30 ሺህ ሰው ያሳተፈው 'ብኩን' ፊልም!
ከትግራይ እስከ አማራ እና አፋር ክልሎችን አዳርሶ ቢያንስ 600,000 ሺህ ህዝብ እንዳለቀበት የሚገመተው የሰሜኑ ጦርነት ዳፋ ገና ተነግሮ እንኳን አላለቀም።
በውጊያ ወቅት ሞተው አስከሬናቸው ገና ያልተቀበሩ በርካቶች አሉ፣ የአካል ጉዳተኞች ዊልቼር ሳያገኙ መሬት ለመሬት እየዳሁ እያየን ነው፣ የተደፈሩ ሴቶች ስነ ልቦና ገና አልተጠገነም፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው እንቅስቃሴ ገና ከመሬት አልተነሳም፣ የሰላም ስምምነቱን ማፅናት ላይ እንኳን ከሰሞኑ እንደሰማነው ውይይት ገና እየተደረገ ነው።
በዚህ ሁሉ መሀል በታንክ፣ ጀት፣ መድፍ፣ ክላሽ እና RPG የታገዘ በጭካኔ የተገዳደልንበትን ፊልም በ30 ሺህ ህዝብ አጅቦ የሚተርክ ፊልም በተለይ አሁን ባለንበት ወቅት ምን ሊጠቅመን ነው?
ዳግም ግጭት የመቀስቀስ ሙከራ ወይስ ሌላ? በዚህ ፊልም እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም... ወዘተ ለዘላለም ያጡ ወገኖች አሟሟታቸውን በፊልሙን ቢመለከቱ ምን ይሰማቸዋል?
ከማውቃቸው ሰዎች ተደጋግሞ እንደሰማሁት የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ፊልሙ በብዙ መቶ ሚልዮን ብሮች እንደወጣበት፣ በመንግስት በኩል የቁሳቁስ እና የሰው ሀይል ድጋፍ ተደርጎለት እንጂ ተጨማሪ ብዙ መቶ ሚልዮን ብሮች ሊያስወጣ የሚችል ፊልም እንደሆነ ተናግሯል።
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ወደ አሜሪካ ፊልሙን ለትርዒት ይዞ በሄደበት ወቅት "ፊልሙን እዚህ አሜሪካ ተቃውመው የሚንከባለሉ ሰዎች ይኖራሉ" ሲል እንደነበር በስፍራው የነበሩ ሰዎች አጫውተውኛል።
ጊዜውን ያልጠበቀ 'ብኩን' የሆነ የ image ግንባታ ፊልም ብዬዋለሁ። Timing የሚባል ነገር ወሳኝ ነው።
@EliasMeseret