እብዱ ዮሐና
....................ምዕራፍ ስምንት(14)«አቤቱ ደጉ ኢየሱስ ሆይ! ደስታስ ምንድን ነው?
እንዴትስ ይገለፃል?
ክብርና ንብረት ለማካበት የወንዶችን ጉልበትና የሴቶችን ክብር እየገዛ ባለ አንድ ልዑል ሊገለጽ ይችላልን?....
ዓይኖችን በሚያጥበረብሩ ሜዳሊያዎችና በፈርጥ የተንቆጠቆጡ የሀር አልባሳት ለሚለብሱ ንጉሦች በአካልም ሆነ በመንፈስ እንደ ባሪያ በማገልገላችን ደስታ ሊገኝ ይችላልን? ደከም ያለ አቤቱታ ማሰማት ስንጀምር ጐራዴ የታጠቁ ወታደሮቻቸውን አዝምተው፣ ምድሪቷን በሴቶቻችንና ልጆቻችን ዋይታና ደም ሲያጥለቀልቋት ተንበርክከን በምንማፀናቸው በኛ የተጨፈለቅነው ህዝቦች ዘንድ ይሆን ደስታ
የሚገኘው?......
«አቤቱ በፍቅርና በምህረት የተሞላኸው እየሱስ ሆይ! ኃያሎቹ እጆችህን ዘርግተህ ከቀማኞች ጠብቀን፡፡ ወይም የጨቋኞች እጅ ስለከበደን በመስቀልህ ጥላ ስር እየተጠበቅን በሰላም ወደ ምናርፍበት መቃብራችን ይወስደን ዘንድ ሞትን ላክልን፡፡ እዚያ ሆነን ያንተን መምጣት እንጠብቃለን፡፡ አቤቱ ታላቁ እየሱስ! በእውነቱ ይህ ህይወት በጨለማ ክፍል ውስጥ ያለ ጠባብ እስር ቤት ሆኖብናል፡፡ አስፈሪ መናፍስት ዳንኬራ የሚረግጡበት፣ የሞት መንፈስ ህይወት የዘራበት አሰቃቂ ህይወት ነው፡፡ በሕይወት ዘመናችን የምናሳልፋቸው ቀናትስ ቢሆኑ?.....
የምሽቱን ጨለማ በመፍራት በድሪቶ በተሸፈነ የአረጀ አልጋችን ስር የሚሸሸጉ፣ ጐህ ሲቀድና የመኖር ፍቅራችን ወደ እርሻ መሬታችን በመራን ቁጥር ደግሞ እንደ እርኩስ መንፈስ ከራሳችን በላይ ተሰቅለው በመስኩ ላይ የሚጠብቁንን አሰቃቂ የባርነት ህይወታችን የሚጠቁሙን የሰላ ጐራዴዎች እንጂ ሌላ ምንድ ናቸው? .......
«አቤቱ እየሱስ! ዛሬ ትንሳኤህን ለማስታወስ እዚህ የመጡትን እነዚህን የተጨቆኑ ድሆችን ምህረት ስጣቸው፡፡ ዳግም ለፍርድ በምትመጣበት ዕለት በስምህ አንድ ሆነው በአንድ ላይ የሚሰባሰቡትን እነዚህን ህዝቦችን በደካማነታቸውና በትሁትነታቸው ራራላቸው፡፡››
ህዝብ በዙሪያው ተሰብስቦ እንደቆመ ከሰማዩ ጋር ይነጋገር የነበረው ዮሐና፣ በዚህ ንግግሩ የተደሰቱት ጥቂቶቹ ሲያወድሱት ሌሎቹ ደግሞ ተበሳጭተው የስድብ ውርጅብኝ አወረዱበት፡፡
አንደኛው ወገን ጮህ ብሎ «በመለኮታዊ ኃይል ፊት ስለ እኛ የተናገረው በሙሉ እውነት ነው» ሲል፣ ሌላኛው ወገን ደግሞ፣ «ሰይጣን ተጠናውቶታል፡፡ የሚናገረውም በአንድ እርኩስ መንፈስ አንደበት ነው› አለ፡፡ ሌላኛውም ቀበል አድርጐ «እንደዚህ ያለ ዘግናኝና የማይረባ ንግግር ከዚህ ቀደም ከአባቶቻችን እንኳን በፍጹም ሰምተን አናውቅም፡፡ አሁንም ቢሆን ለመስማት አንሻም፡፡ ንግግሩን ቶሎ ማስቆም አለብን!» በማለት ጮኸ፡፡
ሌላኛው አራተኛው ሰው ግን አጠገቡ ወደቆመው ሰው ጆሮ ጠጋ ብሎ፣ «ንግግሩን ስሰማ ውስጤ በሆነ አዲስ መንፈስ የተሞላ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ የተናገረው በአንድ የተለየ መለኮታዊ ኃይል ነው» አለ፡፡ አንደኛውም መልስ ሰጠው፡፡ «ባልከው ነገር እስማማለሁ፡፡
.........ይቀጥላል............👍👍👍👍👍👍👍👍
https://t.me/Asresee
https://t.me/Asresee
https://t.me/Asresee