ኢትዮጵያ ክሪፕቶከረንሲን ለመገበያያነት ለመጠቀም የሚያስችል መመሪያ ልታወጣ እንደምትችል የብሔራዊ ባንክ ገዢ ጥቆማ ሰጡ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የክሪፕቶ አሴትን” እና የዲጂታል ገንዘብን በኢትዮጵያ መጠቀም የሚያስችል መመሪያ ወደፊት ሊያወጣ እንደሚችል የተቋሙ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ። ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን የሚያወጣው በማዕከላዊ ባንኪንግ፣ በገንዘብ ፖሊሲ እና በገንዘብ አስተዳደር ያሉ ዓለም አቀፍ “ለውጦችን” እና “እድገቶችን” እያየ መሆኑን አቶ ማሞ ተናግረዋል።
አቶ ማሞ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዋጅ ማሻሻያ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ወቅት ከፓርላማ አባል ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ነው። በዘጠኝ ክፍሎች እና በ57 አንቀጾች የተዘጋጀው ይህ አዋጅ፤ ከ16 ዓመት በፊት የወጣውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅን ያሻሻለ ነው።
የአሁኑ አዋጅ ካካተታቸው አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ክሪፕቶከረንሲ እና የዲጂታል ገንዘብን መጠቀም የተመለከተው አንዱ ነው። አዋጁ “አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብሔራዊ ባንክ ካልፈቀደ በስተቀር፤ ክሪፕቶከረንሲ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ በመጠቀም ክፍያ መፈጸም አይችልም” ሲል ክልከላ ያስቀምጣል።
አዋጁን በመተላለፍ በእነዚህ መንገዶች ክፍያ የፈጸመ ማንኛውም ሰው፤ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣም ተደንግጓል። ክሪፕቶከረንሲን በተመለከተ በአዋጁ የተቀመጠውን ድንጋጌ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የጠቀሱት ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ አፈጻጸሙን እና ቁጥጥርን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርበዋል።
“የዲጂታል ከረንሲ [ግብይት] ቴክኖሎጂ ያመጣው ነው። ግዴታ መጠቀም አይቀርም። አለም በ21ኛው ክፍለ ዘመን እየሄደበት ያለ ነው። በቢትኮይን፣ በዲጂታል ከረንሲ፣ በክሪፕቶከረንሲ እየተገበያየ ነው ያለው” ያሉት ዶ/ር ፈትሂ፤ የዲጂታል ገንዘቦችን የሚጠቀሙ ሰዎች “አድራሻቸው በግልጽ ሳይታወቅ፤ በኦንላይን፣ በምናባዊ የሚፈጽሙት ነገር መሆኑ” ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
የዲጂታል ገንዘብን የሚጠቀሙ ሰዎች “ሀገር ውስጥም ሆነው፣ ከሀገር ውጭም ሆነው፣ ትራንዛክሽኑ በማይታይ በምናባዊ መንገድ” ክፍያ እንደሚፈጽሙ የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ “ይህንን ብሔራዊ ባንክ እንዴት ነው የሚቆጣጠረው?” ሲሉ ጠይቀዋል። “[በአዋጁ] ‘ክፍያ መፈጸም አይቻልም” ተብሏል። ብሔራዊ ባንክ እንዴት ነው የሚፈቅደው? እንዴት ነው የሚቆጣጠራቸው? አሰራሩ፣ ስርዓቱ ምን ይመስላል? ለቁጥጥርስ ይመች ይሆናል? ቴክኖሎጂውስ አለን ወይ? መቆጣጠርስ በትክክል እንችላለን ወይ? መንግስት በትክክል ማግኘት የሚገባውን ግብር ማስከፈል እንችላለን ወይ?” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል።
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ገዢ “ክሪፕቶ አሴት” ወይም “ቢትኮይን” የሚባለውን “በሁለት መንገድ” መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል። “ክሪፕቶ ማይኒንግ” የሚባለው የዳታ ማዕከል ኢንቨስትመንት “ምንም ችግር የሌለበት” እና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ “በስፋት” “በስራ ላይ ያለ” መሆኑን አቶ ማሞ አስረድተዋል። ይህ ኢንቨስትመንት፤ በኢትዮጵያ “የኃይል አቅርቦት” እና “ግሪን ኢነርጂ” መስፋፋት ጋር የተገናኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
“አሁን ኢትዮጵያ በስፋት የክሪፕቶ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ነው ያለችው። ይሄ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ነው” ሲሉም የብሔራዊ ባንክ ገዢው ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የክሪፕቶ ማይኒንግ በዚህ ደረጃ ላይ ቢገኝም፤ “የክሪፕቶ አሴትን” እንደ ገንዘብ መጠቀም በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ የተፈቀደ አለመሆኑን አቶ ማሞ አስገንዘበዋል።
“በአጠቃላይ የዓለም የገንዘብ ፖሊሲ ዳይናሚክ ምን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ለምሳሌ አሁን የምንጠቀመው ገንዘብ (currency) ብር ነው። አሁን ብዙ ማዕከላዊ ባንኮች እየጀመሩ ያሉት የማዕከላዊ ባንክ ዲጄታል ገንዘብ አለ። አሁን ሰው የሚጠቀመው ካሽ እየቀረ፤ ወደ ዲጂታል ገንዘብ ሺፍት እየተደረገ ነው ያለው” ያሉት አቶ ማሞ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህን የዓለም አቀፍ ሁኔታ ከግምት በማስገባት “በተለየ መልኩ” መመሪያ እንደሚያወጣ ጥቆማ ሰጥተዋል።
“ይሄ የክሪፕቶ አሴትን፣ ቢት ኮይንን፣ የማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ከረንሲን በተመለከተ የዓለም የማዕከላዊ ባንኪንግ፣ የገንዘብ ፖሊሲ እና የገንዘብ አስተዳደር በሂደት እየተቀየረ ስለሚሄድ ዳይናሚክ የሆኑ ለውጦችን እና ዴቨሎፕመንቶችን እያየ ብሔራዊ ባንክ እንደሌሎቹ ማዕከላዊ ባንኮች፣ እንዳስፈላጊነቱ መመሪያ ሊያወጣ ይችላል” ብለዋል የብሔራዊ ባንክ ገዢው።
በአዲሱ አዋጅ “ክሪፕቶ አሴትን መጠቀም አይቻልም” ያሉት አቶ ማሞ፤ በአዋጁ የተቀመጠውን ድንጋጌ አፈጻጸም በተመለከተ ብሔራዊ ባንክ “ቁጥጥር እንደሚያደርግ” አስታውቀዋል። የክሪፕቶ ገንዘብ መጠቀም አሁን ቢከለከልም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደ ሌሎች ሀገራት መሰል ባንኮች “በሂደት ሁኔታዎችን እያየ” እና “ነገሮችን እያገናዘበ” መመሪያ እንዲያወጣ በአዲሱ አዋጁ ኃላፊነት እንደተሰጠውም ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
@Ethionews433 @Ethionews433