ነቢዩ ﷺ አደራ ያሉትን ዊትር ሶላት በህይወት እስካለን በረመዷን ውስጥም ከረመዷን ውጭም አደራ!!—————
ዊትር ማለት:- በቋንቋ ደረጃ ነጠላ ቁጥር ማለት ነው። ለምሳሌ:- 1:3:5:7… እንደማለት ነው። ነቢዩ (
ﷺ) "
አላህ ነጠላ (ብቸኛ) ነው፣ ነጠላ የሆነን ነገር ይወዳል" እንዳሉት ማለት ነው፣ [ነሳኢይና ትርሚዚይ ዘግበውታል።]
ዊትር ሸሪዓዊ ትርጉሙ:- ከዒሻ ሶላት በኋላ የሱብሂ ሶላት ወቅት እስኪገባ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የምትሰገድ እጅግ በጣም ጠንካራ ሱንና የሆነች ነጠላ ቁጥር (1፣3፣5፣7፣9 ረከዓ) የሆነች ሶላት ናት።
ነቢዩን ﷺ እንወዳለን ስንል በምላስ ብቻ ሳይሆን፣ ዲኑን ለማሰራጨት በነበራቸው ጉግት፣ ህዝባቸውን ከሺርክ ወደ ተውሒድ ለመጥራት በነበራቸው የማይነቃነቅ ወኔ፣ ዘውትር ከቢድዐ በማስጠንቀቅ ላይ በነበራቸው ፅኑ አቋም፣ በስነ-ምግባራቸው፣ በቸርነታቸው፣ በአዛኝነታቸው፣ በቅንነታቸው፣ ቤታቸው ሲገቡ ሲወጡ ከቤተሰባቸው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ለሶላት በነበራቸው ልዩ ውዴታ፣ በሚያበዟዋቸው በነበሩ ጠንካራ የሱና ሶላቶች… ወዘተ፣ በሁለመናቸው ወደን ልንከተላቸው ይገባል!!።
አንዱን ጥሎ ሌላውን ማንጠልጠል ከአንድ ትክክለኛ የነቢዩ
ﷺ ወዳጅ ነኝ ከሚል ሰው አይጠበቅም!!። አንድ ሰው ምን ቢያቅተው ነቢዩን
ﷺ ከልቡ የሚወዳቸው ከሆነ ጠንካራ ሱናዎቻቸውን ለመከተል መጣጣር አለበት።
ጠንካራ ከሆኑ የነቢዩ
ﷺ ሱናዎች ውስጥ ይህችን ከዒሻ ሶላት በኋላ ጀምሮ የሱብሂ ሶላት እስኪገባ ባለው ጊዜ ውስጥ የምትሰገደዋ ዊትር ሶላት ጠንካራ ሱናቸው ናት። ይህቺ ጠንካራ የሆነችው ሱንና ሶላታቸው በረመዷን ወር ብቻ የምትሰገድ ሳትሆን በህይወት እስካለን ልንሰግዳት የምትገባ ነቢዩ
ﷺ ይህቺን ዱኒያን ለቀዋት እስኪሄዱ አቋርጠዋት የማያውቁ ጠንካራ ሱናቸው ናት።
ይህችን ጠንካራ የሆነችዋን ሱናቸውን ነቢዩ
ﷺ ለአቢሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) አደራ ብለውታል። ሶሃቦችን አደራ ያሉበት ነገር ደግሞ ለኡማው ሁሉ አደራ ነው።
①, ከአቢሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ እንዲህ አለ:- «ወዳጄ (
ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሶስት ነገሮች መክረውኛል:- (ከረመዷን ውጪ ካሉ) ሁሉም ወራቶች ሶስት፣ሶስት ቀን እንድፆም፣ ከአዶሃ ሶላት ሁለት ረከዓ (ቢሆን እንኳን) እንድሰግድ፣ ሶላተል ዊትርንም ከመተኛቴ በፊት (ቢሆን እንኳ) እንድሰግድ።» [ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።] የአዶሃ ሶላት ሁለት ረከዓ ብቻ አይደለም፣ 2፣2 እያደረጉ እስከ 8ና 4 ረከዓ መስገድ ነው፣ ነገር ግን ምን ቢያቅትህ 2,ረከዓ ቢሆን እንኳን ስገድ ማለታቸው ነው።
የሶላተል ዊትርም የተሻለና በላጩ ጊዜ ከሌሊቱ የመጨረሻው ክ/ጊዜ የለይል ሶላት መስገጃ ማብቂያ ሰዓት አካባቢ ነው። አንድ ሰው ከተኛው በኋላ ላልነሳ እችላለሁ ብሎ ከፈራ ግን የዒሻ ሶላት ከተሰገድ በኋላ ባለው ጊዜ ከመተኛቱ በፊት ሰግዶ መተኛት ይችላል።
②, ከጃቢር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (
ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:- «
