Posts filter


“የትግራይ ሰራዊት በዲዲአር ስም እንዲበተን እየተደረገ ነው” - በደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሓት

ቅዳሜ ታህሳስ 12 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራ የህወሓት ቡድን  የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት እና በመልሶ ማዋሃድ ሥራ ስም፣ የትግራይ መሰረታዊ ጥያቄ ሳይመለስ የቀድሞ ተዋጊዎች እንዲበተኑ እየተደረገ ነው ሲል ክስ አሰምቷል።

የህወሓት አንዱ ክፋይ በመቐለ ከተማ፣ “የእምቢታ ዘመቻ” ብሎ የጠራው ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲፈፅም የተሰጠው ሥራ ሙሉ በሙሉ ወድቋል” በማለትም ገልጿል።

በሌላ በኩል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ለሦስት ቀናት ያካሔደውን ስብሰባ አስመልክቶ በአወጣው መግለጫ፣ “ክልሉን ወደ ግርግር እና የአመፅ ተግባር ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ ላይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አይታገስም” ብሏል።

የሁለቱ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽኩቻ  አሁንም ድረስ መፍትሄ ሳያገኝ እንደዘለቀ ነው፡፡


በገበያ ላይ የሚገኙ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ የፀረ-ወባ መድሀኒትቶች ማህበረሰቡ ከመጠቀም እንዲቆጠብ ተገለጸ

ቅዳሜ ታህሳስ 12 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በገበያ ላይ የሚገኙ አንዳንድ የፀረ -ወባ መድሀኒቶች ጥራታቸው ያልተረጋገጠ እና ለጤና ጎጂ በመሆናቸው ማህበረሰቡ ከመጠቀም አዲቆጠብ አሳስቧል፡፡

ደህንነት እና ጥራታቸው በባለስልጣኑ ያልተረጋገጡ መድሀኒቶች ለጤና ጎጂ እና የከፋ ችግር የሚያስከትሉ በመሆናቸው በምስሉ ላይ የተዘረዘሩትን መለያ ቁጥር የያዙ መድሀኒቶች ከመግዛት እንዲቆጠቡ እንዲሁም በቤት ውስጥ የሚገኝ ከሆነም ማህበረሰቡ በአፋጣኝ እንዲያሶግዱ  ባለስልጣኑ መመሪያን አስተላልፏል፡፡

መድሀኒቶቹም ማላሪያ ቤንን ጨምሮ ስምንት ያህል ሲሆኑ  ማህበረሰቡ ከመግዛትም ሆነ ከመጠቀም እንዲቆጠብ እንዲሁም የመድሀኒት መደብሮች ለገበያ እንዳይቀርቡ ነው ባለስልጣኑ የጠቆመው፡፡


በክልሎች የሚገኙ አየር ማረፊያ ተርሚናሎች ለአካል ጉዳተኛ ደንበኞች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ክፍተት አለባቸው ተባለ

ቅዳሜ ታህሳስ 12 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አደረኩት ባለው ጥናት እና ሪፖርት የአካል ጉዳተኞች በአየር መንገድ አገልግሎቶች ላይ ምቹ መገልገያዎችን ለመስጠት ክፍተት እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡

ይህን ተከትሎም በተለይም በክልሎች ላይ የሚገኙ የአየር ማረፊያ ተርሚናሎች ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ አገልግሎት ምቹ እንዳልሆነ እና ተጠቃሚዎቹም ለተጨማሪ እንግልት እየዳረጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሪፖርቱም በክልል በሚገኙ አየር ማረፊያ ተርሚናሎች ወደ አውሮፕላን ለመግባትም ሆነ ከአውሮፕላን ወጥቶ ለመሄድ የመጓጓዣ አገልግሎት የማይሰጥ በመሆኑ በተለይ በዝናብ ወቅት እና በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች አካል ጉዳተኞች ለተጨማሪ እንግልት መዳረጋቸው ማወቅ መቻሊን አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የአውሮፕላን በሮች ላይ የሚገጠም ተሻጋሪ ድልድይ እንዲሁም የአውሮፕላን ደረጃዎች የሚያሻግር መኪና በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው እና በተለይም በሀገር ውስጥ በረራ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ጥቅም ላይ የማይውሉ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም የዐይነ ስውራን አቅጣጫ መጠቆሚያ ነጭ በትር እና የእግር ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው ክራንቾች ካርጎ እንዲገቡ የሚጠየቅበት ሁኔታ መኖሩ፤ መስማት ለተሳናቸው እና ለዐይነ ስውራን መንገደኞች በአየር መንገዱ ውስጥ ሲስተናገዱም ሆነ በረራ ላይ ሳሉ መረጃ በተገቢው እና በተሟላ መልኩ እንደማይደርስ ኢሰመኮ በአደረገው ጥናት ለማወቅ ችሏል፡፡

