ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: not specified


በዚህ ቻናል የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርቶች እና የአበው ቀደምት የተናገሯቸው መንፈሳዊ ንግግሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶችና መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
not specified
Statistics
Posts filter


ባሎች ለሚስቶቻቸው ሊያሳዩአቸው የሚገባ
           ፍቅር በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስትህ ለአንተ ትገዛልህ ዘንድ ትሻለህን? ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት አንተም እንዲሁ ለሚስትህ አድርግላት፡፡ ሕይወትህን ስለ ርሷ አሳልፈህ መስጠት ካለብህ ስለርሷ ሕይወትህን አሳልፈህ ስጥ፤ መከራም መቀበል ካለብህ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ፡፡

አንተ ይህን ብትፈጽመው ስንኳ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ካደረገላት ጋር ሲነጻጸር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንተ ይህን ያደረግኸው ከአንተ ጋር ፈጽማ ለተዛመደችህ ለአንዲት ሴት ነው፡፡ “እርሱ ግን ከእርሱ ለተመለሰችውና ለጠላቸው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፡፡” ርሱ ከርሱ የተመለሰችውንና የጠላችውን እንዲሁም ያቃለለችውን ገንዘቡ ሲያደርጋት በማስፈራራት፣ በማስገደድ ወይም ይህን በመሳሰሉ ነገሮች አልነበረም፤ ነገር ግን ኀዘን ባልተቀላቀለበት ፍጹም በሆነ ፍቅር በመሆን ነበር፡፡ አንተም ለሚስትህ እንዲሁ አድርግላት አዎን! ምናልባት ሚስትህ አንተን ልታመናጭቅህ፣ ልትንቅህ፣ ልታፌዝብህም ትችላለች፤ ቢሆንም ግን አንተ ለርሷ ካለህ አርቆ አሳቢነት ንጹሕ ፍቅርና ኀዘኔታ የተነሣ ልትታገሣት ይገባሃል፡፡

ከሰው ሁሉ ጋር ተስማምቶ ለመኖርም ከእነዚህ የተሻሉ ነገሮች ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተለይም ለባልና ለሚስት፡፡ አንድ ሰው አገልጋይ ባሪያውን በማስፈራራት ለመግዛት ቢሞክር ለጥቂት ጊዜአት ሊገዛለት ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባሪያ እንዲህ ዓይነት አገዛዝ ስለማይመቸው ከእርሱ ፈጥኖ ይሸሻል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው የሕይወቱን አጋር፣ የልጆቹን እናት፣ የደስታው ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ሚስቱን በፍቅርና በፍጹም አክብሮት እንጂ ልክ እንደ ባሪያ በፍርሃት ሰንሰለት በማሰር ወይም በማስጨነቅ ርሷን ሊገዛት መሞከር አይገባውም፤ ሚስት በባልዋ ምክንያት የምትሸበር ከሆነ አንድነታቸው ምን ዓይነት አንድነት ነው? ከባሪያ ጋር እንደ መኖር ከሚስት ጋር መቀመጥ ለባል የሚፈጥርለት ምን ዓይነት ደስታ  ነው? አዎን ይልቁኑ አንተ ስለ ርሷ ስትል ብዙ መከራዎችን መቀበል ሲገባህ በተቃራኒው በቁጣ ርሷን በማስጨነቅና በማሸበር ታስፈራራታለህን? ክርስቶስ እንዲህ አላደረገም፡፡

“በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ አንዲቀድሳት ስለ ርሷ (ስለ ቤተ ክርስቲያን) ራሱን አሳልፎ ሰጠ ፡፡ ከቃሉ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን (እኛ) አስቀድማ ንጽሕት አልነበረችም፤ ጉድፍ ነበረባት፤ መልከ ጥፉም ነበረች፡፡ ስለዚህም ለእርሱ የተገባች አልነበረችም፡፡ አንተ እንደ ቤተ ክርስቲያን የሆነችውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ አትመርጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ የተለየችውን ያህል ከአንተ ፈጽማ የማትስማማውን ሴት ሚስትህ ትሆን ዘንድ ወደ አንተ አታቀርባትም፡፡ እርሱ ግን እጅግ መልከ ጥፉ ብትሆንም አልጠላትም፣ አልተጸየፋትም፣ ስለ መልከ ጥፉነቷ የተጻፈውን መስማት ትፈልጋለህን? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ርሷ ምን እንደሚል ስማ “ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ” (ኤፌ.፭፡፰) አላት፤ የገጽታዋን መጥቆር ትመለከታለህን? ከጨለማስ የበረታ ጥቁረት ምን አለ? የአመሏን መክፋት ደግሞ ስማ “በክፋትና በምቀኝነት” ይልና “የምንኖር” ይላል፤ ስለ ነውሮቿ ደግሞ “የማንታዘዝና የምንስት ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ” ይላታል (ቲቶ.፫፡፫)፡፡

ነገር ግን ለርሷ ስለተደረገላት በጎነት ምን ማለት ይቻለኛል? ርሷ ስንፍናን የተሞላችና ክፉ አንደበት የነበራት እንዲሁም በነውሮቿ ሁሉ ያደፈች ብትሆንም እነዚህ ሁሉ ጠባዮቿ ከርሷ አላራቀውም፡፡ ነገር ግን ልክ የደስ ደስ እንዳላት ልጃገረድ በአፍቃሪም ዘንድ ለምትወደድ ውብ ሴት እንደሚደረገው ርሱ ስለ ርሷ ራሱን አሳልፎ የሰጠ አይደለምን? ይህንንም በማድነቅ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት ስንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኛል” ይልና “ነገር ግን ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና”(ሮሜ.፭፥፯-፰) ብሎአል፡፡ በዚህ መልክ ርሷ ለርሱ  ትሆን ዘንድ አቀረባት፤ በመንፈሳዊ ውበትም አስጌጣት፤ ንጽሕት አደረጋት፤ ስለ ርሷም ራሱን አሳልፎ ለመስጠት ስንኳ የጨከነ ሆነ፡፡

(የትዳር አንድምታ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ ገጽ 17-19 - በመምህር ሽመልስ መርጊያ)

2.7k 0 112 6 74

“ላገቡት” የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር

ባልና ሚስት አንድ መኾናቸውን ብዙ ጊዜ ስለ ተማራችሁት እርሱን አልደግምላችሁም፡፡ ከዚህ ተነሥቼ ግን ጥያቄ ልጠይቃችሁ፦ ከሰውነታችሁ ውስጥ አንዱ ሕዋስ ቢታመም ቆርጣችሁ ትጥሉታላችሁን? ከሕመሙ ይፈወስ ዘንድ የምትጥሩ አይደላችሁምን? ለትዳር አጋራችሁም እንደዚህ መኾን አለባችሁ፡፡ እንደዉም'ኮ፥ ከሰውነታችሁ ሕዋስ ውስጥ ያለው በሽታ አንዳንዴ ላይድን ይችላል፡፡ የትዳር አጋራችሁ ግን፥ ምንም ክፉ ቢኾንም ሊለወጥ ይችላል፡፡ በሰውነታችን ላይ የሚኖረው አንዳንዱ ችግር ለምሳሌ ልምሾ እጅ ወይም እግር ሥራ መሥራትን ሊከለክለን፣ በሌላዉ የሰውነታችን ክፍል ላይ ጫና ሊያሳድርብን ይችላል፤ ነገር ግን ይበልጥ እንክብካቤ እናደርግለታለን እንጂ ቆርጠን አንጥለዉም፡፡ ታዲያ መዳን ለማይችለው ሰውነታችን ይህን ያህል እንብካቤ እያደረግንለት ሳለ፥ የመዳን (የመለወጥ) ዕድል ያለው አካላችንን (ባለ ትዳራችንን) መቁረጥ (መፍታት) እንደ አማራጭ ማስቀመጣችን እንዴት ብናብድ ነው?

7.6k 1 189 9 172

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ለንስሓ ልጁ በሰርጓ ቀን መገኘት ባለመቻሉ የላከላት ደብዳቤ

“ልጄ! ለሰርግሽ የነፍስ አባትሽ እኔ ጐርጐርዮስ ይህን ግጥም ስጦታ አድርጌ ልኬልሻለሁ፡፡ አባት ለሚወዳት ልጁ ሊሰጣት የሚችለው የተሻለው ምክርም ይህ እንደ ኾነ አምናለሁ፡፡

ኦሎምፒያታ ሆይ፥ እውነተኛ ክርስቲያን ለመኾን ያለሽን ፍላጎት ዐውቃለሁና በደንብ አድምጪኝ! እውነተኛ ክርስቲያን እንዲሁ መኾንን የሚመኝ ብቻ ሳይኾን እንደዚያ ለመኾን ሊጥር ይገባዋል፡፡

ከኹሉም በላይ፥ እግዚአብሔርን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ከእርሱ ቀጥሎም በቅዱስ ወንጌል እንደ ታዘዘው እንደ ጌታችንና መድኃኒታችን [ኢየሱስ ክርስቶስ] አድርገሽ ባልሽን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ስለዚህ እጠይቅሻለሁ! ጌታዋንና ፈጣሪዋን [ኢየሱስ ክርስቶስን] የማታከብርና የማትወድ ሴት በዚህ መንገድ ባልዋን እንዴት አድርጋ ልታከብረውና ልትወደው ትችላለች?

“በጋብቻሽ ውስጥ የትዳር አጋርሽ ይኾን ዘንድ እግዚአብሔር መርጦ ለሰጠሽ ባል ያለሽ መውደድ፣ ስሜትና ፍቅር እጅግ ኃያል ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይህ ሰው አሁን የሕይወትሽ ዓይን፣ የልብሽም ደስታ ነውና፡፡

እግዚአብሔርን እንደምትወጂው፥ ባልሽንም ያለ ቅድመ ኹኔታ ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ አንቺ ሴት እንደ ኾንሽና ታላቅ የኾነ ዓላማና ግብ እንዳለሽ፥ ኾኖም ዓላማሽና ግብሽ የቤትሽ ራስ ሊኾን ከሚገባው ባልሽ የተለየ እንደ ኾነ ዕወቂ፤ ተረጂም፡፡ ባንቺ ዕድሜ ላይ ያሉት አንዳንዶች ኹለቱም ፆታዎች እኩል [ራስ ናቸው] ብለው የሚሰብኩትን አትስሚ፤ የጋብቻንም ግዴታ [ወይም ዋና ዓላማ] አስቢ፡፡ እነዚህን ግዴታዎች [ወይም ዓላማዎች] ስታውቂ የቤተሰብሽን ተግባራት ለማከናወን እንደ ምን ያለ ትዕግሥትና ጽናት እንደሚያስፈልግሽ ታውቂያለሽና፡፡ እንደ ሚስት እጅግ ጥንካሬን ገንዘብ የምታደርጊውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

“ወንዶች እንዴት በቀላሉ የሚቈጡ መኾናቸውን በርግጥ ልታውቂ ይገባሻል፡፡ አይችሉም፤ ብዙ ጊዜም እንደ በረኻ አንበሳ ይኾናሉ፡፡ እንግዲህ ሚስት ጸንታ ልትቆምና የነፍስ ልዕልናዋን ልታሳይ የሚገባት በዚህች ቅጽበት ነው፡፡ አንበሳን የማስለመድ ሥራ መሥራት አለብሽ፡፡ አንበሳን የሚያስለምድ ሰው አንበሳ ሲያገሳ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝም ጸጥ ይላል፡፡ በጸጥታውና በርጋታውም የአንበሳውን ቊጣ ይቈጣጠራል፡፡ በርጋታና በለሆሳስ ኾኖ ያናግረዋል፤ ይደባብሰዋል፤ በቀስታ ያሻሸዋል፤ በጥቂት በጥቂቱም አንበሳው ቊጣውን ይተዋል፡፡

ባልሽ ስሕተት ሲሠራ በፍጹም ልትነቅፊው፣ ልትንቂው ወይም ልታስነውሪው አይገባም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ መሥራት ያለበትን ነገር ባይሠራና ከዚሁ የተነሣም ውጤቱ ደስ የማያሰኝ ቢኾን፣ ወይም እጅግ የምትፈልጊውና አግባብ ነው ብለሽ የምታስቢውን ባያደርግ እንኳን ባልሽን መናቅ ከአንቺ ልታርቂ ይገባል፡፡ ክፉዎች አጋንንት ዘወትር ቤታችሁን ለማፍረስና የጥንዶች መንፈሳዊ አንድነትን ለመበተን እንደሚሞክሩ ዕወቂ፡፡”

(ከገብረ እግዚአብሔር ኪደ ከትንሿ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ የተወሰደ)

5.9k 0 194 4 160

አንድ ደቂቃ ወስደው ያንብቡት ድንቅ ምክር ነው
(ለሌሎች ያጋሩት)

በሠርጉ ዋዜማ እናት ወንድ ልጇን ምን አለችው?


የኔ ልጅ አሁን አንተ ትልቅ ሰው ነህ። ነገ ሌላ እናት ታገኛለህ አዲስ ሰው ምግብህን ያበስላል ምስጢርህን ይካፋላል እኔ ከእንግዲህ ይህንን አላደርግም አዲሷን እናትህን ውደዳት። እሰከመጨረሻው በእጆቿ ላይ ከመተኛትህ በፊት ምክሬን ልስጥህ!

አንድ ቀን ከአባትህ ጋር እየተነጋገርን ነበር በጣም በስሜት ሆነን እንጯጯህ ነበር በቁጣ ስሜት ውስጥ ሆነን ሳላ እኔ በድንገት አንተ የማትረባ ስለው በጣም ተሸማቀቀ ወደ እኔ እየተመለከተ እንዴት እንደሱ ትያለሽ ? ሲለኝ ቀበል አድርጌ አዎ አንተ የማትረባ ሞኝ እብድ ብዬ ያለ የሌለውን የስድብ ናዳ አወረድኩበት ታድያ እሱ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ? እሲቲ ገምት? ሊደበድበኝ ይችል ነበር ግን እጆቹን ሳያነሳ ምንም ሳይለኝ መዝግያውን አላትሞ ወጥቶ ሄደ።

ልጄ አባትህ ቢመታኝና ፊቴን ቢያበላሸው አንተ ዛሬ በተበላሸው ፊቴ ታዝንብኝና ታፍርብኝ ነበር እሱንም እንደ አባት አትቆጥረውም ሁሌ ታዝንበት ነበር የምትኮራበት አባት አይሆንህም ነበር።

ልጄ ሚስትህን እንዳትመታት! ብትሰድብህም ብታዋርድህም ከአጠገቧ ለግዜው ዞር በል ኋላ ላይ ነገሮች ይስተካከላሉ። እንግዲህ ሚስትህ ስታበሳጭህ ይህንን የእኔን ታሪክ አስታውስ!

ካቋረጥኩበት ልቀጥል...... ልክ ብቻየን ትቶኝ እንደሄደ ስለሰደብኩት በጣም ፀፀተኝ .. ታድያ የተጣላን ቀን ምሽት አንድ አልጋ ላይ አብረን አደርን በሚቀጥለው ቀን ማድረግ የሚገባኝን ሁሉ አድርጌ ይቅርታ ጠየኩት እርሱም ተቀበለኝ .. ታድያ የዛን ቀን ምን አደረኩ መሰለህ የሚወደውን ምግብ አዘጋጅቼ ስሰጠው ደስ እያለው በላ ካዛ ቀን በኋላ ከአፌ ክፉ ቃል አልወጣኝም ለእሱ ያለኝ ክብር እስር እጥፍ እየጨመረ መጣ።

አንድ በጣም አስፈላጊ ነገር ማድርግ ያለብህ ነገር አለ። ሚስትህን። በደንብ አድምጣት ጋሻና መከታ ሁናት በጭንቅ ግዜ ከጎኗሁን ጓደኞችህ ቢጠሉዋትም ያንተ ንግስት እንደሆነች አሳያቸው ታውቃለህ አጎትህ አይወደኝም ነበር አባትህ ግን ስለኔ ያለውን አሳምኖት ሓሳቡን አስለውጦት እኔን ይደግፈኝ ነበር።

