Hawassa's Memory-የሐዋሳ ትዝታ


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic
Category: Transport


ሐዋሳ የፍቅር ሐገር! መልካም ገፅታዋን ለማስጠበቅ የትም የሚኖር፣ ሐዋሳ የተወለደ፣ ያደገ፣ ለስራ ወይም ለመዝናናት የመጣ እንዲሁም ለሚያውቃትና ሊያውቃት ለሚፈልግ ትዝታውን በፍቅር ይለዋወጣል

Related channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Category
Transport
Statistics
Posts filter




በመጨረሻም ከተማችንን ስላገለገሉ እናመሰግናለን አልናቸው፡፡ እርሳቸውም አይ ለራሴ ጥቅም ሰራሁ እንጂ ህዝብን መች አገለገልኩ ብለሽ ነው አሉኝ፡፡ ያኔ ትዝ ይለኛል በአብዛኛዎቻችን ቤት የቡታጋዝ ተጠቃሚ በነበርንበት ጊዜ ከ1 ሌትር ጀምሮ ነጭ ጋዝ ይሸጡ ነበር፡፡ እሳቸው በአቅራቢያው ለዝቅተኛው ማሕበረሰብ ባያቀርቡ ከየት እንጠቀም ነበር? ብቻ ብዙ የሰሩ ሰዎች ብዙ ማውራት አይፈልጉም፡፡ ለእሳቸውም ለሚወዷቸው ባለቤታቸው እዲሁም በአጠቃላይ ለቤተሰቦቻቸው መልካም ምኞታችንን ተመኝተን ከእሳቸውም ከወይንዬም ምርቃትን ተቀብለን ለቀጣይ ሳምንት ጋቢ ለምናለብሰው አባት ቤት መንገጃችንን አቀናን፡፡ መልካም ዕለተሰንበት!

ሊዲያ /የሚኬ ባለቤት/ ስለቅንነትሽና ስለመልካም ትብብርሽ ሳላመሰግንሽ ማለፍ ንፉግነት ነው፡፡ ነፍፍፍፍፍ አመት ኑሪልኝ እህቴ፡፡

ምስጋና፡ ለፍቅሩና ጓደኞቹ እንዲሁም ለዶ/ር ዘነበ (አልፋኬር መካከለኛ ክሊኒክ) Zenebe Mekonnen

በሐና በቀለ
*
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!


#የተዋጣለት_መርከበኛው_ነጋዴ| ኃይለ ጋሼ
#Hawassa| በልጅ ወግ አክብረናል
ኃ/ሚካኤል ገ/ሚካኤል) - ቶታል ማደያ ባለቤት

ኅይለ ሚካኤል የቤታቸው ታላቅ ወንድም ናቸው፡፡ ስለዚህ ታናናሾቻቸው እንደሀገራቸው ባህል ስምን በማስቀደም ኃይሌ-ጋሼ ይሏቸው ነበር፡፡ይህ በጉራጌ ማህበረሰብ የቤቱ ታላቅ አጠራር ነው። ቢሆንም ኋይለሚካኤል ገብረሚካኤል የሚለው የመታወቂያ ስማቸው ተዘነጋና አብዛኛው ሰው በኃይለጋሼ ነው የሚያውቋቸው፡፡

የተወለዱት ሰባት ቤት ጉራጌ እዣ ወረዳ በ1939 ዓ.ም ሲሆን በ4 ዓመታቸው በ1943 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሄዱ ይናገራሉ፡፡

በ1947 ዓ.ም ሚኒሊክ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከ9 እስከ 12 ተምረው በኋላ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ስለነበራቸው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲነሰ ተቀላቅለዋል።
ይሁን እንጅ ዶርም ገብተው የሚማሩ ልጆች ውስን ስለነበሩ ዶርም ያልደረሳቸው ደግሞ ዩኒቨርሲቲው በወር በሚሰጠው 20 ብር ቤት ተከራይተው እንዲማሩ ያመቻች ስለነበር እኔም ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ስለነበርኩ ይህንን ለአባቴ ነገርኩት፡፡ ነገር ግን አባቴ አልተስማማም፡፡ እሱ ይፈልግ የነበረው እዚያው ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ ዶርም ይዤ እንድማር ነበር፡፡ ከ3 ወራት በላይ ትምህርቴን መቀጠል አልቻልኩም፡፡

በ1959 ዓ.ም የኢትዮጵያ የመርከብ ድርጅት ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ማስታወቂያ በመለጠፍ - “አለምን መዞር ሲያምራችሁ ካፒቴን ኢንጅነር ትሆናላችሁ” ይባል ነበር፡፡ ይህንን ማስታወቂያ አይተው ጓደኞቼ ሲነግሩኝ ለመመዝገብ ስሄድ የሚፈልጉት 15 ተማሪዎች ስለነበር እኔንና አንድ ተማሪን ተጠባባቂ አድርገውን እሮብ ተመለሱ አሉን፡፡ ባሉን ቀን ስንመለስ ሁለታችንን ተቀበሉን፡፡

ከዚያም እኔን የቀጠረኝ መስሪያ ቤት የንግደ ድርጅት ነው፡፡ ከዚያም ለትምህርት ምፅዋ ወሰዱን፡፡ እዚያ ስንደርስ ያሉት የባሕር ኃይል ነበር (የጦር መርከብ)፡፡ የንግድ መርከብ ትምህርት አልነበረም፡፡ ሆኖም ግድየለም እዚያው ተማሩ ተብለን ለ2 ዓመት እዚያው ተማርን፡፡ ከ2 ዓመት ቆይታ በኋላ ከእኛ በፊት የነበሩ የንግድ መርከብ ተማሪዎች እስከአሁን የተማርነው አስፈላጊ እንዳልሆነ ነግረውን እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተመልሰን ጠየቅናቸው፡፡

የንግድ መርከብ ትምህርት ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ መርከብን የሚሰሩት ሆላንዳዊያን ነበሩ፡፡ ስለዚህ ከሆላንድ መንግስት ጋር ተነጋግረው ለ2 ዓመት እዚያ ተምረን ተመለስን፡፡ እዚያ ከተማርን በኃላ ወደመርከብ ወጣሁ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለ19 ዓመታት መርከብ ላይ ነበር የሰራሁት፡፡ "

የኃይለጋሼ ወላጅ አባት አቃቂ ቃሊቲ ነዳጅ ማደያና ሆቴል ነበራቸው እንዲሁም ሀዋሳ ቶታል ማደያ በ1960ዎቹ መጨረሻ የከፈቱት ሲሆን የኃይለጋሼ ታናሽ ወንድማቸው ያስተዳድሩት ነበር፡፡ በኋላ በ1970 ዓ.ም አባታቸው በመኪያ አደጋ ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ወንድማቸው ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ኃይለጋሼ ሀዋሳ ነዳጅ ማደያ የመስራት እቅዱ ባይኖራቸውም የአባታቸው ድንገተኛ ሞት ወደሀዋሳ መጥተው ቶታል ማደያውን በ1971 ዓ.ም ጀምሮ ማስተዳደር እንደጀመሩና ሀዋሳ እስከዛሬዋ ጊዜ ድረስ እንደኖሩ ነው የነገሩኝ፡፡

ኃይለጋሼ የሐዋሳውን ማደያ ተረክበው በሚሰሩበት ወቅት ባለቤታቸው ወ/ሮ ወይኒቱ ታደሰ ደግሞ ከቶታሉ ጀርባ በቆርቆሮ የተከለለ ቤት ውስጥ ምግብ ቤት በመክፈት ይሸጡ ነበር፡፡ በዋናነት የሚሰራው ክትፎና ፍርፍር ሲሆን ደንበኞቻችን ክትፎና ፍርፍር ሲያዙ አንድ “ኮርኒስ” የሚል ስም አወጡለት ለምግብ፡፡
እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዋሳ ከተማ የአቦካዶ ጁስ ወ/ሮ ወይኒቱ አዘጋጅታ ትሽጥ እንደነበር ኃይለጋሼ ነግረውኛል፡፡ ግን አንድ ምግብ ስንት ነበር? አልኳቸው፡፡ አንድ ምግብ በሁለት ብር ከሃምሣ ሳንቲም ነበር አሉኝ፡፡ ከዚያም አሉ ኃይለጋሼ በጣም ለመደልንና ስራውን በስፋት እየሰራን አጠገቡ መሬት ማዘጋጃ ሲሰጠን በ1981 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የንግድ ቤት ፎቅ መጀመሪያ የሆነውን በማስገንባት በ1983 ዓ.ም ስራውን በአዲስ መልክ ቀጠልን፡፡

በጊዜው ታዋቂ የሚባሉ ሆቴሎች እነማን ነበሩ? አልኳቸው፡፡ ዋቢሸበሌ፣ ያማረ ሆቴል፣ ብሔራዊ ሆቴል፣ ሸዋበር ሆቴል፣ ሰጎን ሆቴል፣ አንበሳ ሆቴል፣ ዋርካ አጠገብ አለማየሁ ሆቴል እና ሌሎችም ነበሩ፡፡