በአጠቃላይ ከዓለም አቀፍ በረራዎች አንጻር ሲታይ የሀገር ውስጥ በረራ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች በማክበር ረገድ ክፍተት መኖሩ በክትትሉ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል።


#ማስታወቂያ


"በምክክር ሂደቱ የህብረተሰቡ የመደማመጥና የመወያየት ፍላጎት የሚደነቅ ነው" - ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር)

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል የምክክር ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡ የመደማመጥና የመወያየት ፍላጎት የሚደነቅ ነው ሲሉ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ከሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የህብረተሰብ ክፍሎች የምክክር መድረክ በትናንናው እለት መጠናቀቁን አስመልክቶ ኮሚሽኑ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በምክክሩ ሂደት ሁሉም ድምፆች ሲደመጡ፣ አንዱ የሌላውን ሀሳብ ሲያዳምጥ ተመልክተናል፣ ይህም ምክክሩ ያዳበረው የዴሞክራሲ ባህል ነው ሲልም ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።

በምክክሩ ሂደት ጠለቅ ያሉ የአጀንዳ ግብአቶች ተነስተዋል ያለው ኮሚሽኑ፤ የክልሉንና የሀገሪቱን ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ አጀንዳዎች መቅረባቸውንም ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምክክር ማድረጋቸው ለሌሎች ክልሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።


አሜሪካ በሰሜን ወሎ ቡግና ወረዳ ለተከሰተው ድርቅ እና የምግብ እጥረት ምግብ እየተላከ መሆኑን አስታወቀች

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የተከሰተውን ድርቅ እና የምግብ እጥረት ተከትሎ እርዳታ ወደ ስፍራው እየተላከ መሆኑን አስታውቋል።

ኤምባሲው በኦፊሴላዊ የፌስቡክ ገፁ እንዳስታወቀው በወረዳው እንደተከሰተ ከሰሞኑ እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች ላይ ክትትል አድርጓል።

"የኢትዮጵያ ህዝብን ለመደገፍ አጋሮቻችን ምግብ እና አልሚ ምግቦችን ወደተጠቁት ስፍራዎች እየላኩ ነው" ያለው ኤምባሲው ሁኔታውን በቀጣይም በመከታተል ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ አስታውቋል።


ፓርቲው የተሳሳተ የሴት እና የአካል ጉዳተኞች አባላትን ቁጥር በመናገር የወሰደውን ገንዘብ ባለመመለሱ ታግዷል- ምርጫ ቦርድ

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለጋምቤላ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ ከ2መቶ ሺህ ብር በላይ ለወሰደበት ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡

ፓርቲው መጀመሪያ ለቦርዱ በቃለ መሀላ ጊዜ ያሳወቀው የሴት አባላት ቁጥር 32 ሺህ 453፤ የአካል ጉዳተኛ ብዛት ደግሞ 1ሺህ 123 እና 3 የአካል ጉዳተኛ አመራር የነበረ ሲሆን በድጋሜ ያሉትን ብዛት ማስረጃ ሲጠየቅ የሴት አባላት 1ሺ225 የአካል ጉዳተኛ 13 በማለት ለቦርዱ ማሳወቁ ተገልጿል ፡፡

