“ጠላፊው ከላካቸው ሽማግሌዎች ውስጥ የፖሊስ አዛዦች ይገኙበታል”- የጸጋ ቤተሰቦችበሀዋሳ ከአንድ ሳምንት በፊት የተጠለፈችው ጸጋ በላቸው እስካሁን ያለችበት አልታወቀም።
ጠለፋው እንዴት እንደተፈጸመና ጠላፊው ምን ፍላጎት እንዳለው አል ዐይን ቤተሰቦቹን አነጋግሯል።
ወይዘሪት ጸጋ፥ ግንቦት 15፣ 2015 አመሻሽ ላይ ከስራ ወደ ቤቷ ለማምራት ታክሲ የምትይዝበት ቦታ ላይ ነው የመንግስት መኪና በያዘና አስቀድሞ ለፍቅር ጓደኝነት በሚፈልጋት ግለሰብ የተጠለፈችው። “ከቤቷ ውጭ አድራ ስለማታውቅ አከራዮቿ ወደ ጓደኞቿ እና ፍቅረኛዋ ደወሉ፤ ከዚያም እኔ ጋር ጠዋት ደውለው ጠየቁኝ” የሚለው ወንድሟ ታምሩ በላቸው ፥የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ግን የጠላፊውን ስም ጠርታ የት እንደሄዱ ጭምር እንደነገረቻቸው ይገልጻል።
ጠላፊው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የአቶ ጸጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ መሆኑን መግለጿንም ያስታውሳል።እነ ታምሩ ይህን መረጃ ይዘው ይገኙበታል ወደተባለው ይርጋለም ከተማ ከፖሊሶች ጋር ይጓዛሉ፤ ይሁን እንጂ ይርጋለም እንዳሉ “ሀገረሰላም ቡርሳ ነን” የሚል የጽሁፍ መልዕክት ደረሳቸው።
ከይርጋለም ወደ ሀገረሰላም በመጓዝም ወደ ቡርሳ የገጠር መንደር ማቅናታቸውን ነው ወንድሟ ታምሩ የሚያስታውሰው።“በጨለማ 3 ኪሎሜትር አካባቢ በእግር ሄደን ቡርሳ ደረስን፤ የአክስቱ እና የአጎቱ ቤት ተጠቁመን አይተን ተመለስን፥ ከፖሊስ ጋር ሌሊት 10 ስአት ሄድን እስኪነጋ ጠብቀን እያንዳንዱን ቤት ፈተሽን ግን እህቴን ልናገኛት አልቻልንም። እህቴ ተግታበት የነበረው ቤት ባለቤት እና የጠላፊው የእህቱ ወንድም በቁጥጥር ስር ዋሉ” ይላል።
ጠላፊው ሀገረ ሰላም ሲገባ “እንደ ጀግና ተኩሷል” የሚለው ታምሩ፥ “እህቴንም ከአዲስ አበባ እንዳመጣትና ሊያገባት መሆኑን ሲናገርና ከጓደኞቹ ጋር ሲጨፍሩ መታየታቸውን” ከሀገረሰላም ነዋሪዎች መስማታቸውን ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጸጋ ቤተሰብ ነግረውናል።ጸጋ በቡርሳ ለማምለጥ ሞክራ መያዟንም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሯቸው በማከል።
የጸጋ እና የጠላፊው ጥያቄ ምንድን ነው?
ጸጋ በላቸው ከተጠለፈች ስምንተኛ ቀን ቢሆናትም ድምጿን የሰማሁት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ይላል ወንድሟ ታምሩ።“እኔን ነጻ ማውጣት አትፈልግም ወይ? እኔን ነጻ በሚያወጣ መልኩ ተደራደር” ብላኛለች፥ ይሁን እንጂ ለድርድር ከተቀመጥን ደግሞ እሷ በሰላም የምትወጣበትን ዋስትና አላገኘንም ባይ ነው። ጠላፊው ግለሰብ ደግሞ ሽምግልና መቀመጥ ግዴታ መሆኑን ደጋግሞ መግለጹን ነው የሚናገረው። በሽምግልና የማይፈታ እና ጉዳዩን በህግ የሚይዙት ከሆነም እንደሚገላት እየዛተ ነው። “ሊልካቸው ያሰቡ ሽማግሌዎች ደውለው አውርተውኛል፤ እስካሁን የት እንዳሉ አያውቁም፤ ደህንነቷን አላረጋገጡልኝም" ይላል ታምሩ በላቸው።
የጸጋ በላቸው ጠለፋ ከቤተሰቦቿ አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሆኖ መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል። እናትና አባቷ እስካሁን የልጃቸውን ጠለፋ እንዳልሰሙ ነግሮናል።“አባቴ ሆስፒታል በህክምና ላይ ነው፤ እናቴም እያስታመመችው ነው፤ በጣም የሚወዷትን ልጃቸውን ጠለፋ ከሰሙ ወላጆቼን በሞት አጣቸዋለሁ” ሲልም ስጋቱን ይገልጻል።
እጮኛዋን ለማግባት እየተሰናዳች የነበረችው ጸጋ፥ ጠላፊዋ ሽማግሌ ልኮ ሚስቴ ካላደረኩሽ እያላት ነው። በቴክስት የተለያዩ መልዕክቶችን ሲልክና ፍላጎቱን ሲገልጽ መቆየቱን የሚያወሱት ቤተሰቦቿ በዚህ ዘመን የጠለፋ ወንጀል ይፈጸማል ብለው በፍጹም እንዳልጠበቁ ይናገራሉ።
የሃዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የጸጥታ አካላ ጉዳዩን ያልሰማ የለም የሚሉት ቤተሰቦቿ፥ መረጃው እንዴት እንደሚሾልክ ባናውቅም ደብዛውን አጥፍቶ ስምንት ቀናት መቆጠራቸውን ያነሳሉ።ጠላፊው ሊልካቸው ካሰባቸው ሽማግሌዎች ውስጥ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ከፍተኛ የስራ ድርሻ ያላቸው ግለሰብ እንደሚገኙበት በመጥቀስም፥ የህግ ያለህ እያሉ ነው ቤተሰቦቿ።
የጸጋ ቤተሰቦች ከጠላፊው ጋር ተመሳጥራ ያስጠለፈቻት ብለው የሚጠረጥሯትና በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው ባልደረባዋም በ30 ሺህ ብር ዋስ መውጣቷን ገልጸዋል።(ምንጭ፣ አልአይን)
@ethio_mereja_news@ethio_mereja_news