🔈 #የተማሪዎችድምጽ
" በዩኒቨርሲቲው አመራር ለደህንነታችን ስጋት ወደ ሆነ አካባቢ ትሄዳላችሁ ተብለናል "- ተማሪዎች በቁጥር 1,300 አካባቢ ይሆናሉ የተባሉ የደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎች ከዋናው ግቢ 5 ኪ/ሜ ያህል ርቆ ወደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ትዘዋወራላችሁ መባላቸው ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ የሚዘዋወሩበት ግቢ " በመንግስት እና በታጣቂዎች መካከል አልፎ አልፎ የተኩስ ልውውጥ የሚደረግበት አካባቢ ነው " ያሉ ሲሆን " በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች እየለቀቁ ባለበት ሁኔታ ዩኒቨርሲቲው ለደህንነታችን ስጋት ወደ ሆነ አካባቢ ትሄዳላችሁ ብሎናል " ሲሉ ቅሬታቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አቅርበዋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጤና ካምፓስ ከደብረማርቆስ ከተማ በ5 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን በ2015 ዓ/ም ህዳር ወር ጀምሮ ለ7ወር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በክልሉ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከየካቲት 7/2016 ዓም ጀምሮ ተማሪዎቹን ወደ ዋናው ግቢ በማዘዋወር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አደርጎ ነበር።
እስከ አሁን በዋናው ግቢ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት የጤና ተማሪዎች " ከሚመጣው ቅዳሜ 10/05/17 ዓም ጀምሮ ወደ ቀድሞ ግቢ እንደምንዘዋወር ተነግሮናል " ብለዋል።
ተማሪዎቹ ትዘዋወራላቹ የሚል ውሳኔ ከሰሙበት ቀን ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
በ 02/05/2017 ዓም የጤና ኮሌጅ ዲን አና ሌሎች የጤና ትምህርት ክፍል ተጠሪዎች በተገኙበት ባደረጉት ስብሰባም " ለሚደርስባቹ የህይወት አደጋ ዩኒቨርሲቲው ምንም አይነት ኃላፊነት አይወስድም እርስ በእርሳቹ ተጠባበቁ አናንተ ስትሄዱ የቦታዉ ሰላም ይረጋገጣል " መባላቸውን ተናግረዋል።
በትላንትናው ዕለት የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ የሚመለከታቸው የክፍል ተጠሪዎች በተገኙበት በድጋሚ ባደረጉት ስብሰባ ተማሪዎች ውሳኔያቸውን እስከ አርብ እንዲያሳውቁ እና ከቅዳሜ ጀምሮ እንደሚዘዋወሩ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ምን ምላሽ ሰጠ ?
ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የዩኒቨርሲቲው አመራር ዝርዝር ማብራሪያ ጠጥተዋል።ምን አሉ ?" እንዲሄዱ የሚደረግው የቦታ ጥበት በመኖሩ ነው ተማሪዎቹ መጀመሪያ ግቢያቸው ይህ አልነበረም ተደርበው ነው ያሉት።
የትምህርት ማቴሪያሎቻቸው በሙሉ እዛ ነው የሚገኙት ዩኒቨርሲቲውም የሚቀበላቸው አዳዲስ ተማሪዎች አሉ ይሄ ሁሉ ተጨማምሮ የመማሪያ ክፍል እጥረት ስላለ እና ጸጥታውም በአንጻራዊነት መሻሻል ስለሚያሳይ ነው እንዲሄዱ የተወሰነው።
ተማሪዎቹ ' እንሂድ ' ብለው ሰኔ ወር ላይ ጠይቀው ነበር እንዲዘገዩ ያደረግነው እኛ ነን በወቅቱ ጸጥታው ይህንን ለማድረግ የማያስችል በመሆኑ አሁን እንሂድ ስንል ነው ቅሬታ የተፈጠረው " ብለዋል።
በአካባቢው በሚታየው የጸጥታ ችግር አካባቢያቸውን የሚለቁ ሰዎች እንዳሉ ተሰምቷል ምን አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታዎች ኖረው ነው ተማሪዎቹ የሚዘዋወሩት ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ አመራሩን ጠይቋል።
እሳቸውም ፦
" አካባቢውን እየለቀቀ ያለ ሰው አለ የሚለው ውሸት ነው የሚለቅ ሰው ሊኖር ይችላል ክረምት እና ከክረምት በፊት በፍርሃት የሚወጡ ነዋሪዎች ነበሩ አሁን ግን ነዋሪውን በአካል አወያይተናል ነዋሪውም መምጣታቸውን ይፈልጋል።
ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ ነው ልል አልችልም ካለው ተለዋዋጭ ሁኔታ አንፃር አሁን ያለንበትም ተቋም ቤቱም ሆነ ከተማው ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ግን የተለየ ስጋት የለም የሚል ድምዳሜ ነው ያለው " ብለዋል። በዋናው ግቢ ቆይተው ቢማሩ ለደህንነታቸው የበለጠ አስተማማኝ አይሆንም ወይ ? ስንል ጥያቄ አንሰተናል።" እዚህም ቢሆኑ እዛም ቢሄዱ ችግር የሚመጣ ከሆነ ሊደርስባቸው ይችላል ' ያኛው ግቢ የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ያደርገናል ' ብለው ቢያስቡ እንኳ በአሁኑ ሰዓት በዋናው ግቢ ትምህርቱን ለማስቀጠል የማያስችሉ ሁኔታዎች አሉ ትምህርቱ እየተጎዳ ስለሆነ " የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።[ዘገባውን ያሰናዳው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ነው]
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news