከማታለል፣ የእራስን ዋጋ ከማሳነስ፣ ክብርን ዝቅ ከማድረግ ውጪ የሚያመጣልን ነገር የለም።

አዎ! ያሰብከውን ላለማድረግህ ቆጥረህ የማትጨርሳቸው በቂ ምክንያቶች ይኖሩሃል፤ ብታደርገውም ለማድረግህ እጅግ ብዙ በቂና ከዛ በላይ ምክንያቶች ይኖሩሃል። ለሁለቱም ሚዛን የሚደፉ ምክንያት ቢኖርህም ሚዛኑ ግን አንተ ነህ፤ እራስህ ላይ የምትወስነው፣ አዋጩን የምትመርጠው፣ ጠቃሚውን የምታደርገው አንተ ነህ። የምክንያት ለውጥ አድርግ፤ ላለማድረግ የምትደረድረውን ምክንያት ማድረግ በሚያስችሉህ ጠንካራ ምክንያቶች ተካቸው፤ በእነርሱ ለውጣቸው። ላለህበት ሁኔታ ያደረሱህ ነገሮች በተናጥል ሳይሆን በጋራ ለዚህ አብቅተውሃል። አዎንታዊ ምክንያቶችህም ብቻቸውን ሳይሆን ከቆራጥነትህ ጋር፣ ውሳኔህን በማካተት፣ በህይወት አላማህ በመደገፍ ተዓምራዊውን ህይወት ወዳንተ ያመጣሉ። ሰበቦችህን አሸጋሽግ፤ ምክንያቶችህን አቀያይር። አሉታዊዎቹን አስቀር፣ በአዎንታዊዎቹ ተመራ፤ ብርታቶችህን ምረጥ ጥንካሬህን አስቀድም፤ ያሰብከውን ትልቅ ነገር አድርገህ ተገኝ።


የታየህን አሳይ!
፨፨፨//////፨፨፨
አዲስ ንጋት፣ አዲስ ጀምበር፣ አዲስ ብረሃን፣ ልዩ በረከት፣ ልዩ ስጦታ ከአምላክ ውጪ ከሌላ የማይታደል፣ ከማንም የማይሰጥ እጅግ የተዋበ ስጦታ ዛሬ። በግሩም ቀን ግሩም ተግባር ያስፈልገናል። የአምላክን ድንቅ ስራ ማስታውስ፣ በፈጣሪ መልካም ተግባር መደነቅ፣ የእጆቹን ስራዎች ማስታወስ፣ በየመንገዱ የወደቁ ነፍሳትን መርዳት፣ ለወገን መድረስ፣ ወገንን ማሳረፍ፣ ከጎኑ መቆም፣ ከመጣበት መከራ በተቻለን አቅም ለመታደግ መጣር ይጠበቅብናል። አንዳንዴ ተፈጥሮ ትዛባለችና የእኛን የማስተካከል ድርሻ ትፈልጋለች። ሚዛኑን የሳተ ኑሮ መጨረሻው ጥፋት ነውና ሙሉ በሙሉ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ማድረግ ባትችል እንኳን ደጋፊውን መደገፍና፣ ከጎን መቆም ትችላለህ። የንጋትህ እዳ አለብህ፣ በሰላም ያየሃት፣ በጤና የደረስክባት ብሩህዋ ዛሬ አደራ ጥላብሃለች። ያለምክንያት ለዛሬ አልደረስክም፣ የዛሬን ብረሃን በሙላት አልተመለከትክም።

