ቅምሻ - ፩
አሐቲ ድንግል - አንዲት ድንግል ድንግል ማርያም ለምን አንዲት ድንግል ትባላለች?እመቤታችን ድንግል ማርያም በምድርም በሰማይም አቻ የማይገኝላት አንዲት ድንግል ናት። ከኪሩቤል የምትበልጥ ከሱራፌልም የምትልቅ በራሷ ላይ ትእምርተ መስቀል ያለው አክሊልን የተቀዳጀች በወንጌል የተፃፈች አንዲት ድንግል አለች። ይላል ቅዱስ ያሬድ።
ከዚህም ተነስቶ አንድ ሰው ተነስቶ በወንጌል ሌሎች ደናግል የሉምን? ስለምን በወንጌል የተጻፈች አንዲት ድንግል ትላለህ? ብሎ ቢጠይቀው ከኪሩቤል የምትበልጥ ከሱራፌል የምትበልጥበት የድንግልና ዘውድ ያላት አንዲት ድንግል አልኩህ እንጂ ደናግላንማ ብዙ ደናግል አሉ ብሎ ይመልስለታል።
ቀጥሎም በመላዕክት ክንፍ የምትጋረድ በክብሩ መንበር በፊት ምህረት የምትለምን በራሷ ላይ ትእምርተ መስቀል ያለው አክሊል የተቀዳጀች አማኑኤል የመረጣት አንዲት ድንግል አለች።
አሁንም ቅዱስ ያሬድን ስለምን አማኑኤል የመረጣት አንዲት ድንግል ትላለህ አርሱ የመረጣቸው ብዙ ደናግላን የሉምን? ብሎ የሚጠይቀው ቢኖር፥ አማኑኤል ሥጋን ይለብስ ዘንድ የመረጣት፤ ከእርስዋም ሥጋን ለብሶ አማኑኤል የተባለባት፥ በመላእክት ክንፍ የምትጋረድ፥ እግዚአብሔር በክብሩ ዙፋን በፊቱ ለመቆም የመረጣት፥ በእናትነት የሰለጠነ የባለሟልነት ዘውድን የተቀዳጀች አንዲት ድንግል አልኩ እንጂ እርሱ የመረጣቸው ደናግላንማ ስንቱ! ብሎ ይመልስለታል።
ደግሞም ፀጉሯ እንደ ሐር ፈትል ያማረ፥ የአንደበቷ መዓዛ እንደ እንኮይ የጣፈጠ ትእምርተ መስቀል ያለው አክሊልን የተቀዳጀች የልዑል ንጽሕት አዳራሽ የሆነች አንዲት ድንግል አለች።
የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆኑ ሌሎች ደናግላን የሉምን ስለምን ለይቶ እርሷን አንዲት ድንግል አለ ቢሉ? ከእርሷ ስጋ ይነሳ ዘንድ እግዚአብሔርን በማህፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን የወሰነች እውነተኛ የእርሱ ማደሪያ ሌላ ድንግል ከማርያም በቀር ወዴት አለ ይለዋል! ብቻዋን የእግዚአብሔር መቅደስ ለመሆን የበቃች እንደሆነች ሁሉ ከቅዱሳን ሁሉ ተለይታ በእግዚአብሔር ተቀባይነት ያለው እንደ እንኮይ የጣፈጠ አማላጅነት ያላት አንዲት ድንግል እርሷ ብቻ ናት! ስለዚህ እንደ ቅዱስ ያሬድ እመቤታችን ብቻዋን አንዲት ድንግል የተሰኘችበት ወላዲተ አምላክነቷ፤ ንፅሕናዋ ፤ማኅደረ መለኮትነቷ አማላጅነቷ እና ዘለዓለማዊ ድንግልናዋ ናቸው ማለት ነው።
፩.
በድንጋሌ ሥጋ ዘለዓለማዊ
በተፈትሆ የማይመረመር ድንግልናዋ ነው። ይህም ሥስት የማይመረመሩ ግብራት አሉት። ድንግል እንደሆነች መፀነስ፥ ድንግል ሆና ሳለ መውለዷ፥ ከወለደች በኋላ ድንግል ሆና መኖሯ ናቸው። እነዚህ በህገ ተፈጥሮ የማይታሰቡ ረቂቅ ግብራት ናቸው። ሰው ድንግል ሆኖ ያለ ወንድ ዘር መፀነስ አይቻለውም፥ በድንግልና እያለ የፀነሰ መሆን አይችልም፥ ሰው በድንግልና መውለድ አይቻለውም፥ ከወለደ በኋላ ደግሞ ድንግል መሆን እንዴት ይችላል? ድንግል የሆነች ሌላ ሰው እናት አይደለችም፥ እናትም ከሆነች ድንግል አይደለችም። ይህ ለአንዲቱ ለድንግል ማርያም ብቻ የተቻለ ነው።
፪.