ነገር ግን ያቀረበውን ቁጥር የሚያስረዳ መረጃ እንዲያቀርብ ቢጠየቅም ማቅረብ ባለመቻሉ በቅድሚያ ፓርቲው ለቦርዱ ባቀረበው የአባላት ብዛት መሰረት የወሰደውን 220 ሺህ 883 ብር ለቦርዱ ተመላሽ እንዲያደርግ ተጠይቆ እንደነበር ምርጫ ቦርድ አስታውሷል፡፡

ይህን እንጂ የተላለፈበትን ትዕዛዝ መፈጸም ባለመቻሉ ፓርቲው እንዲታገድ እና የፓርቲው አመራር ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አግዷል፡፡

በተጨማሪም የወሰደውን የድጋፍ ገንዘብ ለታሰበው አላማ ማዋሉ አጠራጣሪ በመሆኑ የፓርቲው አመራሮች አግባብነት ባለው ወንጀል ህግ ተከሰው እንዲመልሱ መወሰኑን አስታውቋል፡፡


በኦሮሚያ ክልል የሽብር ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች እስከ 23 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እና አካባቢው የሽብር ወንጀል በፈፀሙ ግለሰቦች  ከ1 ዓመት ከ 6 ወር እስከ 23 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ግለሰቦቹ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን እና አካባቢው የሽብር ወንጀል ሲፈፅሙ በፀጥታ ኃይሎች በተካሄደው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ምርምራ ሲካሄድባቸው መቆየቱን ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሽብር ጥቃት በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ የሰው እና የሠነድ ማስረጃ ማቅረቡን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ ክስ መስርቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ ታሕሣሥ 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ወንጀለኞቹን ያስተምራል ሌሎችንም ያስጠነቅቃል በሚል ውሳኔውን ማስተላለፉን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡


"አዲስ የትግል አቅጣጫ እንከተላለን" ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን "የእምቢታ ዘመቻ" በሚል ከትናንት ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በዚሁ ስብሰባም የህወሓት ቡድን በቀጣይ አዲስ የትግል ስልት እንደሚከተል እና አጠቃላይ አባላቶቹ በመጠቀም "የእምቢተኝነት ዘመቻ" ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ለዚህ ዘመቻ "እምቢ ለብሔራዊ ክህደት፣ ለአገዛዝ እና ብተና" የሚል መፈክር እንደተሰጠው አስታውቋል፡፡

ለሙሉ ዘገባ፡ https://addismaleda.com/archives/39637


በአገሪቱ እየታየ ያለው ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ፣የስራ-አጥ ወጣቶች መበራከትና የኑሮ ውድነቱ ጫና የህግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ ስለማድረጉ የሚገልጹት የህግ ባለሙያው አቶ አንዱአለም በውቀቱ እነዚህን ችግሮች መፍታት ላይም ተሰርቷል ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

የህግ ባለሙያው በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያነሷቸውን ነጥቦች ለመመልከት ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ በመጫን ይከታተሉ

https://youtu.be/rVs7dZ6oAj0?si=uppGXSTlw3DiouDX


“አገራዊ ምክክር ለፖለቲካ ፍጆታ እንጅ ለዘላቂ ሠላም እና መረጋጋት ያለውን ቁርጠኝነት አያሳይም” የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ የብልጽግና መንግስት ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የአገራችን ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ከዕለት ወደ ዕለት ከድጡ ወደ ማጡ በሚያስብል ደረጃ ለሁለንተናዊ ምስቅልቅሎሽ እየዳረጉን ነው ሲሉ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖማው ወደ ጦርነት ኢኮኖሚ ተሸጋግሮ ለተለያዩ የልማት መሰረተ ልማት አውታሮች ሊውል የሚችል የዓመታዊ በጀት ከፍተኛው ድርሻ ለጦርነትና ጸጥታ ማስከበር ግብዓቶች እንዲውል፣ልማትና ዕድገት ከቀለም ቅብ ያለፈ መሰረት እንዳይኖረው አድርጓል ሲሉ ኮንነዋል፡፡

እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ ከህዝብ አቅም በላይ ሆኖ ምሬትና ተስፋ መቁረጥ በአደገኛ ሁኔታ የመሰደድን ምርጫ እያጎላው መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ኮከስ መንግሥት አካሂደዋለኹ የሚለው አገራዊ ምክክር ለፖለቲካ ፍጆታ እንጅ ለዘላቂ ሠላም እና መረጋጋት ያለውን ቁርጠኝነት አያሳይም በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የሰላም እጦት ባለበት ምንም አይነት ለውጥ ሳይኖር ምክክር እናድርግ ማለት ትርጉም አልባ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን ቀስ በቀስ "በስልታዊ" ዘዴዎች እንዳዳከመውና ምክር ቤቱም ዓላማውን እንደሳተ እና መንግሥት ከሌሎች አገራት ጋር የሚያካሂደው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከወዳጅነት ይልቅ አገሪቱን በጥርጣሬ እንድትታይ አድርጓታል በማለት ወቅሷል።

በተጨማሪም ግጭትና ጦርነትን እያስፋፉ የይስሙላ አግላይ የምክክርና ውይይት ስብከት ላም ባለዋልበት ኩበት ለቀማ መንከራተት እና የፖለቲካ መብት ጥያቄ አፈናውና በጋራ ምክር ቤት ሥም አሰልቺው የመድብለ ፓርቲ ፕሮፖጋንዳ እንዲሁም ኃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚዲያ ህግ በማሻሻል ሥም ማቀንጨርና ተቋማቱን የማፈን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡




"አዲስ የትግል አቅጣጫ እንከተላለን" ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል

ዓርብ ታህሳስ 11 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ቡድን "የእምቢታ ዘመቻ" በሚል ከትናንት ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በዚሁ ስብሰባም የህወሓት ቡድን በቀጣይ አዲስ የትግል ስልት እንደሚከተል እና አጠቃላይ አባላቶቹ በመጠቀም "የእምቢተኝነት ዘመቻ" ያለው እንቅስቃሴ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ለዚህ ዘመቻ "እምቢ ለብሔራዊ ክህደት፣ ለአገዛዝ እና ብተና" የሚል መፈክር እንደተሰጠው አስታውቋል፡፡

"ሁኔታዎች በመገምገም፣ ያሉ ለውጦችን በማየት አዲስ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ያስፈልጋል። እያደረግነው ያለው ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ይበልጥ ልናጠነክረው ስለወሰንን፥ የተደረሱ መግባባቶች እና ሊደረጉ ይገባል ያልናቸው የትግል ስልቶች በተመለከተ ከከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ጋር መግባባት ስለሚያስፈልግ የተጠራ መድረክ ነው" ሲሉ ዶ/ር ደብረፅዮን መናገራቸውን ዶቼቨለ ዘግቧል፡፡

በሂደት ከፍተኛ ጡዘት ላይ የደረሰው የሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ውዝግብ ወደከፋ አቅጣጫ እንዳያመራ እና በትግራይ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም እንዳያውክ በርካቶች ዘንድ ስጋት እንዳለ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

ይህን ተከትሎ በጉዳ ላይ አስተያየት የሰጡ ምሁራን ህወሓት ቡድኑ በግዚያዊ አስተዳደሩ ላይ ሊያደርገው ያቀደው የፕሬዝደንት ጨምሮ ሌሎች ለውጦች ከፌደራል መንግስቱ በኩል የጠበቀው ምላሽ ስላላገኘ የመረጠው የትግል ስልት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡


#ማስታወቂያ


በምስራቅ አርሲ ዞን ባለፉት ሁለት ቀናት 20 ነዋሪዎች በታጣቂዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገለጸ

ሐሙስ ታህሳስ 10 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሽርካ ወረዳ ታኅሣሥ 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም የወረዳ ቤተ ክህነቱን ሥራ አስኪያጅ ጨምሮ 20 ሰዎች በታጣቂዎች ግድያና እገታ እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ከታገቱት ውስጥም የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና ሌሎች 8 ሰዎች ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ሲሆን ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው እንዲሁም ያሉበት እንደማይታወቅ ተመላክቷል፡፡

ከ80 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ከብቶች በታጣቂዎች የተወሰደ ሲሆን በመንግስት እና በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እየተነፈግን የሚደርስብን ጥቃት በርትቶ ቀጥሎብናል ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸውን ማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ በጀጁ ወረዳ ቡርቃ ጉራቻ ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ 150 ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን 499 አባወራና እማወራ ለስደት መዳረጋቸውን ይታወሳል፡፡