ከዚያም ከምግብ ቤቱ ቀጥሎ በ1987 ዓ.ም ቶታል ባንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ ከተማ የተጀመረ ሲሆን በጊዜው የባንዱ አባል የነበሩት ሐይማኖት ግርማ፣ ቴድሮስ ቬንቼዚ፣ ዝናቡ ገ/ስላሴ፣ ሰብለ መዝሙር፣ ገረመው በቀለ፣ አሰግድና ሌሎችም ነበሩበት፡፡

ከባንዱ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ አርቲስቶችን እንጋብዝ ነበር፡፡ ቴዲ አፍሮን ጨምሮ በብዛት አርቲስቶች ይመጡ ነበር አሉኝ ኃይለጋሼ፡፡

ኃይለጋሼና ወ/ሮ ወይኒቱ በትዳር የተጣመሩት በ1960ዎቹ መጨረሻ ነው። የኃይለጋሼ አባትና የወይንዬ አባት በጣም የልብ ወዳጆች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ካሳንቺስ መንደር አንድ ሰፈር ኖረዋል፡፡ ማህበርም አብረው ጠጥተዋል፡፡ ከአቀራረባቸው የተነሳ እንደቤተሰብ ነው የሚተያዩት፡፡ ሐዋሳ የወይንዬ አባት የመንገድ ትራንስፖርት የመጀመሪያ የመንጃ ፈቃድ ፈታኝ በነበሩበት ወቅት የኃይለጋሼ ታናሽ ወንድም የቶታል ማደያውን ሲያስተዳድሩ የወይንዬ አባት ቤት ሐዋሳ ይኖር ነበር፡፡ ይሄ ሂደታቸው ቤተሰባዊነቱን አጠናክሮላቸዋል፡፡ ይሁንና በዚህ መካከል ኃይለጋሼ እና ወይንዬ ተዋደዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በቤተሰቦቻቸው ዘንድ ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል፡፡
የቤተሰቦቻቸው ምክንያት ደግሞ እኛ ቤተሰብ ነን ጋብቻችሁን አንፈቅድም የሚለው ሀሳብ በሁለቱም ቤተሰቦች ዘንድ ስለነበር፡፡ ጥንዶቹ ግን አሻፈረኝ አሉ፡፡ ተያይዘው መኮብለልን መረጡ፡፡ ከዚያም ወደሀዋሳ በመምጣት መኖር ከጀመሩ በኋላ ወደቤተሰቦቻቸው በመመለስ ይቅርታ ጠይቀው በመታረቅ በቅሬታ የቆየውን የቤተሰቦቻቸውን ፍቅር ዳግም በማደስ ሕይወታቸውን መምራት ጀመሩ፡፡

ባህር ኃይል በነበሩበት ወቅት የትኞቹን ሃገራት አዩ አልኳቸው፡፡ ባህር ያለበት አካባቢ በሙሉ አይቻለሁ፡፡ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ነርዌ፣ ሲውዲን፣ ስፔን፣ ኢታሊ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካንና ሌሎችንም ኢሮፕ ሃገራት በስራው አጋጣሚ እንደሄዱ ነገሩኝ፡፡ በወሬያችን መካከል እንደው ካይዋት ሀገር እዚህች ሃገር ብቀር ያሉበት አጋጣሚ አልነበረም? አልኳቸው፡፡ በፍፁም አንድም ቀን ከሀገሬ ለመውጣት ተመኝቼ አላውቅም፡፡ እንደዚህ ስል ግን ሀገሬ ውስጥ ችግር የለም ማለቴ አይደለም፤ #ግን_ከነችግሩ_ሀገሬን_እወዳታለሁ አሉኝ፡፡ ኃይለጋሼ ከንግዱም ዓለም ባሻገር ጎበዝ ከሚባሉ ፎቶ አንሺዎች መካከልም ነበሩበት፡፡

በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሄድኩበት ወቅት ሀገሬ እንዲህ ተለውጣ ባይ ብዬ እመኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በሂደት ሀዋሳ እንዲህ ተለውጣ እለት እለት ባየሁ ቁጥር ከሰራን እንደምንለወጥ ያመንኩበት ሁኔታ አለ፡፡ የእኛ ልጆች ደግሞ በትምህርትም ቢሆን በጣም ጎበዞች ናቸውና ወደፊት ከዚህ በላይ ሀገራችንን እንደሚለውጡ ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡

አሁን ኃይለጋሼ 78 ዓመታቸው ሲሆን ከወይንዬ ጋር ያፈሩት 6 ወንድ ልጆች እና 10 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡


Video is unavailable for watching
Show in Telegram




#እናመሰግናለን| 7 ደጋጎች
#hawassa| 66,000 ብር
   በአስከፊው የመኪና አደጋ ያጣናቸው 11 ወጣት የደራ ጤና ስፖርት ማህበር አባላት ቤተሰቦች ማቋቋሚያና በህክምና ላይ ለሚገኙት በህይወት ላሉ ማሳከሚያ የበኩሌን በማለት በኮሚቴው በተከፈተው አካውንት 1000610475667 ንግድ ባንክ

1. አሰበ ወልዴ (አዝጋርት ፑቲክ) 10,000
2.ደምሴ አበበ (ካራሶሪያ ጋራጅ) 15,000
3. በሐብቷ አስቻለው በሐብቷ የስፖርት ትጥቅ መሸጫ) 10,000
4. ቢኒያም ተሰማ (ቢኒ መድሐኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አከፋፋይ) 5,000
5. ይዲዲያ ሰለሞን (አሜን መድሐኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አከፋፋይ) 1,000
6. ተስፋፂዮን ዳንኤል (ሐዋራ ፋርማሴቲካል) 15,000
7. አድማሱ ደነቀ 10,000 ብር ድጋፍ አድርገዋል።
በወጣ ይተካ ክብረት ይስጥልን።
    ልዑል አምላክ ከዚህ አይነት ክፉ አደጋ ሁላችንን እንዲጠብቀን እየተማፀንን ሁላችንም ተረባርበን የተቻለንን ድጋፍ እናደርግ ዘንድ ጥሪ እናስተላልፋለን። ቃል የገባችሁ ካላችሁ ከወዲሁ ብታስገቡ ስንል በትህትና እንጠይቃለን።


1. ፋሲካ ደጀኔ በሰመረ በኩል 3000
2. ታዲዮስ ማስረሻ 5000
3. ቢኒያም ገነሞ 500
4. ክፍሌ ቦሌ 1000
5. አሰግድ ዲቃሶ 10,000
6. ፅጌ ግርማ 500
7.መቅደስ መኮንን 1000






#ሁለገብ_አገልግሎት| መምህር ጌታቸው ተክሉ
#hawassa| ፍቅራችንንም ክብራችንንም እነሆ
    የሐዋሳ ትዝታ ተመስርቶ የመጀመሪያውን ጉብኝት በመ/ር ድጋፌ (ነብስ ይማር) ካደረግንበት ቀን ጀምሮ በሐሳብም በምክር ከኛጋር የነበሩ፣ በተለየ የማስታወስ ችሎታቸው የመረጃ ቋታችንም የክብር አባላችንም መሆናቸውን በቅድሚያ መግለፅ እንወዳለን!
   መምህር ጌታቸው ተክሉ
መምህር ጌታቸው ተክሉ ባሳለፉት የስራ ዘመን ለሀገራቸው በብዙ የስራ ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ እንዲያው እኔ በጽሁፍ ለመግለጽ እንዲያመቸኝ መምህር እንዲሁም በመሃል ደግሞ እንደልጅነቴ ጋሼ እያልኩ ጽሁፉን ባስነብባችሁ እሳቸውና አንባቢያኖቻችን ቅር እንደማትሰኙ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ወደ 5፡00 ሰዓት ገደማ በመኖሪያ ቤታቸው ደረስን፡፡ በብዙ ፈገግታ ተቀበሉን፡፡ በጠዋት ከቤት ወጣ ብለው እንደተመለሱ ነገሩን፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የጤና ምርመራ አድርገው አንድ እግራቸውን ከሚያስነክሳቸው በስተቀር ጥሩ ጤንነት ላይ እንዳሉ ሀኪማቸው እንደነገሯቸው አጫወቱን፡፡ እኛም ቀበል አድርገን እግዚአብሔር ከጤና ጋር እድሜን እንዲሰጣቸው ተመኘን፡፡

የመጀመሪያ ጥያቄዬ የነበረው በሚያስተምሩበት ወቅት በጣም ተቆጪ እንደነበሩ ተማሪዎችዎ ነግረውኝ ነበር እርሶ ምን ይላሉ አልኳቸው፡፡ አዎ እቆጣ ነበር ጥፋት ስመለከትና ሳስተምር ሲረብሹኝ አይቼ ማለፍ አልችልም ልክ ናቸው እቆጣ ነበር አሉኝ፡፡ በግል ሕይወትዎና በቤትዎስ ይሄ ባህሪዎ ይንፀባረጋል? አዎ አጠገቤ ያሉ ሰዎች ያውቃሉ ጥፋት ሳይ ፊትለፊት ከመናገር ወደኋላ አልልም፤ ይሄ በቃ ባህሪዬ ነው ምንም ማድረግ እችላለሁ፡፡ አሁንስ ይሄ ባህሪዎ እንዳለ ነው? አይ አሁንማ አረጀሁ ብለው ፈገግ አስባሉን፡፡