ልጄ.. . አንድ ቀን አባትህ 3 ሰዎች ወደ ቤት ጋብዟቸው ነበር አንደኛው የስራ አለቃው ሲሆን ሁለቱ ጓደኞቹ ነበሩ ምግብ አብስዬ ሁሉን አሟልቼ ካቀረብኩ በኋላ አንድ ነገር ረሳሁ ጨው አልጨመርኩም ነበር በጣም አፈርኩኝ አባትህ ወድያው ምግቡን እንደቀመሰ ወደኔ ተመልክቶ ወደ እነሱ ዞር አለና በጤና እክል ምክንያት ከወር በፊት ምግብ ውስጥ ጨው እንዳትጨምር አዝዣት ነበር ብሎ ሲስቅ ሁሉም ሳቁና እባክሽ ጨው ስጭን ብለው ሁሉም እንደፍላጎቱ ጨምረው ተመገቡ።

እንግዶችም በሄዱ ግዜ ተንበርክኮ ጌታ ሆይ ስለዋሸው ይቅር በለኝ አለ።

ሚስትህ ልክ እንደ ህፃን ናት አንዳንዴ ምን ማለት ወይም ማድረግ እንዳለባት አታውቅ ይሆናል ነገር ግን ተነስተህ ስለ እሷ ስትል ተናገርላት።

ልጄ.. . ስለ ግብረስጋ ግኑኝነት ልንገርህ.. .ወሲብ ጥሩ ነገር ነው።ሚስትህ በወሲብ የምትደሰተው ካንተ በላይ ከሆነ አይግረምህ። ታውቃለህ አንዳንድ ቀን እኔን በጣም ያስፈልገኛል እሱ ግን እስከዚህም ይሆናል ሌላ ግዜ ደግሞ እሱን በጣም ያስፈልገዋል እኔ ግን እስከዚህ እሆናለው... አንድ ማውቅ ያለብህ ነገር እራስ ወዳድ አትሁን አንደኛው ሌላኛውን መረዳት አለበት።

አስቸጋሪ ግዜያት ይመጣል አባትህን ለመደገፍ ስል ሁለት ቦታ ስራ እሰራ ነበር  ታድያ አንድ ቀን ምሽት በጣም ደክሞኝ ወደ መኝታ ክፍል ሳመራ እሱ በጣም ተነቃቅቶ ጠበቀኝ ግን አልተቃወምኩም ቢደክመኝም ፍላጎት እንዳለው ሰው ሆንኩለት ነገር ግን እንደጠበቀው ስላልሆንኩለት ፊቴን አይቶ በመረዳት ምን ሆነሻል? አለኝ ምንም አልኩት ከዚያ ስለተረዳኝ እቅፍ አድርጎ የመኝታ ታሪኮችን/bed time story/ እየነገረኝ እንቅልፍ ወሰደኝ ... ወሲብ የሁለት ሰው የእዕምሮና የአካል ዝግጁነት ይጠይቃል። አንዳንዴ ሚስትህን በደንብ ተመልከታትና ተረዳት።

ልጄ.. .ከሚስትህ ጋር የትም መሄድ ልማድ አድርገው ከስራህ ውጭ ሰትሆን ከሚስትህ ጋር አሳልፍ አንድ ሰው ከሚስትህ ውጭ ብቻህን ቤቱ እንድትመጣ ከጋበዘህ ተጠንቀቅ ብልህ ሁን።

እኔን እንደምትወደኝ ችግሮችህን እንደምትነግረኝ አውቃለው አሁን ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሮአል። ከነገ በኋላ ሚስትህ ሁሉንም ነገር ማወቅ አለባት። ከእሷ ጋር ስትጋጭ ወድያው ወደኔ አትሩጥ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ታገሳት ከዚያ ነገሩ ጋብ ሲል ተነጋገሩ ፀልዩበት ስለ እሷ ለሌላ ሰው ለማንም አትናገር ።

በመጨረሻም በየወሩ ከሚስትህ ጋር እየመጣችው ጠይቁኝ ጥሩ ትዳር እንደሚኖርህ ተስፋ አደርጋለው አንተ ምርጥ ልጄ ነህ እግዚአብሔር ይባርክህ ወደ ፈጣሪ ፀልይ ሁሌም የእርሱን እርዳታ እሻ!!

(Anani Moti)

5.9k 0 200 4 218

ተወዳጆች ሆይ! ሌላ ሰው አደረሰብኝ የምትሉት ጉዳት ምንድነው? ተቆጥቶ ሰደበኝ፤ ያለ ስሜም የሆነ ስም ሰጠኝ የሚል ነውን? ታዲያ ይኼ ምን ጉዳት አለው? በፍጹም ጉዳት የለውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ጉዳቶች ሳይሆኑ ትዕግሥተኞች ከሆናችሁ ጥቅማቸው የበዛ ነውና፡፡ ሲጀምር በእናንተ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚፈልገው ሰው የሚያደርገውን አያውቅም፡፡ የሚያደርገው ሁሉ ወዶና ፈቅዶ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እናንተን የጐዳ ቢመስለውም ራሱን እየጐዳ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ችግር ጐጂውና ተጐጂው ማን መሆኑን ለይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ምክንያቱም ይኼንን ለይተን ብናውቅ ኖሮ ራሳችንን ለመጉዳት ባልተነሣሳን ነበር፤ ሌሎች ክፉ ይደርስባቸው ዘንድ ባልጸለይን ነበር፤ ማንንም መጕዳት እንደማንችል በገባን ነበር፡፡ ትልቁ በደል ደግሞ ክፉን መቀበል ሳይሆን በሌሎች ላይ ክፉትን መፈጸም ነው፡፡

ስለዚህ ከዛሬ ጀምራችሁ ሌላ ሰውን በድላችሁ ከሆነ ራሳችሁን ውቀሱ፤ ሌላው ክፉ አድርጐባችሁ እንደሆነ ግን ለእናንተ ያደረገው ነገር መልካም ነውና ጸልዩለት፡፡ ምንም እንኳን ሰውዬው እናንተን ለመጥቀም ብሎ ያደረገው ባይሆንም በመታገሣችሁ ግን ትልቅ ጥቅምን ታገኛላችሁ፡፡ ክፉ አደረገብኝ የምትሉት ሰውዬ ድርጊቱ ክፉ እንደሆነ ሰዎችም የእግዚአብሔር ቃልም ይፈርዱበታል፤ እናንተ ግን እንዲህ ስትታገሡ ለጊዜው ምንም የተጐዳችሁ ቢመስላችሁም ጌታ እንደተናገረ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነው።

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

6k 0 110 1 170

"እስኪ ከእኔ ጋር ሆናችሁ ቅዱስ ዳዊት ምን ያህል እግዚአብሔርን ከልቡ ይወደው እንደነበር እናስተውል። ቀን ቀን ያስባቸው ዘንድ ግድ የሚሉት የመሪዎች፣ የአዛዦች፣ የመንግሥታቱ፣ የሕዝቡ፣ የሠራዊቱና ስለ ጦርነት ውሎዎቹ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ ፖለቲካውና በቤቱ ውስጥ ወይም ከቤቱ ውጪ ወይም በጎረቤቶቹ ዘንድ ስላለው ችግር ማውጣት ማውረዱ ልቡን ከፍለው ይወስዱበታል።

በዕረፍት ጊዜው እያንዳንዱ ሰው ለመኝታው የሚጠቀምበትን ሰዓት እርሱ ደግሞ ለንስሐ ለጸሎትና ዕንባውን ለማፍሰስ ይጠቀምበታል፡፡ እንዲህ ያለ ተግባሩን የሚፈጽመው ዛሬን አድርጎ ነገን ሳያደርግ አይደለም። ወይም ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት ሌሊት በማለፍ አይደለም፤ በእያንዳንዷ ሌሊት እንጂ፡፡ «ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፣ መኝታዬንም በዕንባዬ አርሳለሁ።» የሚለው ቃል የዕንባውን ብዛትና ዕንባው አለማቋረጡን ይገልጽልናል፡፡

