“ … ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል።” (ሉቃ. 11፥39)
ቅዱስ ሉቃስ ወንጌሉን ሲጽፍልን፣ ትኵረት ካደረገባቸው ታላላቅ መንፈሳዊ ነገሮች አንዱ፣ ድኾችን በተመለከተ ነው። በወንጌሉ ውስጥ ኢየሱስ ቤት አልባ ድኻ ነው (9፥58)፣ አገልግሎቱ አምነው በተከተሉት ሴቶች ይደገፍ ነበር (8፥3)፣ አገልግሎቱ ለድኾች ወንጌልን በመስበክ እንደ ኾነ ተናገረ (4፥18)፣ ቅድስት ድንግል ማርያም ድኻ እናት መኾንዋን በመሥዋዕት አቀራረቧ አሳየ (2፥24)፣ “የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤” (1፥53) እንዲል፣ ድኾችን በብዙ እንደሚጐበኝና እንደ አልዓዛር ያሉ ድኾችን በሰማያት በብዙ ደስታ እንደሚያከበር ማስተማሩን ጽፎልናል (16፥19)፤ ይህ ብቻ ሳይኾን ሉቃስ፣ በኤልያስ ዘመን የነበረችውንም የሰራፕታዋንም ድኻይቱን መበለት አንስቶአል (4፥26)።
ጌታችን ኢየሱስ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ “የመላለሙ መሲሕ” መኾኑ ሲገለጥ፣ እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ ድኾችን የሚያስብ፤ የማይዘነጋ መኾኑንም ይነግረናል። ከላይ በርዕሳችንም እንደ ጠቀስነው፣ ከኢየሱስ በተቃራኒ ግን “ሃይማኖት ለበስ ኾነው” ሕግ እየጠቀሱና መቅደስ ተቀምጠው ድኾችን ስለሚያስጨንቁ ፈሪሳውያንና ሕግ ጸሐፎች በወዮታ ሲናገራቸው እናስተውላለን። ኢየሱስ እጁን ሳይታጠብ በገበታ ሲቀርብ፣ ስለ እጅ መታጠብ ሕጋቸው ይጨነቃሉ ነገር ግን ውስጣቸው ስስታምና ስግብግብነት የተጠናወተው ነበር።
ሃይማኖታዊ መልካቸው ውጫዊ እንጂ ውስጣቸው ፍትሕ አልባነት፣ ስግብግብነት፣ ስስታምነት፣ እግዚአብሔርን ባለመውደድ የተሞላ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ይህን ያደርጉ የነበረው፣ የዕውቀት ችግር ሳይኖርቸው እንደ ነበረ ሲናገር፣ “የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ …” ብሎአል፤ ያውቃሉ ግን ወደ መንግሥቱ አይገቡም፤ ሰዎች እንዳይገቡም ዕውቀታቸውን በማጣመም ያቀርባሉ።
ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ሕጉን ተገን አድርገው፣ ከአዝሙድና ከጠጅ ሳር ሳይቀር ከጥቃቅኑ ነገር ከድኾች አስጨንቀው አሥራትን ያስወጣሉ፤ ያወጣሉም። ግን ድኾች የሚገባቸውን ዋናውን ነገር አይሰጧቸውም። ውስጣቸው በክፋትና በመበደል፤ ሌላውን ከመጕዳት የማያርፍ ነበር።
ስለ ድኾች ሳስብ አያሌ ነገር ወደ ልቤ ይመጣል፤ ምዕራባውያን በሌሎች አገራት ላይ ጦርነት የሚቀሰቅሱበት ዋነኛ ምክንያት ጦርነት ከሚደረግበት ምድር ሃብት ለመዝረፍና በራስ ወዳድነት በተለይም አፍሪካን እንደ ፈረንሳይ ያሉ ምዕራባዊ አገራት ውድ ማዕድናትን ለመውሰድና በረጅም እጃቸው በጦርነት ድኾች አገራትን የሚያምሱት የድኾችን መቀነት ለመበዝበዝ ነው፤ በኢትዮጵያ መሪዎች እጅ፣ ዓለም ዓቀፍ የገንዘብ ተቋም የተባለው በስግብግብነቱ አቻ የሌለው አስፈሪና ጨካኝ ድርጅት ድኾችን በማስጨነቅ እየረካ ይመስለኛል … በሚያሳዝን መንገድ፣ አንዱ ከሌላው በስስታምነትና ባለመጥገብ የሚሰበስበው “ብዙ” ነው።
በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ዘንድ ሊረሱ የማይገባቸው ድኾች ተዘንግተው ነበር፤ ይህ የፈጠጠ እውነት እስከ ጌታ መምጣት ድረስ ፈክቶና ጐልቶ ይታይ ነበር። እግዚአብሔር ለድኾች ስስ ልብ ያለውን ያህል፣ ሕዝቦቹ የእግዚአብሔርን ልብ አለመያዛቸው እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው። ኢየሱስ፣ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ትኵረቱ፣ ድኾች፣ እስረኞችና ዐይነ ስውራን ናቸው። እጅግ በሚያደንቅ መንገድ ሉቃስ በጻፈው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተጠቀሰችው የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን አብዛኛዎቹ ድኾች ነበሩ። ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ ፈጽሞ አልናቃቸውም፤ አበረታቸው፤ አጽናናቸው!
ደቀ መዛሙርትም ድኾችን በብዙ ወደዷቸው፤ በጋራ ማዕድ አክብረው አቀረቡአቸው። በብርቱ የእግዚአብሔርም ቃል አጽናኑአቸው! የዛሬዋም ቤተ ክርስቲያንም ድኾችን በማግለል የምታገለግለው የትኛውም “ጠንካራና ሳቢ አገልግሎት” በእግዚአብሔር ፊት ከወቀሳና ከነቀፋ አያመልጥም። አርቲስቶችን፣ ባለሥልጣናትን፣ ዓለም ያገነነቻቸውን፣ ባለጠጎችን … በማቅረብና ድኾችን ችላ ብለን የምንሄድበት መንገድ ርሱ የተወዳጁ የናዝሬቱ ኢየሱስ መንገድ አይደለም!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።
My blog link -
https://abenezerteklu.blogspot.com/2025/03/1139.html