በአንድነቱ ምንታዌ በሦስትነቱ ርባዔ በሌለበት በሥላሴ ስም ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የምሉዓ ጸጋ እስጢፋኖስን ዜና መጻፍ እጀምራለሁ
አባ ጽጌ ድንግል
ቀዳሜ ሰማዕት ወሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስ ቀድሞ ከመምህሩ ከገማልያ ትንቢት የተነገረለትን ሱባዔ የሚቆጠርለትን መሲሕ ሲሰማ አደገ በኋላም ከመጥምቀ መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ ዮሐ 1፥19 የሚለውን የመጥምቁን ቃል በሰማ ጊዜ የቃሉን ትምህርት የእጁን ተዓምራት ለማየት የነበረውን ጉጉት እስከ ሞት ድረስ ሊታመነው ወዶ ተከተለው።
ለብሉያት አዲስ ያልነበረው መጋቤ ብሉይ እስጢፋኖስ የሐዲስ ኪዳን መግቢያ introduction ከመጥምቁ ዘልቆ የሐዲስ ኪዳን ትምህርቱንም ከሊቀ ሊቃውንት ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልና በኑሮ ተማረ።
የመጀመሪያዎቹ ጳጳሳት ሐዋርያት የምዕመናኑን በዘርና በቋንቋ መከፋፈል ዐይተው ለዚያም ምክንያት የነበረውን የመዓድ ጉዳይ የሚያስተባብሩ መንፈስ ቅዱስ የሞላባቸው ሰባት ዲያቆናትን ሲመርጡ በምግባር በሃይማኖት ያጌጠውን በትምህርቱም ጣዕም ወደር የሌለውን አይሁድን በአፍ በመጻፍ አፍ የሚያሲዘውን እስጢፋኖስን ሊቀ ዲያቆናት አድርገው ሾሙት።
የስምንት ሺህ ምዕመናን አባት ሆኖ በአንደበቱና በሕይወቱ ወንጌልን ፤ በደግነቱ ምድራዊ መዓድን እያበላና እያጠጣ የምዕመናንን አንድነት እጅግ አጠነከረው።
ለምቀኝነት አያርፉም የተባለላቸው አይሁድ የአስጢፋኖስን የአገልግሎቱን ርቀት የአዕምሮውን ምጥቀት ተመልክተው በቅናት ተነሳሱበት ፤ የሀሰት ምስክር አቁመው በሸንጎ ፊት አቆሙት የሶስና በሀሰት ክስ ሸንጎ ፊት መቆም ሲማር ያደገው መጋቤ ብሉይ እስጢፋኖስ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ እያሳጣ የተነገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ይናገር በጀመረ ጊዜ መልኩ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስል ነበር ይለናል ጸሐፊው ቅ/ሉቃስ እርሱም እኔን ምሰሉ ያለውን ጌታ በምግባር መስሎት እንደነበር እናስተውላለን። ሐዋ 6፥15
እንግዲህ ይኼኔ ነው በአፍ በመጻፍ መልስ ቢያሳጣቸው ጊዜ ልማዳቸው የሆነው አይሁድ እስከ በወዲያኛው ሊሰናበቱት ማኅበሩንም ሊበትኑ እስጢፋኖስን ከከተማ ውጪ አየጎተቱ ይዘውት ወጡ መጠን አልባ ጥላቻቸውንም የድንጋይ ማዕበል በማዝነብ ይወጡበት ጀመር እርሱ ግን ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ልጅ በቀኝ ቆሞ ያይ ነበር የሚያዘንቡበት የድንጋይ ዝናብ እንዳለ ሊቁ እንደ ገለባ ይመስለዋል በክርስቶስ መዓዛ ፍቅር ታውዷልና ቀኑን ሙሉ ሊገደል ወደደ። ሮሜ 8፥36 ለገዳዮቹም ኦ አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ሐዋ 7፥60 ብሎ ወዳጆቻችንን መውደድ ላቃተን ለእኛ ጠላቶቹን ወዶ አምላኩን መምሰልን አስተማረን።
ጌታ ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ የሞላበትን በሕይወቱ እስከ ሞቱ እርሱን የመሰለውን ፤ ከእርሱ ጋር በአንድ መቅደስ የተራዳውን ገባሬ ሰናይ ዲያቆን ብሎ ሲጣራ በሰማ ጊዜ ከባሕርይ አባቱ ቀኝ ቆሞ ተቀበለው በሰማያዊ አክሊልም አጌጠው እስከ ሞት ድረስ በመታመን የመጀመሪያ የሆነውን (ቀዳሜ ሰማዕት) በሰማያት በሰማያዊ ማዕረግ አኖረው።
ሰኔ 21 የቤተ ክርስቲያን ልደት የሆነባት የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በዓል ነበረች። በዚያች እለት ዲያቆኑ እስጢፋኖስ የኪዳኑን ጸሎት እንደጨረሱ ከሐዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናትና ከሊቀ ሐዋርያት ጴጥሮስ ጋር ገባሬ ሰናይ ዲያቆን ሆኖ ሊቀድስ ገባ በአማናዊቷ ምስራቅ በድንግል ማርያም ፊትም ቆሞ ወደ ምስራቅ ተመልከቱ ይል ነበር።
እስጢፋኖስ ሆይ ከአማናዊቷ መቅደስ ጋራ ወደ መቅደስ በገባህ ጊዜ ምን አስተዋልክ ፤ በአማናዊቷ መንበር ላይ መስዋዕቱ ሲቀርብ ምን ምስጢር ተረዳህ ፤ ማዕጠንቱን ይዘህ ፍሕም በጨመርክባት ሰከንድ ምን ቅኔ ደረደርክ ፤ ወደ አማናዊቷ መቅደስ ወደ አማናዊቷ ታቦት ስግዱ ባልክባት ደቂቃ እንዴት አይነት ስግደት ሰገድክ። ከቅዳሴው ፍጻሜስ በኋላ ወደ እርሷ ቀርበህ ምን ምስጢር አደላደልክ ምን ቅኔ ደረደርክ ፤ አባቴ ሆይ ይህንንስ ኃጢአት ባደቀቀው ሰውነቴ ምስጢር በራቀው አዕምሮዬ ምግባር በራቀው ስብዕናዬ ልረዳው አልችልምና እንዲያው እጹብ ብዬ ልመለስ።
መጋቢያችን በዘር በቋንቋ ለተከፋፈለች የመዓድም ነገር ለጨነቃት ጉባዔ ኢትዮጵያ ትደርስላት ዘንድ ማንን ሐዋርያ ልለምን ጴጥሮስን ነው ዮሐንስን?
በከመ ጸሐፈ ጳውሎስ እንዘ ይብል ሠናየ መልእክተ፤ ናሁ ዘራዕኩ ለውዳሴከ ሕጠተ፤ እርር ሊተ እስጢፋኖስ ፍሬ ከናፍርየ ዘንተ፤ በዘርዐ ሰብእ በሥጋሁ የዐርር ሞተ፤ ወዘዘርዐ በመንፈሱ የዐርር ሕይወተ።
ዲ/ን ዘ፲፪
ጥቅምት 16 2014
@ewkete_orthodox@ewkete_orthodox