እያንዳንዱ ፀጥ ባለ ዕረፍት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ እርሱ ግን እግዚአብሔርን ብቻውን አግኝቶ ለዕንቅልፍ ባልተከደኑ ዓይኖቹ ያለቀስና ያዘነ የግል ኃጢአቶቹን ይነግረዋል፡፡ አንተም ብትሆን እንዲህ ዓይነቱን አልጋ ለራስህ ታበጅ ዘንድ ይገባሃል። በወርቅና ብር ተከበህ መተኛት ከሰዎች ቅናትን ከአርያም ደግሞ ቁጣን ይቀሰቅስብሃል፡፡ እንደ ዳዊት ያለ ዕንባ ግን የሲዖልን እሳት ያጠፋል፡፡

ሌላ አልጋ ደግሞ ላሳይህን? ይህ አልጋ የያዕቆብ ነው። ለስውነቱ ባዶ መሬትን ለትራሱ ደግሞ ድንጋይን የተጠቀመበት አልጋ! ይህ በመሆኑም ያን መንፈሳዊ ድንጋይና ያቺን መላእክት ሲወጡባትና ሲወርዱባት የነበረችውን መሰላል ሊመለከት ችሏል፡፡ (ዘፍ 28፣ ከ1ኛ ቆሮ 10፥4 ጋር አዛምድ፡፡) በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ድንጋዮች ለክርስቶስ ምሳሌ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ እኛም እንዲህ ያሉ ሕልሞች እናይ ዘንድ ሕሊናችንን እንደዚህ ባሉት አልጋዎች ላይ እናሳርፍ፡፡ ነገር ግን ከብር በተሠሩ አልጋዎች ላይ ብንተኛ ደስታን ብቻ ሳይሆን የምናጣው ችግርንም እንጋፈጣለን፡፡

እጅግ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ እኩለ ሌሊት አንተ በአልጋህ ውስጥ ተኝተህ ሳለህ ድሀው ሰው ግን በጭድ ክምር ላይ በደጅህ ወድቆ በብርድ እየተንቀጠቀጠና በረሀብ እየተገረፈ ተዘርግቷል:: አንተ ከስዎች ሁሉ ልበ ደንዳና ብትሆን እንኳ ለዚህ ለድሀ የሚገባውን ሳታደርግለት ለራስህ አላስፈላጊ ምቾቶችን መፍቀድህ እርግጠኛ ነኝ ራስህን እንድትረግም ያደርግሃል። «የሚዘምተው ሁሉ ለጦር ያስከተተውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ትዳር በሚገኝበት ንግድ ራሱን አያቆላልፍም።» (2ኛ ጢሞ. 2፥4) ተብሎ ተጽፏልና፡፡

አንተም መንፈሳዊ ወታደር ነህ፡፡ እንዲህ ያለ ወታደር ደግሞ በመሬት ላይ ይተኛል እንጂ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ አይተኛም፤ እጅግ ያማረ ሽቶም ኣይቀባም፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር በመድረክ ላይ እየተወኑ በግድ የለሽነት ከሚኖሩና ከጋለሞታ ሴቶች ጋር ጊዜያቸውን በማባከን የሚኖሩ የምግባረ ብልሹ ሰዎች ተግባር ነው፡፡ የእኛ ጥሩ መዓዛ ግን ሽቱ ሳይሆን መልካም ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በሽቱ መዓዛ ከሚመጣው ጠንቅ የበለጠ ነፍስን የሚያቆሽሽ ነገር አይኖርም፡፡ በአብዛኛው አፍአዊ (ውጪያዊ) መልካም መዓዛ የሰው ውስጣዊ ማንነት ማደፍና መቆሸሽ ምልክት ነው፡፡

ዲያብሎስ ነፍስን በራስ ወዳድነት ተዋግቶ ሲያሸንፋትና በታላቅ ከንቱነት ሲሞላት አስቀድሞ አቆሽሾት ወይም አጉድፎት ወይም አበልዞት የነበረውን ሰውነት በሽቶ ያጸዳዋል:: ልክ በጉንፋን እንደተያዙና ያለማቋረጥ በአፍንጫቸው የሚወጣውን ፈሳሽ ለማጽዳት ልብሳቸውን፣ እጆቻቸውንና ፊታቸውን እንደሚያጎድፉ ሁሉ እንዲህ ያለው የክፉ ስው ነፍስም ሰይጣን በሰውነቱ ላይ ያፈሰሰበትን ኃጢአት ለማጽዳት ይሞክራል፡፡ ሽቶ ሽቶ ከሚያውድ፣ ከጋለሞታ ጋር ወዳጅነት ከመሠረተ፣ የዳንኪረኛነት ሕይወትን ከሚመራ ሰው ማን ጨዋና መልካም ነገርን መጠበቅ ይችላል? እስቲ ነፍስህ መንፈሳዊ መዓዛን ትተንፍስና ለአንተም ሆነ ለወዳጆችህ ታላቅ በረከትን ታድላቸው፡፡"

(ሀብታምና ድሀ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደሰበከው -ገጽ 21-23 አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው)

7.2k 0 96 4 137



አንተ ሰው እስኪ ንገረኝ!

አንድን የሥጋ ቁስል ለመፈወስ ለእያንዳንዱ ሰው ከባድ ነው፤ የነፍስን ቁስል መፈወስ ግን ለኹሉም ቀላል ነው፡፡ የሥጋ ቁስል ለመፈወስ መድኃኒት ብሎም ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ነፍስን ለመፈወስ ግን ቀላል ብሎም ወጪን የማይጠይቅ ነው፡፡ ሥጋን ከዚያ ከሚያሰቃይ ቁስሉ ለመፈወስ አድካሚ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀዶ ጥገና ምላጭ መቀደድ አለበት፤ መራራ መድኃኒቶችም ሊጨመሩበት ይገባል፡፡ ነፍስን ለመፈወስ ግን እንዲህ ዓይነት ነገር አያስፈልግም፡፡ ፈቃደኛ መኾን ብቻ በቂ ነው፤ ፍላጎቱ ካለ ኹሉንም ነገር ለማድረግ ቀላል ነው፡፡ የእግዚአብሔር መግቦቱም እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው፡፡ ሥጋ ቢቆስል ያን ያህል ከባድ ጉዳትን አያመጣብንም፤ ምክንያቱም ምንም ባንታመምም እንኳን ሞት መጥቶ ይህን ሥጋችን ያፈርሰዋል፤ ያበሰብሰዋልምና፡፡ ነፍሳችን ብትታመም ግን ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ እግዚአብሔር የነፍስን ሕመም ለመፈወስ መድኃኒቱ ቀላል፣ ምንም ወጪና ስቃይ የሌለበት ያደረገውም ስለዚሁ ነው፡፡ ታዲያ ምንም እንኳን በሕመሙ ምክንያት የሚያገኘን ጉዳት ያን ያህል ብዙ ባይኾንም የገንዘብ ወጪን የሚጠይቀው፣ ሐኪም የሚያስፈልገው፣ ብዙ ስቃይ ያለበት ሥጋችን ሲታመም እርሱን ለማከም እጅግ የምንደክም ኾነን ሳለ፥ እጅግ ብዙ ጉዳት የሚያመጣውን፣ እርሱን ለመፈወስ ወጪ የማይጠይቀውን፣ ለማስታመም ሌሎች ሰዎች የማያስቸግረውን፣ እንደ ምላጩና እንደ መራራ መድኃኒቱ ስቃይ የሌለበትን ይልቁንም ከእነዚህ አንዱስ እንኳን ሳይፈልግ በእኛ ኃይል ባሉ ምርጫና ፈቃድ ብቻ መዳን የሚችለውን፣ ይህን ማድረግ ሳንችል ስንቀርም ከባድ ፍርድና ቅጣት ስቃይም እንደሚያገኘን በእርግጥ እያወቅን የነፍሳችንን ቁስል ችላ የምንል ከኾነ ሊደረግልን የሚችል ምሕረት እንደ ምን ያለ ምሕረት ነው? እኮ የምናገኘው ይቅርታ እንደ ምን ያለ ይቅርታ ነው?