አዎ! ጀግናዬ..! የታየህን አሳይ፣ ያለህን አካፍል፤ ብረሃኑን ለሌላውም አብራ፣ የአምላክህ ማመስገኛ ሁን፣ በመፅዋች እጆችህ መፅውት፣ የተራቡ ወገኖችህን፣ የተጠሙ ነፍሳትን ከልብህ አስባቸው፣ በቻልከው ድረስላቸው። ሰው መሆን ፈተና ነው፤ በተለይ የተቸገሩ ነፍሳትን እያዩ ዝም ማለት ሰውነትም አይደለም። ምንም ማድረግ ባትችል ከሁሉ የሚበልጥ ፀሎትና ተማፅኖን በጉያህ ይዘሃል። የፀሎት መፅሐፍህን አንሳ፣ ስለተቸገሩ ነፍሳት ፀልይ፣ ስለደከሙ እናት አባቶች ተማፅኖህን አቅርብ፣ ለሚሰቃዩት እንስሳት ቃልህን አውጣ። አዛኝ ልብ በመከራው ጊዜ እረፍት የለውም፤ በሰቆቃው ሰዓት ሰላም አይሰማውም፤ በእርዛቱ ሰዓት ሳቅ ጫወታ አያምረውም። አስተዋይ ነውና የወገኑ ህመም ያመዋል፤ ስቃዩ ይደርሰዋል፤ ችግሩን ይጋራዋል።

አዎ! ምናልባትም ካለህ መቁረስ ላይጠበቅብህ ይችላል፣ ህመማቸው ከተሰማህ፣ ችግራቸውን ከተጋራህ ግን ትልቁ አበርክቶትህ ይሆናል። ለወገን በማሰብ ውስጥ የሰውነት ደስታ አለ፤ ሰውን በመርዳት ውስጥ ጥልቁ ሰው የመሆን ባህሪ ይታያል። ማንም ለእራሱ እንደፈለገው በልቶ ጠጥቶ ማደር ላይከብደው ይችላል፣ ነገር ግን ሰው የመሆናችን አላማ ለእራስ ጉርሳችን ብቻ እንድንኖር አይደለም። ከእራስህ በላይ እጅህን ለሚጠብቁ፣ ምፁዋትህን ለሚናፍቁ ነፍሳት መድረስ እንዳለብህ አስብ። ተመችቶህም እያማረርክ፣ ሳይመችህም እያማረርክ ህይወትን መግፋት አትችልም። የፈጠሪህን መቅድም፣ የአምላክን መልካም ፍቃድ ጠይቅ። ጠንክረህ አጠንክራቸው፤ ጎብዘህ አጎብዛቸው፣ ሰርተህ አሰራቸው። የመጣህበትን የህይወት አላማ አሳካ። እንዲሁ ከንፈር መጠህ፣ አዝነህ፣ አንገትህን ደፍተህ ዝም የምትል እንዳልሆንክ አስተውል። አቅሙ አለህ፣ ብርታቱ አለህ፣ በበረከቱ ተሞልተሃልና ወገንህን ለመርዳት፣ ለመታደግ እንዲሁ የአምላክህን ፍፁም በረከት ለመቀበል ወደኋላ አትበል።


ከብዶህ አይደለም!
፨፨፨፨///////፨፨፨፨
ብዙ የአዲስ ነገር ፈጣሪነት ጠላት፣ የአዲስ ግኘት ባላንጣዎች ቢኖሩም የምቾት ቀጠና ግን ዋናውና ቀንደኛው ነው። ተመችቶህ የምትፈጥረው አንዳች ነገር አይኖርም፤ ተደላድለህ የተሻለ ነገር ልታስብ አትችልም። በምቾት ውስጥ ምንም አለመኖሩን የምታውቀው በእራስህ ላይ የጨመርከውን ነገር እንደሌለ ስታስተውል ነው። ማደግ እየቻልክ፣ የመቀየር አቅሙ እያለህ በቃኝ ብለህ ባለህበት መርጋትህ የእድሎች ፈጣሪ ሳትሆን እድሎችን ጠባቂ ያደርግሃል። ለመለወጥህ ቢያንስ አንድ ግልፅ ክፍተት ያስፈልግሃል፤ አንድ የማያስተኛ፣ የማያረጋጋ ብርቱ ፍላጎትና ጥማት ያስፈልግሃል። በምቾት ውስጥ ለውጥን የሚያስብ ቢኖርም በጣም ጥቂት ነው። መቾት ተነሳሽነትን ይገድላል፤ ንቃትን ያደበዝዛል።

አዎ! ብዙ ነገር የተሟላበት፣ ወሳኝ የተባሉ አስፈላጊ ግበዓቶች ባሉበት ሁኔታ በእርግጥም ምቾት ሊባል ይችላል። እርሱ ከብዙ ጥረት ሊያግድ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ድህነትን ተላምዶ መመቻቸት፣ አላወቂነትን ተዛምዶ መመፃደቅ ከምቾትነቱ በላይ ስቃይነቱ ያይላል። ህይወትህ መሻሻል ያለበት ሆኖ፣ ማሻሻልና ማስተካከልም እየቻልክ እንደተመቸውና ምንም ለውጥ እንደማይፈልግ መቀመጥ በእርግጥም እራስን አለማወቅ፣ አቅምን አለመረዳትና በበታችነት ስሜት መዋጥ ነው።
ዛሬ ባለህበት ከባድ ሁኔታ ለመቀየር ካልሰራህ፣ ለማደግ እንቅልፍህን ካላጣህ፣ ምቾት የመሰለህን ሁነት መሱዓት ካላደረክ በእርግጥም ማጣትን ለምደሃል፣ ችግርም መገለጫህ ሆኗል ማለት ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ከብዶህ አይደለም፤ አቅቶህ አይደለም፤ ስላልቻልክም አይደለም። ድህነት ያለስራ፣ ያለልፋት፣ ያለትጋት አይናድም፤ አላዋቂነትም ያለትምህርት፣ ያለንባብ፣ ያለእውቀት አይጠፋም። ውስጥህ በሚያውቀው አለለመመችት እንደተመቸህ አድርገህ አትደልለው። ፍላጎትህን ታውቃለህ፣ የሚገባህን፣ የሚመጥንህን አውቀሃል። እንደተመቸህ እያሰብክ አርፈህ ቁጭ በማለትም እንደማይመጣ በሚገባ ትረድተሃል። ይብዛም ይነስም በእውቀትህ ልክ ለመንቀሳቀስ ሞክር፤ እውነተኛውን ምቾት በጥረትህ ውስጥ አግኘው፤ መደላደሉን ህልም ውስጥ ተመቻቸው። ባልተመቸህ ሁነት እንደተመቸህ ማስመሰሉን አቁም፤ መቀየር የምትችለው ብዙ ነገር እያለ ያረጀና ያፈጀ ሃሳብ ይዘህ በስንፍና አትቀመጥ። የቻልከውን ሞክር፣ ጣር፤ በሂደት ህይወትህን እያሻሻልክ በሙላት ነር።


ዘግተህ ስራ!