መምህር ጌታቸው በ1937 ዓ.ም ጉራጌ ዞን በቡኢ ወረዳ (ከቡኢ 16 ኪ.ሜ ወደ ምድረ ከብድ አቦ በሚወስደው መንገድ) ጨላ በተባለው ቦታ ተወለዱ። የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ዳዊት ደግመዋል፣ አስር ዓመት ሲሞላቸው አዲስ አበባ በሚገኘው ልዑል መኮንን ት/ቤት (ያሁኑ አዲስ ከተማ ት/ቤት መርካቶ አወቶብስ ተራ ከ3ኛ ክፍል ጀምሮ በ1952 ዓ.ም) ተምረው በ1961 ዓ.ም የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ። 

  በ1963 ዓ.ም መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብተው አንድ ዓመት ደብረዘይት ተናኜ ወርቅ ሃይስኩል የማስተማር  ብሔራዊ አገልግሎት (National Service)፣ በ1965 ዓ.ም ሐምሌ ወር ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ዲፕሎማቸውን ወስደዋል።

ሲዳሞ ክ/ሀገር ነጌሌ ቦረና ሃይስኩል በእንግሊዝኛ መምህርነት ተመደቡ፡፡ ሁለት ዓመት ካስማሩ በኋላ ቦረና አውራጃ ዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሲቋቋም ከትምህርት ሚኒስተር በውሰት ተወስደው የቦረና አውራጃ እርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ቅ/ጽ/ቤት የዕለት ደራሽ ኃላፊ ሆነው ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል፣ በ1971 ዓ.ም ወደ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የማስተማር ሥራቸውን ተመልሰው እዚያው ቦረና አውራጃ ነጌሌ ሃይሰኩል አስተምረዋል።

#በ1972 ዓ.ም ወደ ሀዋሣ ታቦር ሃይስኩል ተዛወሩ፡፡ በሀዋሣ ታቦር ሃይስልኩል ወስጥ እሰከ 1977 ዓ.ም ካስተማሩ በኋላ መደበኛ ሥራቸውን እየሠሩ ሀዋሣ ማዘጋጃ ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመደቡ፣ በ1978 ዓ.ም የሀዋሣ ከተማ ምክትል ሹም ከዚያም ዋና ሹም ሆነው እስከ 1981 ዓ ም ሚያዚያ ወር ድረስ አገለገሉ።

ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ከማዘጋጃ ቤቱ ሥራ ጎን ለጎን የክፍለሀገሩ የቁጥጥር ኮሚቴ አባል ሆነው አገልግለዋል። የሀዋሣ ወረዳ መምህራን ማህበር ተመራጭ ሆነው በገንዘብ ያዥነት  ሠርተዋል።

ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ቢሮ፣ የቦረና አስተዳደር አካባቢ ፀሐፊ (ሸንጎ ፀሐፊ) ሆነው ተሹመዋል። ቦረና አሰተዳደር አካባቢ እስከ 1983 ዓ.ም ከቆዩ በኋላ በ1984 ዓ.ም ወደ ታቦር ሃይሰኩል ተመልሰው ጡረታ እስከወጡበት እስከ 1994 ዓ.ም ድረስ አስተምረዋል።

ጋሽ ጌታቸው የጡረታ መብታቸውን ካስከበሩ በኋላ:-
1ኛ/አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ ሀዋሣ ቅርንጫፍ፣ በአስተዳደርና  በተማሪዎች ጉዳይ ኃላፊነት ለሁለት ዓመት፣
  2ኛ/ በደቡብ ኢትዮጵያ የግል ኮሌጅ በዲንነት፣ በአስተዳዳሪነት፣ በውስጥና በውጭ ግንኙነት፣ የኃላፊነት ቦታዎች ለ16 ዓመታት  ሠርተዋል፣
3ኛ/የደቡብኢትዮጵያ ክልል የግል ኮሌጆች ማሕበር ጸሐፊ ሆነው ሠርተዋል።
  እኝህ ሁለገብ የብቃት ማሳያ የሆኑት ብርቱ አባታችን ባሳዩት የስራ ትጋት በተለያዩ ጊዜያት ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል ከሽልማቶቹም መሐከል፡-
   1ኛ/በትምህርት ቤት ደረጃ የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀት በ1976 ዓ.ም
    2ኛ/በሲዳማ አውራጃ ት/ቤቶች ጸ/ቤት ደረጃ ካሉ መምህራንና ሠራተኞች መካከል ተመርጠው የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል (1975 ዓ.ም)
  3ኛ/በሲዳሞ ክ/ሀገር ት/ቤቶች ደረጃ ካሉ መምህራንና ሠራተኞች መካከል ተመርጠው የምስጉን መምህርነት የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል።
መጥቀስ ይቻላል።