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ - ትምህርት በእንተ ሐውልታት መጽሐፍ #በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ የተተረጎመ)

14.2k 1 169 7 148


8.1k 0 110 7 335

"የህይወት እናት ድንግል ማርያም ሆይ ትንሳኤሽ ሳይሆን ሞትሽ ይደንቀኛል፤ እርገትሽ ሳይሆን ወደ መቃብር መውረድሽ ይገርመኛል፤ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ሆይ ትወጂኛለሽን? ብየ አልጠይቅሽም ፍቅርን የወለድሽ አንቺ ለአለሙ ሁሉ ፍቅርሽ የበዛ ነውና፤ አትናፍቂኝምን? ብየም አልጠይቅሽም ዘወትር እኔን ለመጠበቅ ከጎኔ እንደማትለይ አውቃለሁኝና፤ ሆኖም እመቤቴ ሆይ፦ እንደ ቶማስ አይሽ ዘንድ በእጅጉ እጓጓለሁ የቶማስ ንፅህናና ቅድስና ግን የለኝም እንደ ዮሃንስ ከጎንሽ ልሆን እጓጓለሁ የዮሃንስ ፀጋ ግን የለኝም።

እናቴ ሆይ፦ እንደ ኤልሳዕ የልቦናዬ አይን በርቶ ሰማያዊ ክብርሽን ላይ አልተቻለኝምና አዝናለሁ ኤልሳዕ በፀሎት ሃይል የግያዝን አይን እንዳበራ አንቺም አይኔን ታበሪልኝ ዘንድ ሃይልሽን በእኔ ላይ አበርቺ፡፡


ድንግል ሆይ፦ ይህን የምል የእምነት ማረጋገጫ ፈልጌ አይደለም በልጅሽ መሰረትነት የታነፅኩኝ በልጅሽ ስምም የተጠመቅኩኝ ነኝና፤ ነገር ግን ስለምትናፍቂኝ ይህን አልኩኝ ስለዚህም ነይ ነይ እምየ ማርያም እያልኩኝ እንደ እናቶቼም እለምንሻለሁ፡፡ የብርሃን ልብስሽን ለብሰሽ ነይ የክብር አክሊልሽን ደፍተሽ ነይ አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ነይ እናይሽ ዘንድ ነይ፡፡"

11.2k 1 139 11 330

አበው ስለ #እመቤታችን_ዕረፍት እንዲህ አሉ፦

"ሌሎች በድንግልና የኖሩ ሴቶች "ለሞት የሚሆኑ ልጆችን አንሰጥህም" በማለት ሞትን ተቃወሙት፡፡ ድንግል ማርያም ግን አንድ ልጅ በመውለድ በልጅዋ ሞት ራሱ እንዲሞት አደረገችው፡፡ ከዐለት ጋር እንደተጋጨ የተፈረካከሰው በማሕፀንዋ ፍሬ ነውና ሞት ወደ እርስዋ ሲቀርብ ተብረከረከ።"
#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘኑሲስ

"ልጃቸው ተሰብስበው ወዳሉበት መጥታለችና አዳምና ሔዋን ዛሬ ደስ አላቸው። በዚህች ቀን ታላቁ ዳዊት በራሱ ላይ የተዋበ አክሊል የደፋችለትን ሴት ልጁን አይቶ ደስ አለው። በዚህች ቀን ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት የተናገረላት ድንግል ወደ ሙታን ሥፍራ ልትጎበኘው መጥታለችና ደስ አለው። በዚህች ቀን ብርሃን ሲበራባቸው አይተዋልና ነቢያት ሁሉ ከመቃብራቸው ራሳቸውን ቀና አደረጉ። አርያም በጣፋጭ የመላእክት ዝማሬ ተሞላ፣ ምድር ደግሞ ኀዘንን በተሞሉ በሐዋርያት ለቅሶ ተሞላች፡፡ ሙታንም ሕያዋንም ትርጉሙን ሊገልጹት በማይችሉት [የተለያየ] ዜማ ሰውና መላእክት በዚያች ዕለት አብረው ጮኹ።"
#ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ

"የቃሉ አገልጋዮችና ምስክሮች የነበሩት ሐዋርያት በሥጋ የወለደችውን የእናቱን ዕረፍትና እርስዋን የሚመለከቱ የመጨረሻዎቹን ምሥጢራትም ማየት ነበረባቸው፡፡ ይህም የሆነው የክርስቶስ የዕርገቱ የዓይን ምስክሮች እንደሆኑ ሁሉ የወለደችውም እናቱ ወደዚያኛው ዓለም ለሸጋገርዋ ምስክሮች መሆን ስላለባቸው ነው።"
#ቅዱስ_ዮሐንስ_ዘደማስቆ

(በ Deacon Henok Haile የተሰበሰበ)




ስጋዋንም ያሳዪት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ስጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው። ሀዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን እርገቷን ስለ አላዩ እጅግ አዘኑ ስጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው። ከዚህም በኃላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ስጣቸው እነርሱም እስከ ነሀሴ አስራ ስድስት በረስፋ ኖሩ።

የእመቤታችንም የእድሜዋ ዘመን ስልሳ አራት አመት ነው በአባትና እናቷ ቤት ሶስት አመት ከሰባት ወር በቤተ መቅደስም አስራ ሁለት አመት በዮሴፍም ቤት ሰላሳ አራት አመት ከሶስት ወር ከጌታ እርገት በኃላ በወንጌላዊ ዮሀንስ ቤት አስራ አራት አመት ነው።

የህይወት የድኅነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በፀሎቷም ከክፉ ነገር ይጠብቀን፤ በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።

(ስንክሳር ዘተዋሕዶ - #ስንክሳር_ዘወርኀ_ጥር)

10k 0 85 4 78

#በዓለ_አስተርዕዮ_ማርያም - #ጥር_21
ጥር ሀያ አንድ በዚች ቀን አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም የእረፍቷ በአል መታሰቢያ ነው። ያን ጊዜ እመቤታችን በልጅዋ በጌታችን በፈጣሪያችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከበረ መቃበሩ ቦታ ትፀልይ ነበረ ከዚህም አለም እንደምትለይ መንፈስ ቅዱስ ነገራት ከዚህም በኃላ ከደብረ ዘይት ደናግል መጡ ጌታችን ነግሮዋቸዋልና እርሷም ነገረቻቸው።

በዚያንም ጊዜ እመቤታችን እንዲህ ብላ ፀለየች፦
"ልጄ ወዳጄ ጌታዬና ፈጣሩዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናዬን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሀንስን በዚች ሰአት አምጣው።እንዲሁም ህያዋን እንደሆኑ ሀዋርያትን ሁሉንም ነፍሳቸውንም የለየሀቸውን አምጣቸው አንተ የህያዋንና የሙታን አምላክ ነህና ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

በዚያንም ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ከኤፌሶን አገር ዮሀንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ማርያም አደረሰችው ሰገደላትና በፊቷ ቁሞ እንዲህ አላት ሰላምታ ይገባሻል ጌታችንን ፈጣሪያችንንና መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለድሺው ፀጋን የተመላሽ ደስ ይበልሽ አንቺ ከዚህ አለም ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘላለም ህይወት ትሄጂአለሽና። ይህም ስሙ ክብር ምስጉን የሆነ ጌታችንና ፈጣሪያችን ድንቆች ተአምራቶችን በአንቺ ላይ ከገለጠ በኃላ ነው።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላትእግዚአብሄርንም እንዲህ ብላ አመሰገነችው ፈጣሪዬ ጌታዬ ላንተ ምስጋና ይሁን አንተ የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና አሁንም ነፍሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊአሳርጓት ከሚመጡ መላእከቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ።

በዚያንም ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ቃል መጣ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ ሀዋርያትም ሁሉ ከምድር ዳርቻ በደመና ተጭነው ለሰማይና ለምድር ጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ወደ ሆነች ወደ ቅድስት ድንግል ይደርሳሉ።

ወዲያውኑ ሁሉም ሀዋርያት የሞቱትም ከመቃብራቸው ተነስተው ወደ እመቤታችን ደርሰው ሰገዱላት አምላከችን ከአንቺ የተወለደ ፀጋን የተመላሽ ሆን ደስ ይበልሽ እርሱ ከዚህ አለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት።