በዝምታ ውስጥ፣ ያለምንም ኮሽታ፣ ምንም ሳታሳዩ እንዲሁ በድብቅ ስትቀየሩና ስታድጉ ሰዎች መቼና የቱጋ ሊያጠቋችሁ እንደሚችሁ አያውቁም። የዓለም ጥበበኞች፣ የምድር ታላላቅ መሪዎች፣ ህይወትን በአግቡ የተረዱ፣ አቅማቸውን በሚገባ ያወቁ፣ ተደብቆ የማደግ ሃይል የገባቸው ሰዎች ትናንትም ተደብቀው ይሰራሉ፣ ዛሬም ዝም ብለው ይሰራሉ፣ ነገም እንዲሁ ከብዙዎች ተሸሽገውና አቀርቅረው ራሳቸውንና ግዛታቸውን ይገነባሉ። ሰው አውቋችሁ እናንተ ግን ራሳችሁን ባታውቁት፣ ሰው አጨብጭቦላችሁ እናንተ ግን ውስጣችሁ ባዶነት ቢሰማችሁ፣ ዓለም ስማችሁን እየጠራ አመስግኗችሁ እናንተ ግን ራሳችሁን መውደድና ማክበር ቢሳናችሁ ትርፋችሁ ምንድነው? የምርም ምንም ትርፍ የላችሁም፣ እንዴትም ሰላማችሁን ልታገኙ አትችሉም። መስሎን እንጂ ከውጭ የሚመጣ ነገር ሊያሳርፈን አይችልም፣ መስሎን እንጂ ከዓለም የምናገኘው ነገር ሙሉ ሊያደርገን አይችልም። በጥቅሉ የህይወት ትርጉም ያለው ግልፅ በወጣውና ሰው በሚያውቀው ማንነታችን ውስጥ ሳይሆን በተደበቀውና ማንም ሰው በማያውቀው የብቸኝነት ህይወት ውስጥ ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ተደብቆ የሚሰራን ሰው ሰዎች አያውቁትም፣ ሰዎች ሊረዱት አይችሉም፣ ሰዎች በፍፁም ሊገባቸው አይችልም። ብቻህን ስትሆን ምን ታደርጋለህ? ማንም በሌለበት፣ ከፈጣሪ በቀር ማንም በማያይህ ሰዓት ምን ትሰራለህ? ማንም ሰው ሰፊ ማህበራዊ ህይወት ቢኖረው እንኳን ብቻውን ሲሆን የሚያደርገውን ነገር መርጦ የሚያደርግ ከሆነ ያለምንም ጥርጥር ህይወቱ ከብዙዎች የተሻለ መሆኑ አይቀርም። ብዙዎች ብቸኝነትን አጥብቀው ይፈራሉ፣ ብዙዎች ተደብቆ ማደግ ያስጨንቃቸዋል፣ ብዙዎች ሰው ካላያቸው የሰሩም አይመስላቸውም። ነገር ግን በቀዳሚነት የሚኖረው ለሰው ወይም ለዓለም ሳይሆን ለራስ ነው። ራስህን ካላዳንክ የዘመናት ልፋትና ጭንቀትህ ሁሉ ከንቱ ነው። ጥረትህ ሁሉ አደባባይ በወጣ ቁጥር፣ ለውጥና እድገትህ ሁሉ ግልፅ በሆነና ሰዎች ባወቁት ቁጥር እንቅፋቶችህ እየበዙ፣ በላይ በላይ መሰናክሎች እየተደራረቡብህ፣ አቅምና ተነሳሽነቱ እያጣህ ትመጣለህ። ሀይልና ብርታትህ፣ ንቃትና አሸናፊነትህ ከማንም እንዴትም ልታገኘው የማትችለው ስጦታህ እንደሆነ አስተውል።

አዎ! ብዙ የለውጥና የእድገት መንገዶች ይኖራሉ፣ ብዙ የስኬትና የከፍታ መንገዶች አሉ ነገር ግን የትኞቹም ተደብቆ የማደግን ያህል በቀላሉ ለትልቅ ውጤት ሊያበቁ አይችሉም። ብዙ ጠላት ካልፈለክ በርህን ዘግተህ ስራህን ስራ፣ ብዙ እንቅፋት ካልፈለክ ለሰው ሁሉ ሚስጥር ሁን፣ ረጅም ርቀት መጓዝ ከፈለክ ለማንም የግል ጉዳይህን አታሳውቅ። ብዙዎች ግልፅ አለመሆን ንቀት ይመስላቸዋል፣ ብዙዎች ራስን ከድራማ አርቆ በራስ የግል መንገድ መጓዝ ጥላቻ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሰው መሰለው ማለት እውነት ነው ማለት አይደለም። ትልቁ ድል ራስን ንቆ በሰው መከበር ሳይሆን ከሆነ ራስን አክብሮ በሰው መከበር ካልሆነም ራስን አክብሮ፣ ራስን ከልብ ወዶ በሰው በመገፋት ብዙ አለመረበሽ ነው። የየትኛውም ታላቅ ስኬት ሚስጥርህ አንተ ጋር ነው፣ የማንኛውም መሰረታዊ ለውጥህ መነሻ አንተጋር ነው። ህይወት ትርጉም የሚኖራት ዘመኑን በሙሉ ለሰው በመኖር ሳይሆን ለራስ ኖሮ ለሰው በመትረፍ ውስጥ ነው። ጊዜ ወስደህ ከሰው ሁሉ ተሸሽገህ በመኖርህ እትሸማቀቅ፣ ከምንም በፊት ለራስህ ለመድረስ በመሞከርህ አትፈር። ዘግቶ መስራትህን መገለጫህ፣ ተሰውሮ ማደግንም ማንነትህ አድርጋቸው።


