በኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርዲንግ ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቀቀበአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥር የሚገኘው የሕክምና ትምህርት አገልግሎት ጥራት ማሻሻያና ኢኖቬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር ጽ/ቤት፣ ከጤና መረጃ ሥርዓት አስተዳደር ዳይሬክተር ጽ/ቤት፣ ከመረጃና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለሆስፒታሉ ሠራተኞች በኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርዲንግ ዙሪያ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል፡፡
የሕክምና ትምህርትና አገልግሎት ጥራት ማሻሻያና ኢኖቬሽን ኮርፖሬት ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ስንታየሁ አበበ የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖለጂ የተደገፈ እንዲሆንና ፋይሎችን በዲጂታል አደራጅቶ ለመያዝ እንዲረዳ ሥልጠናው መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ይህም አሠራር የተገልጋዩን እንግልት በማስቀረት የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሕክምና አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃኑ አንዳርጌ ሆስፒታሉን በሙሉ አቅሙ ሥራ ለማስጀመር መልካም ጅማሮ መኖሩን ጠቅሰው ሥልጠናው መረጃዎች ለዘመናት እንዲቆዩ የሚያደርግና የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሠጣጥ የሚያዘምን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ ከሕንጻው ግንባታ ጀምሮ ለዲጂታል ሥራዎች ምቹ ሆኖ መሰራቱን የገለጹት ዶ/ር ብርሃኑ ሠልጣኞች ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ለሥራው ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የዘርፉ ባለሙያና አሰልጣኝ ምሕረት ብሩክ እና ናትናኤል አምሳሉ በጤና ሚኒስቴር በኩል Bahmni/EMR የተሰኘ የኤሌክትሮኒክ ሜዲካል ሪከርዲንግ ሲስተም መኖሩን ጠቅሰው በሲስተሙ በርካታ ሆስፒታሎች እየተጠቀሙበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ይህንን ዲጂታል አሠራር በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለማስፋፋት እየተሰራ ሲሆን ለሆስፒታሉ ሠራተኞች የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ ሥራ አካል ነው ብለዋል፡፡ ሲስተሙ ሥርጭት ክፍል፣ ካርድ ክፍል፣ ቤተ ሙከራ፣ የዕለት ገቢ ሰብሳቢ ሥራዎችንና ክፍሎችን እርስ በእርስ የሚያገናኝ መሆኑን አክለው ተናግረዋል፡፡
ሰልጣኝ ረ/ፕሮፌሰር ግስላ እንዳሻው እና ዶ/ር ታረቀኝ ማርካ በሰጡት አስተያየት ሲስተሙ ከወረቀት ንኪኪ የጸዳና አላስፈላጊ ወጪን የሚያስቀር፣ ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ እንዲሁም ዘመኑን የሚመጥን አሠራር ለመዘርጋት የሚያመች መሆኑን ከሥልጠና ግንዛቤ አግኝተናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሥልጠናው በሶፍትዌሩ አሠራር ላይ በተግባር የተደገፈ ዕውቀትና ክሂሎት ማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
የካርድ ክፍል ሠራተኞች፣ ሥርጭት ክፍል ላይ የሚሠሩ ነርሶች እና ሐኪሞች እንዲሁም ሌሎችም በሥልጠናው ተሳትፈዋል፡፡
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ -
https://www.amu.edu.et/ቴሌግራም -
https://t.me/arbaminch_universityፌስቡክ -
https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityccd/ዩቲዩብ -
https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVAየሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት