#Explainer ለመሆኑ ጎብኝ ሲባል ማንን ያካትታል? ከጎብኝዎች የተገኘ ገቢስ እንዴት ይሰላል?
የአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎችን ማስተናገዱን እና በዚህም ከ2.41 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በትናንትናው ዕለት አስነብቦ ነበር። ለመረጃውም በምንጭነት የክልሉን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጠቅሷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ክልሎችም እንዲህ ያሉ ቁጥሮችን በየጊዜው ሲናገሩ ይደመጣል። ይህን የተመልከቱ ሰዎች ቁጥሮቹ መጋነናቸውን በመጥቀስ አስተያየታቸው ሲሰጡ የሚታይ ሲሆን ለኢትዮጵያ ቼክም የአጣሩልን ጥያቄዎች ይመጣሉ።
- ለመሆኑ ጎብኝ ሲባል ማንን ያካትታል? ከጎብኝዎች የተገኘ ገቢስ እንዴት ይሰላል?
የተመድ የዓለም ቱሪስም ድርጅት (UNWTO) የቃላት መፍቻ ጎብኝ ወይም ዕንግዳ (visitor) ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ የሚጓዝ፤ በሄደበት አዲስ አካባቢ ከአንድ ዓመት በላይ የማይቆይ፤ ጉዞውም ከቅጥር ውጭ ለንግድ፣ ለጉብኝት፣ ለግል ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ይዘረዝራል።
ተጓዡ በሄደበት አካባቢ ከአንድ ቀን በላይ ከቆየ ቱሪስት (tourist) ሊባል እንደሚችል የሚበይነው ድርጅቱ ከአንድ ቀን በታች ወይም በደርሶ መልስ ወደመኖሪያቸው የሚመለሱትን ሽርሽር አድራጊዎች (same-day visitor or excursionist) ይላቸዋል። ጎብኝ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተጓዦችን ያጠቃልላል።
ከጎብኝዎች የሚገኝ ገቢ ደግሞ ጎብኝው በአካባቢው በቆየበት ጊዜ ለምግብ፣ ለምኝታ፣ ለአስጎብኝ፣ ለትራንስፖርት፣ ለስጦታ ዕቃዎች መግዣ ወዘተ ያወጣል ተብሎ የሚገመተው ወጭ ላይ መሰረት እንደሚያደርግ የዓለም ቱሪስም ድርጅት የቃላት መፍቻ ያስረዳል።
- የአማራ ክልልን በሩብ አመቱ የጎበኙት እነማናቸው? ገቢውስ ከምን ተገኘ?
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ በሩብ አመቱ ክልሉን ጎበኙ ያላቸውን ዋና ዋና ተጓዦችን ዘርዝሯል። በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም በግሸን ደብረ ከርቤ በዓል አከባበር ብቻ አንድ ሚሊየን ሃይማኖታዊ ጎብኝዎች ወደ አካባቢው መጓዛቸውን የገለጹ ሲሆን በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦችን ለመጎብኘትም በየሳምንቱ መጨረሻ የእረፍት ቀናት ከአዲስ አበባ በርካታ ጎብኚዎች እንደሚመለጡ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከነሐሴ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል፣ የመስቀል፣ የግሸን ደብረ ከርቤ በዓላትና ሌሎች ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትንም አስረድተዋል።
ከጎብኝዎቹ መካከልም 6,328 የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች መሆናቸው ተገልጿል።
ከጎብኝዎች ተገኘ የተባለው ገቢ የተሰላው አንድ የውጭ ወይም የሀገር ውስጥ ጎብኝ እንደ አካባቢው ሁኔታ በቀን ለመኝታ፣ ለምግብ፣ ለአስጎብኝ፣ ለጫማ ማስዋብና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚያወጣው ታስቦ መሆኑ ቢሮው ባጋራው መረጃ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ቼክ
@EthiopiaCheck