የልባችሁን ምረጡ!

እውነት እውነቱን አውሩ፣ ግልፅ ግልፁን አስቀምጡ። አሁን ላይ ተስፋችሁ ማነው? ያኖረኛል ብላችሁ የምታስቡት አካል ማነው? ሁሉነገራችሁን ብታጡ እንኳን ያ አካል አብሯችሁ ስለሆነ ብቻ ሙላትና እረፍት የሚሰማችሁ ማነው? ሰውን ተስፋ የሚያደርግ በርሱም ላይ የሚተማመን እርሱ የተረገመ ይሁን እንዲል መፅሐፍ። ይሔን እንኳን እያወቃችሁ በሰው ተደግፋችኋልን? ይሔን እየሰማችሁም ሰውን ተስፋ አድርጋችኋልን? ለማን ምንያህል ቦታ መስጠት እንዳለባችሁ ካላወቃችሁ መቼም ቢሆን ልባችሁ ሊያርፍ አይችልም። የሚያኖራችሁ ፈጣሪ ሆኖ ሳለ የማያኖራችሁ የሰው ልጅ ላይ አትጣበቁ፤ ብትወድቁ የሚያነሳችሁ፣ ብትሳሳቱ የሚያርማችሁ፣ ብትጠፉም የሚመልሳችሁ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ ሰውን ከልክ በላይ በሰው ወይም ባላችሁ ነገር ላይ አትደገፉ። አፈጣሪ ውጪ ሌላው ምድራዊ ነገር ጠፊና አጥፊ ነው። ሲታይ ራሱ የማይጠፋ ይመስላል ነገር ግን ይጠፋል፣ ሲታሰብ ብዙና ሀይለኛ ይመስላል ሲጨበጥ ግን ምንም ነው። ሳይጨልም ንቁ፣ ጊዜው ሳያልፍ ተማሩ።

አዎ! ጨለማ በብረሃለን ይጠፋል፣ ብረሃን ለጨለማ እጁን ይሰጣል። ተፈጥሮ ፈረቃ አላት። ያለምንም ፈረቃ፣ ያለምንም የጊዜ ገደብ፣ ያለምንም እርከን የሚሰራ ግን ፈጣሪ ብቻ ነው። ዓለምን ከጥግ እስከ ጥግ አይታችኋታል፣ ባታዩአትም ስለርሷ ብዙ ሰምታችኋል፣ የምድር ምርጫ ምን አንደሆነ፣ ከእናንተ ምን እንደምትፈልግ፣ ማንስ ደግሞ እንደሚያዋጣችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ። የልባችሁን ምረጡ፣ ለሚያሳርፋችሁ ቦታ ስጡ፣ የሚያኖራችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። በራሳችሁ ብርታት ብቻ ዛሬ ያላችሁበት ስፍራ አልደረሳችሁም፤ በዙሪያችሁ ባሉ ሰዎች እርዳታ ብቻ አሁን ያገኛችሁትን ነገር አላገኛችሁም። ባፈራችሁት ንብረት ወይም በገነባችሁት ዝና ብቻ ነፃ አልወጣችሁም። አወቃችሁትም አላወቃችሁትም፣ አስተዋላችሁትም አላስተዋላችሁትም፣ የሚገባውን ቦታና ክብር ሰጣችሁት አልሰጣችሁትም በእያንዳንዱ ጥቃቅን እርምጃዎቻችሁ ውስጥ ፈጣሪ ነበረ፣ ዋናው የእርሱ ስራ ነበረ።