  የትምህርትደረጃቸው፡-
1. ዲፕሎማ በእንግሊዝኛ ቋንቋ
2.በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ (አማርኛ) ቢ ኤ ዲግሪ (1976 ዓም)
3. Higher Diploma Licence a Certified Professional Teacher Educator (DiLLA UNIVERSITY) January 2007

ጋሽ ጌታቸው አሁን የ79 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ባለትዳር እና የ6 ልጆች አባት ሲሆኑ 10 የልጅ ልጆቸን አይተዋል፡፡ ባሳለፉ የስራ ዘመናቸው ሀገርንና ህዝብን በታማኝነትና በቅንን እንዳገለገሉ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ደስተኛ ነኝ የቀረኝን ዕድሜ ፈጣሪን እያመሰገንኩ እኖራለሁ ብለውናል፡፡   

እኛም ህዝባችንን ያገለገሉ ባለውለታዎችን ለመሸለም 30 ሰዎችን ስንመርጥ ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች ባሻገር “የሐዋሳ ትዝታ” ፔጅ እንዲቀጠል በመምክር፤ በማበረታታት፣ ልክ ያልሆኑ ጽሁፎችን ሲመለከቱ በዚህ ቢስተካከል በማለትና በመገሰጽ እሳቸው ካሉበት ዕውቀት ጋር አነፃፀረው ሳይንቁ ትችላላችሁ ጎበዞች በማለት በሀሳብ በመደገፍ እስከአሁኗ ጊዜ ድረስ አብረውን ስላሉ ምስጋናችንን ብቻ ሳይሆን ክብራችንንም ለመግለፅ እንወዳለን።

ጋሼ ክብረት ይስጥልን፡፡ በድጋሚ ረዥም ዕድሜን ከጤና ጋር ተመኘንልዎት፡፡ 

በሐና በቀለ
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!




#አንድ_አበባ_ለአንድ_ባለውለታ| እንድትሳተፉ ተጋብዛችኋል
#hawassa| 30ዎቹ ባለውለታዎች
     ፍቅርን በአበባ ክብርን በጋቢ ማልበስና ታሪክ በመሰነድ እናመሰግናቸዋለን። መሰል ትውልድ እንዲፈጠር አክብሮታችንን በልጅ ወግ ቤታቸው በመገኘት መግለፅ አለብን።
ሰላም ውድ ቤተሰቦች።
  ከተማችን በርካታ ባለውለታዎች እንዳሏት ይታወቃል። በተለያየ የሙያ ዘርፍ ለከተማችን ብሎም ለማህበረሰባችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አባትና እናቶችን ሳናመሰግን፣ ሳናከብርና ፍቅራችንን ሳንገልፅ ብዙዎች አልፈውብናል። እኛም ከዚህ አለም መለየታቸውን #በህልፈት መርሐግብራችን ስንገልፅ "መልካም እንደነበሩ፣ ስለሰሩት ጀብዱና ስለተወጡት ማህበራዊ ሐላፊነት...ወዘተ ምስክርነት ሲሰጥ ተመልክተናል። ነገር ግን ሰው ህይወቱ ካለፈ በኋላ መሆን የለበትም።
   ይህንን ልምድ መቀየር ስለሚገባ ባለውለታዎቻችን #በህይወት_እያሉ ታሪካቸውን መሰነድ፣ ማክበር፣ ማመስገንና እውቅና መስጠት መለመድ አለበት። በዚህ መሰረት የጀመርነው በህይወት ላሉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አስተዋፅኦ ያበረከቱ #ባለውለታዎችን #በልጅ_ወግ ፍቅራችንን #በአበባ ክብራችንን #ጋቢ በማልበስና ታሪካቸውን በመሰነድ ማቅረብ ጀምረናል። የመጀመሪያ ዙር #30ዎቹ_ባለውለታዎች ዘውትር እሁድ እየቀረበ ይገኛል።
    ሐሳባችንን ስንገልፅላቸው ደግፈው የምናለብሰውን ጋቢ (30 ጋቢዎች) መግዣ ያበረከቱልን በባህር ማዶ የሚኖሩት ፍቅሩና ጓደኞቹ ከፍ ያለ አክብሮት አለን። ለዝግጅታችን መሳካት የናንተ የሐሳብም ሆነ የገንዘብ ድጋፍና ማበረታቻ፣ የኛም የኒዜ፣ እውቀትና የገንዘብ አስተዋፅኦ ድምር ውጤት ነውና እጅግ እናመሰግናለን።
    በዚህ መርሐ ግብር  ክብራችንን በጋቢ፣ ፍቅራችንን በአበባ የምንገልፅ ሲሆን ጋቢ ተገዝቶ ተሰናድቷል አበባውን ግን በየሳምንቱ 300 ብር እኛው እየገዛን ወደ ሰባት የሚጠጉ ባለውለታዎች ጋር ደርሰናል። የቀሩ ወደ 23 ባለውለታዎች ይዘን የምንቀርበውን #የአበባ_ወጭ በመሸፈን ግለሰቦች አልያም ድርጅቶች ከጎናችን ትሆኑ ዘንድ በፍቅር እንጠይቃለን።
      #አንድ_አበባ_ለ_አንድ_ባለውለታ ዋጋው 300 ብር ብቻ!
ማስታወሻ:- የምናቀርባቸው ባለውለታዎች በቅደም ተከተል አይደለም። በአንደኛ ዙር ሲመለመሉ ባላቸው የአስተዋፅኦ መጠን ሳይሆን ከያንዳንዱ ዘርፍ random ነው።
      አበባ ለመግዛት 1000175666137 CBE መጠቀም አልያም በኢንቦክስ ያናግሩን።
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!




