ወሳኝ የጥቢ፞ ህግጋት
~
በሃገራችን ወላጆች ልጆቻቸውን ጎረቤት ወይም ጓደኛ ዘንድ ጥለው ሲሄዱ የተተወባት እናት ልጁን ማጥባት የተለመደ ነው። ነገር ግን የሚከተለው ሸሪዐዊ ህግጋት እንዳለ ስለማያውቁ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት አይሰጡትም። ይሄ ትልቅ ርእስ ስለሆነ እናቶች ተገቢውን ጥንቃቄና ክትትል ሊያደርጉ ይገባል።
በኢስላም ጥቢ፞ ከተራና አላፊ እለታዊ ክስተት ያለፈ ትርጉም አለው፡፡ ማለትም አጥቢና ጠቢን ያማከሉ ሰፋ ያሉ ሸሪዐዊ ህጎች ስላሉ ሙስሊሞች ተያያዥ ብይኖችን ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ውስጥ አንዱ እናታችን ዓኢሻ ረዲየላሁ ዐንሃ ያስተላለፈችው ሐዲሥ ነው፡፡ በዚህ ሐዲሥ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-
"الرَّضَاعَةُ تُحَرِّمُ مَا تُحَرِّمُ الْوِلَادَةُ".
“ጥቢ፞ መዋለድ (ከመጋባት) የሚከለክለውን ይከለክላል፡፡” [ቡኻሪ፡ 2646] [ሙስሊም፡ 1444]
ስለዚህ ጥቢ፞ ከስጋዊ ዝምድና ጋር የሚጋራቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው። እነዚህም አራት ናቸው፡-
① ጋብቻ:–
በስጋ እናት ሰበብ ለመጋባት ክልክል የሆነ ሁሉ በተመሳሳይ በጥቢ፞ እናት ሰበብም ክልክል ይሆናል። ዝርዝሩ ወደፊት ይመጣል።
② እይታ (ነዞር):–
በስጋ እናት ሰበብ መመልከት የሚፈቀድ ሁሉ በተመሳሳይ በጥቢ፞ እናት ሰበብም የተፈቀደ ይሆናል። ስለዚህ እናቱን፣ እህቱን፣ አክስቱን፣… ማየት፣ መጨበጥ፣ መሳም እንደሚፈቀደው ሁሉ በጥቢ፞ ሰበብ ተመሳሳይ ብይን የሚይዙንም መመልከት፣ በሰላምታ መጨበጥና መሳም ይፈቀዳል። ስጋት እስከሌለ ድረስ።
③ ተገልሎ መቆየት:–
እንደሚታወቀው ለአንድ ወንድ ከአጅነቢያ ሴት ጋር ከሰው እይታ ተገልሎ መቀመጥ አይፈቀድም። ነገር ግን ከስጋ እናት፣ እህት፣… ጋር ተገልሎ መቀመጥ እንደማይከለከለው ከጥቢ፞ እናት፣ እህት፣ አክስትም፣… ጋርም ተገልሎ መቀመጥ አይከለከልም።
④ የጉዞ ጓደኛ መሆን:–
አንድ ወንድ ለወላጅ እናቱ፣ ለእህቱ፣ ለአክስቱ፣… የጉዞ ጓደኛ እንደሚሆነው ሁሉ ለጥቢ፞ እናቱ፣ እህቱ፣ አክስቱም መሆን ይችላል።
•
መጠነኛ ትንታኔ
~
1. አንድ ሰው ልጅ እያለ አንዲት ወላጅ እናቱ ያልሆነች ሴት ብታጠባው ያቺ አጥቢ እንደ እናቱ ትታሰባለች፡፡ ሴቶች ልጆቿ እንደ እህቶቹ፣ ወላጆቿ እንደ አያቶቹ፣ እህቶቿ እንደ የሹማዎቹ፣ ስታጠባው ጊዜ ያለው ባሏ እንደ አባቱ፣ የባሏ ወላጆች እንደ አያቶቹ፣ የባሏ እህቶች እንደ አክስቶቹ፣ የባሏ ሌሎች ሚስቶች እንደ አባቱ ሚስቶች፣ ባሏ ከሌላ ሚስት የወለዳቸው ልጆች ልክ እንደ እህትና ወንድሞቹ ይቆጠራሉ፡፡
የጠባችው ሴት ከሆነችም ተመሳሳይ ንፅፅር እንሰራለን፡፡ ባጭሩ የአጥቢዋ ወንዶች ልጆች ለጠቢዋ ወንድሞቿ፣ የአጥቢዋ ወንድሞች ለጠቢዋ አጎቶች፣ … ይሆናሉ፡፡ አጅነቢዮች አይሆኑም።
2. ልክ በመዋለድ (በስጋዊ ዝምድና) የተነሳ ለማግባት እንደማትፈቀድ ሴት፣ በጥቢ፞ የሷን ብይን የምትይዝን ሴትም (ለምሳሌ የጥቢ፞ እህት፣ የጥቢ፞ እናት፣ የጥቢ፞ አክስት፣ የጥቢ፞ የሹሜ፣ …) አንድ ወንድ ሊያገባ አይፈቀድለትም፡፡ ጋብቻ ተፈፅሞ ከሆነም መለያየት ግዴታ ነው፡፡