አዎ! ጀግናዬ..! ብትረሳ ብትረሳ እስከዛሬ ያኖረህን፣ እዚህ ያደረሰህን፣ ብዙ ብዙ ነገር ያሳለፈህን የእርሱን የፈጣሪህን ውለታ እንዳትረሳ። በሁለት እግር ቆሞ መሔድ ትልቅ ፀጋ ነው፣ በራስ ፍላጎት ወደ ብዙ አቅጣጫ መንቀሳቀስ ስጦታ ነው፣ ሌላው ቢቀር ለማማረርና የጎደለውን ነገር ለመጠየቅ እንኳን መመረጥ ያስፈልጋል። የትናንት ከባድ አስጨናቂ ጊዜ እስኪያልፍ ረጅም ነበር ሲያልፍ ግን ምንም ነው። ለሰውም ይሁን ለሰዎች ውለታቢስ አትሁን፣ አምላክህንም የምትፈልገውን ለመጠየቅ አትፈር። ከላይ ከላይ ሳይሆን  የውስጥህን አውጥተህ ፈጣሪህን ጠይቅ። ሀሳብ ይዘህ አትተኛ፣ ራስህን እያስጨነክም ህይወትህን ለመግፋት አትሞክር። ልብህ አይደንግጥ፣ ውስጥህም አይረበሽ። ህይወት ብለህ የምትኖረውን ኑሮ በአምላክህ ፍቃድና በራስህ መንገድ ለመኖር ራስህን አሳምን።
ውብ ምሽት ይሁንልን!
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


ፍረሃትህን ልቀቀው!

አዎ! ፍረሃትን ታውቀዋለህ፣ ያሳጣህን በግልፅ አይተሃል፤ ያስመለጠህን፣ የሰወረብህን ግሩም እድል ታስታውሳለህ። ድፍረት በማጣትህ በሰዎች ፊት ለመሸማቀቅ ተገደሃል፤ ሃሳብህን መግለፅ እስኪያቅትህ ሃፍረት ይዞሃል። በፍረሃትህ ምክንያት የደረሰብህ በደል፣ ያጣሀው እድል፣ የቀረብህ አጋጣሚ እጅግ ብዙ ነው። ፍረሃትህን የምትጋፈጥበትን እድሎች እያሳለፍክ መቼም ከፍረሃትህ ልትላቀቅ አትችልም፤ ፍረሃትህን አንግበህ፣ ፊትለፊትህ አስቀምጠህ፣ ዘወትር ስለእርሱ እያሰብክ፣ እየተጨነክ ያሰብክበት ቦታ መድረስ፣ የተመኘሀውንም ማሳካት አይሆንልህም።

አዎ! ጀግናዬ..! ፍረሃትህን ልቀቀው፤ ከማንነትህ ነጥለው፤ እራስህን ነፃ አውጣ። ፈሪ እንደሆንክ ከተሰማህ፣ አይናፋርነተህ ዋጋ እንደሚያስከፍልህ ካወክ፣ የሰዎች ሃሳብ አስተያየት ስጋት ላይ እንደሚጥልህ ካሰብክ ትልቁ ምክንያትህ እውነት ያልሆነው የፍረሃት ስሜት እንደሆነ ተገንዘብ። ከፈቀድክለት አሳስሮ ያስቀምጥሃል፤ ቀና ማለት ብትፈልግም እዛው ያስቀርሃል፤ ተለይተህ መታየትህ ብቻህን ባህር ውስጥ እንደተጣልክ እንዲሰማህ ያደርግሃል፤ አቅም እንዳጣህ፣ ጉልበት እንዳነሰህ ያበረከርክሃል፤ ካሰብከው ድንቅ ህይወት በብዙ ርቀት ወደኋላ ያስቀርሃል፤ ለእራስህ ያለህን ግምት እያወረደ የበራስ መተማመን ባዳ ያደርግሃል።

አዎ! የምትለቀው እንዲይዝህ፣ እንዲቆጣጠርህ የፈቀድከው አንተ ስለሆንክ። መርጠሀውም ሆነ ተገደህ ባንተ ላይ ለሚሆነው እያንዳንዱ ስሜትና ተግባር ሃላፊት የምትወስደው አንተ ነህ። መጋፈጥ የምትፈልጋቸውን አሉታዊ ስሜቶች መጋፈጥ ይኖርብሃል። ፍረሃትን ሙሉ በሙሉ በአንዴ ማጥፋት ባትችልም በፍላጎትህና በተነሳሽነትህ ልክ ግን በሂደት ቦታውን ለድፍረት ማስለቀቅ ትችላለህ። ፍረሃትህን ለመሻር፣ እራስህን ለማሳየት፣ በእራስህ ቀለም ለመታየት አንድ ነገር አስብ። ፍረሃትን ያንገሱብህ ሃሳቦች በሙሉ ያንተ አይደሉም፤ እውነትም አይደሉም። ፍረሃትህን በለቀከው ልክ ከውሸት ነፃ ትወጣለህ፤ እውነትን በድፍረት መኖር ትጀምራለህ። የህይወት ጠዓም እውነት ውስጥ ነው፤ እውነት ደግሞ ፍረሃትና ስጋት ውስጥ የለም። የህይወት ከፍታ ከድፍረት ጀርባ ነው፤ ከመጋፈጥ፣ ከመጀመር፣ ከመሞከር ቦሃላ የሚመጣ ነው። ህይወትህን ለማጣጣም፣ ደስታህን ለመሸመት እስራትህን ፍታ፤ ፍረሃትን ልቀቀው፤ በድፍረት ያሻህን አድርግ፤ ከሰዎች አሉታዊ መልከታ ይልቅ ለእራስህ አዎንታዊ፣ አስደሳችና አሻጋሪ ሃሳብ ቅድመያ ስጥ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን!
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


ቀዳሚውን አስቀድም!

የማይተውህ የማይፋታህ ምቾት አለ፤ በዙሪያህ ሁሉ ቀላል ነገር አይጠፋም፤ አንተ ባለህበት ሁሉ ጊዜያዊ ደስታን የሚሰጥህ ነገር አታጣም። አንዳንዴ ከስራ ዝለት በላይ የሃሳብ ዝለት ሲበዛብን እንመለከታለን። የሚያደክምህ የስራ ልፋት ብቻ አይደለም፣ ታታሪነትህ ብቻም አይደለም የማያባራ በስራ ያልተቋጨ፣ በስንፍና የተረታ ሃሳብም እንዲሁ ያደክማል። ስጋዊው ሰውነት አብዝቶ እረፍትን ይወዳል፣ ስንፍናን ይፈልጋል፤ እንዲሁ ድካምና ጥረትን ይጠላል። በዚህ ስሜት ግን ለውጥ ምኞት ብቻ ይሆናል፤ እድገትም ቅዠት ብቻ መሆኑ የማይቀር ነው።

አዎ! ጀግናዬ..! ቀዳሚውን አስቀድም፤ ዋጋ ለሚገባው ዋጋ ስጥ፤ ጠቃሚውን ምረጥ፤ መደገፍ ስትፈልግ ተደገፍ። ሰው ነህና ባለመቻልህ ሃፍረት አይሰማህ፣ ባሰብከው ቦታ ባለመገኘትህ አትሳቀቅ። ይልቅ ችለህ የምትገኝበትንና ጥረትህን የምታሻሽልበትን መንገድ አጥና። የእወቀትህን ጥቅም የምትረዳው ያልቻልከውን ችለህ ስትገኝ፣ ያልጨረስከውንም ጨርሰህ ስትገኝ እንደሆነ ተገንዘብ። የዛሬው ምቾት ቀጠናህ ነገ የስቃይ ቀጠና ሊሆንብህ እንደሚችል አስብ። የሚጨምር ፍላጎት አለህ፣ የሚያድግ አምሮት አለህ፣ የደስታህ ምክንያቶች ይቀያየራሉ፣ ስልቹነት አይጠፋህም፣ ባሉበት መቆየት የሚያማርርህ ጊዜ ይመጣል፣ አዲስ ነገር ይናፍቃል፣ ከቀድሞው የተለዩ እይታዎች ይከሰታሉ። በዚህ ሰዓት ሲመቹህ የነበሩ ነገሮች መጎርበጥ ይቸምራሉ።