#አንጋፋዋ_ሾፌር| ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ
#hawassa| በልጅ ወግ አክብረናል

በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ብርቅ በነበረበት ዘመን እሳቸው ግን ኧረ እናንተ እድሉን ስጡኝ እንጂ ምን ገዶኝ በሚገባ ኃላፊነቴን እወጣለሁ በማለት ከ30 ዓመታት በላይ በሹፍርና አገልግለዋል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ከበደ ባሌ ክ/ሀገር የተወለዱ ሲሆን የ10 ዓመት ልጅ እያሉ ነው ወደሀዋሳ አክስታቸው ቤት የመጡት፡፡ በ19 ዓመታቸው የተዳሩት ወ/ሮ ወይኒቱ ቦረና ከዚያም ያቤሎ ከባለቤታቸው ጋር እየኖሩ ባሉበት ወቅት በጊዜው በነበረው ጦርነት 2 ልጆቻቸውን ይዘው ወደሀዋሳ ከተማ ተመለሱ፡፡

በ1970 ዓ.ም የአሁኑ ግብርና ኮሌጅ በፊት አዋሳ እርሻ ኮሌጅ በሚባልበት ወቅት በ21 ዓመታቸው ኮሌጁ እንጀራ ጋጋሪ ማስታወቂያ አውጥቶ ስለነበር ተወዳድረው ገቡ፡፡ ነገር ግን ብዙም በስራው አልዘለቁበትም፤ ሁለት ወር ከሰሩ በኋላ ይህቺ ወጣት ልጅ በአግባቡ እንጀራ እየጋገረች አይደለም ብለው የተማሪ ምገባ ክፍል በመስተንግዶነት እንዲሰሩ ተደረገ፡፡

ከዚያም የሴቶች ጥበቃ ተፈልጐ ስለነበር ወደዚያ በመዛወር ለ3 ወራት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር  ወታደራዊ ትምህርት በመውሰድ መሣሪያ መፍታት፣ መግጠም ተምረው ሲመለሱ ጥበቃና ፍታሽ ሆነው አገልግለዋል፡፡ 

በኋላ ግን ይላሉ ወ/ሮ ወይኒቱ 1986 ዓ.ም እኔ እና 15 ወንዶች ሹፍርና እንድንሰለጥን መስሪያ ቤቱ ባመቻቸልን ዕድል ስልጠናውን ጨርሰን ላይሰንስ ይዘን ተመለስን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 3ኛ መንጃ ፈቃድ ድረስም መስሪያ ቤቱ አስተምሮኛል፡፡ ከዚያም የኮሌጁ ትራንስፖርትና ገራዥ ክፍል ከጥበቃ ተዛወርኩ፡፡ በጊዜው የነበሩ ፕሮፌሰር ዝናቡ ገ/ማሪያም እና ፕሮፌሰር አድማሱ ፀጋዬ ሌሎችም ጥሩ ዶክተሮችና ሰራተኞች ነበሩ እኔ እንድማርና እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ  አጽተዋፅኦ አድርገውልኛል ይላሉ፡፡

ከስልጠናው በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑልኝም፡፡ በቢሮ ደረጃ የሴት ሾፌር ተቀጥራም ሰርታም ስለማታውቅ ከወንዶቹ እኩል ሰልጥኜ ብመጣም መኪና ሊሰጡኝና ወደስራ ሊያሰማሩኝ ፈቃደኛ ስላልነበሩ ያለስራ 10 ዓመታትን ተቀመጥኩ፡፡