ማሳሰቢያ፡-
~
1. ዋጋ የሚኖረው ጥቢ፞ በሁለት አመት የህፃንነት እድሜ ክልል ውስጥ የተጠባ ጥቢ፞ ከሆነ ነው። [አልበቀራ: 233] ከሁለት አመት እድሜ በላይ እያለ የተፈፀመ ጥቢ፞ ከቁምነገር አይቆጠርም።
2· ጥቢ፞ው አምስት ጊዜና ከዚያ በላይ የጠባ ከሆነ ነው፡፡ [ሙስሊም: 1452]
አንድ ጊዜ ጡቱን ከያዘ በኋላ ለመተንፈስ፣ ውሃ ለመጠጣት፣ ወደሌላኛው ጡት ለመቀየር የሚኖረው ቆይታ ተፅእኖ የለውም። ረጅም ጊዜ ካልኖረ በስተቀር እንደ አንድ ነው የሚቆጠረው። ይሄ አንድ ተብሎ በዚህ መልኩ አምስት ጊዜ ከተጠባ የጥቢ፞ ህግጋት ታሳቢ ይሆናሉ። ከአምስት ጊዜ ያነሰ ጥቢ፞ ከግምት አይገባም፡፡
3. የጥቢ፞ ህግጋት የሚመለከተው የጠባውን አካል ብቻ እንጂ ያልጠቡ የስጋ ወንድሞቹንና እህቶቹን አይደለም፡፡ ማለትም የጠባው አካል ከጠባበት ቤት ቤተሰብ ይሆናል፡፡ እንጂ የሱ የስጋ ቤተሰቦች በሱ መጥባት የተነሳ ለጥቢ፞ እናቱ ቤተሰብ አይሆኑም፡፡
ምሳሌ፡- ፋጢማ፣ ሙሐመድን ብታጠባ እሷ ለሱ እናቱ ነች፡፡ ልጆቿም እህቶቹና ወንድሞቹ ናቸው፡፡ ሴቶች ልጆቿን እህቶቹ ስለሆኑ ሊያገባ አይፈቀድለትም፡፡ ነገር ግን ህጉ እሱን እንጂ የስጋ ወንድምና እህቶቹን አይመለከትም፡፡ ምክንያቱም የፋጢማ እናትነት ለሱ እንጂ ለነሱ አይደለምና፡፡
4. የጥቢ፞ ህግ እስከ መዋረስ፣ ቀለብ መስፈር፣ ለጋብቻ ሃላፊ (ወሊይ) መሆን አይደርስም፡፡ ማለትም ለምሳሌ በጥቢ፞ የተነሳ እናቱ ወይም አባቱ የሆነ ሰው ስለሞተ ንብረት መውረስ አይችልም፡፡ ለጥቢ፞ እህቱ የጋብቻ ወሊይ መሆን አይችልም። ለወላጅ እናቱ ቀለብ የመስፈር ግዴታ ስላለበት ዘካ መስጠት አይፈቀድለትም፡፡ ለጥቢ፞ እናቱ ግን ቀለብ ግዴታ ስላልሆነበት ዘካ መስጠት ይችላል፡፡
5. ጥቢ፞ ተከስቷል ወይስ አልተከሰተም በሚለው ላይ ጥርጣሬ ካለ መነሻ የሚሆነን ጥቢ፞ውን እንደሌለ መቁጠር ነው፡፡ በጥርጣሬ ላይ ተመርኩዘን የጥቢ፞ን ህግጋት አንተገብርም፡፡
የጥቢ፞ው መጠን ላይ ከተጠራጠርንም እርግጠኛ የሆንበትን ማለትም ዝቅተኛውን እንወስዳለን፡፡ [አልሙግኒ፣ ኢብኑ ቁዳማ: 7/537]
6· በጥቢ፞ ጉዳይ ታማኝ ከሆነች የአንዲት ሴት ምስክርነት ብቻውን በቂ ነው። ለምሳሌ አንዲት ሴት ቀርባ "ሁለቱንም አጥብቻቸዋለሁ" ካለች ምስክርነቷ ተቀባይነት አለው። ተጋብተው ከሆነ ይለያያሉ። [ቡኻሪይ: 2659]
7· የተብራራ ያልሆነ ድፍን ምስክርነት ተቀባይነት የለውም። ስለዚህ የጥቢ፞ውን ዘመንና ቁጥር በተጨባጭ መግለፅ ያስፈልጋል። ይሄ ባልሆነበት የጥቢ፞ን ህግጋት አንተገብርም። [አልሙግኒ፣ ኢብኑ ቁዳማ: 7/537]
አዋቂው አላ፞ህ ነው። እርምት ያለው ሰው ቢያጋራኝ ደስ ይለኛል።
(ኢብኑ ሙነወር፣ ረቢዑል አወል 17/1441)
(ህዳር 04/2012)
=
* የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/IbnuMunewor* የዋትሳፕ ቻናል፦
https://whatsapp.com/channel/0029VaA3X1e5kg7BlsJboa2M* ፌስቡክ
https://www.facebook.com/Ibnu.Munewor?mibextid=ZbWKwL