በዚያንም ጊዜ እመቤታችን በአልጋዋ ላይ ተቀመጠች ሀዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው ፈጣሪዬ ፈጣሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኃችሁ እንደማየው አሁን አውቅሁ ከዚህ ከስጋዬም ወጥቼ ወደዘላለም ህይወት እሄዳለሁ ነገር ግን ትነግሩኝ ዘንድ እሻለሁ ከዚህም አለም እንደምለይ ከወዴት አወቃችሁ ።

ጴጥሮስና ሐዋርያት ሁሉም ወዳንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን በደመና ላይም በተጫን ጊዜ ወዳንቺ እንደ አይን ጥቅሻ ፈጥነን ደረስን አሏት።

እመቤታችንም ማርያምም ይህን ነገር ከሀዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ አለች ጌታዬና ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክቡር ምስጉን የሆነ ስምህን ፈፅሜ አመሰግናለሁ።የእኔን የአገልጋይህን መከራ ተመልክተህ ድንቅ ኃይልህን አድርገህልኛልና ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል።

ፀሎቷንና ምስጋናዋን ስትጨርስ ሀዋርያትን እንዲህ አለቻቸው እጣን አምጥታችሁ በማጠን የጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ስሙን ጥሩት እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ ።በዚያንም ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እልፍ አእላፍት መላእክት አጅበው እያመሰገኑት መጣና አረጋጋት ያዘጋጀላትንም ተድላ ደስታ ነገራት በዚያንም ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተደረገ እውሮች አይተዋልና፣አንካሶች ቀንተው ሄደዋልና ደንቆሮዎች ሰምተዋልና ለምፃሞች ነፁ አጋንንትም ከሰዎች ወጥተው ሄዱ ዲዳዎች ተናገሩ በሽታና ደዌ ያለበት ሁሉ ዳነ እመቤታችን ድንግል ማርያም ወዳለቸወበት ቤት በቀረብ ጊዜ ከደዌያቸው ይፈወሳሉና።

ከዚህም በኃላ እመቤታችን ተወዳጅ ልጅዋን እንዲህ አለችው በአየር ውስጥ ተበትነው ከሚኖሩ ከሚያስደነግጡ ግሩማን መላእክት የተነሳ ከእሳት ባህርም እፈራለሁ ጌታችንም ከእናንተ ለማንም በአለሁ ላይ ስልጣን የለውም አላት።

ከስጋዋም የምትለይበት ጊዜ ሲደርስ ሀወሰርያትና ደናግል ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኑዋት እጃዋን በላያቸው ዘርግታ ባረከቻቸው በዚያንም ጊዜ ጌታችን ንፅህት ነፍሷን ከስጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሀን ልብስ አጎናፅፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት ስጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው ወደ ጌቴሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሀዋርያትን አዘዛቸው።

ነፍሷ ከስጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሀንን እያየች ነበር የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስም እንግዲህ ስጋሽን ተድላ ወዳለበት ገነት አፈልሳለሁ ዳግመኛም ስጋሽን ከነፍስሽ ጋር አዋህጄ አስነስቼ መላእክት በውስጡ በፊትሽ ሆነው በሚያመሰግኑበት ተመሳሳይ በሌለው ተድላ ደስታ በአለበት ማደሪያ አኖርሻለሁ አላት።

እመቤታችንም እንዲህ አለች አቤቱ በረቀቀ ጥበብህ ይህን ሁሉ የሰራህ አመሰግንሀለሁ ሁለተኛም ልመናዬን ትሰማ ዘንድ እለምንሀለሁ በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሆኖ ስሜን ጠርቶ ወዳንተ የሚለምነውን ከመከራው ሁሉ አድነው በሰማይም በምድርም በስራው ላይ ሁሉ አንተ ከሀሊ ነህና መታሰቢያዬን በውስጧ የሚያደርጉትን ቦታ ሁሉ ባርክ በእኔ ስም የሚያቀርቡትን የሁሉንም መስዋእታቸውን ተቀበል።

ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰላት የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ ደስ ይበልሽ ከእኔ ከአባቴ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ፀጋ ክብር ባለሟልነት ተሰጥቶሻልና ስምሽንም ጠርቶ የሚለምን ሁሉ በዚህም አለም በሚመጣውም አለም አይጠፋም።

እመቤታችንም ከአረፈች በኃላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴሴማኒ ሊወስዷት ሀዋርያት ገንዘው ተሸከሟት። አይሁድም በሰሙ ጊዜ ስጋዋን ሊአቃጥሉ ወጡ ከእነርሱም አንዱ ከምድር ላይ ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ ያን ጊዜ ከእግዚአብሄር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋዋ ላይ ተንጠለጠሉ።

ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ ብሎ ለመነ የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ እለምንሻለሁ በሀዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደኅነኞች ሆኑ።

በቀበሩዋትም ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ እረፍቷም የሆነው እሁድ ቀን በጥር ወር በሀያ አንድ በዚች ቀን ነበረ ጌታችንም ብርሀናውያን መላእክትን ላከ እነርሱም ስጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በእፀ ህይወት ስር አኖሩዋት።

ሀዋርያ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲአሳርጓት እመቤታችንን አገኛት መላእክትም ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም ና እጅ ንሳ አሉት እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ ከዚህም በኃላ ወደ ሀዋርያት ደረሰ ። እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበርዋትም ነገሩት ቶማስም ስጋዋን እስከማይ አላምንም አላቸው።

8.4k 0 116 1 69

"...ክርስቲያኖች ግን ክርስቲያኖች ለመኾናቸው መታወቅ የሚገባቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ምሥጢራትን ሲቀበሉ ብቻ ሳይኾን የትም ቦታ በሚኖሩት የቅድስና ሕይወት ነው፡፡ በአፍአ የከበሩ ሰዎች በአፍአ ከሚያሳዩት ምልክት እንደሚታወቁ ኹሉ፥ እኛም ልንታወቅ የሚገባን በነፍሳችን ክብር ነው፡፡ በሌላ አገላለጥ አንድ ክርስቲያን መታወቅ ያለበት በተሰጠው ልጅነት ብቻ ሳይኾን ለልጅነቱ እንደሚገባ በሚያሳየው አዲስ ሕይወትም ጭምር ሊኾን ይገባል፡፡ ይህ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃንና ጨው ሊኾን ይገባዋል፡፡ ለዓለም ብርሃን መኾንህስ ይቅርና ለራስህ እንኳን ብርሃን መኾን ካልተቻለህ፣ የሚሰፋ ቁስልህን በዘይት ማሰርም ካቃተህ፥ ክርስቲያን መኾንህን የምናውቀው እንዴት ነው? ወደ ተቀደሰው ውኃ ገብተህ በመጠመቅህ ነውን? በዚህስ አይደለም ! ይህስ እንዲያውም ዕዳ ፍዳ ይኾንብሃል [እንጂ ክርስቲያን መኾንህን እንድናውቅህ አያደርገንም]፡፡ ይህ ሀብት (ልጅነት) ታላቅ ነውና ለዚህ ሀብት እንደሚገባ ለማይኖሩት ሰዎች ዕዳ ፍዳ መጨመሪያ ነው፡፡ አዎን፥ ክርስቲያን ለዓለም ብርሃኑን ማብራት ያለበት ከእግዚአብሔር በተቀበለው ጸጋ ብቻ ሳይኾን እርሱ ራሱም ድርሻውን በመወጣት ነውና፡፡ ክርስቲያን ካልኾኑት ይልቅ በኹለንተናው በአረማመዱ፣ በአተያዩ፣ በአለባበሱ፣ በአነጋገሩ ብልጫ ሲኖረው ነውና፡፡ ይህንም የምለው ልጅነትን የተቀበሉ ክርስቲያኖች ልጅነትን ተቀበሉ በመባል ብቻ ሳይኾን የሌሎች ሰዎች ረብ ጥቅም ይኾን ዘንድ ለተቀበሉት ልጅነት የሚገባና ሥርዓት ያለው ሕይወት እንዲኖሩ ስለምሻ ነው፡፡