ከሌሊት በመጨረሻው ክፍለ ጊዜ ላልነሳ እችላለሁ ብሎ የፈራ ሰው በመጀመሪያው ክ/ጊዜ ዊትሩን ይስገድ፣ ከሌሊቱ በመጨረሻው ክ/ጊዜ መነሳትን የከጀለ ሰው በመጨረሻው ክ/ጊዜ ይስገድ፣ የሌሊቱ የመጨረሻው ክ/ጊዜ ሶላት መላኢካዎች የሚሳተፉበት ነው። (በመሆኑም) ይህ የተሻለ (በላጭ) ነው።» [ሙስሊም ዘግበውታል።]
ዊትር ሶላት ምንም እንኳን ግዴታ ባይሆንም፣ ነቢዩ
ﷺ ልዩ ትኩረት ሰጥተውት የቁርኣን ባለቤት የሆነውን ሙስሊም ያዘዙበት የጠነከረ ሱና ነው።
③, ከዐሊይ ኢብን አቢ ጧሊብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ፣ የአላህ መልእክተኛ (
ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:- «
እናንተ የቁርኣን ባለቤቶች ሆይ! ዊትር ሶላትን ስገዱ፣ አላህ ነጠላ (ብቸኛ) የሆነ ጌታ ነውና ነጠላ የሆነን ነገር ይወዳል።» [አቡዳውድ፣ ነሳኢይና ትርሚዚይ የዘገቡት ሲሆን ትርሚዚይ ሀዲሱን ሀሰን ነው ብለውታል።]
ነቢዩ
ﷺ ለዊትር ሶላት ሚስቶቻቸውን (ቤተሰቦቻቸውን) ይቀሰቅሱ ነበር።
④, እውነተኛዋ የእውነተኛው ልጅ የሆነችው እናታችን ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች:- «የአላህ መልእክተኛ (
ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከለይል ሶላት ይሰግዱ ነበር፣ ዊትርን በሰገዱ ጊዜ “ዓኢሻ ሆይ! ተነሺ ቁሚ ዊትርን ስገጂ ይሉኝ” ነበር።» [ሙስሊም ዘግበውታል።]
ለይል ሶላትን የሚሰግድ ሰው ዊትርን የሚሰግደው የለይሉን 8,ረከዓ ከሰገደ በኋላ ነው።
⑤, ከኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ፣ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ይሉ ነበር:- «
በሌሊት የሶላታችሁን መጨረሻ ዊትር አድርጉት።» [ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።]
በዊትር ሶላት ውስጥ ከፋቲሃ ቀጥሎ ሶስቱን ሱራዎች መቅራት የተወደደ (ሱንና) ነው።
⑥, ኡበይ ኢብን ከዕብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ:- «
ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በሰቢህ ኢስሚ ረቢከል አዕላ፣ በቁል ያ-አዩሃል ካፊሩን፣ በቁል ሁወ አላሁ አሀድ ዊትር ያደርጉ ነበር።» [ኢማሙ አህመድ፣ አቡዳውድና ነሳኢይ ዘግበውታል።]
የቁርኣን ሱራዎች ቅደም-ተከተሉን በጠበቀ መልኩ ይቀራቸዋል።
ዊትር ሶላትን ከሶስት ረከዓ በለይም መስገድ ይፈቀዳል። ዋናው ግን ከላይ በመግቢያው እንደጠቀስኩላችሁ ነጠላ የሆነ ቁጥር መሆን አለበት።
⑦, እናታችን ዓኢሻ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች:- «
ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በዘጠኝም በአምስትም ረከዓ ዊትር ያደርጉ ነበር።» [ሙስሊም ዘግበውታል።]
✍🏻 ኢብን ሽፋ (
t.me/ibnshifa)
የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም 👇👇 ቻናላችን #join በማድረግ ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifahttps://telegram.me/IbnShifa