ድንግል በቃሏ - በቃሏም ድንግል
የቃል ድንግልና በሦስት ወገን ነው። እኒህም ክፉ አለመናገር፥ ምስጋና አለመብላትና በጎውን መናገር ናቸው። ሰው በንግግሩ ብዙ ኃጢአቶች ይሰራል። ሐሜት፣ ማጉረምረም፥ ቁጣ፥ ብስጭት፥ መዋሸት፥ መርገም፥ መሳደብ፥ ዋዛ ፈዛዛ፥ ያለጊዜው መሳቅ መሳለቅ፥ ዘፈን፥ ተውኔት፥ ድንፋታ፥ መንፈግ ነገር ማመላለስ፥ ቃል መለዋወጥ፥ አደራ መብላት፥ በሀሰት መማል፥ ሰጥቶ መንሳት፥ ክህደት፥ ማታለል፥ ማስነወር፥ አድልዎ፥ መጠራጠር፥ ማሽሟጠጥ፥ አሽሙር፥ ኃጢአትን ማመስገንና ማስፈራራት እነዚህን የመሳሰሉ ሁሉ ናቸው።
እመቤታችን በማንም ክፋትን ተናግራ አታውቅም አንደበቷ የለዘበ የለመለመ ነው። ቅዱስ ገብርኤል ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰው ልቡና የማይታሰብ ዕፁብ ድንቅ የመውለዷን ዜና ሲነግራትም እኔ ወንድ ሳላውቅ እንዴት ይሆንልኛል ብላ ነገሩን ወደ መረዳት ተሻገረች እንጂ ይህ የማይሆን ነገር ነው ብላ ወደ መጠራጠር ወይም መልአኩን ወደ መንቀፍ አልቃጣችም። የአንደበት ድንግልና ማለት የማይቻል ጭንቅ ፍጹም ከተፈጥሮ ህግ በላይ የሆነን ነገር በመስማት ጊዜም ቢሆን ያለመጠራጠር በሃይማኖት መጠየቅና ፍፃሜውን በትዕግሥት መጠበቅ ነው።
መከራ በደረሰ ጊዜ ብዙ የቃል ድንግልና ያላቸው ቅዱሳን ችግሩን የፈጠሩትን ከመንቀፍ ይልቅ በእኔ ችግር የተከሰተ ነው ብለው ራሳቸውን ይወቅሳሉ። ነገር ግን እነርሱ ቀድሞ መበደላቸውን እያስታወሱ ነው። የድንግል ማርያም ግን የሚደንቀው ምንም ነውር የሌለባት ስትሆን በቃሏ ድንግል ስለሆነች እኔ ኃጢተኛ ነኝ ትል ነበር። በብስራተ መልአክ አምላክን የፀነስኩ እናት ነኝ ስትል ገናንነቷን አትናገርም። መልካም በመናገር ንግግሯ ሁሉ ሃይማኖት ተስፋና ፍቅር ናቸው።
፫.
ድንግል በኅሊናሃ - በኅሊና ድንግልና የፀናች አንዲት ድንግል፦ሰው በተግባር ቢነጻ በንግግር አይነጻም፥ በንግግር ቢነጻ በኅሊናው መንፃት አይቻለውም። ጻድቃንም ቢሆኑ ወድቀው ተነስተው በተጋድሎ ለክብር ይበቃሉ እንጂ ከጅማሬ እስከ ፍፃሜው አለመበደል ከቶ የተቻለው የለም። እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን በኅሊናዋ እንኳን ያልበደለች ፍጽምት አንዲት ድንግል ነች። ጽድቅን ሁሉ የተሞላች ድንግል ማርያም ንጽሕት በመሆኗ በኅሊናዋን ድንግልና፤ የቃሏን ድንግልና፤ የስጋዋን ድንግልና በአንድ ላይ "እንዘ ኢይአምር ብእሴ" "ወንድ ስለማላውቅ" በሚል የንፅህና ሸማ ጠቅልላ ተናገረች (ሉቃ.፩፥፴፬) በዚህ ድንግልናዋም አምላክን ለመፀነስ በቃች።.....(ቀጣዩን መጽሐፉን ገዝተው ያንብቡ)
(ከርዕሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ አሐቲ ድንግል መጽሐፍ ገፅ 241-251 የተቀነጨበ)
▫️
@diyakonhenokhaile https://t.me/diyakonhenokhaile