1600 ዓመታትን ያስቆጠሩ ቅርሶች የሚገኙበት የግል ሙዚየምበሐረር ከተማ የሚገኘው የቀድሞው የተፈሪ መኮንን ታሪካዊ ጫጉላ ቤት አሁን ታሪካዊ ቅርሶች ተሰባስበው የተቀመጡበት የኢትዮጵያውያን፣ የውጭ አገር ዜጎችንና ቱሪስቶችን ቀልብም የሚስብ ልዩ ሙዚየም ሆኗል።
ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የተለያዩ እምነቶች እንዲሁም ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ በ10ሺዎች የሚገመቱ ቅርሶችን አሰባስቦ የያዘ ነው፤ በበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚው በሀረሚያ ዩኒቨርሲቲ የክቡር ዶክትሬት በተበረከተላቸው ውልደት፣ እድገት፣ ትዳር እና ኑሯቸውም በሀረር ከተማ የሆነው አብደላ አሊ ሸሪፍ የመሰረቱት “ሸሪፍ ሙዚየም”።
ከ1600 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ቅርሶች፣ ከአክሱም ዘመን ጀምሮ መገልገያ የነበሩ ሳንቲሞች፣ የትየለሌ ዓመታትን ህልው መሆን የቻሉ የሃይማኖት መጻሕፍት፣ የነገስታት ሰይፍ እና መሰል የጦር መሳሪያዎች፣ ንጉሳዊያን የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፣ የተፈረሙ ውሎች እና ሌሎችም እጅን በአፍ የሚያስጭኑ ታሪካዊ ቅርሶችና ሰነዶች በሸሪፍ ሙዚየም ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ተቀምጠዋል።
በቀደምት ሀረሬዎች የተዘጋጁ በአረብኛ ፊደል በኦሮሚኛ ቋንቋ የተጻፉ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት፣ በሀረር እናቶች በጥበብ እና በጥንቃቄ የተሳሉ የሃይማኖት መጻሕፍት ሽፋን እንዲሁም ሌሎች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ መጻሕፍት በሙዚየሙ ውስጥ እንደልብ ማግኘት ይቻላል፡፡
ሀረሬዎች ይገለገሉባቸው የነበሩ ሳንቲሞች እኛ በዚህ ዘመን ከምናውቃት አምስት ሳንቲም በመጠን 3 እጥፍ የሚያንሱ ሲሆን በአስገራሚ መልኩ በዚች እጅግ ጠባብ ዲያሜትር ባላት ሳንቲም ውስጥ “ነብዩ መሀመድ የአላህ መልዕክተኛ” የሚል ጽሑፍ ታትሞ ይታያል።
ከ1600 ዓመታት በፊት መገበያያ የነበሩትን የአክሱም ሳንቲሞችን ጨምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያሉ ገንዘቦች እና በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎችም ግብይት ይፈጸምባቸው የነበሩ ጥንታዊ ገንዘቦች በሙዚየሙ ውስጥ ከአስፈላጊው ገለጻ ጋር በክብር ተቀምጠው ትውልድ ይጎበኛቸዋል፣ ይደነቅባቸዋል፣ ታሪክ ይማርባቸዋል።
ሙሉ ታሪኩን ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇
https://shorturl.at/pqtwx