📖ከአፍ የሚወጣ እሳት
"አፌ ይለፈልፋል እንጂ ውስጤ እኮ ንጹሕ ነው" አለች አባ ፊት ቀርባ - በክፉ ንግግርዋ ብዙ ሰው ያስቀየመች ሴት::
አባ መለሱላት :-
ልክ ነሽ ልጄ እባብም እኮ መርዙን ከተፋ በኁዋላ ውስጡ ንጹሕ ነው!
ምላስ አጥንት የለውም ነገር ግን አጥንት ይሰብራል:: እግዚአብሔር ምላስን እንደ ጆሮ ክፍት አላደረገም:: በከንፈርና በጥርስ ሸፍኖታል:: ትንሽ አሰብ አድርገን እንድናወራ ነው:: "ሰው ለመናገር የዘገየ ለመስማት የፈጠነ ይሁን" የሚለው ቅዱስ ያዕቆብ ስለ አንደበት ሲናገር "ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል" እንዳለ የምላስ ኃይል እጅግ ከባድ ነው:: ከአፍ የሚወጣ እሳት ብዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል::
ሰው በዱላ ቢደበደብ ታክሞ ቁስሉ ያገግማል:: ክፉ ንግግር የሚያቆስለው ቁስል ግን በቀላሉ አይሽርም:: ዱላ የሚያርፈው ሥጋ ላይ ሲሆን መጥፎ ንግግር ግን ነፍስ ላይ ነው:: ክፉ ንግግሮች ሰውን ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ሊያመርሩት ይችላሉ::
(ሌላ ነገርዋን ትተነው) ሚሼል ኦባማ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ በጣም ልብ የሚነካ ነገር ስትናገር ሰማሁ። ስለወረደባት ስድብ ስታስታውስ "አንዳንድ ክፉ ቃላት የነፍስን ቅርፅ ይቀይራሉ" ብላ ነበር:: እውነት ነው በመራር ቃላት የነፍሳቸው ቅርፅ ከተቀየረ ስንቶች ናቸው? የማይዘነጉት ንግግር እድሜ ልክ የሚያቆስላቸው : የአንድ ሰው ከባድ ስድብ በራስ መተማመናቸውን የነጠቃቸው : የአንድ ሰው "አትችልም" የሚል ድምፅ እጅና እግራቸውን ያሰራቸው እጅግ ብዙ ናቸው:: ሰው ለማሳቅ ተብለው የተሰነዘሩ "ትረባዎች"ና አጥንት ሰባሪ ቀልዶች ቂመኛ ያደረጉዋቸው ሰውን ሁሉ ያስጠሉአቸው ስንት ናቸው? በስድብ ብቻ የፈረሱ ቤቶች አሉ:: ስለተሰደቡ ብቻ በሕዝብ ላይ የሚፈርዱ ዘር እስከማጥፋት የተነሡ አሉ:: ተናጋሪው በጥፋታቸው ውስጥ ትልቅ ድርሻ እና ተጠያቂነት እንዳለው ግን ይዘነጋል::
እግዚአብሔርም "እንደ ዋዛ ለተናገራችሁት ቃል በፍርድ ቀን መልስ ትሠጡበታላችሁ" ብሎአልና ለሰዎች የምንሰነዝረው እያንዳንዱ ቃል ያስጠይቀናል::በተቃራኒው ለሰዎች ጥሩ ቃል መናገርን ብዙ ዋጋ አንሠጠውም:: ለስድብ የማናቅማማ ሰዎች ለምስጋና ሲሆን ግን እንሽኮረመማለን::ፊት ለፊት አሳምረን የምንሳደብ ሰዎች ለማመስገን ሲሆን "በፊትህ ማመስገን እንዳይሆንብኝ" እንላለን::ሆኖም ብናወጣው ሰዎች የሚነገራቸው ጥቂት በጎ ቃል ሰብእናቸውን ይገነባል:: ፈጣሪ "ብርሃን ይሁን" ብሎ በቃሉ እንዳበራው ማድረግ ባይቻልህ እንኩዋን በጥቂት በጎ ቃላት የአንድን ሰው ቀን ማብራት ትችላለህ::
ከምንም ሥጦታ በላይ መልካም የምስጋና ቃላት በሰው ልብ የሚቀር ውድ ሥጦታ ነው::ባል ለሚስቱ ከሚገዛው ሥጦታ በላይ "ባልዋም ያመሰግናታል" የሚለውን ቃል ቢፈጽምላት ደስታ ይሆንላታል:: ልጆች ከብዙ ሥጦታዎች በላይ ከወላጆቻቸው የሚሰሙት የፍቅር ቃል ይሠራቸዋል::
የእስክንድርያው ፊሎ ለልጅ አባትና እናቱ ከሀገሪቱ ንጉሥና ንግሥት በላይ ናቸው ይላል:: የንጉሥ ቃል የሹመት ቃል ነውና ልጆች በወላጆቻቸው የሚሰሙት "ጎሽ" የሚል ቃል ከፍ ያደርጋቸዋል::
"ልጅሽ ትምህርት የማይገባው ደደብ ስለሆነ ትምህርት ቤት አትላኪው" የሚልን ደብዳቤ "ልጅሽ በጣም ጎበዝ ስለሆነ እሱን ማስተማር ስለማንችል በቤት አስተምሪው" ብላ ያነበበች እናት ትልቅ ሳይንቲስት አፍርታለች::
ብርሃን ይሁን ! ምድር ታብቅል! ብሎ የፈጠረን አምላክ በአርኣያው ፈጥሮናልና በቃላችን የምናሳምም ሳይሆን የምንፈውስ እንሁን::
እናንተ ግን ንግግራችሁ በጨው እንደተቀመመ ይሁን። ✍ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
@kidestaresema@kidestaresema6@kidestaresema