በአዲስ አበባ የጤና መድህን አገልግሎት ምዝገባ ከጥቅምት እስከ ህዳር 30 እንደሚካሄድ የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ አሳወቀ‼️ቢሮው የጤና መድህን አባልነት ምዝገባን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዮሐንስ ጫላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ፍትሐዊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከሚያከናዉናቸዉ ተግባራት መካከል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዋነኛዉ መሆኑን ገልጸዋል ።
ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ባለፉት ዓመታት በርካታ የከተማዋን ነዋሪዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል የሆኑ ሲሆን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ በድግግሞሽ አባላትና ቤተሰቦቻቸዉ በተመላላሽና በተኝቶ ህክምና ከጤና ጣቢያ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ሆስፒታል ባሉት የጤና ተቋማቶች የአገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በዚህ አመትም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ነባር አባላቶቻችን ሙሉ ለሙሉ እድሳታቸዉን እንዲያድሱና ተጨማሪ 10 በመቶ በላይ አባላቶችን በመጨመር በአጠቃላይ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡
የ2017 ዓ.ም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ምዝገባ ወቅት ከጥቅምት 1 እስከ ህዳር 30 በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የነባርና አዲስ አባላት ምዝገባ መካሄድ መጀመሩን አሳውቀዋል።
ክፍያዉን አስመልክቶም፤ የመደበኛ መዋጮ መጠን 1500 ብር ሲሆን የደሀ ደሀ ለሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ሙሉ ለሙሉ በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ይሆናል፡፡
ይህ ማለት ነባር አባል 1500 ብር ሲሆን ለአዲስ አባል ደግሞ የመዋጮ 1500 ብር እና የመመዝገቢያ 200 ብር በጠቃላይ 1700 ብር ዓመታዊ መዋጮ ይከፍላል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ዕድሜያቸዉ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆች እና በአባሉ ጥላ ስር ለሚኖሩ ተጨማሪ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸዉ 750 ብር ይከፈላል፡፡
በኢ መደበኛ ክፍል ኢኮኖሚ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተቀመጠዉን መዋጮ በመክፈል ዓመቱን በሙሉ በሁሉም ዉል በተገባባቸዉ የጤና ተቋማት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉም ብለዋል፡፡
አክለዉም ዋናዉ ነገር ጤና ነዉና ህብረተሰቡ ዛሬ ነገ ሳይል የምዝገባ ጊዜዉ አጭር መሆኑን ተገንዝቦ በሚኖርበት ወረዳ ጤና ጣቢያ በመሄድ ምዝገባ ማድረግ አለበት ያሉት ኃላፊዉ ህብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን እንዳለበትና አባል ለመሆን ወደምዝገባዉ ሲሄዱም የነዋሪነት መታወቂያን ጨምሮ መሟላት የሚገባዉን በሟሟላት ስራዉ የተቀላጠፈ እንዲሆን ማገዝ እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡
👇👇
የቴሌግራም ቻናላችንን join በማድረግ ወቅታዊ መረጃዎችን በቀላሉ ይከታተሉ፣ሊንክ👇
👇👇
https://t.me/+Vl6V8k9V3YNEOp2shttps://t.me/+Vl6V8k9V3YNEOp2s