ለሃይቅ ከተማ ወንድሞች!
~
ሰሞኑን ከደዕዋ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ግርግር እንደነበረ ስለሰማሁ ለናንተም፣ ተመሳሳይ ሁኔታ ላላቸው ሌሎች አካባቢዎችም ከጠቀመ በሚል ትንሽ ለማለት ወደድኩ።
1ኛ፦ በቅድሚያ በተቻለ መጠን መስዋእትነት ከፍላችሁም ቢሆን ደዕዋችሁን ከግጭት አርቁ። በግርግር አትታወቁ። ለሁከት ፈጣሪዎች እድል አትስጡ። እናንተ ብትሸሹ እንኳ እምቢ ብለው ብጥብጥ ለማስነሳት የሚፈልጉ ስለሚኖሩ ነገሮችን በጥንቃቄና በሹራ (በመመካከር) ያዙ።
2ኛ፦ የሚቃረኑ አካላትን ጭምር ለመመለስ አልማችሁ ስሩ። አብዛኞቹ የሌሎች መጠቀሚያ እየሆኑ እንጂ በውል ለይተው አይደለም በተቃውሞ የሚሰለፉት።
3ኛ፦ ብልጥ ሁኑ። ሃላፊነት ላይ ካሉ አካላት ጋር ላለመጋጨት ሞክሩ። በለዘበ መልኩ እነሱንም ለመያዝ ሞክሩ። እነሱስ የኛው ወገኖች አይደሉ? መያዙ ቢቀር ለማለስለስ ጣሩ። ስማችሁን ለሚያጠፋ አካል ሰበብ ላለመስጠት የምትችሉትን ሁሉ ጥንቃቄ አድርጉ።
4ኛ፦ የጎንዮሽ ፍትጊያ ካለ አስወግዱ። የከፋ ተቀናቃኝ ኃይል ባለበት ሌሎች ውዝግቦችን አስወግዱ ወይም ቀንሱ። ተከባበሩ። ተደማመጡ። ተናበቡ።
5ኛ፦ ስጋት ከሌለ እስከ ገጠር እየወጣችሁ በርትታችሁ ስሩ። የሚያዳምጥ ወይም የሚቀበል ቀለለ ብላችሁ ሞራላችሁ እንዳይቀዘቅዝ። እንቅስቃሴያችሁ ሰሞንኛ አይሁን። ወረተኛ እንዳትሆኑ። ከየትኛውም አካል በሚመጣ ጫና አትታጠፉ ፣ እጅ አትስጡ። የነብያችንን ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እና የቀደምቶችን ታሪክ አስታውሱ።
6ኛ፦ ቁርኣን ማስተማር ላይ አድምታችሁ ስሩ። ከሌሎች የተሻለ ለውጥ የሚታይ ከሆነ ለሌላውም ደዕዋ ስንቅ ይሆናችኋል።
7ኛ፦ ተማሪዎች እና ሴቶች ላይ በሚገባ ስሩ። ቋሚ ፕሮግራም ይኑር።
8ኛ፦ ደዕዋችሁ ዘርፈ ብዙ ይሁን። ሁለት ሶስት ርእስ ላይ አትገደቡ። የሰዎችን ልብ በተለያየ አቅጣጫ አንኳኩ።
9ኛ፦ የሚቻላችሁ ከሆነ ማህበራዊ ስራዎች ላይ ለምሳሌ ደካማን አስተባብሮ መርዳት፣ ማቋቋም፣ ቤታቸውን ማደስ፣ ምስኪኖችን ማሳከም፣ ዘካተል ፊጥርና መሰል ሶደቃዎችን በተቀናጀ መልኩ በመሰብሰብ መስራት ለደዕዋውም እገዛ ይኖረዋል።
በተረፈ እኔ የሃይቅ ከተማን አንድ አመት ተምሬባታለሁ። ያኔ ከደዕዋ አንፃር የረባ እንቅስቃሴ የሌለባት በጣም የቀዘቀዘች ነበረች። ዛሬ የአላህ ፈቃድ ሆኖ በናንተ ጥረት ጥሩ ለውጥ አለ። በዚህ ለውጥ ላይ ትንሽም ብትሆን ድርሻ ያላችሁን ሁሉ አላህ ይመንዳችሁ። ከዚህም የበለጠ ለውጥ ይኖር ዘንድ በርትታችሁ፣ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ስሩ። ይሄ ኃላፊነት የከተማው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የተሁለደሬ ወረዳን ወንድም እህቶችን ይመለከታል። ማእከሉ ሲጠነክር ነውና ለገጠሩ የሚተርፈው ከአካባቢው ርቆ ያለውን ተወላጅ ጨምሮ ሁሉም በሚችለው በደዕዋው ስራ ላይ መረባረብ ይገባል።
ወንድማችሁ ኢብኑ ሙነወር
=
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor