በቡድን የመጥጠርነፍ ጣጣ
~
በደዕዋ ላይ የተሰማራ ወይም ወደ ደዕዋ የተጠጋ ሰው ለሌሎች የሚያሳድረው ውግንናም ይሁን ጥላቻው ቡድናዊ ተፅእኖ የተጫነው እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል። በተቋማትና ማህበራት የታቀፉም ይሁኑ በሆነ የጋራ አመለካከት የተሳሰሩ አካላት ጥንቃቄ ካላደረጉ ስብስባቸውን ያማከለ ቡድናዊ ዝንባሌ (ተሐዙብ) የሚይዙበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ስብስቡን ወይም የጭፍራውን ቁንጮዎች በጭፍን የመከተል ጥፋት ሊኖር ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል። ብዙ ጭፍራዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አይነት ጥርነፋ አላቸው። በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአብዛኛው አባላት ባያምኑበት እንኳ የፓርቲውን እንጂ የግላቸውን አቋም ባደባባይ አያንፀባርቁም። በኢስላም ስም የሚደራጁ ስብስቦችም ይሄ ባህሪ የሚታይባቸው በብዛት ይገጥማሉ። ማዶና ማዶ ከሚኖሩ አሰላለፎች ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ።
1ኛ፦ መፅነፍ፦
የፀነፈ አቋም ለደዕዋ እንደማያዛልቅ፣ የትም እንደማያደርስ፣ በመጨረሻም እርስ በርስ መበላላትን እንደሚያስከትል የታወቀ ነው። ይሄ ከጥንት እስከ ዛሬ ያሉ ፖለቲካዊም ይሁን ሃይማኖታዊ አደረጃጀቶችን ያየ ሁሉ የሚያስተውለው ነው። በዚያ ላይ በተመሳሳይ አጀንዳ አንዱን መውጋት፣ ሌላውን ማለፍ አይነት መርህ የለሽነት ላይ ይጥላል።
ነጥቤ ምንድነው? በዚህ አይነት ስብስብ ታቅፈው ግን ውስጥ ላይ ችግሮች መኖራቸውን እያወቁ "ለምን?" ለማለት በመንጋው እንዳይወገሩ ፈርተው በዝምታ የሚጓዙ አካላት አሉ። "ለምን?" ያሉ ለታ የሚወሰድባቸው እርምጃ ማዶ ላይ ካሉት የከፋ ስለሚሆን በቡድን ተጠርንፈው፣ በፍርሃት ተሸብበው፣ ውስጣቸው ያለውን እምነት መኖር አቅቷቸው ካቦዎቹ በቀደዱላቸው ቦይ ይፈስሳሉ። ይሄ በብዙ ፅንፈኛ ቡድኖች ውስጥ ያለ ተጨባጭ ነው።
2ኛ፦ መላሸቅ፦
በዚህም ላይ አንዳንዶች የተጨመላለቀ አካሄድ በጭፍራቸው ሲፈፀም ሲያዩ ከመሸማቀቅ ውጭ "አልበዛም ወይ?" ለማለት ቡድናዊ ትስስር ወይም ጥቅም ያሰራቸው ብዙ የውስጥ ቆዛሚዎች አሉ። መላሸቁ በበዛ ቁጥር ቁዘማቸው ይረዝማል። ውስጣቸው ይታመማል። ቢሆንም ራሳቸውን መሆን መወሰን አይችሉም። ራሳቸውን ችለው ቢንቀሳቀሱ ከዚህ ሰቀቀን ነፃ ይሆኑ ነበር። ችግሩ ቀድመው በቡድን ተጠርንፈዋል። የጭፍራው ካቦዎች በተጣጠፉ ቁጥር ያለምርጫቸው ይተጣጠፋሉ። በወረዱበት ቁልቁለት ሁሉ ይወርዳሉ። በማያምኑበት መድረክ ሲያሰማሯቸው ይሰማራሉ። ወይ ራሳቸውን ከጥፋቱ አግልለው ሰላም አያገኙ። ወይ ጭንቅላታቸውን እንደ ካቦዎቻቸው ደፍነው አይገላገሉ። እንዲሁ ከሁለት ያጣ ጎመን።
በየትኛውም ቡድንተኛ ጭፍራ ውስጥ መጥጠርነፍ የህሊና ሰላም፣ የልቦና ረፍት ያሳጣል። ከኢኽላስ ያርቃል። አስመሳይነትን ያላብሳል። መርህ የለሽ ያደርጋል። ስለዚህ ከራስህ ጋር ተጣልተህ የሌሎች አጫፋሪ ከምትሆን ራስህን ነፃ አውጣ። ከአጉል ስብስብ አግልል። መንጋ ጋር አትጓዝ። እንዲህ አይነት ስብስብን በተመለከተ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፦
فَاعْتَزِلْ تِلكَ الفِرَقَ كُلَّهَا، ولو أَنْ تَعَضَّ بأَصْلِ شَجَرَةٍ، حتَّى يُدْرِكَكَ المَوْتُ وأَنْتَ علَى ذلكَ!
"ከነዚህ አንጃዎች በሙሉ ራቅ። የዛፍ ስር ነክሰህ መያዝ ቢኖርብህ እንኳ! (ያን አድርገህ ራቅ።) በዚህ ላይ ሆነህ ሞት እስከሚያገኝህ ድረስ።" [አልቡኻሪይ፡ 3606] [ሙስሊም፡ 1847]
የሚገርመው በሁለቱም ጫፎች ተሰልፈው ከነሱ የማይሻሉ አካላት በቀደዱላቸው እየፈሰሱ አበሳቸውን የሚያዩ ክፍሎች መኖራቸው ነው። ወንድሜ ጉዳዩ ከዘላለማዊ ህይወትህ ጋር ይገናኛል። የኣኺራህ ጉዳይ ላይ ሌሎች እንዲወስኑ አትፍቀድ። ከሰመመንህ ውጣ። አይንህን አሸት አሸት አድርግና ከማን ኋላ እንደተሰለፍክ ተመልከት። ልጅ ቢጎትተው፣ ጅል ቤጎትተው ሳያቅማማ የሚከተለው ግመል ነው። ሰው ተደርገህ ተፈጥረሃልና በተግባር ሰው ሁን።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor