የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴት የእስልምና እምነት ተከታይ ተማሪዎች ጉዳይ‼️
[ይህ ዘገባ የዶቼ ቬለ ነው]
የዲላ ዩኒቨርስቲ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች በአለባበሳቸዉ ምክንያት ወደ ዩኒቨርስቲዉ ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ መከልከላቸዉን አስታወቁ።ተማሪዎቹ እንደሚሉት በኢስላማዊ አለባበሳቸዉ ምክንያት ወደ ዩኒቨርስቲዉ ግቢ መግባት ተከልክለዉ በየመሳጂዶች ለማደር ተገድደዋል።ተማሪዎቹ አክለዉ እንዳሉት ሒጃብና ኒቃብ ለብሰዉ ወደ ማደሪያ ግቢ እንዳይገቡ የዩኒቨርስቲዉ የፀጥታ ኃይላት ያገዷቸዉ ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ነዉ።ሰኞ ዕለት 44 ሴት የእስልምና እምነት ተከታይ ተማሪዎች ከስግደት መልስ ወደ ግቢው ለመግባት መሞከራቸውን ከተማሪዎቹ ሁለቱ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ ነገር ግን ሂጃብ ካላወለቁ ወደ ግቢው መግባት እንደማይችሉ በግቢው የፀጥታ አባላት እንደተነገራቸው የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ ሴት የፀጥታ አባላት ማንነታችንን ከመታወቂያ ካርዶቻችን ጋር አገናዝበው እንድንገባ ብንጠይቅም ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ በመጨረሻም ሁላችንም ወደ መስጂድ በመመለስ አሁንድረስ እዚያው ተጠልለን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማብራሪያ
ዶቼ ቬለ በተማሪዎቹ ቅሬታ ላይ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ሥራአስኪያጅ ከማል ሀሩን በተማሪዎቹ የቀረበው አቤቱታ በደቡብ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መረጋገጡን ተናግረዋል ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውጭ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ምክር ቤቱ የትምህርት ሚንስቴርን በደብዳቤ መጠየቁን የጠቀሱት የምክር ቤቱ ዋና ሥራአስኪያጅ “በጉዳዩ ላይ ከሚንስቴሩ ሃላፊዎች ጋር በመምክር ዘላቂ እልባት ለመሥጠት የሚያስችል የጋራ መድረክ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል ።“ ብለዋል ፡፡
የዲላ ዩኒቨርስቲ ባለሥልጣናት ቀጥታ መልስ መስጠት አልፈለጉም
ዶቼ ቬለ የተማሪዎቹ ቅሬታ እና የጠቅላይ ምክር ቤቱ ደብዳቤ ይመለከተዋል የተባለውን የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ሃላፊዎችን ጠይቋል ፡፡ ይሁን አንጂ ሃላፊዎቹ “ በተቋም ደረጃ በዩኒቨርሲቲው የፌስ ቡክ ገጽ ምላሽ ሰጥናል ፡፡ ከዚያ ውጭ የምንጨምረው የለም “ ብለዋል ፡፡ የሐዋሳዉ ዘጋቢያችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ እንደዘገበዉ ዛሬ አኩል ቀን ላይ በዩኒቨርሲቲው የፌስ ቡክ ገጽ የሰፈረው መግለጫ በዩኒቨርሲቲው ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ ተከልክሏል በሚል የሚናፈሰው መረጃ «መሠረተ ቢስ ነው» ይላል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ሂጃብ መልበስ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን እንዳልተከለከለ የጠቀሰው የዩኒቨርሲቲው መግለጫ “ ተቋሙ ሴኩላሪዝምና ብዝሃ ሃይማኖትን ተረድቶና አክብሮ እየሠራ ይገኛል “ ብሏል ፡፡
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news