አሁን ግን ከሌሎች ከማያምኑት ብልጫ ኖሮህ እንዳየው በምፈልገው ሕይወት፥ በኹሉም ረገድ ተቃራኒ ኾነህ አይሃለሁ፡፡ ለምሳሌ ከቦታ አንጻር፥ ቀኑን ኹሉ የፈረስ እሽቅድምድምንና ተውኔትን፣ ነውርን የተሞሉ ትርኢቶችንና የክፉዎችን ማኅበር፣ ርኵሰትንም የተሞሉ ሰዎችን ስትመለከት እንደምትውል አይሃለሁ፡፡ ከፊትህ አንጻር፥ ዘወትር ያለ ልክና እንደ አመንዝራ ሴት ስትስቅ እመለከትሃለሁ፡፡ ከአለባበስህ አንጻር፥ ከተዋንያንና ጠቢባን ነን ከሚሉ ሰዎች ምንም እንደማትለይ አስተውልሃለሁ፡፡ ከሚከተሉህ ሰዎች አንጻር፥ ብዙ ውዳሴ ከንቱንና ሽንገላን እንደምትሻ አይሃለሁ፡፡ ከንግግርህ አንጻር፥ ምንም ደኅና ነገር፣ በቁዔት ያለው ቃል፣ ለሕይወታችን የሚረባ ንግግር እንደሌለብህ አደምጣለሁ፡፡ ከማዕድህ አንጻርም ከዚያ ጽኑዕ የኾነ ወቀሳ የሚያመጣብህ እንደ ኾነ አያለሁ፡፡

ታዲያ እስኪ ንገረኝ ! ክርስቲያንን ክርስቲያን ከሚያስብሉት ነገሮች እጅግ የራቅህ ኾነህ እያለ፥ ክርስቲያን መኾንህን መለየት የምችለው በምንድን ነው? ክርስቲያን መባልህስ ይቅርና፥ ሰው ብዬ ልጠራህ የምችለውስ እንዴት ነው? እንደ አህያ ትራገጣለህና፤ እንደ ኮርማ ትሴስናለህና፤ እንደ ፈረስ ከሴቶች ኋላ ኾነህ ታሽካካለህና፤ እንደ ድብ ሆዳም ነህና ፤ ሥጋህን እንደ በቅሎ ሥጋ ትሰገስጋለህና፤ እንደ ግመል ቂም ትይዛለህና፤ እንደ ተኵላ ትነጥቃለህና፤ እንደ እባብ ትቈጣለህና፤ እንደ ጊንጥ ትናደፋለህና፤ እንደ ቀበሮ ተንኰለኛ ነህና፤ እንደ እባብ ወይም እንደ እፉኝት በጕረሮህ መርዝ አለና፤ እንደ ክፉ ጋኔን ከወንድምህ ጋር ትጣላለህና፡፡ ታዲያ ክርስቲያን የሚለውስ ይቅርና፥ በምንህ ሰው ብዬ ልጥራህ? ሰው የሚያስብል ምልክት ሳይኖርህ እንዴት ብዬ ከሰው ዘንድ ልቊጠርህ? የንኡሰ ክርስቲያኖችና የክርስቲያኖች ልዩነት ባሰብሁ ጊዜ ልዩነቱ የሰውና የአርዌ ገዳም ያህል ይኾንብኛል፡፡ ታዲያ ምን ብዬ ልጥራህ? አርዌ ገዳም ብዬ ልጥራህን? እንዲህስ አልልህም፤ ጭካኔህ ከአራዊተ ገዳም በላይ ነውና፤ [በሌላ መልኩ ደግሞ እነርሱ እንደዚያ የኾኑት ከተፈጥሮአቸው የተነሣ እንጂ እንደ አንተ ወደውና ፈቅደው አይደለምና፡፡] ታዲያ ምን ብዬ ልጥራህ? ጋኔን ልበልህን? እንዲህስ አልልህም፤ ጋኔን የሆድ ባሪያ አይደለምና፤ ፍቅረ ንዋይም የለበትምና፡፡ ታዲያ ከአራዊተ ገዳምም ከአጋንንትም የሚብስ ክፉ ግብር ከያዝህ፥ ንገረኝ - ሰው ብዬ እጠራህ ዘንድ ይገባኛልን? ሰው ለመባል እንኳን የሚበቃ ምግባር ከሌለህስ፥ ክርስቲያን ብለን ልንጠራህ የምንችለው እንዴት ነው?"

(የማቴዎስ ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተረጎመው ድርሳን 4፥14-15 ገጽ 80-82 በገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተተረጎመ)

9.4k 0 116 10 114



“ማግባት ለሚሹ”
የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ምክር

ከምንም በፊት የጋብቻ ዓላማን ማወቅ አለባችሁ፡፡ በሕይወታችን ለምን ጋብቻ እንደሚያስፈልገን መረዳት አለባችሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገርን አትጠይቁ፡፡ እናስ የጋብቻ ዓላማው ምንድነው? ለምንድነው እግዚአብሔር ጋብቻን የሰጠን? ብጹዕ ጳውሎስን እናድምጠው፤ እንዲህ ያለውን፦ "ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑሮው፤ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራሷ ባል ይኑራት" (1ኛ ቆሮ.7፥2)። "ከድህነት ይወጣ (ትወጣ) ዘንድ" ነው የሚለውን? ወይስ "ሀብት ለማግኘት ሲባል" ነው የሚለውን? አይደለም፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚለው? ከዝሙት እንጠበቅ ዘንድ፤ ራሳችንን መቆጣጠር እንችል ዘንድ፤ ንጽህናን ገንዘብ እናደርግ ዘንድ፤ በትዳር አጋራችን ደስ ተሰኝተን እግዚአብሔርን እናመሰግን ዘንድ፡፡ አያችሁ ይኼ ነው የጋብቻ ስጦታው ይኼ ነው የጋብቻ ፍሬው፤ ይኼ ነው የጋብቻ ጥቅሙ፡፡

ስለዚህ ልጆቼ! እማልዳችኋለሁ ትልቁን ጥቅም ዘንግታችሁት ዓይናችሁን በትንሹ ላይ አታሳርፉ፡፡ የትዳር አጋርን ስትመርጡ የሀብት ጉዳይ የእናንተ ትልቅ አጀንዳ ሊኾን አይገባም፡፡ ስለ ሀብት ብሎ የትዳር አጋርን መምረጥ ድንቁርና ነው፤ ሀብት ነገ ሊጠፋ ይችላልና፡፡ ስለዚህ ለትዳር የምትመርጡት ሰው ከምንም በላይ መንፈሳዊ ሀብቱን ተመልከቱ፡፡ በዚህም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ይበልጥ የሚጠቅማችሁ ይኼ ነውና፡፡

አባቶች ሆይ! አብርሃምን ምሰሉት፡፡ አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ሚስትን ሲፈልግለት፦ ሀብትን አላየም፤ የንጉሣውያን ቤተሰብን አልተመለከተም፤ አፍአዊ ውበትን መመዘኛ አላደረገም፤ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መስፈርትን አልደረደረም፡፡ የነፍስ ንጽህናን እንጂ፡፡

እናቶች ሆይ! ሴት ልጆቻችሁን እንደ ርብቃ አሳድግዋቸው፡፡

እናንተ ማግባትን የምትሹ ወጣቶች ሆይ! ይስሐቅን ምሰሉት፦ ዘፈንን፣ ዳንኪራን፣ ሳቅና ስላቅን፣ የከበሮንና የዋሽንት ጫጫታን፣ ሌላውንም የዲያብሎስ ትርኢት በሰርጋችሁ ቀን አታስቡ፡፡ ከዚህ ይልቅ በምታደርጉት ኹሉም ላይ እግዚአብሔር እንዲቀድማችሁ ለምኑት፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ትዳራችሁ ፍቺ፣ ዝሙት፣ ቅናት፣ ጭቅጭቅ፣ ንትርክ የሌለበት ኾኖ ይፀናላችኋል፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ፥ ሌላው በረከትም ተትረፍርፎ ይመጣላችኋል፡፡ የአውሎ ነፋስ ዓይነት በዙሪያችሁ ቢነፍስም፥ አትነዋወፁም፡፡