ከዚያ ግን በስምሪት ክፍሉ የነበሩ ሀላፊ መኪና ይሰጣትና ሻሸመኔ ደርሳ ትመለስ ብለው አዘዙና አንድ ታዛቢ ሹፌር ተመደበልኝ፡፡ ትንሽዋን ቴዮታ ሰጡኝና ሻሸመኔ፣ አርሲ ኔጌሌ፣ ቱላ፣ ይርጋዓለም ደርሼ ስመለስ ይርጋዓለም ከሄደች በንሳ ደርሳ ትመለስ ተባልኩ፡፡

በሹፍርና የመስራት ፍላጎቱም ስለነበረኝ ከዚያ በተጨማሪ ተከልክዬ የተቀመጥኩበት እልሁም ተጨምሮበት ስራዬን በጥንቃቄና በትጋት እሰራ ነበር፡፡

ኋላ ብቃቴን ስለተመለከቱ የምርምር ስራን የሚሰሩ ባለሙያዎችን፣ አስተማሪዎችንና ዶክተሮችን ይዤ ወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ አድርሻቸው መለስኳቸው፡፡    

አሁን የእኔ ጊዜ መጣ ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ከዚያም ፒካፕ መኪና ሰጡኝ፤ ቀጠሉና ላንድክሩዘር ብቻ እንዲህ እንዲያ እያልኩ የተገኘነው መኪያ እየቀያየርኩ ሀገራችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ማዳረስ ጀመርኩ፡፡ በሹፍርና ህይወቴ ብዙ የኢትዮጵያ ሃገራትን አይቻለሁ፡፡ በዚያ ደግሞ ትልቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡

ወ/ሮ ወይኒቱ ሲናገሩ ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጣም ታላላቅ ሰዎች ብዙ ምሁራን ያሉበት ቤት ነው ያንን ቤት በጣም እወደዋለሁ፡፡ ብዙ ያየሁበት ጊቢ ነው፡፡ ልጅነቴን ያስታውሰኛል፡፡

ከለሊሉ 9 ሰዓት ከወንዶች እኩል በመነሳት የተማሪዎችን ምግብ የሚያበስሉ ሰራተኞችን ከየቤታቸው በመሰብሰብ 12 ሰዓት ወደቤት እመለስ ነበር፡፡ ከዚያም  ቀን እንዲሁ መምህራኖችን በማመላለስ ሰርቻለሁ፡፡

ነገር ግን ስራው እየተደራረበ ድካም ሲበዛብኝ የቅርብ የስራ ኃላፊ የሆነውን ግለሰብ የለሊቱ ስራ እንዳልተመቸኝ ባሳውቅም በወቅቱ ድካሜን ተረድቶ ቅሬታዬን ስላልተቀበለ አንድም ቀን በዚህ መልኩ ስራዬን እለቃለሁ ብዬ ባላሰብኩት ሰዓት 5 ዓመት ለጡረታ ሲቀረኝ የምወደውን ሞያና ዩኒቨርስቲ ለመልቀቅ ተገደዱ፡፡

እኛ ወ/ሮ ወይኒቱ እቤት በሄድንበት ወቅት ጋቢ ስናለብሳቸውና ለሴቶች ተምሳሌት ኖት ስላገለገሉን እናመሰግናለን ስንል በጉንጫቸው የሚወርደውን እምባ እየጠራረጉ ለካስ መስራቴን ለሕዝብ መድከሜን የሚያውቅልኝ ትውል አለ አመሰግናለሁ ነበር ያሉን፡፡

ሆኖም ግን የጡረታ መብታቸውን ካስከበሩ በኋላ መሪ ለቆ ወደቤት መግባት ለእኔ ከባድ ነበር የሚሉት ታታሪዋ ሾፌር ኦዲት ቢሮ ለ11 ወራት እንዲሁም አሁን የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫ በሾፌርነት 9 ዓመት ያገለገሉ ሲሆን አሁንም በስራ ላይ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የመድሐኒት አቅራቢ አገልግሎት ሀዋሳ ቅርንጫፍ ኃላፊ ለሆኑት አቶ ዘመን ለገሰን የከበረ ምስጋና አቅርቢልኝ እሱ መልካምና የልጅ አዋቂ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም መስሪያ ቤቱ ላሉ ሰራተኞች ስለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አሁን ወ/ሮ ወይኒቱ 68 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ባለትዳር እና የ2 ሴቶችና የ4 ወንዶች በአጠቃላይ የ6 ልጆች እንዲሁም 10 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
 
እኛም ታታሪዋን ሾፌር ለብዙ ሴቶች እህቶቻችን ተምሳሌት ነዎትና በድጋሚ  እያመሰገንን ቀሪ ዘመንዎን አምላክ ይባርክልዎት ማለት ወደድን፡፡

በሐና በቀለ
የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ!
የፍቅር የሰላምና የአንድነት አርበኞች!
#awassa



15 last posts shown.