መቀሌ ከተማ በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች የተመደቡ ከንቲባዎች በስራ ገበታ ላይ የሉም ተባለ

ታኅሳስ 09 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች የተመደቡ ከንቲባዎች በስራ ገበታ ላይ የሌሉ ሲሆን የከንቲባ ፅህፈት ቤት ታሽጎ በፀጥታ ሃይሎች ጥበቃ ስር እንደሚገኝ ተገልጋዮች መናገራቸው ተገልጿል።

በአስተዳደሩ ዋና በር በቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ተገለግጋዮች ሲገቡ ሲወጡ ይታያሉ ፤ ፍትሻ በሚካሄድበት ቦታ ከተለመደው በተለየ ብዛት ያላቸው የፀጥታ አካላት እንደሚስተዋሉ ተመላክቷል።

ለሙሉ ዘገባ፡ https://addismaleda.com/archives/39613


አድናቂዎቹና ተቃዋሞዎቹ መሳለመሳ የሚሄዱለት፣ታምነው የሚታዘዙለት በእሱ የፖለቲካ ሂደት ተስፋ ያላቸው እንዳሉ ሁሉ ተጠራጣሪዎቹና በጥንቃቄ የሚመለከቱትም በርካታ የሆኑት ጃዋር መሃመድ ሲራጅ አልጸጸትም ሲል ከሰሞኑ ተከስቷል፡፡

በሻሸመኔ ስለተፈጸመ የአንድ ወጣት አሰቃቂ ደቦኛ ፍርድ፣በእሱ ምክንያት ሁከት ውስጥ ገብታ፣የዜጎቿን ደም አፍስሳና በርካታ ውድመቶች ደርሰውባት ስላሳለፈችው አዲስ አበባ ፣ሰርቶ መለወጥን እያሰበ በሜጫ አንገቱ ስለተቆረጠ የአሩሲ ገበሬ ይሆን? ለሚሉና ለሌሎች የተቃዋሚዎቹ ወቀሳም አነጋጋሪ ምላሽን የሰጠበትን ጥንቅር በአዲስ ማለዳ ትንታኔ ቃኝተነዋል ከታች ያለውን ማስፈኝጠሪያ በመጫን ሙሉ ዝግጅቱን ይከታተሉ፡፡

https://youtu.be/_Iw9nn3JSmE


የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሕግ በተቀመጡት መስፈርቶች ብቻ የተከናወኑ ናቸው ሲል መከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ

ማክሰኞ ታህሳስ 08 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ሕፃናትን ጨምሮ ሰዎችን ከሕግ ውጪ መያዛቸውን በተመለከተ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

በመግለጫውም ከመከላከያ ሰራዊት መስፈርቶች ውጪ፣ “ለምልመላ” በሚል ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በግዳጅ በመያዝ የተሳተፉ መኖራቸዉንም ደርሼበታለሁ ብሎ ነበር፡፡

ይህን ተክሎ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መከላከያ ሚኒስቴርም በሁሉም ክልሎች የሚከናወኑ የሰራዊት አባላት ምልመላ ሥራዎች በሕግ በተቀመጡት መስፈርቶች መሠረት ብቻ የተከናወኑ ስለመሆናቸው በማረጋገጥ የሚረከብ መሆኑን ለኢሰመኮ ኅዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴር በዚህ ዓመት እየተደረገ ያለውን ምልመላ አፈጻጸም ለመፈተሽ ከከፍተኛ ሙያተኛ መኮንኖች የተውጣጣ ከ7 እስከ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅሮ በማጣራት መስፈርቶቹን የሚያሟሉትን ብቻ ለይቶ ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት ማስገባቱን በደብዳቤዉ ማስታወቁን ኢሰመኮ ገልጿል፡፡

ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በክልሎች በተከናወነው የምልመላ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ካሉ ግን ከክልሎች ጋር በመነጋገር ለማጣራት የሚቻል መሆኑን ሚኒስቴሩ አመላክቷል፡





20 last posts shown.