እናንተ ልጃገረዶች ሆይ! ርብቃን ምሰሏት፡፡ የትዳር አጋራችሁን ፍጹም ለማፍቀር የተዘጋጃችሁ ኹኑ፡፡ ይህን ያደረጋችሁ እንደኾነ ቤታችሁ ፍጹም ሰላማዊ ባሎቻችሁ የምትልዋቸውን የሚያደርጉና በፍቅራችሁ የሚንበረከኩ ይኾናሉ፡፡ ትዳር እንዲህ ኾኖ ሲጀመር፥ እግዚአብሔርንና ወላጆቹን ደስ የሚያሰኝ ልጅ ይገኝበታል፡፡

የቤት ዕቃዎችን መግዛት ስንፈልግ፥ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ የሻጮቹን ማንነት አይተን፣ የዕቃዉንም ጥንካሬ አገላብጠን ተመልክተን ነው የምንሸምተው፡፡ ሚስት ስናገባም ከዚህ የበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የገዛነው ዕቃ ችግር ቢኖርበት ለሸጠልን ሰው መመለስ እንችላለን፡፡ ሚስት ስናገባ ግን ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ አንችልም፤ እስከ ዕድሜአችን ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ነው የምትኾነው፡፡ ክፉ ናት ብለን ብንመልሳት፥ በሕገ እግዚአብሔር መሠረት አመንዝራ እንኾናለን፡፡ ስለዚህ፥ ሚስት ስትመርጡ የሀገራችሁን ሕገ መንግሥትን ብቻ አታንብቡ፤ ከኹሉም በፊት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አንብቡ እንጂ፡፡

12.4k 1 452 18 381

"የወንድምህን ኃጢአት መሸፈንና የእርሱን ኃጢአት እንደራስህ አድርግህ በእርሱ ፋንታ መሞት ካልቻልክ ቢያንስ ስለ ኃጢአቱ አትፍረድበት።››

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

10.8k 0 189 2 290

ሸጋ መልዕክት አላት፦

አባት ልጁ ከቤት ወጥቶ መኪና እንዳይገጭበት፣ ወድቆ እንዳይሰበርበት፣ ድንገት በአከባቢው የሚያልፉ ከብቶች ገፍተው እንዳይጥሉበት መውጫው በሩን ይዘጋበታል፡፡ ይኼኔ ልጁ በሩ ለምን እንደተዘጋበት አያውቅም፤ ልጅ ነውና፡፡ አባቱ የጠላው መስሎትም ምርር ብሎ ሊያለቅስ ይችላል፡፡ ማልቀስ ብቻ አይደለም፤ ቂምም ሊይዝበት ይችላል፡፡ አባቱ ግን በሩን የዘጋበት ምክንያት ያውቃል፤ ጠልቶት ሳይሆን ይጐዳበታልና ልጁ ቢያለቅስም አይከፍትለትም፡፡

እውነተኛው አባታችን እግዚአብሔርም አንዳንድ ጊዜ የማይጠቅሙን ይልቁንም ክፉኛ ሊጎዱን የሚችሉ በሮችን ይዘጋብናል፡፡ ከእውቀት ከፍለን የምናውቅ ልጆቹ ነንና አባታችን ለምን እንደዘጋብን ለጊዜው አይታወቀንም፤ ብቻ የከለከለን ይመስለናል፡፡ በመሆኑም ቂም ልንይዝበት ልናማርረውም እንችላለን፡፡ እርሱ ግን ይታገሠናል፤ ለእኛ የሚያስባት መልካሚቱን በር እርሱ ያውቃታልና ይከፍትልናል፤ በእኛ እይታ መልካም የምትመስለንን ነገር ግን ክፉይቱን በር ይዘጋብናል፡፡

ቅዱስ አባት ሆይ ስለ ከፈትክልን ብቻ ሳይሆን ስለ ዘጋህብንም በር እናመሰግንሃለን፡፡ አሜን!

10.2k 0 150 5 323

የቤተክርስቲያንን መብትና ጥቅም ለማስከበር እና የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በጥብቅ እየተሰራ ነው።

ጥንታዊት፣ታሪካዊትና ዓለም አቀፋዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለማስፋፋት በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሌሎችን መብትና ጥቅም ባለመንካት በትዕግሥትና በማስተዋል የምትጓዝ አገራዊ ኃላፊነት የሚሰማት ሰላምን አብዝታ የምትሰብክ መንፈሳዊት ተቋም መሆኗ ይታወቃል።

ቤተክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮቷን ለማስፋፋት በተጓዘችባቸው አያሌ ዓመታት አገራችን ኢትዮጵያ የራሷ ፊደላትና የራሷ የቀን አቆጣጠር ባለቤት እንድትሆን ያስቻለች፣በሊቃውንቶቿ የመጠቀ እውቀት አማካኝነት የሥነ ጥበብ፣የሥነ ስዕል፣የዕጽዋትና የጠፈር ምርምርና ጥናቶችን በማከናወን ተጨባጭ ውጤቶችን ለዓለም ያበረከተች ጥንታዊት ተቋም ስለመሆኗም አያሌ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።

ይሁን እንጂ ይህች ለአገረ መንግስት መመስረትና መጽናት፣ለእውቀት መስፋፋት፣ ለአብሮነት መጎልበት፣ ትውልድን በሥነ ምግባር ቀርጻ ፍቅርና አንድነትን በተግባር የሰበከች እናት ቤተክርስቲያን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ አካላት መብትና ጥቅሟን የሚነኩ፣ በአስተምህሮቿ፣ በዕምነቷ፣ በንዋያተ ቅድሳቶቿ ላይ መሰረታቸውን ያደረጉና ትዕግስቷን የሚፈታተኑ ክብርና ሉአላዊነቷን የሚዳፈሩ እኩይ የትንኮሳ ተግባራት እየተፈጸመባት ይገኛል።

ስለሆነም በተደጋጋሚ እየተፈጸሙባት የሚገኙትን እነዚህን እኩይ ተግባራት ከዚህ በላይ በዝምታና በትዕግስት ማለፍ መንፈሳዊ ተልዕኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ የሚያደርጋት ከመሆኑም በላይ መብቷን በእጅጉ የሚጋፋ፣ጥንታዊያን አባቶች ለሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚያ ሲጠቀሙባቸው የነበሩና በትውልድ ቅብብሎሽ አሁን ያለው ትውልድ የተረከባቸው ንዋያተ ቅድሳቶቿን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ከመፈጠሩም በላይ በሥርዓተ አምልኮዋ ላይ በማላገጥ በምዕመናን ዘንድ ቁጣ እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት እየተፈጸሙ በመምጣታቸው ምክንያት እነዚህ እኩይና ጸብ አጫሪ ተግባራት ሕጋዊ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ የግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።
 
ስለሆነም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ ማጥናት፣መከታተልና ሕግን መሰረት ያደረገ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድግ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘችው ወቅታዊ ሁኔታውን በዝርዝር በማጥናት ተቋማዊ እልባት የሚያገኝበትን መንገድ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ ያደረገች ሲሆን የቤተ ክርስቲያናችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕግ አግባብ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ፍትሕ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊውን መረጃ በማሰባሰብና በማደራጀት ክስ መመስረት የሚያስችለውን ሁኔታ በማመቻቸት ወደ ተግባር ለመለወጥ በዝግጅት ላይ  ይገኛል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ከፍ ሲል እንደተገለጸው በጠቅላይ ቤተክህነት ከሚገኙ መምሪያዎች መካከል ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን መምሪያዎች በማካተት የተቋቋመው ኮሚቴም ዝርዝር ጥናቶችን በሚገባ በማጥናትና ችግሮቹን ለይቶ ከመፍትሔ ሀሳብ ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ በማቅረብ በቤተክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር አማካኝነት ተቋማዊ አቋም የሚወሰድበትና በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የማያዳግም መፍትሔ የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን እየገለጸች በሁለቱም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ በተከታታይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲገለጽ የምታደርግ መሆኑን ከወዲሁ እያስታወቀች በጉዳዩ ዙሪያ ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ ምዕመናንና ምዕመናት በተቋቋመው ኮሚቴ አማካኝነት የሚደረግላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለቤተክርስቲያናችን መብት መከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እናት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታቀርባለች።

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
      መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
                 አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
            ጥር ፲፯ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም

(ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን)

20 last posts shown.