አዎ! ከዛሬው ምቾትህ በላይ የነገው ሰላምህ ይበልጥብሃል፤ ከዛሬው መደላደል በላይ የነገው እረፍት ይሻልሃል። ከዛሬ በላይ የነገውን ውጤት የምታስበልጠው ነገ ከዛሬ በላይ ዋጋ ኖሮት ሳይሆን የዛሬ ምቾትህ፣ ዛሬህ የተሻለ ነገር ለመፍጠር አለመሞከርህ፣ አለመጣርህ ውጤት አልባ ባዶና በቁጪት የታጀበ ነገን እንደሚያስረክብህ በግልፅ ስለገባክ ነው። ምርጫዎች አሉህ፤ የምታስቀድመውንም ታውቃለህ። ምቾትህን አብዝተህ አትውደድ፣ አንድ ቀን እንደሚሰለችህ አስብ፣ ለውጥ እንደሚያስፈልግህ አትዘንጋ፣ ቢያንስ በተወሰኑ ጊዜያት አዳዲስ ነገሮች እንደሚያስፈልጉህም አስታውስ።
ውብ ምሽት ይሁንልን!
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


መድመቁን እወቅበት!

ሌሎች ማድረግ የማይፈልጉትን አንተ ታደርጋለህ፤ ብዙዎች ማወቅ ያልፈለጉትን አንተ ታውቃለህ፤ ሌሎች መማር የማይፈልጉትን አንተ ትማራለህ፤ ብዙዎች ለመስራት የሚያፍሩበትን አንተ ትሰራለህ፤ እነርሱ የማይመርጡትን የተለየ ምርጫ አንተ ትመርጣለህ፤ ብዙዎች የሚጠየፉትን ስራም በኩራት ትሰራለህ። የክብርህ ማነስ ከሰዎች መለየትህ ሳይሆን ሌሎች ስለቆዩ ብቻ በማትፈልገውና በማይገልፅህ ስፍራ መቆየትህ ነው። በመንጋው መዋጥህ መኖርህን እንዳያሳጣህ ተነጥለህ መታየቱን፣ አዲስ ተግባር መተግበሩን አትፍራ።

አዎ! ጀግናዬ..! እለት እለት በእራስህ ቀለም መድመቁን እወቅበት። እነርሱ ማድረግ የማይፈልጉትን ስላደረክ፣ በእርግጥም እነርሱ ያላገኙትን ነገር ታገኛለህ። አቅምህንና የሚያዋጣህን የምታውቀው አንተ እስከሆንክ ድረስ ማንም የህይወት ምርጫህን እንዲወስንልህ አትፍቀድ። ብዙዎች ባለመፈለግ ቢያፈገፍጉ አንተ ግን ከብዙዎች ተነጥለህ፣ ከጥቂጦቶች ትቀላቀላለህ፣ በእራሳቸው መንገድ ከሚጓዙት ጋር ጉዞህን ትቀጥላለህ፤ የብዙዎች ምኞት የሆነውን ህይወት አንተ ትኖረዋለህ፣ ለብዙዎች ሃሳብ የሆነውን ነገር አንተ በቀላሉ ትፈፅመዋለህ፣ ለብዙዎች ቅንጦት የሆነውንም ለእራስህ መደበኛ ታደርገዋለህ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን!
(Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪

20 last posts shown.