ሐሙስ ምሽት!መጋቢት 21/2015 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ ፍትህ ሚንስቴር በሕወሃት ከፍተኛ የሲቪልና የወታደራዊ መኮንኖች ላይ የመሠረተውን የወንጀል ክስ ማቋረጡን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ዙሪያ ያለው ተጠያቂነት "ዓለማቀፍ ተሞክሮን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታይ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል" ብሏል። ሚንስቴሩ፣ በሕወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔልንና የአሁኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በሲቪል የፖለቲካ አመራሮች ላይ የመሠረታቸውን ክሶች ያቋረጠው፣ ፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት ፕሪቶሪያ ላይ በደረሱበት ሰላም ስምምነት መሠረት እንደኾነ ጠቅሷል። ሚንስቴሩ ክሶቹን ያቋረጠው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሃትን ከአሸባሪነት መዝገብ በሰረዘ ማግስት ነው።
2፤ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን 250 ሺህ የሚደርሱ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ መልሶ ለማቋቋም 29 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም 555 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ ዲፕሎማቶች ባቀረበው የገንዘብ ልገሳ ጥያቄ መግለጡን ዋዜማ ሰምታለች። ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ተዋጊዎችንና ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ወደ ኅብረተሰቡ ለመቀላቀል ባዘጋጀው ዝርዝር ሰነድ ዙሪያ፣ ከዲፕሎማቶች ጋር ሰሞኑን መወያየቱን ዋዜማ ተረድታለች። መንግሥት ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ወጪ እንደሚሸፍንና፣ ላንድ የቀድሞ ተዋጊ መቋቋሚያ ከ36 ሺህ እስከ 60 ሺህ ብር እንደሚሰጥ በሰነዱ ተገልጧል። በመልሶ ማቋቋሙ፣ የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች ታጣቂዎችን ለማካተት የታቀደ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዙር ግን የትግራይ፣ አማራና አፋር ተዋጊዎች ብቻ ይካተታሉ ተብሏል።
3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን ባንድ ድምጸ ተዓቅቦ አጽድቋል። አዋጁን ለምክር ቤቱ ያቀረበው የሕግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ፣ ዲጂታል መታወቂያ ሁሉን ዓቀፍ፣ ወጥ እና አስተማማኝ በሆነ ሥርዓት የዜጎችን መረጃ ለመያዝ የሚረዳና በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልጽነትንና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል መኾኑን ገልጧል። መንግሥት በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ስር የተቋቋመው የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ለወራት የሙከራ ሥራዎችን ሲተገብር መቆየቱ ይታወቃል።
4፤ ኢዜማ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባለፈው ዓመት መጋቢት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያስሾሟቸው የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ቦርድ አባላት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ኢዜማ፣ የገዥው ፓርቲ አባላት የሆኑ የቦርድ አመራሮች የተሾሙት ከመገናኛ ብዙኀን አዋጅ በተቃራኒ ነው በማለት ተችቷል። ዐቢይ፣ መንግሥታቸው ነጻ መገናኛ ብዙኀንና ነጻ ሃሳብ እንዲኖር ጥረት እያደረገ መኾኑን ሰሞኑን ለምክር ቤቱ መናገራቸውን የጠቀሰው ኢዜማ፣ የሃሳብ የበላይነት ሊሰፍን የሚችለው ግን መንግሥት መገናኛ ብዙኀንን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ብሏል። ኢዜማ፣ ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙኀንን በተጽዕኖው ስር በማስገባቱ፣ ሃሳቦቼ የመደመጥ ዕድል ተነፍጓዋል በማለትም አማሯል።
5፤ ኢሰመኮ በፖለቲካ ፓርቲዎች "የመሰብሰብ መብት ላይ የሚጥሏቸው ገደቦች" እና በአባሎቻቸው ላይ የሚደርሱ እንግልቶች" ለዘለቄታው መቆም አለባቸው ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። ኢሰመኮ፣ በእናት ፓርቲ እና በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የመሰብሰብ መብታቸው እንደተገደበ አረጋግጫለሁ ብሏል። የጎጎት የጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ ምስረታ አስተባባሪዎችም "እንግልትና እስራት" እንደደረሰባቸው ኢሰመኮ ገልጧል። በፓርቲዎች ላይ የሚፈጸሙባቸው ክልከላዎችና እገዳዎች፣ "የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና የመሳተፍ መብቶች ጥሰቶች" እንደኾኑ ኢሰመኮ ጠቅሷል። መንግሥት በፓርቲዎች ላይ "ድንገተኛና ከታሰበላቸው ዓላማ በላይ የኾኑ ርምጃዎችን ከመውሰድ እንዲቆጠብ" እና ይልቁንም ለስብሰባ ተሳታፊዎች ጥበቃና ከለላ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ኢሰመኮ ገልጧል።
6፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደሳለኝ ቦኮንጆ ማንነታቸው ባያልታወቁ ታጣቂዎች ዛሬ መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። የከተማ አስተዳደሩ፣ የፓርቲው ሃላፊ ለሥራ ከቤታቸው ሲወጡ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደተገደሉ ገልጧል። የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም፣ ግድያውን የፈጸመው "የታጠቀ ኃይል" ነው በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በነቀምቴ ከተማ በመንግሥትና የፓርቲ ሃላፊዎች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።
7፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከኡጋንዳ የተነሱ ኡጋንዳዊያን የአንድ እምነት ተከታዮች የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው ደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ንያንጋቶም ወረዳ ውስጥ መስፈራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ዛሬ በሰጡት መግለጫ ማረጋገጣቸውን መግለጫውን የተከታተሉ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የአንድ እምነት ተከታዮች "የመጨረሻው ምጽዓት" ኡጋንዳ ውስጥ ሊጀምር ተቃርቧል በሚል እምነት ወደ ኢትዮጵያ እንደተሰደዱ ከሳምንታት በፊት የኡጋንዳ ዜና ምንጮች ዘግበው ነበር። መለስ፣ ኡጋንዳዊያኑ ስደተኞች የገቡበትን መንገድ ወይም ብዛታቸውን ይግለጡ አይግለጡ ግን ዜና ምንጮቹ አልጠቀሱም።
8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 53 ብር ከ8978 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 54 ብር ከ9758 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ5273 ሳንቲም እና መሸጫው 64 ብር ከ7978 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ብር ከ5007 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ6707 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። #ሼር በማድረግ ተባበሩኝ🙏
👉ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ👇👇👇
@emsmereja